
በኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች የተጀመሩበት ጊዜ ከክርስቶስ ልደት ቀደም ብሎ መሆኑን መዛግብትና ድርሳናት ይጠቁማሉ። የባህል ስፖርቶች ይህን ያህል ዘመን ያስቆጥሩ እንጂ አድገውና ዘምነው የዘመናዊ ስፖርቶቻችን መሠረት ለመሆን ግን አልታደሉም።
ለዚህ አንዱ ምክንያት ሙሉ ትኩረታችንን በዘመናዊው ስፖርት በማድረግ፣ ከመንግሥታዊ ፖሊሲዎች አንስቶ የባህል ስፖርቶቻችን ሥፍራ ሳይሰጣቸው መቆየታቸው ነው። ሌላው በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ የባህል ስፖርት ምንነትና ጠቀሜታን ካለመረዳት የተፈጠረ ስለመሆኑ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል የመክፈቻ መርሀግብር ላይ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ካደረጓቸው ንግግሮች ለመረዳት ይቻላል።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን እየተመለከትናቸው ያሉ ተስፋ ሰጪ ነገሮችም አሉ። የባህል ስፖርቶችን ተስፋ እያለመለሙ ካሉ ነገሮች መካከልም አንደኛው በየዓመቱ እየተካሄደ ያለው የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ነው።
የባህል ስፖርቶች በውድድርና በፌስቲቫል መልክ በየዓመቱ መካሄዳቸው ያለው ጠቀሜታ የማያጠያይቅ ቢሆንም፤ በተጓዘባቸው 22 ዓመታት ውስጥ ግን መሠራት የነበረበትን ያህል ተሠርቶበታል? የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻርም እንደ ሀገር ሁሉንም አሳታፊነቱና የብሔር ብሔረሰቦች የተሳታፊነት ፍላጎትም ከፍ ያለ መሆኑ እንደ ጥንካሬ ሊነሳ ይችላል። በዘንድሮው ውድድርና ፌስቲቫል ላይም ከትግራይ ክልል ውጪ ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ከመገኘታቸው በተጨማሪ ብዛት ያላቸው ተወዳዳሪዎችን ማሳተፋቸውም ይበል የሚያሰኝ ነው። እስካሁንም ድረስ ብዙ ሊገፋበት ያልተቻለውና ለቀጣይም በተለየ መንገድ ሊታሰብበት የሚገባ አንድ ነገር ግን አለ።
ይህም በውድድርና ፌስቲቫሉ ላይ እየታዩ ያሉ የባህል ስፖርት አይነቶች ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸው ነው። ዘንድሮ እየተካሄደ ባለው ላይ የተካተቱ የባህል ስፖርቶች 11 ናቸው። እስከዛሬ ድረስ ሕግና ደንብ ወጥቶላቸው በውድድር ለመካተት የቻሉ ደግሞ 13 ደርሰዋል። ተፈራ መኮንን የተባሉ የባህል ስፖርት ተመራማሪ ከዓመታት በፊት ባደረጉት ምርምር የደረሱበት ውጤትም፤ በሀገራችን 294 የባህል ስፖርቶች አሉ የሚል ነው። በዚህ ቁጥር መሠረት ስናሳለው ኢትዮጵያ ካላት የባህል ስፖርቶች ሀብት፣ በሀገር ደረጃ ለመጠቀም የቻለችው 5 ከመቶውን ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
አብዛኛዎቹ የባህል ስፖርቶች በተወሰኑ ማህበረሰቦች ውስጥ ብቻ የሚገኙ መሆናቸውን የተናገሩት የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሕይወት መሐመድ፤ “ስፖርቶቹ የሚከወኑት በተወሰኑ ማህረሰቦች ውስጥ ብቻ ከሆነ በውድድር መልክ ለማካተት ያስቸግራሉ። በሁሉም ዘንድ በቀላሉ ሊዘወተሩ የሚችሉና ለአሠራርም ምቹ መሆን አለባቸው” በማለት ለዳኝነት አመቺ በሆነና ሁሉንም ተወዳዳሪ በእኩል ለመዳኘት ሕጎችን ማውጣቱ ትልቅ ፈተና መሆኑን ይገልጻሉ። በብዙ አካባቢዎች ላይ የሚዘወተሩ አንዳንዶቹ፣ የየማህበረሰቡ የአጨዋወት ስልትና ሕጎች ልዩነት ስላላቸው ሁሉን ያማከለ ሕግና ደንብ ለማውጣት ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረግን እንደሚጠይቅም ወይዘሮ ሕይወት ይናገራሉ፡፡
የዘንድሮው ውድድርና ፌስቲቫል አዲስ ነገር ይዞ ብቅ ብሏል። ይህም በስፋት በአፋር ማህበረሰብ ዘንድ የሚዘወተረው “ኮኤሶ” የሚባለው የጨዋታ ዓይነት ነው። አንድን የባህል ስፖርት ወደ ውድድር መድረክ ለማምጣት ያለው ፈተና ቀላል አለመሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ምሁራን እና ከአፋር ክልል የባህል ስፖርት ባለሙያዎች ጋር በተደረገ የረዥም ጊዜ ጥረት በስተመጨረሻ ለማሳካት ተችሏል። ይሁንና የኮኤሶ የባህል ስፖርት በሆሳዕና እየተካሄዱ ባሉ መርሀ ግብሮች ውስጥ በውድድር መልክ የማይካተት መሆኑን ፕሬዚዳንቷ አስታውቀዋል። ይህም ለሁሉም አዲስና ገና በዘንድሮው ዓመት የመጣ በመሆኑ በውድድር መልክ ከማሳተፍ ይልቅ አስቀድሞ የስፖርቱን ዓይነትና ምንነት ማስተዋወቅ ስለሚያስፈልገው ነው ይላሉ፡፡
በባህል ስፖርቶች ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ሲካሄዱ የቆዩበትን መንገድ ማስተካከልና ለቀጣይ ማሻሻል ያስፈልጋል። የባህል ስፖርቶች መገኛ ታች ያለው የማህበረሰብ ክፍል፣ በዋናነትም በባላገሩ ዘንድ ሆኖ ሳለ ውድድርና ፌስቲቫሎቹ የተጀመሩት ከላይ ነው። በፌዴራል ደረጃ የሚካሄደው እንዳለ ሆኖ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳ ወርዶም በቀበሌ ደረጃ ውድድሮችን ማዘጋጀት ይቻላል። ከዘመናዊ ስፖርቱ ጎን አንድ ላይ እንዲሄድ ማድረግ ይገባል።
በ1990 የወጣው የስፖርት ፖሊሲ፤ የባህል ስፖርቶችን በተመለከተ ብዙ ነገሮችን ቢያሰፍርም ተግባራዊነታቸው አናሳ ሆኖ ቆይቷል። በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ሳያገኝ የቆየ ስለመሆኑም በተለያዩ ጊዜያቶች ፌዴሬሽኑ የበጀት እጥረት መፈተኑ አንዱ ማሳያ ነው። ከዚህ አንጻርም ፌዴሬሽኑ በአሁኑ ሰዓት በጥሩ መሻሻል ውስጥ እንዳለ ፕሬዚዳንቷ ይናገራሉ። የፌዴሬሽኑ አቅሙን እያጠነከረ ብዙ ጊዜያት ሳይሠሩ የቆዩ በርካታ ሥራዎችን በአሁኑ ሰዓት በማከናወን ላይ እንዳለም አስረድተዋል። ከእንቅስቃሴዎቹ መካከልም፤ የባህል ስፖርቶችን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ማካተትን ይጨምራል። ኢትዮጵያን በባህል ስፖርቶቿ ለዓለም ለማስተዋወቅ ከሚሠሩ ሥራዎች ጎን ለጎን፣ በሀገር ውስጥ በፍጥነትና በስፋት ማጠናከሩ ዘላቂ መፍትሄን ያመጣል ብለው ያምናሉ።
ትውልዱን ከባህል ስፖርት ጋር ከማቆራኘት አንጻርም፤ የባህል ስፖርቶችን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ማካተት፣ በትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ከሚካሄዱ የዘመናዊ ስፖርቶች ጎን ለጎን የባህላዊ ስፖርቶችም እንዲካተቱበት ማድረግና በታዳጊ ፕሮጀክቶች ላይ መሥራትን የመሳሰሉት ይገኙበታል።
የባህል ስፖርቶች የራሳቸው የሆነ የውድድር ሥፍራ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር የተነሱ ሃሳቦች ባይኖሩም፤ የባህል ስፖርቶቻችንን ወደ ዘመናዊ ዓለም በማምጣት ሀገራችንን ለማስተዋወቅ ስናስብ፤ የመወዳደሪያ ሥፍራዎች ብቻ ሳይሆን፣ የባህል ስፖርት የማዘውተሪያ ማዕከላትን በየአካባቢው ሊኖር የግድ ነው። የሠለጠኑ ዳኞችን ከመፍጠር አንጻር ብዙ መሠራቱን የሰሞኑ ዝግጅት ይመሠክራል። ከዚህ ባለፈ ስፖርቶቹን ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲሄዱ የማድረግና ተተኪዎችንም የማፍራት እንቅስቃሴዎች በበለጠ ተጠናክረው ሊቀጥሉም ይገባል፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም