የአሜሪካና የብራዚል የጸጥታ አካላት በሠሩት ኦፕሬሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ አስተባባሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። የአሜሪካ እና የብራዚል ሕግ አስከባሪዎች ባደረጉት ኦፕሬሽን፤ ዩናይትድ ስቴትስ ላይ የተመሠረተ ሕገወጥ ዓለም አቀፍ የሰዎች አዘዋዋሪ ነው ተብሎ የተከሰሰው ሰነድ አልባ ብራዚላዊ ስደተኛ ተይዟል።
ተጠርጣሪው የ41 ዓመቱ ፍላቪዮ አሌክሳንደር አልቬስ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ወደ አሜሪካ በማምጣት ክስ የተመሠረተበት ሲሆን፤ በተለይ ብራዚላውያን ስደተኞችን ከሀገራቸው በሜክሲኮ በኩል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሕገወጥ መንገድ ሲያጓጉዝ ነበር ተብሏል።
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውሩን ለመፈጸም ከተለያዩ ከተሞች ለሚነሱ በረራዎች ከ 100 በላይ የግል አውሮፕላን ትኬቶችን ግዢ ስለመፈጸሙ አቃቤ ሕግ ማስረጃ አቅርቦበታል።
በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን እና በሜክሲኮ ያሉ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በማስተባበር ክፍያ እንዲሰበስብ አድርጓል ተብሏል።
አልቬስ ከዚህ ቀደም በ2004 በካሊፎርኒያ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተከስሶ ወደ ብራዚል የተባረረ ሰው ሲሆን፤ ይህ ሰው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ገብቶ ሕገወጥ ድርጊቱን ሲፈጽም እንደነበር ተነግሯል።
ተባባሪ ናቸው የተባሉት ግለሰቦች ማንነት በፍርድ ቤት ሰነድ ላይ ተገልጿል፤ ተባባሪ አካላቱም ከዚህ ቀደም አብረው ሲሠሩ የነበሩ ናቸው ተብሏል። ለአብነትም ተባባሪ ነው የተባለው ተጠርጣሪው ሌኖ ራውሊንሰን ሲልቫ ኦሊቬራ በወንጀል ክሱ ላይ የብራዚል የሰዎች ኮንትሮባንድ ድርጅት መሪ እንደሆነ ተገልጿል።
በብራዚል ፖሊስ የተደረገ ፍተሻ ኦሊቬራ አልቬስን ጨምሮ ከድርጅቱ አባላት ጋር ለመነጋገር ይጠቀምበት የነበረው ሞባይል ተገኝቷል።
የፍርድ ቤቱ ሰነዱ አልቬስ በድርጅቱ የአሜሪካ ሕገወጥ አዘዋዋሪ መሆኑን እና በ2021 አጋማሽ ላይ ቡድኑን የተቀላቀለው በሜክሲኮ ባደረገው የሰው አዘዋዋሪ ጥቆማ መሆኑን አስቀምጧል።
በአሜሪካ ባለሥልጣናት ማንነታቸው ያልታወቁ አራት ተዛማጅ ተጠርጣሪዎችም ረቡዕ በፒትስበርግ፣ ሃሪስበርግ እና ፊላደልፊያ ተይዘዋል።
የብራዚል የፌዴራል ባለሥልጣናት የዓለም አቀፉ ኦፕሬሽን አካል በመሆን ርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። ከክሱ ጋር በተያያዘም ፍርድ ቤቶች 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ንብረት እና የተጠርጣሪዎቹን ፈንድ አግደዋል።
የብራዚል ፌዴራል ፖሊስ ዕረቡ በሰጠው መግለጫ ላይ “ተጠርጣሪዎቹ ከተለያዩ ከተሞች የመጡ ነዋሪዎችን በማታለል በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት ተይዘዋል” ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም