አሜሪካ ለሀገራት የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ የምታቋርጥ ከሆነ መከላከል በሚቻል በሽታ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ሕይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋም አስጠነቀቀ፡፡
በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ወሳኝ ክትባቶችን በማቅረብ የሚታወቀው ጋቪ የተባለው ድርጅት ኋላፊ ዶ/ር ሳኒያ ንሽጣር የአሜሪካ ርዳታ መቋረጥ በዓለም አቀፍ የጤና ደህንነት ዋስትና ላይ አስከፊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ለቢቢሲ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
ሃላፊው ይሄን ያሉት የድርጅቱ ሶስተኛ ለጋሽ ሀገር የሆነችው አሜሪካ ድጋፏን ለማቋረጥ መሰናዳቷን ኒውዮርክ ፖስት መዘገቡን ተከትሎ ሲሆን ጋቪ እስከ አሁን የርዳታ መቋረጥ ማሳወቂያ ከአሜሪካ መንግሥት ያልደረሰው ሲሆን በያዝነው በፈረንጆቹ 2025 ለእንቅስቃሴው የሚሆን ሶስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ርዳታ ለማግኘት ከዋይት ሃውስ እና ከጎንግረሱ ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ እ.ኤ.አ ከ2026 እስከ 2030 ድረስ ለድርጅቱ አሥራ አምስት በመቶ ድርሻ ያለው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ባለፈው ጥር ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ አሜሪካ ከባሕር ማዶ የምታደርገው ወጪ የአሜሪካን ጥቅም ያስቀደመ እና ሀገራዊ ፋይዳ ያለው እንዲሆን አቅጣጫ ማስቀመጣቸው አይዘነጋም፡፡
በትራምፕ ውሳኔ ውዝግብ ውስጥ የገባው የዓለም የጤና እና ሠብዓዊ መብት ተቋም አሜሪካ ውሳኔዋን እንድታጤነው በተደጋጋሚ ጊዜ የጠየቀ ሲሆን ርዳታው የሚቆም ከሆነ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ዓለም አቀፉ የልማት ዘርፍ በዓለም ዙሪያ የሠብዓዊ መርሃ-ግብሮች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ በማምጣት ስሙ ይነሳል፡፡
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት በቅጽል ስሙ ዩ.ኤስ.ኤይድ በአጭሩ ዶዥ እየተባለ በሚጠራው የኤለን መስክ ወጪ ቅነሳ መሥሪያ ቤት በመጀመሪያ ኢላማ ውስጥ ከገቡት መሀል ሲሆን በትራምፕ አስተዳደር ለዘጠና ቀናት የርዳታ እግድ ተጥሎበታል፡፡
የጋቪ የገንዘብ አቅርቦት የሚቆም ከሆነ በመላው ዓለም ክትባት ከሚያስፈልጋቸው አምስት መቶ ሚሊዮን ህጻናት ውስጥ ሰባ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ክትባት እንደማያገኙ የገለጹት ሃላፊው ይህ ማለት እንደፈንጣጣ፣ ቲቢ፣ የሳንባ ምች እና ፖሊዮን በመሰሉና መከላከል በምንችላቸው በሽታዎች ሞት ይከሰታል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥታት እና የጤና ኤጀንሲዎች ኢቦላ፣ ኮሌራ እና ኤምፖክስ የመሳሰሉ በሽታዎችን ለመከላከል እና ደህንነትን ለማስጠበቅ የክትባት ክምችታቸው ላይ ጠባሳ ያሳርፋል መባሉ ተሰምቷል፡፡ በጤናው ዘርፍ ላይ የተሠማራው፤ ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በበኩሉ አሜሪካ ርዳታውን የምታቋርጥ ከሆነ በተረጂ ሀገራት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በሚመለከት ከጋቪ አስተያየት ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ አንጸባርቋል፡፡
የቡድኑ የአሜሪካ የመርሀ ግብር ተጠሪ ካሪ ቴቸር ‹‹የዚህ ፖለቲካዊ ውሳኔ አንድምታ መላውን ዓለም ከማስጨነቅ ባለፈ ውጤቱም አስከፊ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሌሎች በርካታ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ተቋማት የርዳታው መቋረጥ ስለሚያስከትለው ጉዳት ተመሳሳይ አቋም መያዛቸው ነው የታወቀው፡፡
የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠርን ጋቪን ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ እና በዋነኛ መርሀ ግብሮች የአሜሪካ ርዳታ መቋረጥ ባሳደረው ጫና ዙሪያ ከዋሽንግተን ባለሥልጣናት ጋር እየመከረ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሜሪካ ውሳኔዋን በመመልከት የድጋፍ ማቋረጥ ሃሳቧን እንድትተው ጫና መፍጠር ማስፈለጉ ወሳኝ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም