
ማዕከሉ ለኤግዚቢሽን አገልግሎት የሚጠቀምባቸው ሰፋፊ ሼዶች ቢኖሩትም፣ ግቢው በሙሉ በድንኳኖች ተሞልቷል። ለማስተዋወቅ የቀረቡ ትላልቅ ተሽከርካሪዎችም በብዛት ይታያሉ። ጎብኚዎችን፣ አምራቾችንና አገልግሎት ሰጪዎችን ዘና የሚያደርጉ ሙዚቃዎች ይሰማሉ፤ የካፌና መሰል አገልግሎቶችም በስፋት ይታያሉ።
ድንኳኖቹም ሼዶቹም በተለያዩ ድርጅቶች ምርቶችና አገልግሎቶች ሰጪዎች ተሞልተዋል። የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ፣ የአግሮ ኢንዲስትሪ ምርቶች፣ የቴክኖሎጂና ሌሎች ኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት ቀርበዋል። ሸማቾች ይጎበኛሉ፤ ይገዛሉ፤ አምራቾች/ ሻጮች / ደግሞ ያስጎበኛሉ፤ ያስተዋውቃሉ፤ ይሸጣሉ፤ ትስስር ይፈጠራሉ።
ይህ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንና ገበያ ልማት ማዕከል “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ቃል ሰሞኑን የተስተናገደው 14ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት፣ ምርትና አገልግሎትን ያስተዋወቀ፣ ግብይት የተካሄደበት፣ ለቀጣይ ልማትና ግብይት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ትስስርም የተፈጠረበት ተብሏል።
በኢትዮጵያ የንግድና ማሕበራት ምክር ቤት እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር በጋራ የተዘጋጀው ይህ ኤግዚቢሽን ከመጋቢት 4 ቀን 2017 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ነው የተካሄደው። በንግድ ትርኢቱ በርካታ የአገር ውስጥ አምራቾች እና ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል። በዋናነት የንግድ አካላት የእርሰ በርስ ትውውቅ እና ትስስር፣ የቴክኖሎጂ፣ የእውቀት እና የንግድ ልውውጥ ያደረጉበትና ሸማቾችም ምርቶችና አገልግሎቶችን መሸመት የቻሉበት ነው።
በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ የተገኙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶክተር) እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና በየደረጃው ያሉ የማህበራት ምክር ቤቶች በአዋጅ በተሰጣቸው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት በንግድና አገልግሎት እንዲሁም በአምራች ዘርፍ በመሰማራት በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅሰቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ያለመ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመተግበር ቀጣይነት ያለው እድገትን ማረጋገጥ፣ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን ማሻሻል፣ ተቋማዊ ለውጥ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። የንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤቶች የግሉ ዘርፍ የጋራ ድምፅ በመሆን ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ ሚና እንዲወጣ ለማስቻል እና የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስፋት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው መረዳት ያስፈልጋል።
ሚኒስትሩ ኢግዚቢሽኑ የንግዱን ማሕበረሰብ እና ሸማቹን በማስተሳሰር ረገድ የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። የንግዱ ማሕበረሰብ ጠንካራ፣ ተወዳዳሪና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት እውን ለማድረግ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ አገሪቱ እያስመዘገበች ያለችውን ዕድገት በማስቀጠል ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል።
በአጭር እና በመካከለኛ ጊዜ ከሚጠበቁ የማክሮ ኢኮኖሚ ውጤቶች አንፃር የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በመንግሥት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እና በጥራት አንዲጠናቀቁ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተቀመጠው መሰረትም መንግሥት የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። ለንግድ ሥራ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር እየተከናወነ ባለው ተግባር የንግዱ ማሕበረሰብ የንግድ ፍቃድ እና የምዝገባ አገልግሎቶችን በኦንላይን እንዲያገኝ እየተደረገ ነው።
በአገር ውስጥ ንግድ ብቻ ታጥሮ የነበረው የአስመጪነት እና የላኪነት እንዲሁም የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን ተደርጓል። ለአገር ውስጥም ሆነ ለአገር አቀፍ ገበያ የሚቀርቡት ምርቶችና አገልግሎቶች ጥራትን ለማላቅ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ የሚያደርግ የጥራት መንደር ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል።
የፖሊሲ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው ምክንያት ከወጪ ንግዱ በዓመት ይገኘ ከነበረው የውጭ ምንዛሬ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የላቀ ውጤት ለማግኘት ተችሏል። ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሦስት ነጥብ 84 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ተችሏል። ይህም የእቅዱ 146 በመቶ ሲሆን፣ ወርቅ፣ ቡና፣ የቅባት እህሎች እና የቁም እንስሳት ከ100 በመቶ በላይ ውጤት ተገኝቶባቸዋል።
የዘንድሮው 14ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት፤ በእነዚህ ደማቅ ድሎች ታጅቦ የተካሄደ ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ የለውጥ ፈር ቀዳጅ የሆነው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን በማጠናከርና ወደ ባህል በማሻገር በትጋትና በትክክል ከተሰራ ከዚህ የበለጠ ውጤት ማግኘት እንደሚቻልም አረጋግጠዋል።
የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ፣ በሥራ እድል ፈጠራና በሌሎችም ያለውን ሚና በማጎልበት እና ለአገሪቱ እድገት ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖረው ለማድረግ ዘርፉን በጠንካራና በሳል አመራር በሙሉ አቅም ለመደገፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ መንግሥት በአገሪቱ እየተመዘገበ ካለው እድገት እና ፖሊሲ አንፃር የተቃኘ ግልፅና ወጥነት ያለው አሰራር በመዘርጋት የሚታየውን የሕግ እና የአሰራር ክፍተት በመድፈን የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ የክትትልና የድጋፍ ሥራም ይሰራል።
ከዚህም ባሻገር መንግሥት ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግ ለማዕድን፣ ለቱሪዝም፣ ለአይሲቲ ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ተግባሮችን እያከናወነ ነው። የአገሪቱ ባለሀብቶች በግላቸውም ሆነ ከውጭ አቻዎቻቸው ጋር በመሆን በዘርፉ ኢንቨስት ቢያደርጉ ውጤታማ የሚያደርጋቸው ሁኔታ ተፈጥሯል።
በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ውስጥ የመሪነት ሚና የሚጫወት፣ ጠንካራና ዘላቂነት ያለው አቅም እንዲፈጠር ብሎም ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የግሉ ዘርፍ ሚና ወሳኝ ነው።
የኢትዮጵያን ምርቶች፣ አገልግሎቶችና ግብዓቶች በማስተዋወቅ፣ ለአገሪቱ ኢንዱስትሪ ልማት እድገት፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለንግድ ሥራ መስፋፋት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች የቀረቡበት እንዲሁም በሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች መካከል የገበያ ትስስር፣ የእውቀትና የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ነው። ከመላው አገሪቱ የተወጣጡ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ የሆኑበት ኤግዚቢሽኑ ከውጭ የመጡ የንግድ አካላት የተሳተፉበት እንደመሆኑ ልምድ ለመለዋወጥ እና ትስስር ለመፍጠርም ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
መንግሥት አስፈላጊውን የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በሚያደርገው ርብርብ የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ሚኒስትሩ በማስገንዘብ፣ የግሉ ዘርፍም ለስኬቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለግሉ ዘርፍ የሚያደርገውን ክትትል እና ድጋፍ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር የሥራ ግንኙነት በማድረግ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤትም የንግድና ኢቨስትመንት ተግዳሮቶችን በጥናት በመለየት ለመፍታት የጀመረውን አሰራር እንዲያጠናክር አሳስበዋል። የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ትግበራ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት አቶ ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው እንዳሉት ምክር ቤቱ የተቋቋመው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የመሪነት ሚና የሚጫወት ጠንካራ እና ዘላቂ አቅም ያለው የግል ዘርፍ በመፍጠር ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ ነው።
የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ውሰጥ ወሳኝ ሚና መጫወት የሚያስችሉት ፖሊሲዎች ተቀርፀው ተግባራዊ መሆን ከጀመሩ አንስቶ ዘርፉ ደረጃ በደረጃ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን ድርሻ አያበረከተ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ልማት ለማሳደግ መንግሥት ተግባራዊ ያደረጋቸውን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎች ውጤታማ የማድረጉ ሥራ ለተወሰኑ አካላት ብቻ የሚተው እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብር፣ የልማት አጋሮች ድጋፍ፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና በተለይ ደግሞ የመላው ማሕበረሰብ ያልተቆጠበ ድጋፍን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት ከመንግሥት፣ ከምክር ቤቱ፣ ከአጠቃላይ የንግዱ ማሕበረሰብ፣ ከልማት አጋሮች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እንደሚሰራም አመላከተዋል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት እንዳስታወቁት፤ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ቀጣይ እድገት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ሊወስኑ ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ አገሪቱ ለንግድና ኢንቨስትመንት ያላት ምቹነት ነው። ምክር ቤቱ ይህን ምቹ ሁኔታ እውን ለማድረግ ከመንግሥት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት እየሰራ ይገኛል ።
ፕሬዚዳንቱ ለዚህም ማሳያ አርገው የጠቀሱት ይህን በተከታታይ እየተካሄደ ያለውን የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የንግድ መድረክ ነው። ይህ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከምክር ቤቱና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ሲካሄድ የቆየ ኢግዚቢሽን የትብብሩ አንድ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ትርዒት ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ ኢንተርፕራይዞች እና የውጭ ሀገሮች የንግድ ተቋማት መሳተፋቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ልምድ ለመለዋወጥ እና ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። በንግድ ትርኢቱ ለተሳተፉ፣ ስፖንሰር ላደረጉ እና በተለያየ መልክ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የንግድ ትርኢቱ የንግዱን ማሕበረሰብ እና ሸማቹን ከማገናኘት ባለፈ የዕውቀት፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር እንዲሁም ጥራትና ውድድርን መሰረት ያደረገ ግብይት እንዲጠናከር እያስቻለ መሆኑንም ጠቅሰው፣ የግሉ ዘርፍ ከሃገራዊ ተሳትፎ ባለፈ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ዕድሎችንም ለመጠቀም የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ያመላከተ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ይህ የኢትዮጵያን ይግዙ ኤግዚቢሽን ለ13 ተከታታይ ዓመታት ተካሂዷል። በዘንድሮው ኤግዚቢሽን ላይ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞችና ኩባንያዎችን ጨምሮ ከሕንድ፣ ከሳኡዲ አረቢያ፣ ከቻይና፣ ከታይዋን እና ከሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት የመጡ ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ የቢዝነስ ተቋማት ተሳትፈውበታል።
የኤግዚቢሽኑ ትልቁ ዓላማ የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎት ለዓለም ማስተዋወቅ ነው። በሀገር ውስጥ የሚገኙ የንግድ ተቋማትም እርስ በርስ እንዲተዋወቁና እንዲተሳሰሩም ማድረግንም ያለመ ነው። አንዱ ከሌላኛው እንዲማር፣ አንዱ ለሌላኛው ገበያ እንዲሆን የራሱን ደካማ እና ጠንካራ ጎን የሚያውቅበት በጎውን ደግሞ በአቻ ለአቻ የንግድ መድረኮች አማካይነት የሚጋራበት፣ ለወደፊቱም በምን መልኩ ማምረት እና ማሻሻል እንዳለበት ለማመላከት ያግዛል።
ዋና ጸሀፊው፤ የንግድ ትርዒቱ የኢትዮጵያ ምርት እና አገልግሎት በዓለም ገበያ ይበልጥ ታዋቂና ተወዳዳሪ እንዲሆን እንደሚያግዝ ገልጸው፣ ተሳታፊዎቹ የእርስ በእርስ የቴክኖሎጂ ሸግግር የሚያደርጉበት መሆኑንም አስታውቀዋል። ቴክኖሎጂዎችን በምን መልኩ አገኛለሁ የሚለውን መልስ እንዲሁም ተፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን ማወቅ እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ገበያ አባል መሆኗንም ጠቅሰው፣ በዚህም ከ54 የአህጉሪቱ አገራት ጋር ስምምነት መፈረሙን ገልጸዋል። ቀጣናው ሀገሮቹ ነፃ ንግድ ለመከወን የፈጠሩት ሰምምነት መሆኑን ተናግረው፣ በዚህ ገበያ ውስጥ ኢትዮጵያ አባል መሆኗ ለኢትዮጵያ ምርቶችና አገልግሎቶች ነፃ የንግድ እንቅስቃሴ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ተግዳሮቶች የሚነሱበት እና በአፍሪካ አገራት መካከል ካለምንም እንቅፋት መገበያየት የሚያስችል መደላድል የሚፈጠርበት መሆኑን አስታውቀዋል።
ለአፍሪካ ትልቅ ገበያ ሊፈጥር ይችላል። ኢትዮጵያም በሌላ ገበያ ውስጥ መገበያየት ያስችላታል፤ ምርት እና አገልግሎት የሚሸጥበት ብቻም ሳይሆን ለአገሪቷም ትልቅ ፋይዳ አለው ሲሉም አብራርተዋል።
ለወደፊቱም የአገር ውስጥ ምርቶችን ማበረታታት ያስፈልጋል። ትወልዱም የራሱን እየገዛ በመጠቀም የሀገሪቱን ምርቶች ብራንድ ደረጃ በማድረስ በዓለም ገበያ ውስጥም ተፎካካሪ እንዲሆን ማድረግ ይገባዋል። ይህን ግብ ለማሳካት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም