
ከሊባኖስ ወደ እስራኤል በርካታ ሮኬቶች መተኮሳቸውን ተከትሎ እስራኤል በሊባኖስ የአየር ድብደባ ፈፅማለች። ባለፈው ኅዳር በሁለቱ ኃይሎች መካከል ከተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ይህ የከፋው ግጭት ነው ተብሏል።
የእስራኤል ጦር ኃይል እንዳለው በአየር ጥቃቱ ደርዘን የሚሆኑ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን የመታ ሲሆን የሔዝቦላሕ ዕዝ ላይም ጥቃት ሰንዝሯል። በኢራን የሚደገፈው ሚሊሻ እና ፖለቲካዊ ቡድን በደቡብ ሊባኖስ መሽጎ ይገኛል። የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው አንድ ሕፃንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በአየር ጥቃቱ ሲገደሉ 40 የሚሆኑ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሔዝቦላህ እና የፍልስጤም ተዋጊዎችን ጨምሮ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች በደቡብ ሊባኖስ ይንቀሳቀሳሉ። እስራኤል የመጀመሪያውን የአየር ድብደባ ከፈፀመች ከሰዓታት በኋላ ምሽቱን ሁለተኛ ዙር ጥቃት በሔዝቦላህ ዕዝ ማዕከል፣ መሠረተ ልማት እና የጦር መሣሪያ ማከማቻ ላይ መፈፀሟን ተናግራለች።
ሔዝቦላሕ ቅዳሜ ዕለት የሮኬት ጥቃት የፈፀመው እስራኤል ጋዛ በሚገኘው ሐማስ ላይ ጥቃቷን አጠናክራ መቀጠሏን ተከትሎ ነው። የእስራኤል ጦር በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኘው ሜቱላ ከተማ ላይ የተሰነዘሩ ሶስት የሮኬት ጥቃቶችን ማምከኑንና የደረሰ ጉዳት እንደሌለ አሳውቋል።
ሔዝቦላሕ በጥቃቱ እጁ እንደሌለበት አስታውቆ፤ የተኩስ አቁሙን ለማክበር ዝግጁ እንደሆነ ጠቁሟል። የሰሞኑ ጥቃት እስራኤል እና ሔዝቦላሕ በዩናይትድ ስቴትስ እና ፈረንሳይ አማካይነት የፈረሙት የተኩስ አቁም ስምምነትን ሊያፈርሰው ይችላል የሚል ስጋት አለ። በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት የሊባኖስ ጦር በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በደቡቡ ክፍል ያሰማራ ሲሆን ዓላማው ታጣቂዎች እስራኤል ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት መከላከል ነው።
ሔዝቦላሕ ተዋጊዎቹንና እና የጦር መሣሪያዎችን ከአካባቢው ማስወገድ እስራኤል ደግሞ በጦርነቱ ወቅቱ ከያዘቻቸው መሬቶች መልቀቅ ነበረባቸው። ነገር ግን እስራኤል በየቀኑ በሚባል ደረጃ የሔዝቦላሕ ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ እየፈፀመች ነው። ይህን የምታደርገው ቡድኑ መልሶ እንዳይቋቋም እንደሆነ ትገልፃለች።
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ አሁንም አምስት ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል። የሊባኖስ መንግሥት ይህ ስምምነቱን መጣስ እና ሉዓላዊነትን መንካት ነው ይላል። እስራኤል ደግሞ የሊባኖስ ጦር በአካባቢው በሙሉ ባለመሠማራቱ ድንበሬን መጠበቅ አለብኝ ትላለች።
ባለፈው ጥር ወደ ሥልጣን የመጡት የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን በሀገራቸው የጦር መሣሪያ ሊኖረው የሚገባው መንግሥት ብቻ ነው ሲሉ ሔዝቦላሕን ሸንቆጥ አድርገዋል። ሔዝቦላሕ ከእስራኤል ጋር በገባው ጦርነት ምክንያት ክፉኛ የተዳከመ ሲሆን መሪዎቹ ከመገደላቸው ባለፈም በርካታ አባላቱን እንዲሁም የጦር መሣሪያ ክምችቱን አጥቷል።
የሊባኖስ ወዳጅ የሚባሉ ኃያላን ሀገራት መንግሥትን የሚደግፉት በሊባኖስ እጅግ ኃይለኛው ታጣቂ የሚባለውን ሔዝቦላሕ ካስታገሰ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። ሔዝቦላሕ እስራኤል ላይ ጥቃት መፈፀም የጀመረው ሐማስ ካደረሰው የጥቅምት 7/2023 ጥቃት በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ ጦርነት መክፈቱን ተከትሎ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም