‹‹በደን ውስጥ ያለ ዛፍ ሲያድግ ድምፁ አይሰማም፤ ሲሰበር ግን …›› ሰዎች ሲያድጉና ሲሻሻሉ አዋጅ አያስፈልጋቸውም፤ ይህንኑ ለመስማትም ማንም ጉዳዩ አይደለም። ውድቀታቸውን ግን ሰምቶ ለማዛመት ሁሉም ይፈጥናል። ስለዚህ ውድቀትህን፣ ችግርህን፣ መከራህን ለማንም አትንገር፤ ራሱ ይናገራልና። መልካም ነገርህንም ቢሆን ሆነህ ተገኝ እንጂ፤ ሰው ገዶት አያደንቅህም። መጠበቅም አያስፈልግም፡፡
በሌላ በኩል አንድ ዛፍ በደኑ ውስጥ ሳለ ለብቻው ሲቆም ጫካውን ጫካ፣ ደኑንም ደን ለማድረግ ያደረገውን አስተዋጽኦ ላይገነዘበው ይችላል። ይሁንና ደኑን ደን ያሰኘው ግን የእያንዳንዱ ዛፍ በዚያ ስፍራ መገኘት ነው። ስለዚህ ዛፍ ሲሰበርም ሆነ ሲቆረጥ ደኑ አልተጎዳም አንበል። አንተ ስትጎድል የሚጎድል ነገር አለ። የአንድ ሰው መጉደል ኢትዮጵያን ያጎድላታል ተብሎ ይታሰባልና፡፡
ስለሃገር የሚያስብ ሰውም ይህንን አደራረግ ልብ ብሎ ሊያየውና ሊያስተውለው መቻል አለበት። ዜጋው የሃገሪቱ አንድ አካል ነው። የዜጎቹ መኖርም ነው ሃገሪቱን ሃገር ያደረጋት እንጂ ሃገር ያለ ሰው በፖለቲካዊ እሳቤ የተቀመጠች የአፈርና ድንጋይ ክምር ብቻ ናት። ከህዝቡ ጋር ግን የእያንዳንዱ ዜጋ ክብርም መገለጫ ናት፤ ሃገሩ። እርስ በርስ የምንግባባበት መንገድ ካለም እርሷ ናት፡፡
በደኑ ውስጥ ለመድሃኒት የሚሆን ቅጠልና ስር፣ ለቅመም፣ ለዕጣን፣ ለጎማና ለነዳጅ የሚሆን ዛፍና የዛፍ ዝርያ እንዳለ ሁሉ በሰው ልጅም ውስጥ ምንም እንኳን በትምህርት የሚያዳብር ቢሆንም ሐኪም፣ ሽቱ ቀማሚ፣ ምግብ አዘጋጅ፣ ተሽከርካሪ ፈብራኪ፣ መምህርና ጠበቃ አእምሮ አለ። ይህም ብቻ ሳይሆን ባለተስጥኦ የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች በየዘርፉ አሉ። ሰዓሊያን፣ ቀራፂያን፣ ንግግር አዋቂዎች፣ ዳኞች፣ ድምጻውያን፣ የባህል ሐኪሞች፣ አራሾች እና የሌሎችም ሁሉ ድምር ደግሞ ሃገርን ያስውባል፤ያስከብራልም፡፡
ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ብዙ ሺ የሃገርነት ታሪክ ዓመታት ውስጥ የመጡና ያለፉ፣ የተከሰቱና የታለፉ አደጋዎች እንዲሁም ግጭቶችና ጦርነቶች አሉ።አንዳንዱ ዘመነ መሳፍንትን ሲወክል አንዳንዱ ደግሞ ጠቅላይነትን ያስታውሳሉ። ይሁንና ሁሉም በዘመናቸው የራሳቸውን አሻራ ትተው አልፈዋል። ፍጹም መጥፎ ፍጹምም ደግ የሚባል መንግስታዊ ቅርጽና አካሄድ በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደሌለ ሁሉ በእኛ ሃገርም አልነበረም፤ ወደፊትም አይኖርምም። እያንዳንዱ መንግስታዊ ቅርጽ የራሱ ድክመቶችና የራሱ ጥንካሬዎች አሉትና፡፡
በሁሉም ክፉ ትርክቶች ውስጥ ያለፉት ሁሉም አባቶቻችን ናቸው። ማንም ወደኋላ ሲመለስ ንጹህ የሚባል ታሪክ የለውም። የአማራ ንጽህና፣ የትግራይ ብጽእና፣ የኦሮሞ ቅድስና ወይም በተገላቢጦሽ ዘርን ከእርኩሰት ጋር አያይዞ ሌላው ቅዱስ የሚሆንበት ታሪክ የለንም፤ ሁሉም በሁሉም ውስጥ አልፈዋልና።
የትግራዩ ገበሬ እጆች ሻካራነት፣ የአማራው ገበሬ ተረከዝ ንቃቃታምነት፣ የኦሮሞው አራሽ ትከሻ ድድርነት ያለና የኖረ ዘመንና ዘመናዊነት ካልለወጠው በስተቀር አንዱን ለብቻ አሳራሽ ሌላውን አራሽ የምናደርግበት ብሂል ውሃ የሚያነሳ አይደለም። ሁሉም ባለመሬቶች የሁላችንም አያቶች፣ በሁሉም ገባሮች ውስጥ የሁላችንም ገባርነት አለበትና ማንም ነጻና ንፁህ የለም።
አንዱን ወገንና ዘር ለይቶ በዳይ የማድረጊያ ስልት፣ ዘመን የሞተበት፤ ጊዜ የሻገተበት ወግ ስለሆነ ማንንም ፃድቅ ወይም ኃጥዕ አያደርግም፤ መፍትሔም አያመጣም። በደል ለመፈጸምም የሁሉም እጅ ነበረበት፤ በደል ለመቀበልም የሁሉም ትከሻ አልፎበታል። ሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት የራሱ ባላባትና ጭሰኛ፣ የራሱ ገባርና አስገባሪ፣ የራሱ በዳይና ተበዳይ ነበረው እንጂ ‹‹የእንትንን ዘር እንትን አድርጎ›› የሚለው ብሂል የትም አያደርሰንም። ከዛፎች መካከል አንዳንዱ ዛፍ ደርጅቶ የአንዳንዱን እድገት እንደሚሻማ የሰው ልጅም ይህን በደል በሌላው ወገኑ ላይ መፈጸሙ የማይካድ ነው። ይሁንና ዘመንን የምንለካው በዘመኑ እንጂ፣ ፍትህና ፍርድን የምንሰጠው በሁኔታውና በጊዜው ልኬት እንጂ አሮጌውን ዘመን በአዲስ ዘመን ሚዛን አንሰፍረውም።
ለሃገራችን ዘመኑን የሚመጥን የአስተዳደር መዋቅር በመዘርጋት ማስኬድ ብዙ ቀጠሮ የሚያሰጥ ጉዳይ አይደለም። በተጠና መንገድ አዲስና አዋጭ የሆነ፣ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መዋቅር መዘርጋት የተገባ ነው። ዘመን ባፈጀበት በሻገተ አስተሳሰብ እየተጓተትን የችግራችንና ድህነታችን ምንጭ ሁሉ ‹‹እንትን የተባለው ዘርና ብሔር›› ነው እያልን ማላዘንና በክስ ዘመናችንን መግደል አይገባንም። ‹‹የጎረቤቴ ምርት ያማረበት ዝናቡ ወደ እርሱ ማሣ አጋድሎ ስለሚዘንብ ነው›› ብሎ የራስን የድህነት ምክንያት በጎረቤቱ ሰውዬ ማሣ ውስጥ መፈለግ ነፈዝነት ነው። ጠጋ ብሎ በመጠየቅና አብሮ ማደግ ግን የተመረጠ አካሄድ ነው፡፡
ጥንት ለጦርነት ሲኬድ ዓለማቀፍም ሀገር አቀፍም ህግ የለንም፤ የጦርነት ህግ እንጂ ተዋግተው ያሸነፉትን አካባቢ ንብረት በጠላትነት ምርኮ መበዝበዝ፣ ሰዎቹን በጦር ሜዳ ምርኮ እንደተያዘ ንብረት በባርነት ሰለባ ማድረግ ወግና ህግ ነበር። አሁን ግን በዓለማቀፉ ደረጃ በግጭት ወቅት የተማረከ ጠላትን በሰብዓዊ ክብር መያዝን መጠበቅ አለበለዚያም በወዳጅነት ክብር እንድንንከባከብ የተቀመጠው ህግ ግድ ይለናል።
በትናንት ሚዛን ዛሬ መሸቀብ አይቻልም ይለናል፤ ዘመኑ። በዚህ ዘመን፣ ንኡስ ፓውንዶችን አንጥረው የሚመዝኑ ኤሌክትሮኒካዊ ሚዛኖች አሉን። የሰው ልጅም የፍርድ አያያዝ እንዲሁ ሰብዓዊ ክብሩንና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ጊዜው ያስገነዝበናል። እኛ ግን የጠላንን እስካላጠፋን ድረስ የማያስተኛ፣ያልወደደንን አርቀን ካልጣልን በስተቀር የማናርፍ ሞገደኞች ሆነናል፡፡
ዛፉን መሆን እጣችን ከሆነ ተፈጥሮ በራሱ ጊዜ እስኪፈርድብን ወይም አንዱ በራሱ ምክንያት እስኪቆርጠን ድረስ ለተፈጠርንለት ዓላማ ኖረን ማለፍ ግዴታችን ነው። በነገራችን ላይ ዛፎች ሲቆሙ ቅጠሎቻቸው ወደላይ የሚዘረጉት ለምን እንደሆነ አስባችሁት ታውቃላችሁ? ካላወቃችሁ አንድ ህንዳዊ የሥነ-ተፈጥሮ ባለሙያ ያለንን ላስታውሳችሁ። ዛፎች ህያው ሆነው ሲቆሙ ቅጠሎቻቸውን የሚዘረጉት ኦክስጂን ለስነ-ፍጥረት ለቅቀው ካርበንዳይኦክሳይድ ለማስገባት ብቻ አይደለም፤ይህ የተፈጠሩለት እውነት ነው። እጆቻቸውን የሚዘረጉት ግን ለሰማያዊው አምላክ የማያቋርጥ ምስጋና ለማቅረብ እንደሆነ ይነግረናል። እኔም በእርሱ ሐሳብ እስማማለሁ፡፡
ዛፍና ዜጋ አንድም ለሥነፍጥረት ሁሉ አለዚያም ለክቡር ዓላማ ማለትም ለሰው ልጅ ሁሉ እንዲሁም ለሃገራቸው ጉዳይ ተፈጥረዋልና የሚጠብቅባቸውን ዓላማ ማከናወን ከእነርሱ ይጠበቃል፡፡
ስለዚህ የከበሩ ሃሳቦችን ማለትም የመንፈስ ፍሬ የሆኑትን መልካምነቶች ሁሉ በሌላው የሰው ልጅ ላይ በመዝራት ለህይወት መበርከት የሚገባንን ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። ሰውን ልናከብር፣ ልናሻሽል፣ ልንወድድ፣ ልንረዳ፣ ልንደግፍ ተፈጥረናልና ይህን ማከናወን ግዴታችን ነው፡፡
ሥልጣን ብለን የምንለው ሰው ሰራሹ ስልጣንም ቢሆን ጊዜያዊ አላፊና አዳላጭ በመሆኑ በተራቸው አግላዮች ሲገለሉ፣ ክፉዎች ሲከፋቸው፣ ገፊዎችን ሲገፉዋቸው አይተናል። እናም ያለፍትህ ማንንም ለመግፋት ስልጣን አልተሰጠንምና በተቻለን መጠን ነገራችንን ግልጽ፣ አሰራራችንን ክፍት በማድረግ አቃፊ ደጋፊና ቀራቢና አቅራቢ ልንሆን ይገባል፡፡
ዜጋ የሆነ ዛፍ ለቆራጭ የሚመቻቸው ራሱ የመፍለጫው ዛቢያ ሆኖ ነው፤ እንደሚባለው ራሳችንን በሥርዓት ለማየት ካልቻልን ለጥፋታችን ምንጭ ራሳችን መሆናችንን መዘንጋት አይገባንም፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን የቀዝቃዛውን የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ያሳወጁ ለበርሊን ግንብ መፍረስ ትልቁን ሚና የተጫወቱ ግራናዳ በተባለች ደሴት የተፈጠረውን ውዝግብ በኮማንዶዎቻቸው ያስቆሙ፤ ከሚካኤል ጎርባቾቭ ጋር አስደናቂውን የኒውክሌር ኃይል የጋራ ቁጥጥር ስምምነት የተፈራረሙ ሰው ነበሩ። ነገር ግን ከስልጣናቸው ወርደው ጥቂትም ሳይቆዩ ከፈረሳቸው ላይ ወድቀው በደረሰባቸው ድንገተኛ አደጋ የማስታወስ ችሎታቸውን ሙሉ በሙሉ በማጣትና ‹በአልዛይመር› ህመም በመጠቃታቸው ሲሰቃዩ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ሲሞቱ ግን እቅዶቻቸው አልሞቱም። ቁምነገሩ ከንፈር መጠጣ ሳይሆን ሰው የተፈጠረለትን ዓላማ በትውልድ እያሳኩ ማለፍን ይችሉበታል። አሜሪካውያን አንድ ነገር ፍሬ እንዲይዝላቸው ሲያስቡ 20ም 30ም 40 ዓመትም መጠበቅ ይችሉበታል። የጀመሩት ፕሮጀክት ግብ እስኪደርስም ይጠብቁታል፤ ይኮተኩ ቱታል። ተገቢውን ድጋፍ ሁሉ ይሰጡትና ወደሚፈልጉት ግብ ያደርሱታል።
ዛፎቻቸውን ከችግኞቻቸው ጀምሮ በጥንቃቄ ይይዟቸዋል። ከዚያም ለጣው ላነት የሚሆኑትን ለጣውላ፣ ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚሆኑትን እንደዚያው፣ ለጌጥ የሚሆኑትን ለጌጥነት፣ ለፓርክ የሚሆኑትንም በስርዓት እየለዩ ይጠቀሙባቸዋል፡፡
ለሰው ልጅም ከላይ እንደገለጥኩላችሁ በጥንቃቄ መርጠው ማዘጋጀት ይሆንላ ቸዋል። መሪዎቻቸውን ከጠዋት መኮት ኮት፣ አዛዦቻቸውን በማለዳ ማዘጋጀት፣ ሰራዊቱንም መገንባት ይችሉበታል። ዛፉን የሚያበላሽ በሽታ ሲገባም ደኑን እንዳያጠፋ በተቀናጀ ጥናት ለይተው እርምጃ መውሰድ ያውቁበታል።
እኛስ? እኛ ከእነርሱ የምንማረው ነገር ሊኖረን ይገባል። ይህን ችግራችንንም አንድ ቦታ ማቆም አለብን። የምናቆመው አማራጭ ይዘንና ነገር አቁመን ሳይሆን ባለንበት ሁኔታ ሳለን ሲሆን፣ይህም ግዴታችንም ስለሆነ ነው። ደኖቻችንን አውድመን የትም መድረስ አንችልምና።
አንድ ሰው፣ ‹‹እንደተናገረው ያለተገቢነት ዛፍ የሚቆርጥ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ተብሎ ሊጻፍበት ይገባል። ይህም ሆን ተብሎ ሊነገረው ይገባል። በድርጊቱም እርሱና ልጆቹ፣ ቤተሰቡ የሚያፍሩበትን ቅጣት መጣል የተገባ ነው።›› ሲል አድምጬዋለሁ።
በቅርቡ ከዜና አውታሮች የሰማሁትን አስደናቂ ዜና ላካፍላችሁና ልደምድም። የሪያል ማድሪድ ተከላካይ የሆነው እውቁ ሰርጂዮ ራሞስ አንድ አዲስ ቤት ስፔን ውስጥ ይገዛል። ቤቱ ውብ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ባማሩና ዘመን ባስቆጠሩ የጥድ ዛፎች ያጌጠ ነበረ። ራሞስ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃው እነዚህን በቁጥር መቶ ገደማ የሆኑ ውብ ዛፎች ማስቆረጥ ነበረ። (ኳስ እንደ ልቡ ለመጠለዝ አስቦ ይሆን? እንጃ ብቻ) ይህንን የተመለከቱ ጎረቤቶቹ ዝም ማለት አላስቻላቸውምና ክስ መሰረቱበት። ፍርድ ቤት ቀረበ። ፍርድ ቤቱም ፈጣን የሆነ ብይን ሰጠው። አንደኛ፣ ራሞስ በእያንዳንዱ የጥድ ዛፍ ምትክ ሁለት ዛፍ እንዲተክልና እንዲያሳምር፤ ሁለተኛም 260 ሺ ዩሮ ቅጣት እንዲከፍል ነው የተደረገው። ቅጣቱም ተቆርቋሪነቱም ልባዊና ሩቅ ተመልካችነት ያለበት ነው።
ራሞስ ሃገሩን ለአውሮፓ ዋንጫ በማብቃትና ክለቡን ሪያል ማድሪድን ለተደጋጋሚ የላሊጋ ዋንጫና የአውሮፓ ሊግ ዋንጫ እንዲሁም ለዓለም የክለቦች ሻምፒዮና ያበቃ ሰው ይሁን እንጂ ለተፈጥሮ እንክብካቤ ያለው ግምት አነስተኛ ወይም ምንም ነው። አለማወቁ ግን ከቅጣት አላዳነውም ።
እንዲህ ከተደረገም የጥፋቱን መጠን በመቀነስ የህይወትን ዕድሜ ማራዘም ይሆንልናል። የሃገር እድሜ በደኖቿ የሚተመንብት ዘመን ላይ መድረሳችንን ልጆቿ እንዲያውቁት በማድረግ ህጻናትን ከዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ስለደንና የተፈጥሮ ሃብት በማስተማር ጠበቃ እንዲሆኑ ስለሚረዳ በእጅጉ የተገባ ነው። ተፈጥሯዊ ጥበቃ ዛፍን ብቻ ሳይሆን፣ አየርን፣ ወንዝን፣ ዝናብን፣ ዳመናን፣ ምንጮችን የደኑን አራዊትና እንስሳት፣ አእዋፍና በደረታቸው የሚሳቡና የሚስለከለኩ ፍጥረታትና ሌላውንም መጠበቅ መሆኑን እንዲያጤኑ ማሳወቅ ነው፡፡
የሰው ልጅም ይህንን ማድረግ ለክብሩ፣ለስሙና ለዝናው ብቻ ሳይሆን ተረጋግቶ ህይወትን ማጣጣም እንዲችል ይረዳዋልና ዛፍንና የሰው ልጅን፤ ደኑንና ምድራዊ ፍጥረታትን ሁሉ በማስተሳሰርና በማያያዝ ማሰብ መልካም ነው። ልብ በሉ፣ ምድር እርቃኗን ስትቀር ድንበራችን ወደበረሃማነት እየሰፋ፣ ልምላሜን ፍለጋ እየተሰደድንና መሀሉ ዳር እየሆነ፣ ሃገር አልባ እንዳንሆንም እንጠንቀቅ፡፡
በደን ውስጥ ያለ ዛፍ ሲያድግ ድምፁ አይሰማም፤ ሲሰበር ግን …ምድርም አብራ ትጮሃለች፤ ገደላማው ምድር፣ የገደል ማሚቶ፣ ከፍ ባለ ድምጽ አንድ የህይወት ዛፍ ወደቀ፤ ሲሉ ያስተጋባሉ። በዲጂታል ዘዴ የሚቆረጥ ዛፍ የለንም፤ የሚቆረጥና የሚጠፋ እንዲሁም የሚለጠፍ ስም እንጂ፤ ስለዚህ ዛፍ ሲቆረጥ ዝም አንበል። ስማችንን በአጭር ጊዜ በሥራ እናድሰዋለን። ዛፋችንን ግን ወደነበረበት ለመመለስ ረዥም ጊዜ ይጠይቀናልና እናስብበት። መልካም የአረንጓዴ አሻራ ሳምንት ይሁንልን! እግዚአብሔር ሃገራችንንና ህዝቧን በልምላሜና ሰላም ይባርክልን!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 20/2011
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ