የዩኒቨርሲቲ መንደሩ በቀጣይ አስር ዓመት አካታች ሆኖ ይተገበራል

አዲስ አበባ፦ የዩኒቨርሲቲ መንደሩ ሁሉን አካታች እና ሕዝብን የሚያሳትፍ ሆኖ በመጪው አስር ዓመታት እንደሚተገበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ የፕሮጀክቱን አተገባበር አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ የዩኒቨርሲቲ መንደሩ በውስጡ የሃይማኖት ተቋማትን፣ ሙዚየም፣ የምርምር ተቋማትን፣ የገበያ ማዕከላትን፣ ትምህርት ቤቶችን እና የመኖሪያ መንደርን የሚያካትት ነው።

ልማቱ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን አካቶ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፤ ቀድመው በአካባቢው የነበሩ ተቋማትን የማያፈናቅል እና አሁን እየተተገበረ ያለውን የኮሪደር ልማትም ከግምት በማስገባት የሚከናወን እንደሆነ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው ያሉትን አገልግሎቶች አካቶ የትምህርት ፣ የምርምር ፣ የእውቀት እና የባህል ማእከል ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመው፤ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማትን ለመሳብ ዩኒቨርሲቲዎች ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት የተቀራረበ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

የፕሮጀክቱን አተገባበር አስመልክቶ በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ዝርዝር ጥናት እንደሚደረግና ከኅብረተሰቡም ጋር ሰፊ ውይይት የሚደረግ ይሆናል፤ የዩኒቨርሲቲ መንደሩ ሁሉን አቀፍ በእውቀት የላቀች ተወዳዳሪ ከተማ ለመገንባት እና የትምህርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት ያስችላል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲ መንደር ፕሮጀክት ልማቱ የከተማው ፕላንና ልማት ቢሮ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያጠኑት መሆኑን አቶ አደም ጠቁመው፤የመንደር ግንባታው የአስር ዓመት እቅድ የተያዘለት ሲሆን፤ ሥራው በተለያየ ምዕራፍ ተከፋፍሎ የሚተገበር መሆኑም ተገልጿል።

አሁን ላይ ቦታውን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አውስተው፤ በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎች ዝርዝር ጥናት እንደሚደረግና ከኅብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወካይና የጥናቱ አስተባባሪ ኢሳይያስ ገ/ዮሐንስ (ዶ/ር)፤በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሃሳብ አመንጪነት ከዛሬ አምስት ዓመት ጀምሮ ሲጠና መቆየቱን በማስታወስ፤ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ አንስቶ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል ብለዋል።

በጥናቱም አካባቢው የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት እና የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ የተመሠረተበትና አሁን ላይ ደግሞ በርካታ የትምህርት ተቋማትና ትምህርት ሚኒስቴር ራሱ የሚገኝበት መሆኑን አውስተው፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻውን በእዚሁ አካባቢ ስድስት ካምፓሶች አሉት። በእዚህም አካባቢው በራሱ ሂደት የትምህርት፣ የምርምር፣ የፈጠራ፣ የባህልና የቱሪዝም መዳረሻ አካባቢ እየሆነ የመጣ ነው። አሁን የሚሠራው ሥራ ይህንን ጅምር እንዴት ቅርጽና መስመር እናስይዘው የሚል እንደሆነ አብራርተዋል።

ከመቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ሰባ በመቶ ወጣት በሆነባት ሀገር ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የግድ የሚል ይሆናል ያሉት ኢሳያስ (ዶ/ር)፤ በትምህርት ዘርፍ አካታች የሆኑ የልህቀት ማእከልን ማስፋፋት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከጎረቤት ሀገራትም ኢትዮጵያ መጥቶ ለመማር ፍላጎት በመኖሩ ለእዚህ ስኬታማነት የዩኒቨርሲቲ መንደሩ ውጤታማነት የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው ያብራሩት።

ዩኒቨርሲቲ መንደሩ በሰሜን የሽሮ ሜዳ የገበያ ማዕከልን፣ በደቡብ የአብረሆት ቤተ መጽሐፍትን፣ በምሥራቅ የግንፍሌ እና የቀበና ወንዝን፣ በምዕራብ የቀጨኔ ወንዝ ዳርቻን የሚያካልል እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በአካባቢው ያሉ ተቋማት ባሉበት የሚቀጥሉ ሲሆን፤ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 500 ሄክታር የሚሸፍን መሆኑ ተጠቁሟል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You