ለአርሶ አደሩ የሚቀርበውን የምርጥ ዘር መጠን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ወደ አርሶ አደሩ የሚቀርበውን የምርጥ ዘር መጠን በእጥፍ ለመጨመር እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ አስታወቁ፡፡ ለአርሶ አደሩ የሚቀርበውን ምርጥ ዘር ባለሥልጣኑ ባለው ሃያ ላቦራቶሪዎች ውስጥ ከማሳ ናሙና በመውሰድ የሚመረምር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አምባሳደር ድሪባ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ አብዛኛው ዘር የሚመረተው የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማሳ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ በኢትዮጵያ አርሶ አደሩ ከሚፈልገው ዘር ውስጥ የሚቀርበው የዘር መጠን ከ25 በመቶ አይበልጥም፡፡ ይሁንና ይህንን ክፍተት ለመሙላት በቀጣይ ቢያንስ የሚቀርበውን የዘር መጠን 50 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

የዘር መጠኑን ወደ 50 በመቶ ከፍ ለማድረግ ዘንድሮ እንቅስቃሴውን ጀምረናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የግብርና ሚኒስትር የሚመሩት የጋራ ኮሚቴው ለአርሶ አደሩ የሚቀርበውን የምርጥ ዘር መጠን ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የዘር ምርቱ በእያንዳንዱ ክልል በእጥፍ እንዲጨምርና ክልሎቹ በእጥፍ ሲጨምሩ ደግሞ ባለሥልጣኑም የቁጥጥር ሥርዓቱን በእጥፍ ለመጨመር እየሠራን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አሁን በተቀናጀ ሁኔታ ኮሜርሻል እርሻዎች ምርጥ ዘር ወደ ማምረት እንዲገቡ ለማድረግ እየታሰበ ሲሆን፤ አዲስ ሕግም ወጥቷል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ድሪባ እንደገለጹት፤ ከእዚህ ቀደም ጠቅላላ ምርጥ ዘር የሚያመርተው መንግሥት ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን አዋጁ የግሉ ሴክተር ምርጥ ዘር ማምረት እንዲችል የሚያደርግ ነው፤ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ደግሞ ምርጥ ዘር ወደ አፍሪካ ሀገሮች ኤክስፖርት ለማድረግ በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በኩል ሰፊ ውይይት አድርጓል፤ በጉዳዩ ላይ ሰፊ የጋራ ማሕቀፍም ፈጥሯል፡፡

ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ ምርጥ ዘር ኬንያ ውስጥ ካለ ከኬንያ ሊመጣ ይችላል፡፡ እዚያ ያለው ባለሥልጣን ቁጥጥሩን አረጋግጦ ያመጣል ነው ያሉት፡፡

እኛ የሆርቲካልቸር ዘር ከአውሮፓ ኔዘርላንድስና ከሕንድ እናስገባለን፡፡ በእዚህ መልኩ ከ24 ሺህ እስከ 30 ሺህ ኩንታል ይገባል፡፡ አሁን እየታሰበ ያለው ለኢትዮጵያ እርሻ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገሮችም ለአፍሪካም ጭምር ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ሁሉም ዓይነት አግሮ-ኢኮሎጂ ያላት ሀገር እንደመሆኗ ለዓለምም ጭምር በማሰብ ላይ እንገኛለን ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ባለሀብቱ ኤክስፖርት እንዲያደርግ ይፈለጋል፡፡ ባለሥልጣኑም ደግሞ ኢትዮጵያ የማይመረቱትን ከውጭ በማስገባት ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ጭምር እንዲሸጋገር ለማድረግ አስቦ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከእዚህ አኳያ ግብርና ሚኒስቴርም የምርጥ ዘር መጠን ለመጨመር በእዚህ ላይ በጣም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ነው፡፡

በአጠቃላይ በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ድረስ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ይቀርባል ያሉት አምባሳደር ድሪባ፤ ይህን አንድ ሚሊዮን ኩንታል ዘር ባሉን ሃያ ላቦራቶሪዎች ውስጥ ከማሳ ናሙና በመውሰድ የምንመረምረው እኛ ነን ብለዋል፡፡

አብዛኛው ዘር የሚመረተው ደግሞ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ 60 በመቶ የሚሆነው ዘር የሚመረተው በኦሮሚያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቀጥሎ ትልቁ የሚመረተው በአማራ ክልል ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ እነዚህን የሚመረቱ ዘሮች ባለሙያዎች ናሙና ይወስዱና ወደ ላቦራቶሪ ያስገባሉ፤ ዘሩ ያንን ሒደት ካጠናቀቀ በኋላ ለምርጥ ዘር ያገለግላል የሚል ‘ታግ’ ይደረግበታል፡፡ ከእዚያም ለአምራቹ እንዲቀርብ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ዘንድሮ በምርምር የቀረቡ ከመቶ በላይ የሆኑ ዘሮች በመጀመሪያ ከምርምር፣ ዘር ከተዘራ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ የተባለው ምርታማነት የሚጨምር ወይም የማይጨምር እንደሆነ ክትትል ይደረግበታል ሲሉም ጠቅሰው፤ ውጤቱን በተመለከተ የታየበት ጉድለት በማደግ ሒደት ውስጥ የሚያሳይ ከሆነ ተመራማሪው በቀጣይ ምን ምን ማካተት ይጠበቅበታል የሚለውን እንዲያጤነው ይደረጋል ብለዋል፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You