
በመላ ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች የርኅራሄ፤ የደግነት፤ የመረዳዳት እና የፍቅር ወር የሆነውን የሮመዳንን የፆም ጊዜ ሲጨርሱ የዒድ በዓል ቦታውን ይረከባል። ዒድ የሮመዳን ፆም የፍቺ በዓል ነው።
ዒድ አልፈጥር ሙስሊሞች ለአንድ ወር ያህል በትጋት ሲያከናወኑት የነበረውን የፆም ጊዜ ጨርሰው በዓላቸውን የሚያከብሩበት የደስታ ወቅት ነው። በዚህ የደስታ በዓል ላይ ወዳጅ ከወዳጁ ይጠያየቃል፤ የተራቡና የታረዙ ወገኖች ይጎበኛሉ፤ ሁሉም ያለውን ያካፍላል፤ ደስታ በሁሉም ቤት ይገባል። ዛሬ የሚከበረውም 1446ኛውን የዒድ በዓል እነዚህን ዕሴቶች ተላብሶ የሚከበር ነው።
ዒድ ማለት ደስታ ማለት ነው። ሙስሊሞች ለአንድ ወር ያህል በትጋት ሲያከናወኑት የነበረውን የፆም ጊዜ ጨርሰው በዓላቸውን የሚያከብሩበት የደስታ ወቅት ነው። በዚህ የደስታ በዓል ላይ ወዳጅ ከወዳጁ ይጠያየቃል፤ የተራቡና የታረዙ ወገኖች ይጎበኛሉ፤ ሁሉም ያለውን ያካፍላል፤ ደስታ በሁሉም ቤት ይገባል።
ዒድ የደስታ በዓል ነው። ዒድ አልፈጥር የቅዱሱ ሮመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል በመሆኑ በፆም ውስጥ ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ተግባራት ተቆጥቦ የቆየ ሰውነት ወደተለመደው የአመጋገብ ሥርዓት የሚመለስበትና ይህንኑም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማዕድ አብሮ በመቋደስ በደስታ የሚዋልበት ቀን ነው። በተለይም ልጆች እና ሴቶች ባማሩ ልብሶች አሸብርቀው የበዓሉ ድምቀት ሆነው ስለሚውሉ የበዓሉን ደስታ እጥፍ ድርብ ያደርገዋል።
ዒድ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በዓሉን በጋራ የሚያሳልፍበት የአብሮነት በዓል ነው። ከዚህ ባሻገር ግን በኢትዮጵያ ያለው የዒድ አከባበር ለየት የሚልባቸው ዕሴቶች አሉት። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በፀጋ የተቀበለችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተዋደውና ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ነች። ዒድን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት ደግሞ በክርስትና በዓላት እንደሚደረገው ሁሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው። ይህ አንዱ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ሲሆን ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ መገለጫችን ነው።
ከበዓሉ አንድ ቀን አስቀድሞም ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የኢድ ሶላት መስገጃ ቦታን በማፅዳት በኢትዮጵያኖች መካከል ያለውን አንድነትና መከባበር በተግባር ያሳያሉ። ይህ አኩሪ በዓላችን ከዒድም በኋላ ባሉት ቀናት ጭምር ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው።
ዒድ የስጦታ እና የመረዳዳት በዓል ነው። የዒድ በዓል ሲከበር ሰዎች ስጦታ በመለዋወጥ ፍቅርና አክብሮታቸውን ይገልጻሉ። እንኳን አደረሳችሁ ይባባላሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንም ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ ዕሴት ነው። የእስልምና እምነት በዒድ ወቅት ድሆችን ከሚያስብበትና በዓሉንም በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ከጣለባቸው ትዕዛዞች አንዱ ላጡና ለተቸገሩ ወገኖች የሚደረግ ድጋፍ ዘካተል ፊጥር ይባላል።
የእምነቱ ተከታዮች በጋራ የሶላት ሥነሥርዓት ወደሚያካሂዱበት ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ለተቸገሩ ወገኖች የዘካተል ፊጥር ርዳታ ማድረግ ግዴታቸው ነው። ዘካተል ፊጥር ማለት አማኞች ለተቸገሩ ወገኖቻቸው በነፍስ ወከፍ ሁለት ኪሎ ተኩል ስንዴ ወይም ሌላ ለምግብ የሚውል ነገር በዓይነት የሚሰጡበት ሥርዓት ነው። ዘካተል ፊጥር በችግር ላይ ያሉ ወገኖች የዒድን በዓል እንደሌሎች ወገኖቻቸው ሁሉ በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው ነው።
የዒድ በዓል ሌላኛው መገለጫ ሀብት ካላቸው ሰዎች የሚሰበሰብ ዘካ (ምፅዋት) ለተቸገሩ ሰዎች የሚከፋፈልበት ወቅት ነው። አቅም ያላቸው ወገኖች ከፍ ያለ ገንዘብ ለድሆች የሚያከፋፍሉበት ሥርዓት ሲሆን ይህም ሰዎች ከተራዘመ ተመፅዋችነት ወጥተው ራሳቸውን የማስተዳደር አቅም እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው። ይህ ደግሞ ተረጂነትን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል ነው።
የዘንድሮውን 1446ኛ የዒድ አልፈጥር በዓልን ስናከብር የበዓሉን እሴቶች በመጠበቅ እና በተለይም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፤ የታረዙትን በማልበስ፤ የተራቡትን በማብላት እና በጦርነት እና በግጭት የተፈናቀሉትን ወገኖች ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም