ደንቡን በቁርጠኝነት ተግባራዊ ማድረግ – ለዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት

በአዲስ አበባ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች በርካታ ተጠቃሚነትን አስገኝተዋል። ከእነዚህ ውስጥ በወንዝ ዳርቻ በተንጠለጠሉ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን በርካቶች ከአደጋ ስጋት መታደግ አስችሏል ። ከዛሬ ነገ በደራሽ ውሃ እንወሰዳለን›› ከሚል ሰቆቃ ወጥተው በተሻለ የመኖሪያ አካባቢ ‹‹እፎይ!›› ብለው እየኖሩ ይገኛሉ። በካይነት ካላቸው ስጋቶች ርቀው ስለሚገኙም ጤናቸው በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው።

የነዋሪዎቹ አሁናዊ አካባቢ ፤ በካይ ፈሳሽ እና ደረቅ ቆሻሻ አይታይበትም ። የቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸውም በሚገባ ለምቶ ፤ ጽዱ እና አረንጓዴ ሆኖ ሲታይ ለመንፈስ የሚሰጠው ደስታ ይለያል ። ቀደም ሲል ለጤና ጎጂ የነበረው አካባቢ አሁን የመንፈስ ምግብ ሆኖ መመልከት ዘርፈ ብዙ ጠቀሚታን ይዟል።

በተለይ ዕለት በዕለት ሳየው የኖርኩትና፣ አሁንም ድረስ የምመለከተው ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ የሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ነው። ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር አሁን ያለውን ሁኔታ ለመግለጽ ቃላቶች በቂ አይሆኑም። “ማየት ማመን ” ነው እንዲሉ አይቶ መፍረድ ይሻላል።

ከዚህ ቀድም ወንዙና መዳረሻው በፍሳሽና በደረቅ ቆሻሻ የተበከለ ፤ ወደ ወንዙ የሚወርዱ ቦዮችም ብካይ ፈሳሽን የሚይዙ ነበር። አሁን ግን ቦዮቹ ዝናብ ሲሆን ብቻ ካልሆነ ፍሳሽ አይታይባቸውም።

የወንዙ ዳርቻ የተለያዩ አይነት ዛፎችና ሳር እንዲሁም አበባዎች ተተክለውበት ለዓይን ማራኪ ሆኗል። አካባቢው ለመሮጫ እንዲያመች ሆኖ እየተሠራ ይገኛል። በቀጣይም ሌሎች መናፈሻና መዝናኛ የሚሆኑ ማራኪ ስፍራዎች ሊሠሩባቸው የሚችሉበት እውነታ እንዳለም ያመላክታል።

በቀበናም ሆነ በአፍንጮ በር አካባቢ በወንዝ ዳርቻዎች እየተሠሩ ያሉት ክንውኖች ሲታዩም ወንዞችን ከብክለት የሚታደግ ከመሆኑ በተጨማሪ ለመናፈሻና ለመዝናኛ የሚሆን ነው። ይህ በጎ ጅማሮ ወደ ሌሎቹም ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች በፍጥነት ቢሄድ መልካም ነው።

በተጨማሪ እኔ ዕለት በዕለት የማስተውለው በልደታ በኩል በሳር ቤት አልፎ የሚመጣውና በቄራ አድርጎ ወደ አቃቂ የሚሄደው ወንዝ በጣም ድፍርስና ሽታ ያለው ከመሆኑ ሌላ ነጭ አረፋ እየደፈቀ ሲጓዝ ባየሁ ጊዜ ‹‹የወንዝ ዳርቻ ልማቱ መቼ ይሆን ወደ እዚህ አካባቢ የሚመጣው›› እያልኩኝ እንድናፍቅ አድርጎኛል።

አሁን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወንዞች ድፍርስ ከመሆናቸው በተጨማሪ ክፉ ሽታ አላቸው። ከላይ የጠቀስኩት ወንዝ ግን በተለየ ሁኔታ ነጭ አረፋ በብዛት እየደፈቀ ሲፈስ መታየቱ ‹‹ሀይ ባይ የለውም ወይ?›› የሚያስብል ነው። ይህ ነጭ አረፋ መነሻው ከአንድ ፋብሪካ የሚወጣ ፍሳሽ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፤ እርግጠኛ ለመሆን ግን እንደ ተቋም በቁርጠኝነት ተነሳስቶ መነሻው ከየት እንደሆነ መፈተሽ ያስፈልጋል።

ይህ ነጭ አረፋ በቅርቡ መነሻው ከየት እንደሚሆን መረጋገጡ አይቀርም ባይ ነኝ። ምክንያቱም ምንም አይነት በካይ ፍሳሽ ወደ ወንዝ መልቀቅ እንደማይቻል ደንብ ወጥቶ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯልና። ለዚህ ድርጅቱ ራሱ ፍሳሹን መልቀቅ ያቆማል፤ ወይም ክትትል ተደርጎበት ቅጣት ተጥሎበት ፍሳሹን እንዲያቆም ይደረጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

እንዲህ እንድል ያደረገኝ አዲስ አበባ ውስጥ ቆሻሻና ተረፈ ምርት እንዲሁም የተበከለ ፍሳሽ ወደ ወንዝና ወንዝ መዳረሻ መልቀቅ እንደማይቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ደንብ በማርቀቅ ማጽደቁ ነው። ይህ አዲስ ደንብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017 በሚ ል ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

በዚህ ደንብ ውስጥ በወንዝ እና ወንዝ ዳርቻዎች ምንም አይነት በካይ ፈሳሽም ሆነ ደረቅ ቆሻሻ መልቀቅ እንደማይቻል የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ አይነት በካይ ድርጊትም አስተዳደራዊ ቅጣት ተቀምጧል። አስተዳደራዊ የገንዘብ ቅጣቱ ዝቅተኛው ሁለት ሺህ ብር ሲሆን ከፍተኛው እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ነው።

ድርጊቱን ፈጽሞ የተገኘ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ አስተዳደራዊ ቅጣቱን ያልከፈለ እንዲሁም ድርጊቱን በድጋሚ ፈጽሞ የተገኘ ደግሞ እጥፍ ስለሚከፍል ደንብ መተላለፉ እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ሊያስቀጣ የሚችልበት አጋጣሚም አለ ማለት ነው። በደንቡ ላይ የተቀመጡ አብዛኞቹ አስተዳደራዊ ቅጣቶች 300 እና 400 ሺህ ብር የሚያስቀጡ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የውሃ አገልግሎት እንዲቋረጥ የሚያደርግ አስተዳደራዊ ቅጣትንም ይዟል።

ይህን አስተዳደራዊ ቅጣት ተከታትለው በዋናነት የሚያስፈጽሙ ተቋማት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እና የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ናቸው። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሙያዊ በሆነ ሁኔታ ወንዞቹ እንዳይበከሉ ግንዛቤ ይሰጣል፤ ወንዞቹን በክለው የሚገኙትን ደግሞ በምን መልኩና ልክ እንደበከሉት ደረጃ በማውጣት ለቅጣት አወሳሰኑ እንዲረዳ ሙያዊ እገዛ ይሰጣል። የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በበኩሉ ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎች እንዳይኖሩ ግንዛቤ ያስጨብጣል፤ ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል። እንዲሁም ፈጽመው የተገኙትን አስተዳደራዊ ቅጣት በመቅጣት ደንቡን ያስፈጽማል።

አስተዳደራዊ ቅጣቱ ከፍተኛ ቢመስልም እያደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር ሲታይ ደግሞ የቅጣቱን አስፈላጊነት መረዳት ይቻላል። ለማሳያ ያህል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከ90% በላይ ኢንዱስትሪዎች ተገቢውን ህክምና ሳያደርጉ ቆሻሻቸውን በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ ይለቃሉ። ይህ መረጃ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኘ ነው። መረጃው ወንዞች በምን ያህል ልክ እየተበከሉ እንደሆኑ የሚያሳይና በጣም አሳሳቢና አስደንጋጭ የሚባል ነው።

ይህን ያልኩበት ምክንያት ከኢንዱስትሪዎቹ የሚወጣው ቆሻሻ ከሆስፒታልና ከሌሎች ተቋማት እንዲሁም ከመኖሪያ ቤቶች ከሚወጡ በካይ ከሆኑ ቆሻሻዎች ጋር ተዳምሮ የተለያዩ መርዛማ ኬሚካሎችና ከባድ ብረቶች (heavy metals)፣ መድሃኒትን የተላመዱ ባክቴሪያዎች ፤ ቫይረስና ፈንገሶች በወንዞቹ እንዲሁም በወንዞቹ መዳረሻ እንዲኖር ያደርጋልና ነው።

በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ለኮሌራ፣ ለታይፎይድ፣ ለኢንፌክሽኖች እና ለተቅማጥ እንዲሁም ለውሃ ወለድ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ይጋለጣሉ። በተለይ መርዛማ ኬሚካሎችና ከባድ ብረቶች ‹‹ካንሰር›› በሽታን የሚያስከትሉ ናቸው ። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንደተገኘው መረጃ ።

የአዲስ አበባ ከተማ ወንዞች ከመኖሪያ ቤት፣ ከአምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚመነጩ የተለያዩ በካይ ነገሮች ምክንያት ለምንም አይነት አገልግሎት የማይውሉ ናቸው። በከተማዋ ሰባ ስድስት ወንዞች አሉ፤ ሁሉም በቆሻሻ የተበከሉ ናቸው። ሰባ ስድስቱም ወንዞች የተበከሉ ሆነው ወደ ትንሹ እና ትልቁ የአቃቂ ወንዝ የሚገቡ ሲሆን አባ ሳሙኤል ግድብ በመገናኘት ወደ ታችኛው ተፋሰስ ይጓዛሉ። በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ ነዋሪዎች ደግሞ በከፍተኛ መጠን በተበከለውን ውሃ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲጠቀሙ ይስተዋላል።

ከመኖሪያ፣ ከማምረቻ እና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መንገድ ዳር የዝናብ ውሃ መውረጃ የተገናኙ ፍሳሾች መዳረሻቸው ወንዝ ነው። ይህ በመሆኑም በቀጣይ መፍትሔ ማድረግ ይገባል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 180/2017 አውጥቶ ተግባራዊ ለሚያደርጉ ተቋማት ኃላፊነት በመስጠት አፈጻጸሙን ይከታተላል። ተቋማቱም ደንቡን ለማስፈጸም ተግተው ይሠራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚያ መለስ ግን መሠራት የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።

እነሱም ደንቡን ለማስፈጸም አጋዥ እንዲሆን በመንግሥት በኩል ፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማትን ተደራሽ ማድረግ፣ ከመንገድ ዳር ፍሳሻቸውን ያገናኙ መኖሪያዎችና ተቋማት በሙሉ እንዲያላቅቁ ማድረግ፣ ደረጃውን የጠበቀ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ እንዲኖር ማስቻል፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ እንደ አጀማመሩ ሁሉ ተስፋፍቶ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በከተማዋ የሚገኙ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በምርት ሂደት የሚፈጠረውን ተረፈ ምርት ወይም ውጋጅ ቆሻሻ በአግባቡ አክሞ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ማድረግ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸትና ማገዝ ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት፣ የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGO) እና የልማት ድርጅቶች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች አካባቢን ከብክለት ለመከላከልና የተፈጥሮ ሀብትን ለመንከባከብ እንዲሁም ወንዝና የወንዝ ዳርቻዎች እንዳይበከሉ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017 በሚል ደንግጎ ደንቡን ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። አስተዳደሩ በከተማዋ የሚገኙትን የአምራችና አገልግሎት ሰጪ ኢንዱስትሪ ተቋማት ተወካዮችን በማዘጋጃ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰብስቦ በደንቡ መሠረት ቅጣት እንዳያገኛቸው የሚያመነጩትን የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ እንዲያከማቹ እና መልሰው ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ እንዲፈልጉ አሳስቧቸዋል።

የተቋማቱ ተወካዮች የቅጣት መጠኑ ከፍተኛነትን በመጥቀስ፣ ‹‹የማስተካከያ ጊዜ ይሰጠን›› የሚል ሃሳብ አንስተዋል። አብዛኞቹ ተረፈ ምርታቸውን ወደ ወንዝ ለመልቀቅ እንዲያመቻቸው በማሰብ በወንዝ ዳርቻ ሆን ብለው ተቋማቸውን የመሠረቱ በመሆናቸው በፍጥነት ማስተካከል ይገባቸዋል። ምክንያቱም ደንቡ ከመውጣቱ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ተረፈ ምርታቸውን ወደ ወንዝና ወንዝ መዳረሻ እንዳይለቁ ሲነገራቸው ቆይቷልና።

አስተዳደሩ ባሳሰበው መሠረት ተቋማቱ ካላስተካከሉ ቅጣቱን በቁርጠኝነት ተግባራዊ ማድረግ ይገባዋል። በራሳቸው አቅም ማስተካከል ካልቻሉ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር የሚያስተካክሉበት መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን ዘርፋቸውን መቀየር ይችላሉ። ምክንያቱም የተበከለ ተረፈ ምርታቸው በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ መሆኑን ከላይ በጥቂቱም ቢሆን ለማመልከት ተሞክሯል። ስለሆነም ደንቡን በቁርጠኝነት ተግባራዊ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ያስፈልጋል።

ደንቡን ተግባራዊ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት እንዳይኖር ከሚያደርጉ ስጋቶቼ ውስጥ አንዱን ላንሳና ጽሑፌን ላጠናቅ። ይኸውም ደንቡን የሚያስፈጽሙ አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች ደንቡን ከሚተላለፉ አካላት ጋር በጥቅም በመተሳሰር ድርጊቱን እንዳያስቀጥሉና ዕቅዱን እንዳያደናቅፉ ነው።

አሠራሩን በመከታተልና በመቆጣጠር ቅጣት የማስከፈል ኃላፊነት የተሰጣቸው የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ‹‹ፓራ ሚሊቴሪ›› ኦፊሰሮች ለዚህ ተግባር በጣም የተጋለጡ መሆናቸው ይስተዋላል። በመሆኑም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ፓራ ሚሊቴሪ ኦፊሰሮቹን መከታተል፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በኩል እያንዳንዱ ተቋማት ዘንድ በመድረስ የተረፈ ምርት አወጋገድ ሥርዓታቸውን መፈተሽ ይገባል ባይ ነኝ።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You