በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉንዳኖችን የሰረቁ ፍርድ ቤት ቀረቡ

በኬንያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉንዳኖችን የሰረቁ አራት ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን እነዚህን ጉንዳኖች ሰርቀው ለማጓጓዝ ሲሞክሩ የተያዙት አራት ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል።

የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቋም እንደ አንበሳ እና ዝሆን ያሉ እንስሳት ለመጠበቅ ቢቋቋምም፤ ለጉንዳኖችም ከለላ መስጠቱን በመጥቀስ የፍርድ ቤቱን ጉዳይ “ትልቅ ነው” ሲል አሞካሽቷል።በአፍሪካ የሚገኙትን እነዚህ African harvester ants ተብለው የሚጠሩት ጉንዳኖች እያንዳንዳቸው በዩናይትድ ኪንግደም እስከ 170 ፓውንድ ይሸጣሉ።የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቋም በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ እንስሳት እምብዛም የማይታወቁ እየሆኑ እንደመጡ እና ይህም አደገኛ መሆኑን ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ ለጉንዳኖቹ በተዘጋጀ የፕላስቲክ ቱቦ ውስጥ አስቀምጠዋቸው ነው የተያዙት። ጉንዳኖቹ እስከ ሁለት ወር ድረስ በእዚህ ቱቦ ውስጥ መኖር ይችላሉ።ቱቦውን በመደበቅ ከጸጥታ ኃይሎች ሰውረው ከሀገር ለማስወጣትም አቅደው ነበር ተብሏል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉንዳኖች ቱቦ ውስጥ ገብተው በጨርቅ ተጠቅልለው ተገኝተዋል።የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቋም ቃል አቀባይ ፖል ኡዶቶ ትክክለኛው የጉንዳኖቹ ቁጥር ገና አልታወቀም ብለዋል።

ከአራቱ ተጠርጣሪዎች ሁለቱ የቤልጂየም፣ አንደኛው የቬትናም እና ሌላኛው የኬንያ ዜግነት አላቸው።ጉንዳኖቹ ወደ አውሮፓ ወይም እስያ ለመውሰድ ተዘጋጅተው ነበር ተብሏል።

የጉንዳኖቹ ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ጉንዳኖቹ መኖሪያቸውን ሲያዘጋጁ ለማየት በሚል የሚገዟቸው ሰዎች እየተበራከቱ ነው። ይህ ጉንዳኖቹን የማከማቸት ሂደትም formicariums ይባላል።በጣም ትልቅ መጠን ያላቸው ጉንዳኖች የበለጠ ተፈላጊነት እንዳላቸውም ተገልጿል።

በኬንያ እነዚህ ጉንዳኖች በዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ሕግ ከለላ ይሰጣቸዋል። ከፍተኛ ቁጥጥርም ይደረግባቸዋል።የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቋም ባወጣው መግለጫ “የፍርድ ቤቱ ሒደት ኬንያ ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር ወንጀል ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም ያሳያል” ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You