
ትምህርት ቤቶች የውጤታማ ስፖርተኞች ምንጭ መሆናቸው ይታመናል። ታዳጊዎች ለስፖርት እንዳላቸው ዝንባሌ በትኩረት ቢሠራባቸው በሂደት ሀገርን ማስጠራት የሚችሉ ስፖርተኞች እንደሚሆኑ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችም ያሳያሉ። ከዚያም ባለፈ ታዳጊዎችን በስፖርት እንዲሳተፉ ማድረግ ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ ከማድረግ ጎን ለጎን በትምህርት አቀባበላቸውም ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ይታመናል። በመሆኑም ሀገራት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ታዳጊዎች የስፖርት መሠረት እንዲይዙ ለማድረግ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ይሠራሉ።
የኢትዮጵያም የስፖርት ፖሊሲው ስፖርት ኅብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚሠራበት እና በሚማርበት ስፍራ በስፖርት ተሳታፊ መሆን እንዳለበት ይጠቁማል። በመሆኑም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ታዳጊዎችን በስፖርት ከማሳተፍ ባለፈ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሁም የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች በመኖራቸው ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በተለያየ ዕድሜ እርከን ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሠራ ነው። የስፖርት ተሳትፎና ሥልጠና ማሠሪያው ውድድር እንደመሆኑ በየደረጃው ማዘጋጀት የግድ ቢሆንም በዚህ ረገድ ክፍተቶች አሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ በአንጻሩ የትምህርት ቤቶችንም ይሁን መሰል ውድድሮችን ሳያቋርጥ እያከናወነ ሲሆን፤ አሁንም ከከተማዋ ትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን ከተማ አቀፍ የመምህራን እና የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድርን አስጀምሯል። ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የሚካሄደው ውድድሩ ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲየም የተጀመረ ሲሆን፤ ‹‹የትምህርት ቤቶች ስፖርት ሊግ ውድድርን ባህል በማድረግ ጤናማ፣ ንቁና ብቁ ትውልድ እንፈጥራለን›› በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።
በተማሪዎች መካከል ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም በተለያዩ ውድድሮች ላይ ከተማዋን ሊወክሉ የሚችሉ ስፖርተኞችን ማፍራት የዚህ ውድድር ዓላማ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር መሐሪ ተመስገን ይጠቁማል። የተተኪ ስፖርተኞች ምንጭ የሆኑት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች በመሰል ውድድሮች ማለፋቸውም ወደ ማሠልጠኛ ማዕከላትና አካዳሚዎች እንዲሁም ክለቦች የመግባት ዕድልን ሊያስገኝላቸው እንደሚችልም ይታመናል።
የትምህርት ቤት ዋነኛ አካል የሆኑት መምህራንም ከተማሪዎቻቸው ጎን ለጎን ውድድር የሚያከናውኑ ሲሆን፤ ለስፖርት ፍላጎት ያላቸውን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመም ነው። መምህራኑ በሚሠሩበት ስፍራ የውድድር ዕድል እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የተለየ ተሰጥዖ ያላቸው ደግሞ ከተማ አስተዳደሩን በተለያዩ ውድድሮች የመወከል ዕድል ያገኛሉ።
ውድድሩ የሚካሄደው በሦስት መንገድ ተከፍሎ ሲሆን፤ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል በ6 የስፖርት ዓይነቶች ይደረጋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እግር ኳስና አትሌቲክስን ጨምሮ በ10 ስፖርቶች ሲፎካከሩ፤ መምህራን ደግሞ በ5 ስፖርቶች ውድድራቸውን እንደሚያከናውኑ ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። በየወረዳው፣ በየክፍለ ከተሞች ሲከናወኑ ቆይተው አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ መካሄድ የጀመረው ውድድር ከ26ሺ በላይ ተማሪዎችንና መምህራን ያሳትፋል።
በከተማዋ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች (4ኪሎ፣ ራስ ኃይሉ፣ ጃንሜዳን የመሳሰሉ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከላት እንዲሁም በመደመር ትውልድ የመጽሐፍ ሽያጭ በየስፍራው የተገነቡ የማዘውተሪያ ስፍራዎች) ውድድሮቹን ያስተናግዳሉ። ወቅቱ የትምህርት እንደመሆኑ ውድድሮቹ ከቀን ዘጠኝ ሰዓት በኋላ የሚከናወኑ ሲሆን፤ በዚህም ለተወዳዳሪዎች እንዳይርቁ ትምህርት ቤቶቻቸው የሚገኙባቸውን ስፍራዎች ማዕከል በማድረግ እንደሚካሄዱም ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ።
ከዚህ ቀደም በከተማዋ በየሁለት ዓመቱ ይደረግ የነበረው ይህ የተማሪዎች የስፖርት ውድድር፤ ተማሪዎች ራሳቸውን በውድድር እንዲያጠናክሩ እንዲሁም ተተኪዎችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ያስችል ዘንድ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ የሚቀጥል ይሆናል። ስያሜውም የተማሪዎችና መምህራን ስፖርት ሊግ ሲሆን፤ የትምህርት ሚኒስቴር ባስጀመረው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ስፖርት ሊግ መሠረትም ይከናወናል። ከመጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም የጀመረው ሊጉ እስከ ሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይም ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም