ሁለት የእንግሊዝ የፓርላማ አባላት ወደ እስራኤል እንዳይገቡ ተከለከሉ

እስራኤል ሁለት የብሪታንያ የሕዝብ እንደራሴዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ መከልከሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ላሚ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ አስታወቁ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አባላት ወደ እስራኤል ያቀኑት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ነበር ተብሏል።

እስራኤል ባለሥልጣናት ሁለት የሌበር ፓርቲ የፓርላማ አባላት ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ መከልከሏን እና ማሠሯን የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ተችተዋል። “ርምጃው ተቀባይነት የሌለው፣ ፍሬያማ ያልሆነ እና የሚያሳስብ ነው” ከማለት ባለፈ፤ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ከሁለቱም የፓርላማ አባላት ጋር በመገናኘት ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል።

የእስራኤል ሕዝብ እና የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን ለእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አብቲሳም መሐመድ እና ዩዋን ያንግ በእስራኤል ላይ “የጥላቻ ንግግር” በማሰራጨት እንዳይገቡ መከልከላቸውን አስታውቀዋል፡፡

“በዚህ መልኩ የብሪታንያ ፓርላማ አባላትን ማስተናገድ እንደማይቻል ለእስራኤል መንግሥት ባልደረቦቼ ግልፅ አድርጌያለው” ብለዋል ላሚ።

የኤርሊ እና ዉድሊ የፓርላማ አባል የሆኑት ያንግ እና የሼፊልድ ሴንትራል የፓርላማ አባል የሆኑት አብቲሳም ቅዳሜ ዕለት ከሁለት ረዳቶቻቸው ጋር ከሉተን አየር ማረፊያ ወደ እስራኤል በርረዋል። ምርመራ ከተደረገ በኋላ አራቱም ግለሰቦች እንዳይገቡ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሼ አርቤል መከልከላቸውን ባለሥልጣኑ መግለጹን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።

እስራኤል ይፋዊ የሥራ ጉብኝት መደረጉን አላረጋገጠችም ሲል ጋዜጣው ቢዘግብም፣ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አራቱም የፓርላማ ልዑካን ቡድን አባላት መሆናቸውን አረጋግጧል።

“የእንግሊዝ መንግሥት ትኩረቱ ዳግም ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ደም መፋሰሱን ለማስቆም፣ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ እና በጋዛ ያለውን ግጭት ለማስቆም ድርድር ስለማድረግ ነው” ሲሉ ላሚ በመግለጫቸው መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You