ስለውሻ ስናነሳ በቅድሚያ ከአእምሮአችን የሚመጣው ነገር ስለታማኝነታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ውሻ ታማኝ የቤት እንስሳ ተደርጐም ይወሰዳል፡፡ ይህ በአብዛኛው ትክክል የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡
ለምሳሌ በጦርነት በሚታመሱ አንዳንድ አገራት በፈራረሱ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙት ውሾች ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው የቤት እንስሳ ግን ችግር ሲያጋጥም አብሮ ለመቆየት የሚያስችል ጽናት ያላቸው አይመስልም፡፡ ሰሞኑን ኦዲቲ ሴንትራል ይዞ የወጣው አንድ ዜናም ይህንኑ የውሻ ታማኝነት የሚያረጋግጥ ይመስላል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
ሚሩ የተባለችው ውሻ የተወለደችው ኖቮስብራስክ በተባለው የሩስያ የውሾች ማርቢያ ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡ ገና አምስት ወር ሲሆናትም ውሻ ለሚፈልጉ ሰዎች ተሸጠች፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የገዢዎቹ ስፍራ ደግሞ ሚሩ ከተወለደችበት 800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ በውላቸው መሰረት አሳዳጊዎች ሚሩን ካልፈለጓት የመመለስ ግዴታ አለባቸው፡፡
አሳዳጊዎችም ሚሩን ከወሰዱ በኋላ ማሳደግ ይጀምራሉ፡፡ ነገር ግን ከስድስት ወራት በኋላ ሚሩ ከነዚህ ቤተሰቦች ጋር ልትስማማ አልቻለችም። ለዚህ ምክንያት ደግሞ ሚሩ ለቤተሰባችን “አላርጂክ” ናት የሚል ነው፡፡ በዚህ መሰረት ሚሩን ወደገዙበት ስራ ለመመለስ ጉዞ ይጀምራሉ። ጉዞው ደግሞ በባቡር ሲሆን በሳይቤርያ የእንስሳት ፓርክ ውስጥ አልፎ የሚሄድ ረጅም ጉዞ ነው፡፡
በዚህ መካከል ጉዞ እያደረጉ እያለ 200 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ በመሃል ከባቡሩ ላይ አንድ ነገር ሲወርድ ይሰማሉ፡፡ ጥቂት ቆይቶም ሚሩ አለመኖሯን ያረጋግጣሉ፡፡
ከዚያ በኋላ ሚሩን ለመፈለግ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ይቀራል፡፡ እነሱም ተስፋ ቆርጠው ለውሻ ባለቤቶች ጉዳዩን ካሳወቁ በኋላ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ የሚሩ ዋነኛ ቤተሰቦች ግን በድርጊቱ በጣም በማዘን ማፈላለግ ይቀጥላሉ፡፡ ሆኖም ሚሩ ልትገኝ አልቻለችም፡፡ በአካባቢው ላይ በርካታ የዱር እንስሳት ያሉ በመሆኑ ልትበላ ትችላለች የሚለው ግምት እያየለ መጣ፡፡
ሆኖም ከሁለት ቀናት ተኩል ቆይታ በኋላ ሚሩ ወደመጣችበት መኖሪያ ስፍራ ተመልሳ በአካባቢያቸው በሚገኘው አንድ የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ልትገኝ ችላለች፡፡ በወቅቱም በጣም ተዳክማና እግሯ ተሰብሮ የተገኘች ሲሆን መንጋጋዋም ክፉኛ ተጎድቶ ነበር፡፡
ይህ የሚሩ ተግባር በአንድ በኩል በዚያ አይነት ሁኔታ የመጣችበትን አቅጣጫ ሳትስት 200 ኪሎ ሜትር ተጉዛ መገኘቷ አስገራሚ የተባለ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የጣሏትን ቤተሰብ ፍለጋ እንደዚያ መጓዟ አስገራሚ ተብሏል፡፡ ታዲያ ሚሩ እውነተኛ አፍቃሪ አይደለችም ትላላችሁ?
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2011