በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፦ በተያዘው በጀት ዓመት በትምህርት ለትውልድ የሕዝብ ንቅናቄ ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበትና በቁሳቁስ የሚገመት አበርክቶ መሰብሰብ መቻሉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፤የተቋሙን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት፤ በሀገራችን ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ85 በመቶ በላይ ከደረጃ በታች መሆናቸውን የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን መረጃ ያመላክታል። ይህንን መሠረት በማድረግ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል «ትምህርት ለትውልድ» በሚል መሪ ቃል ሀገራዊ ንቅናቄ ሲከናወን ቆይቷል። በእዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 54 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በመጀመሪያ ዙር ከተሰበሰበው 27 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን የሚገመት ብር ጋር ጠቅላላ ገቢውን 81 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ለማድረስ መቻሉንም አመልክተዋል።

እስካሁን በተሰበሰበው ሀብትም 5 ሺህ 906 ቅድመ አንደኛ ደረጃ፣ 832 አንደኛና መካከለኛ ደረጃ፣ 712 የሁለተኛ ደረጃ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ መከናወኑን ገልጸው፤ በተጨማሪም ከእዚሁ ሀብት ላይ አንድ ሺህ 946 ቅድመ አንደኛ ደረጃ፣ 19ሺህ 354 አንደኛና መካከለኛ ደረጃ፣ አንድ ሺህ 48 የሁለተኛ ደረጃ እድሳትና 10 ሺህ 187 ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የተጨማሪ ክፍሎች ግንባታ መካሄዱንም ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ብዙ ሥራዎች ተከናውነው አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁንም በርካታ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሊንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ተሰበሰበ የተባለው ገንዘብ በቁጥር ደረጃ ትክክል ቢሆንም አብዛኛው ገንዘብ ከአንድ ክልል የተሰበሰበ በመሆኑ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ያመላክታል ብለዋል።

ሰብሳቢው ለሚኒስትሩ ሪፖርት በሰጡት ምላሽ ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት ከተሰበሰበው 54 ቢሊዮን ብር የሚገመት አበርክቶ 45 ቢሊዮን የሚሆነው ከአንድ ክልል የተሰበሰበ ነው። ቀሪው ዘጠኝ ቢሊዮን የሚገመተው ከአስራ አንዱ ክልሎች የተውጣጣ ነው። ከትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት አንዱ እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች በሁሉም አካባቢዎች እንዲከናወን ማስቻል ነው ብለዋል።

ንቅናቄው በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ አካሄድ እንዲተገበር ትምህርት ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር በቅርበት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You