
ዜና ሀተታ
ህጻናትን በሥነ ምግባርና በእውቀት አንጾ የነገ ሀገር ተረካቢዎች ለማድረግ በንባብ ራሳቸውን እንዲያበቁ ማድረግ ይጠበቃል። የህጻናት አእምሮ ልማት ላይ መሥራት ጊዜ የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ አኳያ እንደ ሀገር የህጻናትን የንባብ ልምድ ለማዳበር የሚያስችሉ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች የተዘጋጁ የህጻናት መጻህፍት ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያዩ ግለሰቦች የሚዘጋጁ መጻህፍትና መጽሄቶች ቢኖሩም በተደራሽነት ረገድም ሆነ በቋንቋ ብዝሀነት ውስን መሆናቸውን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በህጻናት የንባብ ባህል ለማዳበርና የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሌሎች የህትመት ውጤቶች ያሳረፈውን ሀገራዊ ዐሻራ በህጻናትም ለመድገም ብላቴናት መጽሄትን ማሳተም ከጀመረ ስምንት ወራትን አስቆጥሯል ። በትናንትናው እለትም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአማርኛ በሚያሳትማት ብላቴናት የልጆች መጽሄት ላይ የአርታኢያን መድረክ በማዘጋጀት ውይይት አካሂዷል። በመድረኩም ጅምሩ አበረታች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መጽሄቷን ማጠናከርና በማህበራዊ ሚዲያውም ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
በመድረኩ ብላቴናት የልጆች መጽሄት ከሥነልቦና አንጻር ለልጆች ያላትን ፋይዳ በተመለከተ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር ብሩክ ገብረማርያም ጹሁፍ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ የህጻናት መጽሄት በአዋቂዎች እንደሚዘጋጁ ገልጸው፤ አዘጋጆቹ ሁሌም የልጆችን ሥነልቦና ለማወቅ ራስን ማዘመን እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
መምህር ብሩክ እንደሚያብራሩት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያዘጋጃት ብላቴናት የልጆች መጽሄት ህጻናት ሀገራቸውን፣ አካባቢያቸውን ከዚህም ባለፈ ሳይንስና ቴክኖሎጂን እንዲያውቁ መልዕክት የሚተላለፍባት ናት። መጽሄቷን የሚያነቡ ህጻናት ለፈጠራና ለምርምር እንዲነሳሱ አርዓያ የሚሆኑ ልጆች የሚቀርቡበት መሆኑ ተነሳሽነት በመፍጠር ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው።
መምህር ብሩክ በመጽሄት ዝግጅት ወቅት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ሲጠቅሱም፤ ልጆች እንዲያነቧቸው የሚዘጋጁ ጽሁፎች ላይ ነባር አሉታዊ አመለካከቶችን ወደ አወንታዊ ይዘቶች መቀየርን፣ ብዝሃነትን እና ልዩ ፍላጎትን ማካተት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም የብላቴናት መጽሄትን ሲያዘጋጅ በመጽሄቷ የሚወጡ ማስታወቂያዎች ህጻናት ጋር የሚስማሙ እና ትምህርታዊ ሊሆኑ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በበኩላቸው ብላቴናት የልጆች መጽሄትን ከህትመት ባለፈ በማህበራዊ ሚዲያዎች ማቅረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያዘጋጃት ብላቴናት የልጆች መጽሄት ከልጆች ባለፈ ለወላጆችም ተደራሽ ልትሆን ይገባል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መጽሄቷን በህትመት ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በማህበራዊ ሚዲያዎች በማቅረብ ወላጆችም እንዲያነቧትና እውቀትና መረጃዎችን እንዲወስዱባት ማድረግ የሚጠበቅ ይሆናል።
እስካሁን በተስተናገዱት ህትመቶች በመጽሄቷ የቀረቡት አምዶች ህጻናትን በሚመጥን መልኩ መቅረባቸውን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ፤ ልጆች አዋቂዎችን የሚጠይቁበት አምድ መኖሩ ጥሩና የሚበረታታ ነው። የህጻናት መጽሄት ሲዘጋጅ ከሌላው በተለየ ምንም ዓይነት ስህተት ሊገኝበት አይገባም። ከሃሳብ መረጣና ከዝግጅት ጀምሮ ቃላቶችን በትክክል ማረም ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
አሁን ያለው የመጽሄቷ አዘገጃጀት ጥሩ ቢሆንም በቀጣይ በመጽሄቷ አጫጭርና አዝናኝ ጹሁፎች ሊካተቱ እንደሚገባ፤ የፊት ገጹ ልጆችን በሚመጥን መልኩ ውበት ሊኖረው የሚገባና ተለዋዋጭ ያልሆነ ወጥነት ያለው በቀላሉ ሊለይና ሊወደድ የሚገባ መሆን አለበት። በተጨማሪ የኋላ ሽፋኑም በቀጣዩ ህትመት ስለሚስተናገዱት ጉዳዮች የሚጠቁም ቢሆን ይመረጣል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከብላቴናት የህጻናት መጽሄት በተጨማሪም በቅርቡ ናኦታ የተሰኘች በአፋን ኦሮሞ የምትታተም የሕጻናት መጽሄት በቅርቡ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም