‹‹ የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ዕድገቷን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ያመላክታል›› – የዓባይ ውሃ ተደራዳሪ ተ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)

-የዓባይ ውሃ ተደራዳሪ ተ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ መምህር

ሰሞኑን አፍሪካውያን ብድር ቢከለከሉ፣ የዲፕሎማሲ ጫና ቢደረግባቸው፣ የራሳቸውን ሃብት በዜጎቻቸው ማልማት እንደሚችሉ በተግባር የታየበት የዓባይ ግድብ፤ ሊመረቅ ጫፍ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አብስረዋል። የመላው አፍሪካ መቻል የታየበት፤ የአፍሪካውያን ኩራት የሆነው ይህ ግድብ ብዙ መከራ የታየበት መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ግብፅን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትም አመላክተዋል።

እነዚህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳቦች የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ይስማሙባቸዋል። ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር አብረው የዓባይ ግድብ እንዲገነባ ከፊት ቆመው እየታገሉ ብዙ መከራዎችን ያሳለፉት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ መምህር እና የዓባይ ውሃ ተደራዳሪ ተ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን ለመጠቀም ብዙ ፈተናዎችን ማለፏን አስታውሰዋል። የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ልማቷን በማስፋፋት ዕድገቷን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን የሚያመለክት መሆኑንም ተናግረዋል።

ወደ ፊትም የሌሎችን ሀገሮች በከፋ ጉዳት ላይ የማይጥል መሆኑን ባረጋገጠ መልኩ ልማቷን እንደምትቀጥል ተደራዳሪው ተ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) አመላክተዋል። እስከ አሁን ስታካሂድ የነበረው የውሃ አጠቃቀም ይህንኑ መሠረት ያደረገ እንደነበር በማስታወስ፤ ወደ ፊት ሊገነቡ የታሰቡትም ሆኑ መገንባት ያለባቸው የኢትዮጵያን ልማት እና የኢኮኖሚ ሉዑዋላዊነት ከፍ የሚያደርጉ፤ ሕዝቡን የሚጠቅሙ ግድቦች የሚሠሩት ኢትዮጵያን እንደሚጠቅሙ ታስቦ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ላይም የከፋ ጉዳት እንደማያስከትል ታቅዶባቸው እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይም የውሃ ሃብቷን በምታለማበት ጊዜ በምንም መልኩ ሶስተኛ ወገን ገብቶ ይህንን ብታደርጉ ብሎ የሩቅም ሆነ የቅርብ አካላት ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚሞክርበት ዕድል ዝግ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል። ሌሎች ሀገሮችም ይህንኑ ተረድተው፤ ሊያምኗት እና ተፅዕኖ ከመፍጠር ይልቅ ከጎኖ መቆም እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ተደራዳሪ ተ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፤ በቀጣይም ያለምንም ጥርጥር ለአገራቸው ለኢትዮጵያ ለወገናቸው ወደ ኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል። ‹‹በእኛ ዘመን እኛ ትክክለኛ ነን ብለን ያመንበትን ሠርተን ለማለፍ ዝግጁ ሆነናል። የሠራነውንም ውጤቱን ለማየት በቅተናል። ይህ ተጠቃሽ ታሪክ ሆኗል። ወደፊትም እንሠራለን የሚል እምነት አለኝ ›› ብለዋል።

ውሃውን የመጠቀም ጉዳይ የሚቀጥል እንጂ፤ በዚሁ የሚቆም አለመሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ እርሳቸው እና ጓደኞቻቸው በሀገር ፍቅር ስሜት ለኢትዮጵያ ክብር የሚቻላቸውን እንዳደረጉት ሁሉ በቀጣይ ዘመንም መጪው ትውልድ ሌሎች ከዚህም የበለጡ ችግሮች ቢያጋጥሙ በፅናት ችግሮችን ለመፍታት እና የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዓባይ ግድብን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ መምህር እና የዓባይ ውሃ ተደራዳሪ ተ/ፕ/ር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ ለመጠናቀቅ ጫፍ መድረሱ የፈጠረቦት ስሜት ምን ይመስላል?

ተ/ፕ/ር ያዕቆብ (ዶ/ር)፡- የዓባይ ግድብ በሙሉ ስሜት እና በሙሉ ቁርጠኝነት በመንፈስም በገንዘብም ሕዝብን ከዳር እስከ ዳር ያንቀሳቀሰ እና ሁሉንም ያሳተፈ ነው። ሁሉም በደስታ ስሜት ውስጥ እንደሚሆን አምናለሁ። ጠቅለል ባለ መልኩ ከኢትዮጵያዊነት አንፃር ሲታይ ውጤት ላይ መድረሱ በጣም አስደሳች ነው።

በሁለተኛ ደረጃ እኔ የዓባይ ውሃ ተመራማሪ እና ለረዥም ዘመናት የሃይድሮ ፖለቲክስ አስተማሪ ሆኜ ቆይቻለሁ። ግብፅ እና ኢትዮጵያ በውሃ ፖለቲካ የነበሩበትን ሁኔታ በደንብ አውቃለሁ። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያን ድል አድራጊነት ያመላከተ ግድብ፤ እንዲህ ዓይነት ውጤት ላይ መድረሱ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል። ይህንን መደበቅ አልችልም።

እንዲሁም ከሌሎች ተደራዳሪ የኢትዮጵያ ጓደኞቼ ጋር ተሰልፌ የዓባይ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ግድብ ጉዳይ ላይ አተኩሬ ብዙ ነገሮችን ሥሠራ ቆይቻለሁ። ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ባለቤት በመሆኗ ከወንዙ ጥቅም ማግኘት መብቷ መሆኑ እንዲረጋገጥ፤ ግድቡ እንዲጠናቀቅ እና ግድቡ የኢትዮጵያ በውሃ ሃብት የመጠቀም መብቷ እንደሆነ ማሳያ እንዲሆን አንድ ላይ በድርድሩ ተሰልፌ የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ።

በተደራዳሪዎች ጥረት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በአጠቃላይ በሕዝቡ ድጋፍ ይህ ውጤት መጥቷል። ይህ መላው ኢትዮጵያውያንን በጣም ደስ ያሰኛል የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ዓይነት ርብርብ የኢትዮጵያን ጥቅም እና አንድነት የሚያስከብሩ ሌሎችም ሥራዎችን ለመሥራት መረባረብ ይገባል። ይህ ግድብ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት አዳጋች እንደማይሆን እና ኢትዮጵያውያን በልማት ሥራዎች ላይም ለመረባረብ ወደ ኋላ እንደማይሉ የሚያሳይ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል።

አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚኖረው መልዕክት ምንድን ነው?

ተ/ፕ/ር ያዕቆብ (ዶ/ር)፡- ይህንን ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጫፍ እስከ ጫፍ መደገፉ እና ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት መሥራቷ ትርጉሙ ብዙ ነው። በኢትዮጵያውያን ዓቅም የተጀመረው ግድብ ሲጠናቀቅ፤ በዓለም ፊት መታየቱ ቀላል አይደለም። በዋናነት ኢትዮጵያ ልማቷን ለማስፋፋት እና ዕድገቷን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ሃሳብ ላይ መድረሷን የሚያመለክት ነው። ብድርም ሆነ ርዳታ ባናገኝም፣ በተለያየ መልኩ በተለያዩ ጊዜያት ጫናዎች ቢደረጉብንም፣ በራሳችን ሃብት ዜጎቻችንን አስተባብረን ማልማት ችለናል።

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥም ሆና ኢትዮጵያ በምንም ዓይነት ሌሎቹን ለመጉዳት አስባ ሳይሆን፤ እንደውም ሌሎቹ መጠቀም የሚችሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብታ ግድቡን እየሠራች ስኬታማ መሆኗ የሚያስመሰግናት ነው። ምንም እንኳ ግብፅ በብዙ መልኩ ለመግፋት ብትሞክርም፤ የዓባይ ግድብ ግብፅን በከፋ መልኩ እንዳይጎዳ ታስቦበት በመሠራቱ፤ ይህ አሰራር በናይል ተፋሰስም ሆነ በሌሎች ሀገሮች የተለመደ አካሔድ እንዲሆን የሚጠቁም ነው።

ሌሎች ሀገሮችም የሚሠሯቸው ልማቶች ራሳቸውን በሚጠቅም መልኩ ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎችን በጉልህ ሳይጎዱ ማከናወን እንዳለባቸው እና ኢትዮጵያም ይህንን በማድረጓ ሌሎችም የተፋሰሱን ሀገሮች የማስተባበር ዕድል ማግኘቷን የሚያመላክት ነው። ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው እና በሌሎች ሀገሮችም እንደምሳሌ መወሰድ ያለበት ጉዳይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በዓባይ ግድብ ዙሪያ ስታካሂዱት የነበረው ድርድር ምን መልክ ነበረው?

ተ/ፕ/ር ያዕቆብ (ዶ/ር)፡- በቅድሚያ ግብፅ በኋላ ሱዳንም ተደርባ ጠላት ሆነው ዘመዶቻችን ናቸው የሚሏቸውን አንዳንድ የአረብ ሀገራት እንደዚሁም ግብፅን በደንበኝነት የሚያዩ ውስን ሀገሮች በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥሩት ጫና ሲዘንብ እንደነበር ይታወቃል። እኛ ተደራዳሪዎች ደግሞ ግድቡ ገና በመሬት ላይ እየተሠራ በጅምር ላይ እያለ፤ ይህንን ግድብ መሥራት የኢትዮጵያ መብት መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለብን ተማምነን ነበር።

ኢትዮጵያ ግድቡን ስትገነባ የማንንም የሌላ ሀገር ስጦታ፣ ርዳታም ሆነ ተፅዕኖ ሊኖርባት እንደማይገባ ተነጋግረናል። ድርድሩን ባደረግንባቸው ጊዜያት በሙሉ በዋናነት ስንጠብቅ የነበረውና የምንከላከለው ኢትዮጵያ በግብፅም ሆነ በግብፅ አጋሮች በማናቸውም በሌሎች ሀገሮችም ሆነ ድርጅቶች ተፅዕኖ ሥር ሆና ምንም መሥራት ስለማትችል፤ ይህ ተፅዕኖ እንዳይኖርባት አስቀድመን መጋፈጥ ዋና ተግባራችን ሊሆን እንደሚገባ ተግባብተናል።

በድርድሩ ሂደት በመመካከር እና በድርድሩ አውድ ላይ ከምንሳተፍባቸው ጊዜያት በበለጠ ዕውቀት በማሰባሰብ፤ አስፈላጊ መረጃዎችን በማቀናጀት፤ እርስ በርሳችን በመመካከር የምናሳልፈው ጊዜ ረዥም ነበር። በያዝነው እውቀት ላይ ተመሥርተን የኢትዮጵያን አቋም ብቻ  ሳይሆን ኢትዮጵያ አቋሟን በምን ዓይነት መንገድ መግለፅ እንዳለባት አስበን ስናስቀምጥ ቆይተናል። አቋሟ በነጠረ አስተሳሰብ፣ በጥበብ እና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ተግባብተን፤ ጉዳዮችን በደንብ ነቅሰን እያወጣን ይዘን መቅረባችን ድርድሩን በፈለግንበት መንገድ ማስኬድ እና ውጤቱንም የተሳካ እንዲሆን አስችሏል።

ግብፅም አካሄዷ ቀላል አልነበረም። በብዙ መልኩ ተዘጋጅታ አስቀድመን እንድንፈርማቸው የምትፈልጋቸው የስምምነት ሃሳቦች ነበሩ። አንዱ ሃሳብ ሲፈርስባት ሌላ ሃሳብ እያመጣች በብዙ መልኩ ለመፈታተን ሞክራለች። ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ ቀለበት ውስጥ ለመክተት ብዙ ሙከራዎችን አድርጋለች። በእኛ በኩል እነዛን ሃሳቦች በመለየት ጉዳዮቻቸው እና ኢትዮጵያን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከቱ ሁኔታዎች በምንም ዓይነት መስኮት ወይም ቀዳዳ እንዳያስገቡ ተጠንቅቀን ሠርተናል።

በድርድሩ ግድቡ በኢትዮጵያ በሉዑዋላዊ ግዛት ውስጥ የሚገነባ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ባለሙሉ መብት መሆኗን አሥምረንበት ይህንኑ ግብፆችም ሆኑ የግብፅ ወገኖች እንዲረዱት ለማድረግ የተሠራው ሥራም ውጤት አምጥቷል። ከግድቡ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ክርክሮችም ሆኑ ሃሳቦች በዚህ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ማድረግ ችለናል።

በኢትዮጵያ በኩል የተከራካሪዎቹ ዕውቀት፣ ክህሎት እና የሀገር ፍቅር እንዲሁም የመንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፍ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደራዳሪዎችን እና መንግሥትን የሚጠብቅበትን በመወጣቱ፤ እነዚህ ሁሉ ሲጠቃለሉ ለእዚህ ውጤት አብቅቶናል ማለት እችላለሁ። በዋናነት ደግሞ ሕዝቡ ሲያደርግ የነበረው ድጋፍ የኢትዮጵያ መብት አስከብሮ ግድቡ እንዲጠናቀቅ ዋነኛው መንገድ መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ሁለቱ ሀገራት በተለይ ግብፆች በድርድሩ ላይ ያሳዩዋቸው የነበሩ አቋሞችን እንዴት ይገልፁዋቸዋል?

ተ/ፕ/ር ያዕቆብ (ዶ/ር)፡- ግብፅ ቀደም ሲል ከእንግሊዝ እና ከሱዳን ጋር ያደረገቻቸው ስምምነቶች ነበሩ። ያ የቅኝ ግዛት ስምምነታቸው ውሃውን በተመለከተ ግብፅ የተፈጥሮ ሃብቷ እንደሆነ የሚያስቀምጥ ነው። ውሃው ሙሉ ለሙሉ የመጠቀም መብት ያላቸው ሱዳን እና ግብፅ ናቸው በሚል ያስቀመጡት ስምምነት እንዲጠበቅ ግብፅ ትፈልጋለች። ስለዚህ ሱዳኖች እና እነርሱ ብቻ መጠቀም ይፈልጉ ነበር። ደጋግመው የሚገልፁት እነዛ ስምምነቶች እንዲፀኑ ነበር።

በእነርሱ በኩል የሚቀርበው ሃሳብ ፍትሃዊነት የጎደላቸው እና ተቀባይነት ሊኖራቸው የማይችል ሃሳቦች ናቸው። በኢትዮጵያ በኩል ግን የሚቀርበው ምክንያታዊ እና ትክክለኛ ሃሳብ ነበር። በእኛ በኩል የተሰጣቸው መልስ፤ በግብፅ የሚጠቀሱት ስምምነቶች ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት በመሆኑ፤ ኢትዮጵያን አይመለከቱም። ሁለተኛ ኢትዮጵያ እነዛን ስምምነቶች አሉ ብላ መቀበል አትችልም።

ምክንያቱም እነዚህ ስምምነቶች የሚያስቀ ምጧቸው ሃሳቦች የኢትዮጵያን መብቶች የሚፃረሩ በመሆናቸው፤ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ይህንን ሊቀበሉ አይችሉም። ኢትዮጵያም ይህንን ስምምነት ልትሸከም አትችልም የሚል ፅኑ አቋም በመያዝ በዚህ ላይ መደራደር እንደማይችሉ አሳውቀናቸዋል። ደጋግመን የኢትዮጵያን መብት ማስከበር የግድ መሆኑን አስረግጠን ነግረናቸዋል።

ሌላው ግብፆች በድርድሩ ላይ የሚሔዱበት መንገድ፤ በተቻለ መጠን አሞላሉን እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲወስኑ ለማድረግ በብዙ መልኩ ሞክረዋል። በተጨማሪ ግድቡን ኢትዮጵያ ብቻዋን ሳይሆን ከእነርሱ ጋር አብራ እንድታስተዳር፤ ይህንንም ኢትዮጵያ እንድትቀበል ፍላጎት እንዳላቸውም ሲያመላክቱ ነበር።

እንዲሁም በየጊዜው ከውሃው ጋር ተያይዞ በግብፅ በኩል ያለውን መረጃ ኢትዮጵያ ሳትቀበል፤ ከግድቡ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም መረጃ ኢትዮጵያ በነፃ ለግብፅ እንድትሰጥ እና ሌሎችም ተጨማሪ የእነርሱን ጥቅም ብቻ የሚያስከብሩ ፍላጎቶች ነበራቸው። እነኚህ ሁሉ ፍላጎቶች የኢትዮጵያን መብት የሚፃረሩ በመሆናቸው ሊሆኑ እንደማይችሉ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ኢትዮጵያ በግድቧ ላይ ውሃ የምትሞላበት ሂደት ራሷን በሚጠቅም ሌሎችን በማይጎዳ መንገድ ታደርጋለች። ከዚህ ውጪ የግብፅን ፍላጎት ተቀብላ ተፅዕኖ ስር እንደማትወድቅ ግብፆች እንዲረዱት ተሠርቷል። በዚህ ላይ ሰፊ ክርክር ቢያደርጉም በግድቡ አሞላል ሂደት ላይ ይህን አድርጉ ያንን አታድርጉ ማለት እንደማይችሉ ተገልፆላቸው፤ ባይዋጥላቸውም ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ ፍላጎት ግድቡ እንዲሞላ ማድረግ ተችሏል።

ግድቡን አብረን እናስተዳድር ለሚለው ጥያቄያቸውም ጭራሽ ሊሆን እንደማይችል በማሳወቅ፤ ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሠራችውን ግድብ ሌሎች መጥተው ሊያስተዳድሩ የሚችሉበት ምክንያት እንደሌለ እንዲያውቁት ተነግሯቸዋል። ኢትዮጵያ በጥንቃቄ እንደገነባችው በጥንቃቄ ራሷ ታስተዳድረዋለች የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ይህንን በተመለከተም ብዙ ጊዜ የተከራከሩት ግብፆች፤ በመጨረሻም ይህ ሊሆን እንደማይችል እንዲረዱት በመንገር በዚህ መልኩ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ደጋግመው ከማንሳት እንዲቆጠቡ እና በዚህ ላይ ምላሽ ማግኘት እንደማይችሉ የማስገንዘብ ሥራ ተሠርቷል።

ሆኖም በቀጣይ መረጃ ይሰጠን በሚል ላቀረቡት ጥያቄም በኢትዮጵያ ያለው መረጃ ግብፅን እስከጠቀመ ኢትዮጵያን እስካልጎዳ ድረስ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗ ተነግሯቸዋል። ነገር ግን በግብፆች በኩል ያለው መረጃ ሳይሰጡ እርሷ መስጠት እንደማትችል እና መረጃ መሰጣጣት የሁለቱም አካላት ትብብር መሆኑን ተነግሯቸው ተግባብተዋል።

እነዚህ የክርክር ጉዳዮች አሁን ሲነገሩ በቀላሉ የተጠቀለሉ ቢመስሉም፤ በጣም ፈታኝ ቀን እና ለሊት ሙግት የተካሔደባቸው ናቸው። አልፎ ተርፎ ሽምግልና የተገባባቸው ሃሳቦች ናቸው። በዚሁ መልክ ተደራዳሪዎችም ሆኑ መንግሥት በከፍተኛ ትዕግስት፣ ዕውቀት እና በታላቅ ጥበብ መንቀሳቀስ ስለቻለ ለኢትዮጵያ የሚፈለገው ውጤት መጥቷል።

አዲስ ዘመን፡- ድርድሩን ስታካሂዱ የነበሩ አጋጣሚዎች ካሉ አስታውሰው ቢገልፁልን ?

ተ/ፕ/ር ያዕቆብ (ዶ/ር)፡- በጣም በርካታ ለሊቶች እና በጣም በርካታ አድካሚ ቀኖች አልፈዋል። አንዳንዴ በተመሳሳይ መልኩ ሳምንታት ይቆጠሩ ነበር። ሁሉም ጊዜያት እጅግ ፈታኝ ነበሩ። አንዱን ከአንዱ ለይቶ አስታውሶ መናገር ይከብዳል። በዋናነት ሂደቱ እጅግ አድካሚ፣ ብዙ ልፋትን፣ ከፍተኛ ትዕግስትን የሚጠይቅ ቢሆንም፤ በመጨረሻ በድል መወጣት መቻላችን እጅግ አስደሳች ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቀጣይ የውሃ ሃብቷን በምን መልክ መጠቀም አለባት ይላሉ?

ተ/ፕ/ር ያዕቆብ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷ ከልማት ፍላጎቷ ጋር አብሮ የሚሔድ ነው። በመሆኑም ምንጊዜም ቢሆን ይህንን የሃብት አጠቃቀም የሌሎችን ሀገሮች በከፋ ጉዳት ላይ የማይጥል መሆኑን ባረጋገጠ መልኩ መቀጠል አለበት። የሚል እምነት አለኝ። እስከ አሁን ድረስ ስታካሂድ የነበረው የውሃ አጠቃቀም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነበር።

ወደ ፊት ሊገነቡ የታሰቡትም ሆኑ መገንባት ያለባቸው የኢትዮጵያን ልማት ከፍ የሚያደርጉ፡ ሕዝቡን የሚጠቅሙ እና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዑዋላዊነት ከፍ የሚያደርጉ ግድቦች ሲሠሩ ቀጣይነት ባለው መልኩ፤ ኢትዮጵያን የሚጠቅሙ በምንም ዓይነት ማንም ጣልቃ በማይገባበት መልኩ የሚከወኑ መሆን አለባቸው።

የውሃ ሃብቷን ኢትዮጵያ በምትጠቀምበት ጊዜ በምንም መልኩ ሶስተኛ ወገን ገብቶ ይህንን ብታደርጉ ብሎ ማንም የሩቅም ሆነ የቅርብ አካላት መጥቶ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚሞክርበት ዕድል መፈጠር የለበትም። በዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በምንም መልኩ ለሌሎች ጣልቃ ገብነት በራችን ዝግ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ በውሃው ራሷንም ጠቅማ ሌሎችን የምትጎዳበት ምንም ዓይነት ሁኔታ አይኖርም የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም በእርሶ በኩል ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚገቡት ቃል ካለ?

ተ/ፕ/ር ያዕቆብ (ዶ/ር)፡- ያለምንም ጥርጥር ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ለወገናችን ወደ ኋላ የምንልበት ሁኔታ የለም። በእኛ ዘመን እኛ ትክክለኛ ነን ብለን ያመንበትን ሠርተን ለማለፍ ዝግጁ ነን። ይህ ተጠቃሽ ታሪክ ሆኗል የሚል እምነት አለኝ። እኔም ጓደኞቼም በሀገር ፍቅር ስሜት፣ ለኢትዮጵያ ክብር የሚቻለንን ሁሉ አድርገናል። በቀጣይ ዘመንም የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።

መጪው ትውልድ ሌሎችም ከዚህም የበለጡ ችግሮች ቢያጋጥሙ በፅናት ችግሮችን መፍታት አለበት። አሁንም ውሃውን የመጠቀም ጉዳይ የሚቀጥል እንጂ በዚሁ የሚቆም አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በውሃ ሃብታችን ለመጠቀም በቀጣይም ሰፊ ሥራዎች መሰራት አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም እናመሰግናለን።

ተ/ፕ/ር ያዕቆብ (ዶ/ር)፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You