በክረምት ወቅት እረፍት ላይ ያለው ተማሪ እንደ አንድ ትልቅ አቅም ሆኖ በተለያየ የስራ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ተደምሮ በቁጥር በዛ የሚሉ ወጣቶች በዚህ ወቅት ሊከናወኑ የተያዙት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የችግኝ ተከላ መርሃግብሮች ውጤታማ እንደሚሆኑ ትልቅ እምነት ተይዟል።
የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በትምህርት በማገዝ፣ የተጎሳቀሉ መኖሪያ ቤቶችን በመጠገን፣ በእድሜና በጤና ችግር ምክንያት አቅማቸው ለደከሙ ወገኖች አለኝታነታቸውንና ወገናዊነታቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ።ወጣቶቹ የአካባቢ ጽዳት እንዲጠበቅ እንዲሁም በችግኝ ተከላ መርሃግብር በመሳተፍ ለደን ጥበቃ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማገዝ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ወጣቱ ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል እምነት ተጥሏል፡፡
የወጣቶች ተሳትፎ አዲስ ባይሆንም የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች የህዝብ ንቅናቄን በመፍጠር መሳተፋቸውና በተለይም በሀገር ደረጃ አራት ቢሊየን ችግኞች በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለመትከል ታቅዷል።
በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ማህበር ይህን ትልቅ አገራዊ ጉዳይ በተልዕኮነት ተረክቦ በክልሉ ያሉ ወጣቶችን ምን ያህል አስተባብሯል? የወጣቱን የክረምት መርሃግብር ተሳትፎ፣ እዚህም እዛም የሚከሰቱ የሰላም መደፍረሶችን በመከላከልና በማስወገድ ረገድ የወጣቱ ሚና ምን ድረስ ነው? ስንል በኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር በኩል እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትና አጠቃላይ በማህበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት አዱኛ አሰፋ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
ፎቶ– ገባቦ ገብሬ
አዲስ ዘመን፡– በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ወጣቶች በክረምት መርሃግብር ያላቸው ተሳትፎና የማህበሩ ንቅናቄ በመፍጠር የሰራው ስራ ቢያጫውቱን?
ወጣት አዱኛ፡– ወጣቱ በበጎፈቃድ አገልግሎት ሲሳተፍ የመጀመሪያው አይደለም።በክረምት በስፋት ቢሳተፍም በበጋም በመሳተፍ ሚናውን በመወጣት ላይ ይገኛል። ከተለያዩ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ጋር በመቀናጀት በመንገድ ሥራ፣ በጽዳትና በተለያዩ መርሃግብሮች በመሳተፍ መልካም የሆነ ተሞክሮ አለው።
የወጣቶቹ ተሳትፎ በክልሉ ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመጓጓዝ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።ለአብነትም ከአዳማ ከተማ ጀምሮ እስከ አፋር ክልል ድረስ በመዝለቅ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሰጥተዋል።በዘንድሮ ክረምትም በቡራዩ ከተማና አካባቢዋ 100ሺ ችግኞች በመትከል ነው የበጎፈቃድ አገልግሎት የጀመሩት፡፡
አዲስ ዘመን፡– የወጣቱ የበጎፈቃድ አገልግሎት ተሞክሮ ካለው ስኬቱ እንዴት ይገለጻል?
ወጣት አዱኛ፡– የስኬቱ አንዱ ማሳያ ወጣቱ የበጎፈቃድ አግልግሎት ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ነው።በተለይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳጠ ናቀቁ ምን እንስራ? ብለው ይጠይቃሉ። ምን ልስራ ብሎ ጥያቄ እስከማቅረብ ደረጃ ላይ መድረሱና ለሰራው ሥራ ምስጋናም ሆነ ጥቅም ሳይፈልግ ጉልበቱንና እውቀቱን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑ ወጣቱ በአጠቃላይ ለሌሎች ወገኖቹ እና ዜጎች ማሰቡን አጠናክሮ መቀጠሉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– የወጣቱ ተሳትፎ በተለይ በገንዘብ ምን ያህል ይገመታል?
ወጣት አዱኛ፡– እኛም በየአመቱ በግምገ ማችን እናያለን።ወጣቱ በጉልበትና በእውቀቱ ብቻ ሳይሆን ለአቅመ ደካሞች የሚውል ገንዘብም በማሰባሰብ ይሳተፋል። አምና ብቻ ወደ ስምንት ሚሊዮን ብር ሰብስበው ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ጥገናና ግንባታ አውለዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ወጣቶች መልካም ነገር እንደሚሰሩ ሁሉ ለጥፋት ኃይሎች መጠቀ ሚያም ይሆናሉና በዚህ ላይ ማህበራችሁ ምን ሰራ?
ወጣት አዱኛ፡– የወጣት ባህሪ ተለዋዋጭ ነው።በስሜት የሚገፉባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። የጥፋት ኃይሎችም በቀላሉ ይጠቀሙ ባቸዋል። እዚህ ላይ ግን ግንዛቤ መያዝ ያለበት ለጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ የሚሆኑት ወጣቶች ሰፊ አይደሉም።ጥቂት ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቱ የጥፋት ኃይሎችንም በማጋለጥ ከፍተኛ ሚና ይወጣል።
የጥፋት ኃይሎች ችግር ከመፍጠራቸው በፊትም ቀድመው መረጃ በመስጠት ተልዕኳቸውን በሚገባ ይወጣሉ። ከዚህ አንጻር ሰላም ፈላጊ ወጣቶች እንዳሉ መረዳት ይቻላል።ዴሞክራሲን የሚለማመዱ ወጣቶች የመኖራቸውን ያህል በጉልበት የሚያምኑም አይጡፉም።በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ችግሮች ውስጥ ወጣቶች ተሳታፊ ናቸው።
አሁንም የሰላም ችግሮች አልጠፉም።ሰላም እስኪረጋገጥ የማህበራችን ወጣቶች ሰላምን በሚያደፈርስ ድርጊት ላይ እንዳይሳተፉ፣ ጥያቄም ካላቸው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንደሚችሉ እንዲሁም መብታቸውን ለመጠየቅ ግዴታቸውንም እንዲወጡ ጥረት እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡– ሀገራዊ ስሜት እየቀነሰ ክልላዊ ስሜት እየጎላ ስለመምጣቱ በብዙዎች ዘንድ ይነሳል።አንተ በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት ይኖርሀል? ይሕ ባህሪ በወጣቱ ላይ እየተንጸባረቀ ነው ብለህ ታምናለህ?
ወጣት አዱኛ፡– ከሀገራዊ ስሜት ክልላዊነት ማመዘኑ አይካድም። እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ ለማስቀረት ውይይትና ምክክር አስፈላጊ ነው። ማህበራችንም መድረክ በማዘጋጀት ከወጣቱ ጋር በተለያየ ጊዜ ተነጋግሯል። ግን በቂ አይደለም። ተከታታይነት ያለው ሥራ መስራት ይጠይቃል። በበጎፈቃድ አገልግሎት ወደ ተለያዩ ክልሎች በሄዱበት ጊዜ በቆይታቸው የአመለካከት ለውጥ እንደነበራቸው ከብዙዎቹ ወጣቶች አስተያየት መረዳት ችለናል።ብዙዎቹም ተለውጠዋል ለማለት እችላለሁ። ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማምጣት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ብዙና አበረታች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡– አመራርና አባላት የሚገና ኙበት ብዙ መድረክ የላቸውም ይባልል እውነት ነውን?
ወጣት አዱኛ፡– አስተያየቱ ከምን የመነጨ እንደሆነ ባላውቅም ከአባላቶቻችን ጋርም ሆነ ከመንግሥት ጋር የምንገናኝበት መድረክ አለን።ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅር አለን። በክልል ላይ ጉባኤ እናካሂዳለን።ሥራችንንም በየስድስት ወሩ እንገመግማለን።
በህግና በደንብ ነው የምንመራው።አንድ ነገር መያዝ ያለበት ሁሉም አባላት በየጊዜው ከአመራሩ ጋር ሊገናኙ አይችሉም። ማህበሩ ከመንግሥት ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር ወጣቱ የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ በማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሳል፡፡
በማህበሩ ሥር ያሉት አደረጃጀቶች ከወጣቱ የሚነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎችን ሰብስበው በማደራጀት ያቀርባሉ። ከአንድ ወር በፊት ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋር ውይይት አካሂደናል። በውይይቱ ከአደረጃጀቱ የተውጣጡ አባላት ተሳትፈዋል። ጥያቄዎች ቢቀርቡም የአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ወጣቶችን ጥያቄ በአንዴ መመለስ አይቻልም።
በክልል ደረጃ ወጣቱ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው።ነገር ግን ቅድሚያ የሚሰጠውን በማስቀደም ደረጃ በደረጃ ምላሽ ይሰጣል።የሀገሪቷንም አቅም ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል።ከመንግሥት ጋር የመወያየት እድል ማግኘት በራሱ አንድ እርምጃ ነው። ከመንግሥት ጋር መቀራረብ ሲፈጠር ችግሮች በሂደት ይፈታሉ።
አዲስ ዘመን፡– በማህበሩ ምን ያህል ወጣቶች ይገኛሉ? የማህበሩ እንቅስቃሴ ምን ድረስ እንደሆነ ብታጫውተኝ?
ወጣት አዱኛ፡– አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ አባላት በማህበሩ ውስጥ ይሳተፋሉ።ሰፊውን ቁጥር የያዘው አባል ቀበሌ ነው የሚገኘው። ማህበሩ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራቸው ሥራዎች የተሻለ አስተሳሰብ ያለውና አእምሮውንም ለመልካም ነገር የሚያውል ወጣት ለማፍራት ሲሆን፣ በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ላይ ከወጣቱ ጋር በመወያየት ይሰራል፡፡
በአጠቃላይ ማህበሩ ወጣቱ የዴሞክራሲ ባህልን እንዲለማመድ ከፍተኛ እድል ይሰጣል። ወጣቱ ስለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በቂ ግንዛቤ ካለው መብትና ግዴታውን ያውቃል። መብቱንም እንዴት መጠየቅ እንዳለበት ይገነዘባል። ማህበ ራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹም እንዲፈቱ ለትም ከመንግሥት ጋር በመሆን ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡ ፡ አዲስ ዘመን፡– የማህበሩ የ2012 ዓ. ም በጀት አመት ዕቅድ ምንድነው?
ወጣት አዱኛ፡– አደረጃጀቶችን ማጠናከር ነው።የወጣት አደረጃጀት እንዴት ነው የሚከናወነው እኔስ መብትና ግዴታዬ ምንድን ነው? እንዴት ነው ይህንን የማስከብረው? በሚለው ላይ ወጣቱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማህበሩ በትኩረት ይሰራል።
ብዙ ወጣቶች ከአደረጃጀት ውጭ ናቸው። ወጣቱ ለዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ከፍተኛ ሚና ስላለው ተሳትፎውን ለማጎልበት በማህበር ውስጥ ሆኖ ቢንቀሳቀስ የተሻለ ስለሚሆን፣ ግንዛቤ በመፍጠር የአባላት ቁጥርን የማብዛት ሥራ ይሰራል።ወጣቱ በየሜዳው ሳይሆን፣ በአዳራሽ ውስጥ በጋራ ሆኖ የመወያየት ባህል እንዲያዳብር በማድረግ ሰፊ ተግባራትን ለማከናወን ነው ማህበሩ ያቀደው።በዚህ ላይ መንግሥትም እንዲያግዘን እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ አመሰግ ናለሁ፡፡
ወጣት አዱኛ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 18/2011
ለምለም መንግሥቱ