
አዲስ አበባ፦ በሸገር ከተማ ባለፉት ሁለት ዓመታት 300 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የኢንቨስትመንት ካፒታል መመዝገቡን የከተማ አስተዳደሩ ገለፀ። የሸገር ኢንቨስትመንት ኤክስፖ በትናንትናው እለት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የውጭ ሀገር አምባሳደሮች እና ባለሀብቶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።
በእለቱም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሸገር ከተማ ከንቲባ (ዶ/ር) ተሾመ አዱኛ በከተማዋ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ የኢንቨስትመንት ሥራ ተሠርቷል። በዚህም በከተማዋ 300 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የኢንቨስትመንት ካፒታል ተመዝግቧል።
ከንቲባው ከተማዋ ከተመሠረተች ጥቂት ዓመት ቢሆንም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልፀው፤ ለአብነትም 40 ቢሊዮን ብር ብድር ለወጣቶች ማቅረብ ተችሏል። ሸገር ከተማ ስትመሠረት ምንም አይነት ሆስፒታል አልነበረም ፤ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ አራት ትልልቅ ሆስፒታሎች ተገንብተዋል ብለዋል።
ከሁለት መቶ በላይ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 140 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ መሠራቱን እና 8 ሺህ የግብርና ምርቶች ማቅረቢያ ሼዶች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።
ሸገርን ስማርት ከተማ በማድረግ ሂደት የመሬት መረጃ አያያዝ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ ተደርጓል፣ ዲጂታል ላይብረሪ እና ኢ ትራፊኪንግንም ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው። በከተማዋም የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር በሚቀጥሉት ዓመታት ከተማዋ ከምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድል ያላት ከተማ ለማድረግ በትኩረት እየተሠ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ከንቲባው ገለፃ፤ የከተማዋ አስተዳደር የከተማውን ነዋሪዎች የሕይወት ደረጃ ለማሻሻል፤ እንዲሁም የሸገር ከተማን የኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት ለማሳደግ እና የከተማውን የኢንቨስትመንት አቅምና ዕድሎች በመለየት፣ በማጥናት፣ ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅና ቅበላን ማስፋፋት፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ እና ኢንቨስትመንት ተጠቃሚነትን ለማስፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ሸገር ከተማ አስተዳደር ቴክኖሎጂን ያማከለ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ቅበላን ተግባራዊ በማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኤክስፖው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ባለሀብቶች በከተማዋ ኢንቨስትመንት ላይ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ሸገርን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጓትን ጉዳዮች ሲያብራሩ ከፍተኛ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ምቹ መሬት መኖሩ፣ የመሬት አስተዳደሩ ዘመናዊ መሆን፣ ከተማዋ የኢንቨስትመንት ማዕከል በመሆኗ እና ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ ሥራዎች የሚሠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባዔ የሆኑት ወይዘሮ ሳእዳ አብዱረህማን በበኩላቸው፤ ሸገር ከተማን የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፤ በከተማዋ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልፀዋል።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) እንዳሉት በኤክስፖው በከተማው የ 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል ኤክስፖ ትናንት መጀመሩን ተናግረዋል።
በኤክስፖ ከ5 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እንደተገኙና ከ190 በላይ ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን ይዘው እንደቀረቡ አመልክተዋል። ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንትም ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ከንቲባው ተናግረዋል።
ኢኮኖሚን ለማሳደግ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ተሾመ (ዶ/ር) ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በተለያዩ ዓለማት የተለመደው ኤክስፖዎችን ማዘጋጀት መሆኑን አብራርተዋል። ይሄንን ታሳቢ በማድረግም የሸገር ከተማ አስተዳደር ያለውን ምቹ ሁኔታን በመጠቀም ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመሳብ ከሰኔ 28 ቀን እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኤክስፖ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን አዘጋጅቷል ብለዋል።
በኤክስፖው ላይ የሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት አምራች ባለሀብቶች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ በመገኘት የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስርን ይፈጥራሉ፣ የልምድ ልውውጥ ያካሂዳሉ፣ ምርቶቻቸውንም እንደሚያስተዋውቁ አመልክተዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም