የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት መርጧል

የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን 24ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያካሂድ ስፖርቱን በቀጣይ አራት ዓመታት የሚመሩ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና ፕሬዚዳንት መርጧል።

ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ አቶ ኪሮስ ሀብቴ በቀጣይ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል።

በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ፉክክሩ ሁለት ዕጩዎች የቀረቡ ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ወይዘሮ መሠረት ደምሱ አንዷ ዕጩ ነበሩ። በምርጫው የቀድሞው የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኪሮስ ሀብቴ በአጠቃላይ ከ12 ድምፅ 9 ድምፅ በማግኝት ያሸነፉ ሲሆን ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመሩ ስድስት ሥራ አስፈፃሚዎችም ተመርጠዋል።

አቶ ኪሮስ ከዚህ ቀደም ፌዴሬሽኑን የኮቪድ ወረርሽኝ ወቅትን ጨምሮ ለዘጠኝ ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መምራታቸው የሚታወስ ሲሆን ከአራት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ኃላፊነት መጥተዋል። አቶ ኪሮስ በተለይም በሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ በነበረበት ወቅት ልጃቸው ሮቤል ኪሮስ ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ ወክሎ ባሳየው ደካማ አቋም መነጋገሪያ እንደነበሩ ይታወሳል። ይህም ፕሬዚዳንቱ በዘንድሮው ምርጫ ከአንድ የሥራ ዘመን በኋላ ወደ ኃላፊነት መምጣታቸውን በበርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ ጥያቄ እንዲፈጠር አድርጓል።

ከምርጫው አስቀድሞ ፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቷ በጠቅላላ ጉባኤው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው። የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ባለፋት አራት ዓመታት የሠራቸው መልካም ሥራዎች በተለይም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ውድድር ሁለት ወርቅ የተገኘበት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ደረጃ የዳኞች የአሠልጣኞች ሥልጠና ወደ ሀገራችን በማስመጣት ሥልጠናው በሀገራችን እንዲሰጥ ተደርጓል ብለዋል። በአፍሪካ ውሃ ዋና ኢትዮጵያ አንድ ቴክኒክ ባለሙያ ማስመረጥ መቻሏ፤ ዓለም አቀፍ ዳኛ ማፍራትና ማስመረጥ የተቻለበት ዓመታት መሆኑ፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ውሃ ዋና ሻምፒዮና የተሳተፈችበት ጊዜ እንደነበረ የገለፁት ፕሬዚዳንቷ የአፍሪካን ውሃ ዋና መምራት የቻልንበት ዓመታት እንደሆነ በንግግራቸው አመላክተዋል።

ወይዘሮ መሠረት አክለውም የውሃ ስፖርቶች በተደራሽነት፣ በጥራትና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲስፋፋ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልፀዋል። ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመፃፃፍ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለታዳጊ ፕሮጀክቶች ድጋፍ ማድረግ የተቻለበትና በዚህም አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ጠቅላላ ጉባኤ ያለፈውን ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ መርምሮ በማፅደቅ፣ የ2016 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ በኦዲት ሪፖርት እና በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ በመወያየት የዕለቱን አጀንዳዎች አፅድቀዋል።

ተሳታፊዎችም በበኩላቸው በጠንካራና በደካማ ጎን የተነሱትን ሃሳቦች በመጥቀስ ባለፉት አራት ዓመታት በውሃ ዋና ጠንካራ ሥራዎች መሠራታቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ዘርፉን በላቀና ሀገራዊ እምቅ አቅምን ባማከለ መልኩ ለማሳደግ በፕሮጀክቶች ላይ እስከታችኛው ማኅበረሰብ ወርዶ መሥራት ዙሪያ ክፍተቶች መኖራቸው፤ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያና የትጥቅና ቁሳቁስ ድጋፍ አነስተኛ መሆን፤ የሚሰጠው ሥልጠና በቂ አለመሆኑንና የቀጣይ ትኩረት ሥራ መሆን አለባቸውም ብለዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You