ማህበራዊ ሚዲያን ለምን አከበድነው?

የማህበራዊ ትስስር ገጾች ከዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን (ሜይንስትሪም ሚዲያዎች) ጋር ቦታ የተቀያየሩ ይመስላል:: ማህበራዊ ገጾች ሊሠሩት የሚገባውን እንቶ ፈንቶና ዋዛ ፈዛዛ የሆኑ ቀላል ነገሮችን ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ላይ፤ በተቃራኒው ደግሞ ጠንካራ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ይተነተናሉ::

ይሄ ነገር እየተለመደ ይመስላል:: ለዚህም ነው አሁን አሁን ማህበራዊ ገጾች ላይ የሚደረግ ነገር እንደ ቁም ነገር ተቆጥሮ ትችትና ወቀሳ እየተደረገበት ያለው:: ማህበራዊ ገጾች ላይ ቀልድና ዋዛ ፈዛዛ የበዛበት ነገር ሲጻፍ ብዙ ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት ‹‹ለምን ቁም ነገር አትጽፍም?›› የሚል ነው::

አዎ! ቁም ነገር ቢጻፍ የበለጠ ጥሩ ነበር፤ ዳሩ ግን እንቶ ፈንቶ ነገሮች ደግሞ ከማህበራዊ ገጾች ሊጠፉ አይችሉም:: የማህበራዊ ሚዲያን ባሕሪ እየዘነጋነው ይመስላል::

ማህበራዊ መገናኛ (ሶሻል ሚዲያ) ማለት ልክ እንደ ማህበራዊ ሕይወታችን ማለት ነው:: ‹‹ማህበራዊ›› የሚል ስያሜ የተሰጠውም ለዚህ ነው:: በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ደግሞ ብዙ ነገሮች አሉ:: ማህበራዊ ሚዲያ ልክ እንደ ማህበራዊ ሕይወታችን ነው ካልን፤ በማህበራዊ ሕይወታችን የሚደረጉ ነገሮች ይደረጉበታል ማለት ነው፤ በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ብዙ ነገሮችን የምናደርገው ብዙ አሰላስለን ሳይሆን ትዝ እንዳሉን ነው::

በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ከጓደኛችን ጋር፣ ከሥራ ባልደረባ ጋር፣ ከጎረቤትና ከቤተሰብ ጋር ሁልጊዜ ጠንካራ ጉዳዮችን አናወራም:: ካፌ ውስጥ ወይም መዝናኛ ቦታ ወይም ቤት ውስጥ ሰብሰብ ስንል ቀልድና ጨዋታዎች ናቸው የሚበዙት፤ ማህበራዊ ሚዲያ ልክ እንደዚያ ማለት ነው:: ተራ ገጠመኞች ሲያጋጥሙን አጠገባችን ላለ ጓደኛ እንናገራለን፤ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንታችንም ልክ እንደዚያ ማለት ነው፤ ተራ ገጠመኞችን ሁሉ ልናጋራበት እንችላለን:: ይሄ ማለት ግን ለሰዎች ምንም ስሜት የማይሰጥ ወይም ከባሕልና ወጋችን ውጭ የሆነ ነገር ሁሉ ይደረግበት ማለት አይደለም፤ እንደዚያ ከሆነ የራሳችንን ክብር ነው የሚያወርደው::

ማህበራዊ ሚዲያ የማህበራዊ ሕይወታችን ነፃብራቅ ነው:: ይሄ ማለት ሀሜትና አሉባልታም ይኖርበታል ማለት ነው:: ዲያቆን ዳንኤል ክብረት (አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የፓርላማ አባል) በአንድ ወቅት በአርትስ ቴሌቭዥን የደረጀ ኃይሌ ‹‹በነገራችን ላይ›› ፕሮግራም ላይ የተናገረውን በየአጋጣሚው ደጋግሜ አስታውሰዋለሁ:: ደጋግሜ ያስታውስኩበት ምክንያት የልቤን ስለተናገረልኝ ነበር::

የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሃሳብ ሲጠቃለል፤ ማህበራዊ ሚዲያ አዲስ ነገር ይዞብን አልመጣም፤ በማህበረሰባችን ውስጥ የነበረውን ነገር ተደራሽ እንዲሆን ነው ያደረገው፤ ሜዳውን ነው የፈጠረው:: ከማህበራዊ የትስስር ገጾች መፈጠር በፊት በጎረቤት፣ በአካባቢ፣ በገበያ፣ በአጠቃላይ በሰሚ ስሚ ይዛመት የነበረን ነገር አሁን በአንድ ጊዜ እንዲጥለቀለቅ አደረገ:: ቡና ላይ ይወራ የነበረ ሀሜት አሁን በብዙ ሺህ ሰዎች ዘንድ በአንድ ጊዜ እንዲታይና እንዲሰማ ሆነ:: ይህ ሲሆን ግን መተግበሪያው ባሕሪዎቻችንን ጭምር ይዞብን የመጣ መሰለን:: እንደ ማህበረሰብ ስንለወጥ ነው የማህበራዊ ገጾቻችን ገጽታም የሚለወጠው:: ምክንያቱም ገጾች ላይ የሚጽፉትም ሆነ የሚያወሩት በየመንገዱና በየመንደሩ ነውር ነገር ሲያደርጉ የምናያቸው ሰዎች ናቸው::

በቀልድና ዋዛ ፈዛዛ ነገሮች በኩል ግን በኢትዮጵያ ብቻ ያለ አይደለም:: በሌሎች የዓለም ሀገራትም ማህበራዊ ሚዲያ ቀለል ላሉ ነገሮች ነው የሚያገለግል፤ እንዲያውም ጠንካራ ሃሳቦችን በማሰራጨት በኢትዮጵያ ያለው ድርሻ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም::

እስኪ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የማህበራዊ ገጾቻቸውን ተመልከቱ:: የሚሰጣቸው ግብረ መልስና የዕይታ ብዛት(view) ከሀገራችን መገናኛ ብዙኃን በታች የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው:: ይሄ ማለት በሀገራችን ማህበራዊ ገጾች ንቁ ተሳታፊ አላቸው ማለት ነው::

ማህበራዊ ገጾች ለምን የጠንካራ ሃሳቦች ማንሸራሸሪያ ሆኑ ቢባል ምናልባትም የዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ጠንካራ አለመሆን ነው:: ፖለቲካዊ ጉዳዮች በስፋትና በድፍረት ስለማይተነተኑ፣ በሀገሪቱ የሚከሰቱ ክስተቶች በፍጥነት ሽፋን ስለማያገኙ ሰዎች ወደ ማህበራዊ ገጾች አዘወተሩ ማለት ነው:: ይህ ነገር ልማድ እየሆነ መጣ፤ አሁን ላይ ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ራሱ ‹‹ሰበር ዜና›› የሚያስተዋውቁት በማህበራዊ ገጻቸው ሆነ:: ማታ ቴሌቭዥን ወይም ሬዲዮ ስንከፍት ምንም አዲስ ነገር አናገኝም:: በማህበራዊ ገጾቻቸው ስናየው የቆየነውን ዜና ነው ማታ ሲያነቡት የምንሰማው:: በማህበራዊ ገጾቻቸው የሚለቁት ደግሞ ላለመቀደም ሲሉ ነው:: ይህ ዘመኑም የሚያስገድደው ሁኔታ ነው::

በሌላ በኩል ማህበራዊ ገጾች ልቅ የሆነ ነፃነት ስላላቸው ሰዎች ያዘወትሯቸዋል:: ዋናዎቹ የኤዲቶሪያል ሕግ አላቸው፣ ያልሆነ ነገር ቢናገሩ ተጠያቂነት አለባቸው፤ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው:: ማህበራዊ ገጾች ግን ባለቤታቸው ማን እንደሆነ ራሱ አይታወቅም፤ ተጠያቂነታቸው ጠባብ ነው:: የሚለቀቀው መረጃ በኤዲቶሪያል ውሳኔ ሳይሆን በአንድ ግለሰብ ፍላጎት ሊሆን ይችላል:: ችግሩ ግን ማህበረሰባችን ደግሞ ይህን አያገናዝብም:: የተባለ ነገር ሁሉ እውነት የሚመስለው ብዙ ነው::

ከምንም በላይ ግን ማህበራዊ ገጾችና ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ቦታ እየተቀያየሩ መሆኑ መጥፎ ልማድ ነው:: የውሃ መራጨትና ከዶሮ ጋር መሯሯጥ የመሳሰሉ የሕጻናት ጨዋታ የሚመስሉ ፕሮግራሞችን በቴሌቭዥን መስኮት እያየን፣ ቀጠናዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትንታኔዎችን ከፌስቡክና ዩትዩብ መከታተል የተገላቢጦሽ ነው::

በርግጥ ዲጂታል ሚዲያው በዓለም አቀፍ ደረጃም ዓይነቱና ተጠቃሚው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ነው:: ‹‹ስማርት ኢንሳይት›› የተባለው ድረ-ገፅ ከዓመት በፊት የማህበራዊ ገጾችን መረጃ አውጥቷል:: በዚህ መረጃ 60 በመቶ (4 ነጥብ 80 ቢሊዮን ሕዝብ ማለት ነው) የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ ማህበራዊ ገጾችን ይጠቀማል:: በቀን ያለው አጠቃቀም በአማካይ 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ነው:: በፊሊፒንስ ተሠራ በተባለ ጥናት ግን አንድ ሰው በቀን 4 ሰዓት ይጠቀማል:: ከማህበራዊ ገጽ ፕላትፎርሞች ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው ፌስቡክ ነው (ይህ እንኳን በግምትም ቢሆን ያስታውቃል):: ቀጥሎ ግን ዩትዩብ ነው::

በሀገራችን ያለው አጠቃቀምም ዓለም አቀፉን ሁኔታ የተከተለ ቢመስልም፤ አሁን ግን ቲክቶክ ሳይበልጥ አይቀርም:: ሆኖም ግን ለጠንካራ ጉዳዮች አገልግሎት ላይ የሚውሉት ፌስቡክና ዩትዩብ ናቸው:: ችግሩ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሀሰተኛ መረጃዎች እየዋለ ነው:: ይህን ልማድ ማስቀረት አለብን:: ይህን ልማድ ለማስቀረት ደግሞ ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን መብለጥ አለባቸው:: መብለጥ ሲባል ማህበራዊ ገጾች ላይ ያለውን ግሳንግስ ሁሉ ይዞ መሄድ ሳይሆን ጠንካራ ጉዳዮችን መተንተን ማለት ነው:: ምክንያቱም የተሻለ ታማኝነት ያላቸው ዋናዎቹ ናቸው:: በማህበራበዊ ገጾች የሆነ ዜና ሲሰራጭ ለማረጋገጥ ወደ ዋናዎቹ ነው የምንሄደው:: ስለዚህ ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ይህን ክብደታቸውንና ታማኝነታቸውን ማስቀጠል አለባቸው::

ለማህበራዊ ገጾች የምንሰጠው ክብደት ግን ልብ መባል አለበት:: ማህበራዊ ሚዲያ በባሕሪው ቀላል ለሆኑ ነገሮች ነውና የግድ ቁም ነገር ብቻ ይጻፍበት ማለት አያስችልም:: ለቁም ነገርና ለጠንካራ ጉዳዮች መገፋፋት ያለብን ዋናዎቹን ነው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You