ዒድ – የስጦታ እና የመረዳዳት በዓል

በሂጅራ አቆጣጠር 12 ወራት አሉ። የሂጅራ አቆጣጠር ጨረቃን መሠረት የሚያደርግ እና ወሮቹ 29 እና 30 ቀናት የሚረዝሙ ናቸው። ረመዳን ከ12 ወራት ዘጠነኛው ወር ነው። ረመዳን ከዓመቱ ወራቶች ሁሉ የተከበረ እና ቁርዓን የወረደበት ቀን ነው።

የረመዳን ወር ልዩ መገለጫዎች ከሆኑት ውስጥ ፆም አንዱ እና ዋናው ነው። የእስልምና እምነት አስተምሕሮ እንደሚያስረዳው ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከምትጠልቅ ድረስ መፆም ለአቅመ አዳም እና ሔዋን ለደረሱ ሙስሊሞች ፈርድ (ግዴታ) ነው።

አልጋ ላይ የዋሉ በሽተኞች፣ መንገደኞች፣ አረጋውያን፣ ጡት አጥቢ እናቶች፣ የስኳር በሽተኞች፣ ወይም የወር አበባ ያላቸው እንስቶች ሲቀሩ ሁሉም ይፆማል። የፆም መንፈሳዊ ሽልማቶች (ሰዋብ) በረመዳን ውስጥ እንደሚባዙ ይታመናል። በዚህ መሠረት፣ ሙስሊሞች ከምግብ እና መጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከትምባሆ ምርቶች፣ ከባለቤታቸው ጋር ፆታዊ ግንኙነት፣ እንዲሁም ከአጠቃላይ መጥፎ ባሕሪያት በመቆጠብ፤ ሶላት እና ቁርዓን መቅራትን በማዝወተር ከንጋት እስከ ፀሐይ መጥለቅ የሚዘልቀውን የፆም ወር ያሳልፋሉ።

ብዙውን ጊዜ ሙስሊሞች በጸሎት፣ በሰላት እና በሰደቃ (ምፅዋት) እንዲሁም ሥነ ምግባራቸውን ለማሻሻል በመጣር የረመዳን ወርን ያሳልፋሉ። ይህም በሀዲስ “ረመዳን ሲደርስ የገነት በሮች ይከፈታሉ፤ የሲዖል (ገሃነም) በሮች ይዘጋሉ እና ሰይጣናት ይታሰራሉ።” የሚለውን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ በሃይማኖቱ ታሪክ ጸሐፍት በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ይታያል። እስላማዊ ዕሴቶችን በተመለከተም እንደዛው። የመቻቻል፤ የመረዳዳት፣ አብሮነትና የመከባበር ባህል የእስልምና ሃይማኖት እሴቶች መሆናቸው ተደጋግሞ የተነገረ ነው።

መረዳዳት፣ መከባበርና የታመመን መጠየቅ በእስልምና ሃይማኖት ሕግ የውዴታ ግዴታ ነው። በሃይማኖቱ የተፈቀደና የታዘዘው መቻቻል፣ መረዳዳት፣ አቅመ ደካሞችን መርዳትና አብሮነት ጥንትም የነበረ አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር የተከበረና የተመረጠ ባሕል ነው።

ሙስሊሞች የርኅራሔ፤ የደግነት፤ የመረዳዳት እና የፍቅር ወር የሆነውን የሮመዳንን የፆም ጊዜ ሲጨርሱ የዒድ በዓል ቦታውን ይረከባል። ዒድ የሮመዳን ፆም የፍቺ በዓል ነው። ዒድ ማለት ደስታ ማለት ነው። ሙስሊሞች ለአንድ ወር ያህል በትጋት ሲያከናወኑት የነበረውን የፆም ጊዜ ጨርሰው በዓላቸውን የሚያከብሩበት የደስታ ወቅት ነው። በዚህ የደስታ በዓል ላይ ወዳጅ ከወዳጁ ይጠያየቃል፤ የተራቡና የታረዙ ወገኖች ይጎበኛሉ፤ ሁሉም ያለውን ያካፍላል፤ ደስታ በሁሉም ቤት ይገባል።

ዛሬ የሚከበረውም 1446ኛውን የዒድ በዓል እነዚህን ዕሴቶች ተላብሶ የሚከበር ነው። ምክንያቱም ዒድ የደስታ በዓል ነው። ዒድ አልፈጥር የቅዱሱ ረመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል በመሆኑ በፆም ውስጥ ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ተግባራት ተቆጥቦ የቆየ ሰውነት ወደ ተለመደው የአመጋገብ ሥርዓት የሚመለስበት፤ እና ይህንኑም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማዕድ አብሮ በመቋደስ በደስታ የሚዋልበት ቀን ነው። በተለይም ልጆች እና ሴቶች ባማሩ ልብሶች አሸብርቀው የበዓሉ ድምቀት ሆነው ስለሚውሉ የበዓሉን ደስታ እጥፍ ድርብ ያደርገዋል።

ዒድ፣ የአብሮነት በዓል ነው። ዒድ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በዓሉን በጋራ የሚያሳልፍበት የፍቅር በዓል ነው። ከዚህ ባሻገር ግን በኢትዮጵያ ያለው የዒድ አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉት። ይሄም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በፀጋ የተቀበለች እና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ከመሆኗ ጋር የሚገናኝ ነው። ዒድን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት ደግሞ በክርስትና በዓላት እንደሚደረገው ሁሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው።

ይህ አንዱ የኢትዮጵያውያን ዕሴት ሲሆን፤ ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ መገለጫችን ነው። ከበዓሉ አንድ ቀን አስቀድሞም ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የኢድ ሶላት መስገጃ ቦታን ለሕዝበ ሙስሊሙ በማፅዳት በኢትዮጵያውያኖች መካከል ያለውን አንድነትና መከባበር በተግባር አሳይተዋል። በመሆኑም ይህ አኩሪ በዓላችን ከዒድም በኋላ ባሉት ቀናት ጭምር ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው። ዒድ የስጦታ እና የመረዳዳት በዓል ነው። የዒድ በዓል ሲከበር ሰዎች ስጦታ በመለዋወጥ ፍቅርና አክብሮታቸውን ይገልጻሉ። እንኳን አደረሳችሁ ይባባላሉ።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ ዕሴት ነው። የእስልምና እምነት በዒድ ወቅት ድሆችን ከሚያስብበትና በዓሉንም በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ከጣለባቸው ትዕዛዞች አንዱ ላጡና ለተቸገሩ ወገኖች የሚደረግ ድጋፍ ዘካተል ፊጥር ይባላል። የእምነቱ ተከታዮች በጋራ የሰላት ሥነሥርዓት ወደሚያካሂዱበት ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ለተቸገሩ ወገኖች የዘካተል ፊጥር ርዳታ ማድረግ ግዴታቸው ነው።

ይህ መሆኑ ደግሞ በችግር ላይ ያሉ ወገኖች የዒድን በዓል እንደሌሎች ወገኖቻቸው ሁሉ በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው ነው። በአጠቃላይ ዒድ የመረዳዳት በዓል በመሆኑ ከዚህ በሻገር እንደሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው በዓል ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት በፀጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የተሰደዱ በርካታ ወገኖች አሉ። በሌላ በኩል በድርቅ የተጎዱ ወገኖችም አሉ።

በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች መደገፍና ተባብሮ ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው መመለስ አንዱ በዒድ ወቅት የሚከወን ተግባር ሊሆን ይገባል። የዒድ በዓል አንዱ መገለጫ ሀብት ካላቸው ሰዎች የሚሰበሰብ ዘካ (ምፅዋት) ለድሆች የሚከፋፈልበት ወቅት ስለሆነ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እንደ ሀገር በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ጫና ማቃለል ይገባል።

ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ኮቪድ 19 አስከትሎት የነበረው ቀውስ ከሌሎች ወገኖች ጋር በመተባበር ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ችግሩን ማለፍ እንደተቻለ ሁሉ፤ በዚህ ወቅትም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ቤት ንብረታቸውን ትተው የተሰደዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን በማገዝ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል። የዒድ-የደስታ፣ የአብሮነት እና የመረዳዳት በዓል መገለጫውም ይኸው ነው፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You