
– ለትንሳኤ በዓል 6 ሺህ 500 እንስሳት እርድ ለመፈጸም ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፡- በቄራዎች ድርጅት ውስጥ ያልታረደ እና በሐኪሞች ጤንነቱ ያልተጠበቀ ሥጋ በሚሸጡ የሥጋ መሸጫ ተቋማት ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ እና ርምጃ እንደሚወስድ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ገለጸ፡፡ በባለፈው ዓመት ኮሚሽኑ በ174 የሥጋ መሸጫ ተቋማት ላይ ሕጋዊ ርምጃ ወስዷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፀጋ ለማ (ዶ/ር)፤ በትናንትናው ዕለት በቄራዎች ድርጅት ተገኝተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ኮሚሽኑ በከተማዋ በሕገ ወጥ እርድ ጤንነቱ ያልተጠበቀ ሥጋ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዳይሆን ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቄራ ድርጅት ውስጥ ያልታረደና በሥጋ ምርመራ ሐኪሞች ጤናማነቱ ያልተረጋገጠ ሥጋ ለተጠቃሚ በሽያጭ እያቀረቡ ያሉ ተቋማት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሆን አስፈላጊውን ርምጃ እንወስዳለን ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በተደረገው የቁጥጥር ሥራ 174 የሚሆኑ የሥጋ መሸጫ ተቋማት ላይ ርምጃ መወሰዱን አውስተው፤ ከቅጣት ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ በሚከበረው የትንሳኤ በዓልም ሕገወጥ እርድንና የሥጋ ዝውውርን የመቆጣጠር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመው፤ ጤንነቱ የተጠበቀና ደኅንነቱ የተረጋገጠ ሥጋ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ለእርድ በሚቀርቡ እንስሳት ላይ የቅደመና የድህረ እርድ ምርመራ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ሥጋ ቤቶችን የማደስ፣ የማረጃ ቁሳቁሶች፣ የሥጋ ማንጠልጠያ መሣሪያዎች፣ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ላይ ምርመራ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ በበዓላት ወቅት ለቤተሰብ ፍጆታ በግል የሚከናወኑ እርዶች አሉ፡፡ እነዚህን እርዶችም በተቻለ መጠን በቄራዎች ድርጅት ውስጥ እንዲከናወኑ ይመከራል፡፡ ለቤተሰብ ፍጆታ በግል የሚከናወኑ የግል እርዶች ላይ ኅብረተሰቡ ለእርድ የሚጠቀምባቸውን የማረጃ መሣሪያዎች ንጽህና ፣ የሥጋ ብልቶችን ማስቀመጫ እቃዎች ንጽህናቸው የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በተጨማሪም በእርድ ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የአካባቢ ብክለትና የንጽህና ጉድለት በመቆጣጠር ከእርድ በኋላ አካባቢው እንዳይበከል የእርድ ቦታዎችን የማጽዳት እና ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ የማስወገድ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቄራዎች ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው፤ ተቋሙ ለትንሳኤ በዓል 6 ሺህ 500 እንስሳት እርድ ለመፈጸም ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል። ድርጅቱ ንጽህናውንና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሥጋ ለማህበረሰቡ ለማድረስ የዝግጅት ሥራ አጠናቋልም ብለዋል።
ተቋሙ ከእዚህ በፊት ከነበሩት ተሞክሮዎች በመነሳት 4ሺህ የቀንድ ከብቶች እና 2ሺ 500 ፍየል እና በግ ይገባሉ የሚል ግምት እንዳለም ተናግረዋል። ደንበኞች የበሬ የእርድ አገልግሎት በአንድ ሺህ 470 ብር፣ በግ እና ፍየል 160 ብር ማግኘት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡
በቄራ ድርጅቱ የሚከናወን የእርድ አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፍ ለማድረግም እንደ ጂፒኤስ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ ተሠርቷል፤ ሥጋውንም በንጽህና እና በፍጥነት የሚያጓጉዙ 40 ተሽከርካሪዎች ተዘጋጅተዋል ሲሉ ገልጸዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም