የመድን ፈንዱ የኢንቨስትመንት ክምችቱ 12 ቢሊዮን ብር ደረሰ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የኢንቨስትመንት ክምችቱ 12 ነጥብ 11 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት አምስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር) የተቋሙን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸምን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የፈንዱ የኢንቨስትመንት ክምችት 12 ነጥብ 11 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ፈንዱ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እና የገንዘብ አቅሙን ለማሳደግ የሰበሰበውን አረቦን እና ተመላሽ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶችን መልሶ ኢንቨስት እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በእዚሁ መሠረትም እስካሁን ድረስ የፈንዱ የኢንቨስትመንት ክምችት 12 ነጥብ 11 ቢሊዮን መድረሱን ገልጸዋል።

ከጠቅላላው የፈንዱ ኢንቨስትመንት ውስጥ 11 ነጥብ 17 ቢሊዮን ወይም 92 ነጥብ 24 በመቶ በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ላይ ኢንቨስት የተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፈንዱ ከአባል የፋይናንስ ተቋማት በየዓመቱ ገንዘብ የሚሰበሰብ ሲሆን፤ ተቋማቱ ካላቸው አማካይ ዓመታዊ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ዜሮ ነጥብ ሦስት በመቶ ለፈንዱ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው አመልክተው፤ ፈንዱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት አምስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ በዕቅዱ መሠረት ከአባል የፋይናንስ ተቋማት የተሰበሰበው ብር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ11 ነጥብ 10 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከተሰበሰበው ውስጥ ሁለት ነጥብ 67 ቢሊዮን ብር ከግል ባንኮች የተገኘ ሲሆን፤ ሁለት ነጥብ 47 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም 59 ነጥብ 49 ሚሊዮን ብር ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተሰበሰበ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በአዋጅ ቁጥር 482/2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ ሥራውን ከጀመረ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሆነው ይኸው ፈንድ፣ ዋና ዓላማው በባንክና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተቀማጭ ገንዘብ ላስቀመጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች የመድን ሽፋን የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You