‹‹የአሁኗን አፍሪካን ወደ ፊት ማሻገር የወጣቶች ድርሻ ነው›› -ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ ፡- ቀደምት የአፍሪካ መሪዎች እና ታላላቅ አባቶች ለአፍሪካ ነፃነት ታግለው እዚህ ያደረሷትን አፍሪካን ወደፊት ማሻገር የወጣቶች ድርሻ ነው ሲሉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የፓን አፍሪካን የወጣቶች አመራር ጉባኤ ትናንት በዓድዋ መታሰቢያ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር፤ ጭካኔ የተሞላበት የባርነት ዘመንን በመጋፈጥ ትልቅ ፈተናን አሳልፈው እዚህ ያደረሷትን የአፍሪካ ቀደምት መሪዎቿና ታላላቅ አባቶቻችን ናቸው፡፡ እዚህ የደረሰችውን አሕጉር ደግሞ ወደፊት ማሻገር የወጣቶች ድርሻ ነው ብለዋል፡፡

በወቅቱ የጽናት ማሳያ የነበሩ የአፍሪካ መሪዎች የነበራቸው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ መፃዒዋን አፍሪካ ለመገንባት ወጣቶች ከፍተኛ ድርሻ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ታላላቅ መሪዎች በነፍጥ ብቻ ሳይሆን በሃሳብ፣ በታላቅ ጥበብ ባደረጉት ተጋድሎ ለአዲሲቷ አፍሪካ መፀነስ እና ለአፍሪካ ኅብረት መመሥረት ምክንያት መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ እየጨመረ በመጣው የጂኦፖለቲካል ውድድር እና የፖለቲካል ውጥረት  ወጣቶችን በዋነኛነት የሚጠቀም መሆኑን አንስተው፤ ይህም ባለፉት ጊዜያት በታሪክ የምናስታውሰው ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን አለመስማማት እና ተስፋ መቁረጥ በፊትም፣ አሁንም በፍጹም መፍትሔ ሆኖ ሊቀመጥ አይችልም ሲሉ መክረዋል፡፡

አፍሪካ በፍጥነት እያደገ የመጣ የሕዝብ ቁጥር፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶች እና በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሏት ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እነዚህ ሀብቶች ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እድገት ትልቅ አስዋፅዖ እንዳላቸው ገልጸዋል ፡፡

ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የወጣት ተወካዮች በዚህ የፓንአፍሪካኒዝም የወጣቶች ጉባኤ ላይ መገኘት የተሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንት ታዬ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ሥራ አጥነት፣ የትምህርት ተደራሽነት ችግር፣ ጤና መጓደል፣ የአየር ንብረት ለውጥ ወጣቶችን የሚፈትኑ ተግዳሮት ናቸው፡፡ የፖለቲካ ውጥረቶች እና ግጭቶች ወጣቶችን እየፈተኑ ያሉ ይገኛሉ፡፡

የአሁኑ ትውልድ በሀሳብ የሚያምን መሪ መሆን፣ ያለፉትን ድንቅ መሪዎች በመከተልና አሁን ያሉ መሪዎችን ለመረከብ ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል ፡፡

ጊዜው መፃዒዋን አፍሪካ የምናልምበት ሳይሆን የምንሠራበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ አፍሪካ አሁን ላይ የሚገጥማትን ዓለም አቀፍ ፈተና ለመወጣት ያሏትን ሀብቶች ኢኮኖሚን ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በቴክኖሎጂ፣ ሥራ ፈጠራ፣ ጥራት ያለው ትምህርት እና ክህሎትን ማሳደግ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለአፍሪካ የሚያስፈልጋት ትብብርና በጋራ መሥራት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር እሳቤን ተግባራዊ ማድረግ ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል። የመደመር እሳቤ ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯንም ጠቁመው፤ በምግብ ራስን ለመቻል የሌማት ትሩፋት የተሰኘ መርሐ ግብር ቀርፃ ተግባራዊ በማድረጓ በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበች መሆኗን ተናግረዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የምንመኛትን አፍሪካ እውን ማድረግ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የታነፀ ትውልድ ማፍራት ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከ30 ዓመት በታች መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ኃይል በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ እርስ በርስ የተሳሰረችና የበለፀገች አፍሪካን እውን ማድረግ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የአሁኑ ትውልድም የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በውስጣቸው በማስረጽ በአንድነት ለአሕጉሪቷ ብልፅግና ሊሠሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የፓን አፍሪካ ወጣት አመራሮች ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤ የጉባኤው ዋና ዓላማ የአፍሪካውያን ወጣቶች በዘላቂ ልማት፣ በሰላም እና በሌሎች አሕጉራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩ መሆኑን ተናግረዋል። የወጣቶችን ትስስር በማጠናከር ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት እንዲሠሩ ለማነቃቃት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በጉባኤውም ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተወካይ ወጣቶች በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You