
«ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አደርጋለሁ» – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፡– የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሬዚዳንትነት የሥልጣን ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ትናንት ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ባለፈው አንድ ወር ገደማ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት፣ የፕሪቶርያን ስምምነትና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ምክር በማከል ሰፊ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የአቶ ጌታቸው ረዳ የሥልጣን ዘመን በሕጉ መሠረት ሲያበቃ የሚቀሩ ቁልፍ ሥራዎችን ለማከናወን ጊዜያዊ መንግሥቱ መቀጠል አለበት የሚል ድምዳሜ በመያዝ ሽግግሩን ማን መርቶ ከግብ ሊያደርስ ይችላል የሚሉ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሰላማዊ መንገድ በአዲስ ባህል የሥልጣን ሽግግሩንና ቅብብሎሹን ለማካሄድ የተዘጋጀ ፕሮግራም በይፋ አከናውነናል ብለዋል።
ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአቶ ጌታቸው ረዳ ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ በመቆየታቸው የነበሩ ድካሞችንና ጥንካሬዎችን በግልጽ እንደሚገነዘቡም በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።
በዚህም ምክንያት አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት በብዙ አካላት የታመነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ሕዝብ የጠማውን ሰላምና ልማት እንደ ሌሎች ወንድሞቹ ወጥቶ የመግባት መሻት በማሳካት ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እጅግ ጠቃሚ ነገር ሠርቶ ለማለፍ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ኃላፊነቶች ለመወጣት በሙሉ ኃይሉ እና በትጋት እንደሚሠራ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ተገልጿል። እነዚህም የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት፣ በጅምር ያለው እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር ማድረግ፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ፤ በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ፤ ለሕዝብ ደህንነት፣ ለሰላም እና ለጸጥታ ጠንቅ የሆኑ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፤ ለዚህም ተገቢውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት።
መደበኛ የልማት ሥራዎች፣ መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችና የመንግሥት ግንባታ ሥራዎች እንዲሳለጡ ፤ ከሕገ መንግሥታዊ እና ከሕጋዊ ሥርዓት፣ ከሀገር ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶርያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ፤ ከክልሉ ከዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን ፤ የሲቪል እና የፖከቲካ መብቶች ተግባራዊ የሆኑበት፣ የፖከቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ አውድ እንዲፈጠር መሥራት።
የክልሉ ሕዝብ፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊ የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ የክልሉ መንግሥታዊ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ሕዝቦች ትስስር እና መልካም ግንኙነት የሚያጠናከሩ፣ ሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ናቸው ። እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ኃላፊነቶች አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በትጋት እና በታማኝነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል ፤ ፊርማቸውንም አኑረዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም