ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎቹ

ዓለማችን በተለያየ የእድገት ሂደት ውስጥ ስትጓዝ ቆይታለች፡፡ ግብርና የመጀመሪያውን የሰው ልጅ ስልጣኔ ያመጣ ሲሆን፤ በተራው ደግሞ የተሻለ ካፒታልና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሚሻው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ቦታውን አስረክቧል፡፡ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ ሀገራትን ለዕድገትና ለብልፅግና አብቅቷል፤ የተሻለ የአኗኗር ሥርዓትን ፈጥሯል፡፡ አሁን ደግሞ ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ነው፡፡ ዘመነ ዲጅታላይዜሽን ዓለም በየዕለቱ አዳዲስ ክስተቶችን እንድታስተናግድና በፍጥነት እንድትጓዝ እያደረጋት ይገኛል።

ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና ገንዘብ፤ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልፅግና የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ የአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በቀጥታ የታያዘው ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው ጋር በመሆኑ የሀገራት ዕድገትም ሆነ ውድቀት ለዘርፉ በሰጡት ትኩረት ልክ የሚለካ ነው፡፡

ይህንኑ እውነታ በመገንዘብም ኢትዮጵያ ከአምስቱ የዕድገት ዘርፎች ውስጥ አንዱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲሆን ፈቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች፡፡ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን በመቅረጽም ሀገሪቱ በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚን ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ስትራቴጂም በዋናነት የዲጂታል መሠረተ ልማት በመገንባት እና በማስፋት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየተገበረች ያለችው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስትራቴጂ የመንግሥትን አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ እንዲሆን በማድረግ ዜጎች ባሉበት ሆነው የመንግሥትን አገልግሎቶች በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ የዜጎች የዕለት ተዕለት ህይወት እንዲቀላጠፍም መሠረት ይጥላል፡፡

ይህንኑ መነሻ በማድረግም ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው ዲጂታል ኢኮኖሚም ከ526 በላይ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዲፈጸሙ፤ የክፍያ ሥርዓቶችም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት እንዲሆኑ እና የተለያዩ መተግበሪያዎች እንዲለሙ ተደርገዋል።

ከታችኛው ቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው አካል ድረስ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እርስ በርሳቸው በማገናኘትና መረጃ በማለዋወጥ ለኅብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፤ ይህም በአገልግሎት አሰጣጡ ለተማረረው ሕዝብ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው፡፡ ለሥራ ፈጠራ ያለው ፋይዳም የማይተካ ሆኗል፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ‹‹ስታርት አፕ ›› ልማት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰላም ይሁን አደፍርስ እንደሚሉት፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የአንድን ሀገር እድገት እና ውድቀት የሚወስንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህንኑ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትም ኢትዮጵያ ከቀረጸቻቸው አምስት የእድገት ዘርፎች ውስጥ አንዱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመሆን በቅቷል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚያብራሩት፤ በተለይም ለእድገት እና ለሥራ ፈጠራ ልዩ አስተዋጽኦ ያለው የስታርት አፕ ትግበራ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ ሀገሪቱ ለቴክኖሎጂ ልማት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ማሳያው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ‹‹ስታርት አፕ›› ከዋና ሥራዎቹ አንዱ አድርጎ በመያዝ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ‹‹ስታርት አፖች›› የማበረታታትና የመደገፍ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል።

የፋይዳ ብ ሔራዊ መ ታወቂያ ዋ ና አ ስተባባሪ አቶ ዮዳሄ አርአያስላሴ በበኩላቸው እንዳብራሩት፤ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና ገንዘብ፣ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ለአንድ ሀገር ዕድገትና ብልፅግና የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡

ይህንኑ እውነታ በመገንዘብም ኢትዮጵያ ከአምስቱ የዕድገት ዘርፎች ውስጥ አንዱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲሆን ፈቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች፡፡ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን በመቅረጽም ሀገሪቱ በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚን ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ስትራቴጂም በዋናነት የዲጂታል መሠረተ ልማት በመገንባት እና በማስፋት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየተገበረች ያለችው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስትራቴጂ የመንግሥትን አገልግሎት በዲጂታል የታገዘ እንዲሆን በማድረግ ዜጎች ባሉበት ሆነው የመንግሥትን አገልግሎቶች በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ የዜጎች የዕለት ተዕለት ህይወት እንዲቀላጠፍም መሠረት ይጥላል፡፡

ለዚህ አንዱ መሠረት የሚሆነው ደግሞ ብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) የተሰኘው የመታወቂያ አይነት ነው፡፡ ፋይዳ መታወቂያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ለዜጎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ቴክኖሎጂ ዓለምን እየቀየረ ነው። የተቀየረ ዓለም ደግሞ የተቀየረ አሰራር ይፈልጋል፡፡ ቀደም ሲል በወረቀት ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች በሙሉ አሁን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ ገብተው ሰው ባለበት ሆኖ አገልግሎቱን የሚያገኝበት እውን ሆኗል፡፡

ቀደም ሲል ሰዎች መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ቀበሌ ወይም ሌላ አንድ መንግሥታዊ ተቋም የመሄድ ግዴታ ነበረባቸው፡፡ ዛሬ ግን አገልግሎቱ ቤታቸው ድረስ እየመጣ ነው፡፡ ፊት ለፊት አገልግሎት ሰጪና ተቀባይ የሚገናኙበት አሰራር እያበቃለት ነው፡፡ ውል የሚፈጽሙ ሰዎች እንኳን ‹‹እርጥብ ፊርማቸውን ካላስቀመጡ ውሉ የጸና አይሆንም›› የሚለው የተለመደ አባባል ቀርቶ ዛሬ ዲጂታል ፊርማ እውን ሆኗል፡፡

መታወቂያንም በተመለከተ በርካታ ሀገራት ከወረቀት በመላቀቅ ወደ ዲጂታል መታወቂያ ተሸጋግረዋል። ለዘመናት ስንገለገልበት የቆየነው በቦርሳችን ይዘናት የምንዞረው መታወቂያ በብዙ ሀገራት እየቀረች መጥታለች፡፡ በምትኩ የወረቀት ሕትመት ሳይኖር ቁጥር ብቻ የአንድ ሰው መታወቂያ ለመሆን በቅቷል ሲሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግስጋሴን አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ሲሳይ አበበ ይባላል። ወጣት የሕክምና ባለሙያ ነው። በተለያዩ የመንግሥትና የግል የሕክምና ተቋማት በሙያው ተሰማርቶ የቆየ ሲሆን፤ በሥራ ቆይታው ከተመለከተው የኅብረተሰብ ችግር በመነሳት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አቋቁሟል።

ኬ .ኤም .ኤስ .ኢ. ቲ .ኤች ኽልዝ ትሬዲንግ አ.ማ (ጤናዎ ዲጂታል ኽልዝ) የዲጂታል ጤና አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ መሥራች የሆነው ዶክተር ሲሳይ ሲናገር፤ እንደ ሀገር የዜጎች መሠረታዊ ፍላጐት የጤና አገልግሎትን ማግኘት ነው። ነገር ግን ዜጎች የሕክምና አገልግሎት ፈልገው ወደ ጤና ተቋማት ሲመጡ ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት እጅግ ይቸገራሉ፤ በተጨማሪም በሀኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን በቀላሉ አያገኙም፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል በማሰብ ነው ወደዚህ ሥራ የገባነው’’ ይላል።

‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ባደረግነው ጥናት 40 ከመቶ የሚሆኑ የሕክምና አገልግሎት ፈላጊዎች ሀኪም አግኝተው ማማከር አይችሉም። 60 ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የታዘዘላቸው መድኃኒት በአቅራቢያቸው ስለማይገኝ ሰዓታትን መድኃኒት በመፈለግ ያባክናሉ›› የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ በተለይ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ማለትም በካንሰር፣ በስኳር፣ ደም ግፊት የሚሰቃዩ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ለዚህ ችግር የተጋለጡ ናቸው ይላል።

የሀገራችን የጤና ሥርዓት ባህላዊ ስለመሆኑ የሚናገረው ዶክተር ሲሳይ፤ በሕክምና ተቋማት ከፍተኛ አገልግሎት ፈላጊ ስላለ በወረፋ የተጨናነቀ ነው፤ የመድኃኒት አቅርቦት ደካማ ነው። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ቢሠራም የሚታየው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከዚህ አኳያ በሀገሪቱ የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ መሥራት የውዴታ ግዴታ ነው ይላል።

ሌላው ወጣት ኦብሳ ሃምዛ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ ወጣት ነው፡፡ ወጣቱ እንደሚለው አንድ ምርት ተመርቶ ከፋብሪካ ወጥቶ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ ድረስ በመሃል ከሰባት እስከ አስር ሰው እየገባ የራሱን ትርፍ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል የሚለው ወጣት ኦብሳ፤ ጉዳቱን ሲያስረዳም ‹‹ለአብነት አንድ ምርት በአንድ መቶ ብር ከተገዘ በኋላ አንድ መንደር ላይ ወዳለ ሱቅ ሲደርስ 180 ብር ይሆናል፡፡ ባለሱቁ ደግሞ ሁለት መቶ ብር አድርጎ ለመጨረሻ ተጠቃሚው ይሸጣል፡፡ ይህ ጤናማ አካሄድ አይደለም›› ይላል።

ስለዚህም ወጣቱ ይህንን ችግር የሚቀርብ መፍትሔ ይዞ መምጣቱን ይናገራል። ዋት ኦብሳ ዲጂታል የገበያ ማዕከል በመዘጋጀት አምራችና ገዥ በቴክኖሎጂው እንዲገበያዩ የሚያደርግ ፈጠራ እውን አድርጓል፡፡ ገዥ የሚፈልገውን የምርት አይነትና ፍላጎት እንዲገልጽ በማድረግ ሦስተኛ ወገን ሳይኖር ለአብነት በፊት 200 ብር ይገዛ የነበረውን እቃ በ100 ብር እንዲያገኝ የሚያስችል አሠራር መሆኑን ይናገራል፡፡ ይህ ደግሞ ለኅብረተሰቡ እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት መባባስ አንዱ ምክንያት ምርት ከማሳ እስከ ገበታ ባለው ሂደት ተሳታፊ የሆኑ አካላት የራሳቸውን ጥቅም ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት በሚፈጠር የንግድ ሰንሰለት መርዘም ምክንያት ነው የሚለው ወጣት ኦብሳ፤ ይህ ቴክኖሎጂ ግን አላስፈላጊ የደላሎች ጣልቃ ገብነትን በማስወገድ ለኑሮ መረጋጋቱ የራሱም አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ይናገራል።

ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ዲጂታላይዜሽንን በማስፋፋት ረገድ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጎ በርካታ ሥራዎች መሥራት ተችሏል። በዚህም ከ526 በላይ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዲፈጸሙ፤ የክፍያ ሥርዓቶችም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት እንዲሆኑ እና የተለያዩ መተግበሪያዎች እንዲለሙ ተደርገዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከተሠሩ ሥራዎች የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ስትራቴጂ አንዱ ነው። ስትራቴጂው በቀጣይ አምስት ዓመት የኤሌክትሮኒክ ዘርፉ የሚመራበትን አቅጣጫ ለማመላከት ታልሞ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ስትራቴጂውን አጠናቅቆ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የመጨረሻ ግብዓት ማሰባሰብ ተችሏል።

ስትራቴጂው በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል ሲሆን፤ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የመተግበሪያ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ አወቃቀር እና በጀትን አካትቶ የያዘ መሆኑ ተገልጿል። ስትራቴጂው ከ2016 እስከ 2020 ዓ.ም ተግባር ላይ የሚውል መሆኑም ተመላክቷል።

እንደ ሀገር በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ የግድ ሆኗል፤ ያለቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ ከባድ እየሆነ መጥቷል። ከእነዚህ ዘመን አፍራሽ የቴክኖሎጂ ዘርፎች መካከል አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቀዳሚውን ስፍራ እየያዘ መጥቷል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነትን ለመጨመር እንዲሁም አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማስተሳሰር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ነው። ሰው ሰራሽ አስተውሎት/artificial in­telligence/ በአሁኑ ወቅት በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣በደህንነት እና በግብርና ዘርፎች ምርታማነትን እና ቅልጥፍናን ለመጨመር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ሆኖ እያገለገለ ነው። በኢኮኖሚው ረገድም መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዚህ ቴክኖሎጂ ድርሻ በዓለም ገበያ 350 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። ይህ ቴክኖሎጂ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን እና ህይወታችንም ሰፊ ድርሻ እየያዘ መጥቷል።

ያደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂው በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠ ቀሙበት ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና፣ የጤና፣ የደህንነት፣ እና መሰል ዘርፎችን አቅም ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል። ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማሽን ወይም ኮምፒዩተር የሰው ልጆችን ተክቶ ማመዛዘን፣ መማር፣ ማቀድ እና ፈጠራዎችን ማከናወን እንዲችል የሚያደርግ ነው። በዚህ ሁኔታ ማሽኖቹ አካባቢያቸውን እንዲገነዘቡ፣ የተገነዘቡትን እንዲተነትኑ ፤ ችግሮችን እንዲፈቱ እና አንድ የተወሰነ ግብ እንዲደርሱ ለማድረግ ያስችላቸዋል። ይህም በተለይ የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ ለምርት መጨመር፣ የጊዜ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ እና ውስብስብ ሥራዎችን ያለ ከፍተኛ ወጪ ለመፈፀም ያስችላል። ከጊዜ አንፃርም ያለማቋረጥ እና ያለ ምንም እረፍት ይሠራል ይህም የኅብረተሰብን ኑሮ የሀገርን ዕድገት እንደሚያቀላጥፍ ያስረዳል።

በ2020 አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮቪድ 19 ለማጥናት ጥቅም ላይ ውሏል። በ2030- አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለዓለም ኢኮኖሚ 15.7 ቢሊዮን ዶላር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ይጠበቃል፤ በዚሁ ዓመትም 50 በመቶ የሚሆነው ሥራ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እንደሚተካ ይታመናል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎት የጥራት እና ተደራሽነት ውስንነት አለበት፡፡ በታዳጊ ሀገራት ደግሞ ችግሩ ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያም ይህንን ችግር ለመቅረፍና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል መረባረብ የግድ እንደሚላት እሙን ነው።

ይህ ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፎች ሰፊ ተግባራት ያሉት በመሆኑ ከቅንጦት ይልቅ ለኅብረተሰብ ያለው አስፈላጊነት ግንዛቤ እያገኘ መጥቷል፤ ቴክኖሎጂው በተለይ በአፍሪካ ከባድ በሽታዎችን ለማስወገድ፣ የጤና እንክብካቤን እና ትምህርትን ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመቀነስ እና በአህጉሪቱ ለሚታየው የምግብ እጥረት የላቁ መፍትሔዎችን ለማምጣት የሚያግዝ በመሆኑ ለጉዳይ ትኩረት መስጠት ይገባል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ለቴክኖሎጂ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ዓለም ካለችበት ነበራዊ ሁኔታ አንፃርና ሌሎች ሀገራት በዘርፉ ከደረሱበት ልህቀት አኳያ አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል። በተለይ የመንግሥት ተቋማት ላይ ያለው የቴክኖሎጂ ፍላጐት አሁንም ገና በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ መረባረብ አስፈላጊ ነው።

ተቋማት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያዘምኑ በፖሊሲ ደረጃ አቅጣጫዎች ቢኖሩም በተግባራዊነቱ ላይ አሁንም ክፍተት አለ። ተቋማት ከለመዱት አሠራር ተላቀው የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አሁንም በትኩረት መሥራት አስፈላጊ ነው።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You