ለበዓል የእህል ገበያ በቂ የአቅርቦት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ ፦ ለበዓል የእህል ገበያ በቂ የአቅርቦት ዝግጅት ማድረጋቸውን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሊበን ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለሙ ረፌራ ገለጹ።

ሰብሳቢው በተለይ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የበዓል ዝግጅትን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል።ይህን ችግር ለመፍታትም ዩኒየኑ ሁልጊዜ በዓላት ሲቃረቡ ከሌላው ጊዜ በተለየ በቂ ምርትና የማድረሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ያዘጋጃል። ዘንድሮም ከወር አስቀድመን ይህንን ታሳቢ በማድረግ እህል የማሰባሰብና ወደ አዲስ አበባ ከሚወስዱ ሸማች ማህበራት ጋር ስምምነት ስናደርግ ቆይተናል ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ብቻ ከጅንአድ ጋር የአስር ሺህ ኩንታል ስምምነት አድርገናል፡፡እስካሁን 4ሺህ 200 ኩንታል የተለያዩ እህሎች ወስደዋል ያሉት አቶ አለሙ፤ በዚህ ሳምንትም በስምምነታችን መሠረት አምስት ሺህ ስምንት መቶ ኩንታል እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

በተጨማሪ ከፋና ኅብረት ሥራ ሸማቾች ማህበርና ከሌሎች ሦስት ማህበራት ጋር በቀጣዩ ሳምንት ከእያንዳንዳቸው ጋር አንድ ሺህ ሁለት መቶ ኩንታል እህል ሊወስዱ ስምምነት ተፈራርመናል። ከሌሎች በአዲስ አበባ የሚገኙ ሸማቾች ማህበራትም ጋር ውል ገብተን እየጨረስን ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ቀናት በስምምነታችን መሠረት ክፍያ ፈጽመው እንደሚወስዱ እንጠብቃለን ሲሉ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በመጋዘኖቻችን በቂ የእህል ምርት አስቀምጠናል ያሉት ሰብሳቢው፤ እኛ የምንሠራው መንግሥትም ያቋቋመን ሸማቹን ማህበረሰብ ከሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ለመታደግና ደረጃውን የጠበቀ ምርት እንዲያገኝ ለማስቻል እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ይህንን ኃላፊነት ለመወጣትም በበዓላትና የእህል ዋጋ ይጨምራል የሚል ስጋት በሚፈጠርባቸው ወቅቶች በልዩ ትኩረት እንሠራለን ያሉት አቶ አለሙ፤ በእንቅስቃሴ ወቅት ምርት እንዳይባክንና በደላሎች ጣልቃ ገብነት ዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት የሊበን ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ገዥዎች ሲፈልጉ የትራንስፖርትም አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You