
በአንድ ወቅት የሀገሪቱ እምብርት በሆነች አንዲት መንደር የነበሩ ሰዎች በባሕላዊ ትውፊቶች ተሳስረው፤ የእያንዳንዱን አዛውንት ቃል እንደ ቅዱስ ቃል ቆጥረው፤ ቀደምት እውቀትን፣ ጥበብን፣ ታሪክን፣ ባሕልንና እሴትን በክብር ለትውልድ እያስተላለፉ፤ በጠንካራ መተሳሰብ፣ መረዳዳትና የአብሮነት ስሜት ተቆራኝተው ይኖሩ ነበር::
በጥንታዊቷ መንደር ውስጥ እንደ እርሻ ማረስ፤ ሰብል መሰብሰብ፤ ድግስ መደገስ በጋራ መሥራት፤ ዓመታዊ በዓላትን በጋራ ማክበር፤ የባሕል ልብስ መልበስ፤ አብሮ መብላት፤ አብሮ መጠጣት፤ በባሕል የሙዚቃ መሳሪያዎች የታጀቡ ሙዚቃዎችን መጫወት፤ መዘመር፤ መደሰትና በጋራ ማምለክ፤ የደስታም ሆነ የሀዘን ጉዳዮች ሲከሰቱ በጋራ መወጣት የተለመደ ነበር::
የመሸበት እንግዳ “አሳድሩኝ” በማለት ወደ ቤታቸው ሲያቀና እናቶች መቀነታቸውን ከወገባቸው ፈትተውና መደብ ላይ አንጥፈው እንግዳውን ማስቀመጥ፤ ለቤተሰቡ የተዘጋ ጀውን ምግብ ብላልኝ በሞቴ በማለት መመገብ፤ የእንግዳውን እግር አጥቦ ባለቤቱ የሚተኛበትን መኝታ ለቆ በማስተኛት በፍቅር ማስተናገድም መገለጫቸው ነበር።
አንድ ቤተሰብ ወዳጅ በእንግድነት ሲመጣበት የአካባቢው ሰው እንደየ አቅሙ እንጀራ፣ ወጥ፣ ዳቦ፣ ቆሎ፣ ጠላ፣ ወተት፣ ቡና እና ቤት ያፈራውን ሁሉ ይዞ እንግዳው ወደ አረፈበት ቤት በመሄድ በጋራ ማስተናገድ የተለመደ ነበር። አባቶች የአካባቢውን ልጆች ሰብስበው እሳት እየሞቁ ለታሪክ ፣ለባሕል፣ ለሀገራዊ ቅርሶች፣ ለትምህርት፣ ለሀገር በቀል እውቀቶች፣ እሴቶችና ለሀገር ፍቅር ክብርና ዋጋ መስጠት ያለውን ማኅበራዊና ሀገራዊ ፋይዳ ማስተማር፤ ፍቅር፣ መከባበር፣ መረዳዳት፣ መደማመጥና አብሮነት ለማኅበራዊ እድገትና ሀገራዊ ሰላም ትልቅ ዋጋ እንዳለው ያስተምራሉ::
ልጆችም ከአባቶቻቸው እግር ስር ተቀምጠው መማርን እጅግ ይወዱትና ይናፍቁት ነበር:: ባገኙትም እውቀት በመከባበር አብረው ይጫወቱ፣ ይቦርቁ፣ ይደሰቱ ነበር:: ይሁን እንጂ ዓለም እየሰለጠነ፤ ቴክኖሎጂ እያደገ ሲመጣ የመንደሯ ፒስታ መንገድ ለዘመናዊው አስፋልት፤ የሚያማምሩት ባሕላዊ ቤቶች ለሕንጻዎች ፤ የገጽ ለገጽ ውይይቶችና ጭውውቶች ለሞባይሎች ፤ፈረሶችና ጋሪዎች ለዘመናዊ አውቶሞቢሎች፤ ኩራዞች ለአምፖሎች ቦታ መልቀቅ ጀመሩ:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ የወጣቶቹም ልብ ከአዛውንቶች አስተምሮ እየራቀ ትኩረት ወደሚሰርቀው ዘመናዊው ዓለም መኮብለል ጀመረ::
ወጣቱ በሞባይሉ አማካኝነት ዓለምን በእጁ ጨብጦ፤ በየትኛውም የዓለም ጠርዝ ስለሚከሰቱ ነገሮች ፈጣን መረጃዎች በደቂቃዎች ይደርሱት ጀመር::
ኢትዮጵያም መልኳ ከላይ የተገለጸውን ይመስላል:: ከጥንት ጀምሮ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ጫፍ ያሉ ሕዝቦቿ በመከባበር በመተሳሰብ በመረዳዳትና በአብሮነት ስሜት ተጣምረው በአንድነት የሚኖሩባት ነች:: ይህም ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበትና እርስ በርስ የሚደጋገፉበት፤ ግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ግጭቶችን የሚፈቱበት፤ ከምንም በላይ ለሀገር ደህንነትና ሰላም ቅድሚያ የሚሰጡበት፤ ለአብሮነትና ለጋራ ጥቅም የሚተጉበት መስመር ነው::
ኢትዮጵያ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የድል፣ የሰላምና የአንድነት ምሳሌ ነች:: ሕዝቦቿ የሀገር ፍቅርንና ብሔራዊ ኩራትን የሚያዳብሩበት እንደ ሕግ ያልተጻፉ፤ ነገር ግን እንደ ሕግ የተቀበሏቸው ትውፊቶችም አሏቸው፤ ከነዚህም ውስጥ ታላላቆችን ማክበር፣ ትህትናን መላበስ፣ ሰላምታ መለዋወጥ፣ እንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ፣ ጋብቻንና ግንኙነትን ማክበር የሚጠቀሱ ናቸው::
የበዓላት፣ የእምነት ቦታዎች፣ የሥራ ቦታ አለባበስ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችም አሏቸው:: እንደ እቁብ፣ እድር፣ ደቦ የመሳሰሉ የመረዳጃ እና የመደጋገፊያ ባሕላዊ ሥርዓቶች አሏቸው:: የግጭት አፈታት ሥርዓቶች፣ የቤተሰብና የማኅበረሰብ ብሎም የማኅበረሰብ መሪዎች የሥራ ክፍፍልና የሥልጣን ተዋረድ፣ የአደባባይ ንግግር ሥርዓቶች፣ ትህትናንና አክብሮትን የተላበሰ የቋንቋ አጠቃቀም፣ የትምህርት ሥርዓት፣ የሀገር ፍቅርና ብሔራዊ ኩራቶችም ማንነታቸውን የሚገልጹ ትውፊቶቻቸው ናቸው::
የኢትዮጵያ ማኅበራዊ እሴቶች እንደየአካባቢው ወግ፤ ልማድና የአኗኗር ዘይቤ ውስን ልዩነቶች ቢታይባቸውም ከተለያዩ የሀገሪቱ ባሕል፤ ታሪክና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው አብዛኛዎቹ ተመሳሳይነት አልያም ተቀራራቢነት አላቸው:: ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የተለያየ መልክዓ ምድር፤ የአየር ንብረት፤ ብሔር ብሔረሰብ ያላት ሀገር ብትሆንም ማኅበራዊ እሴቶችዋን ለዘመናት ጠብቃ በማቆየቷ ሕዝቦቿን የሚገልጽ የራሷ ልምድ፣ ባሕል፣ የአኗኗር ዘይቤና እምነት ያላት ነች::
ሕዝቦቿ በታሪክ፣ በባሕልና በእምነት ተሳስረው፣ ተከባብረው፣ ተዋደው፣ ተጋብተውና ተዋልደው የሚኖሩ ናቸው:: በችግርና በደስታ ተጋግዘው፤ የተጣላን አስታርቀው፤ የተበደለን ክሰው፤ የበደለን ገስጸው፤ የሀገርን ደህንነትና የሕዝብን ሰላም ጠብቀውና አስጠብቀው የሚኖሩ ናቸው:: ታላላቆች የሚከበሩበት፤ የሚደመጡበት፤ ለትምህርት፣ ለእውቀት፣ ለሥራ፣ ክብር የሚሰጥበት፤ የሌሎችን ስሜት ማዳመጥ ቅድሚያ የሚያገኝበት፤ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለእኛ የሚባልበት፤ ሁሉም ሰው የራሱን ኃላፊነት የሚወጣበት ልጆች ተምረው ለቁምነገር የሚበቁበት፤ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው መልካም ነገር የሚያበረክቱበት ዘይቤ ያላቸው ናቸው::
እኛም በዘመናችን ታላላቆችን አክብረን ሲመክሩን ሰምተን፤ ሲናገሩ አድምጠን፤ ሲገስጹን ተቀብለን፤ ለጎረቤት ተልከን፤ በእድሜም ሆነ በእውቀት ከእኛ ከፍ ያለ ሲመጣ ከመቀመጫችን ተነስተንና ሰላምታ ሰጥተን ፤አውቶቡስ ላይ ወንበር ለቀን፤ ታክሲ ሰልፍ ላይ ቅድሚያ ሰጥተን፤ ከሁሉም ጋር አብረን ተምረን አብረን አጥንተን፤ አብረን ተጫውተን፤የተሰጠንን ተካፍለን በልተን፤ ተምረንና ሠርተን ሰው ለመሆን እንጥራለን:: ይሄ በእኛ ተጀምሮ በእኛ የሚያበቃ ሳይሆን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፤ ዛሬም ያለ እና ወደፊትም የሚቀጥል መገለጫችን ነው::
የት፤ መቼና እንዴት ተጀመረ የሚለው ጥያቄ ለተመራማሪዎች የሚተው ቢሆንም ዛሬ ላይ ጠንካራ እሴቶቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሸርሸራቸው በሌሎች ኑሮ፤ ሰላምና ጤና ላይ ተረማምደንና የሌሎችን ሕይወት አጨልመን ያልተገባ ሀብት ለማካበት የምንሯሯጥ በዝተናል::
በየትምህርት ቤቱና በየዩኒቨርሲቲው ጥግ የመኖሪያ ቤቶቻችንን ወደ ጫት መቃሚያ፣ ሺሻ ማጨሻና አልባሌ ተግባራት መፈጸሚያነት ቀይረን የሕፃናትንና የወጣቶችን ሥነ ልቦና ለሚሰልቡና ላልተገባ ሕይወት የሚያመቻቹ ተግባራትን እየሠራን የምንገኝ፤ በብልጭልጭ ነገሮች እያታለልን የሴት ሕፃናትን ሕይወት የሚቀጥፉ አልያም ለከፋ ሕይወት የሚዳርጉ ተግባራትን የምንፈጽምም ብዙዎች ነን::
በትምህርት ሰዓት የደብተር ቦርሳቸውን አንግበው በጆተኒ ቤት፣ ፑል ቤት፣ አልያም በየሻይ ቤት የሚገኙ ተማሪዎች መታየታቸው እየተለመደ መጥቷል::
ትምህርቱን አቋርጦ ወይም ተምሮ ጨርሶ ሥራ ከመፍጠር ይልቅ፤ በየጎዳናው ወዲህና ወዲያ እያለ በአንድ እጁ ሱሪው እንዳይወልቅበት ወደላይ እየጎተተ፤ በሌላኛው እጁ ውሃና መቀስ አይቶት የማያውቅ ጸጉሩን እያፍተለተለ “ጀለስ ለሲጋራ” የሚል ወጣትም እየተበራከተ መጥቷል::
ድንጋይ ላይ ተቀምጦ የሰው ፎቅ አንጋጦ እየተመለከተ “ይህ ነገ የኔ ይሆናል” እያለ በቀን ሕልም የሚዋዥቅ፤ ሠርቶ ከማግኘት ይልቅ በእጁም፤ በሃሳቡም የሰው ኪስና ጓዳ እየበረበረ ሕይወቱን ለመግፋት የሚባዝን ወጣት፤ እንኳንስ እሱ አያት ቅድመ አያቶቹ የማያውቁትን መጥፎ ታሪክ እየመዘዙ ሲሰጡት ተቀብሎ ወንድሙን፤ አብሮ አደጉንና አጋሩን በጥላቻ የሚመለከትና የሚያሳድድ ወጣት ቁጥሩም ቀላል አይደለም::
ትልልቅ ሰዎች በአጠገቡ ሲያልፉ ደህና ዋልክ ልጄ ሲሉት እግሩን አንፈራጦ ምን አገባችሁ በሚመስል ስሜት ዓይኑን ከሞባይሉ ሳይነቅል ግንባሩን ቋጥሮ “ደህና” የሚል ወጣት፤ አባት/እናት/አያት ከውጭ ገብተው ደህና ዋላችሁ ሲሉ ልጅ ሶፋ ላይ ተንጋሎና እግሩን ጠረጴዛ ላይ ሰቅሎ ሞባይሉን እየጎረጎረ “ሰላም ነው” የሚል ወጣት ፈጥረናል:: ይህ ወዴት እንደሚወስደን መገመት አያዳግትም፤
ዛሬም አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ለጋራ እሴቶቻቸውና ለአኩሪ ታሪካቸው ጠንካራ አቋምና ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት እንዳላቸው እሙን ነው:: ይሁን እንጂ አንድ ቤት ውስጥ የአንደኛው ማዕዘን ግድግዳ መቃጠል ሲጀምር ወዲያው ማጥፋት ካልተቻለ ከአንዱ ማዕዘን ወደ ሌላው እየተሸጋገረ ሙሉ ቤቱን ማውደሙ አይቀሬ ነውና ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ የማንነታችን መገለጫ የሆኑ እሴቶቻችንን ለማውደም ብልጭ እልም እያለ ለመጋም እየተጋ ያለውን እሳት ማጥፋት የሁሉንም ዜጋ ኃላፊነት የሚጠይቅ ነው::
እያንዳንዱ ሰው ቤቱንና ደጁን ቢያጸዳ ከተማ ይጸዳል፤ እያንዳንዱ ከተማ ቢጸዳ ሀገር ትጸዳለች:: እናም ግለሰቦች፤ቤተሰብ፤ የአካባቢ ማኅበረሰብ፤ የትምህርት ተቋማት፤ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት…ወዘተ ሁላችንም እንደየ ችሎታችንና እንደየአቅማችን ድርሻችንን በመወጣትና ሀገር በቀል ትምህርቶቻችንን፤ እውቀቶቻችንንና እሴቶቻችንን ከዘመናዊው ሥልጣኔ ጋር እንዲጣጣም በማድረግ ትውልዱ ፈሩን እንዳይለቅ ማገዝ ይጠበቅብናል::
ሙሉእመቤት ጌታቸው
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም