ችግሮችን በጉልበትና በኃይል ለመፍታት የመሞከር አካሄድ አክሳሪ የጥፋት መንገድ ነው!

በመርህ ላይ የተመሠረተ ውይይት ልዩነቶችን በማጥበብ የዘላቂ መግባባት ምንጭ እንደሆነ ይታመናል። በተለይም ሀገር እና ሕዝብን በሚመለከቱ አጀንዳዎች ዙሪያ መግባባት ላይ ለመድረስ በሰከነ መንፈስ በመርህ ቁጭ ብሎ መነጋገር ወሳኝ ነው። ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ከማስፈን ባለፈም ልማት እና ብልፅግናን ለማምጣት የማይተካ አቅም ነው።

ሰላም በግለሰብ፣ በቤተሰብ ፣ በቡድን እና በማኅበረሰብ ውስጥ እየተገነባ የሚሄድ ትልቅ ማኅበረሰባዊ እሴት ነው። በብዙ ጥንቃቄ ተዘርቶ የሚያፈራ፣ ብዙ እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚፈልግ፣ የሰው ልጅን ሁለንተናዊ መሻቶች ተጨባጭ ማድረግ የሚያስችል፤ የሁሉንም ትኩረት እና ኃላፊነት የሚጠይቅ ነው።

የሰላም ጉዳይ ለመንግሥት፣ ለተወሰነ ቡድን ወይም ማኅበረሰብ ብቻ ተለይቶ የሚሰጥ አይደለም። የእያንዳንዱን ሰው የዕለት ተዕለት ሕይወት በከፋ መንገድ የሚፈታተን፣ የሀገራትን ጨምሮ የዓለምን እጣ ፈንታ ሊወስን የሚችል ነው። በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ሊያስከትል የሚችለውም አደጋ ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል እና ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ነው።

ለዚህም በቀደሙት ዘመናት ዓለም ያስተናገደቻቸውን የሰላም እጦት ዓመታት ማስታወስ ተገቢ ነው፤ በግልጽ ከሚታወቁት ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ባለፈ በየዘመኑ በመላው ዓለም የተለያዩ ስሞች እና ምክንያቶች እየተሰጣቸው የተካሄዱ ጦርነቶች የሰውን ልጅ በሰላም እጦት በብዙ ፈትነውታል።

ሀገራችን ኢትዮጵያም ብትሆን በብዙ የጦርነት ትርክቶች የተሞሉ የታሪክ ገጾች ባለቤት ናት። ሕዝቦቿ ለፍትህ እና ለነፃነት ካደረጓቸው እልህ አስጨራሽ የተጋድሎ የጦርነት ታሪኮች በተጨማሪ ብዛት ባላቸው የእርስ በርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች ውስጥ ለማለፍ ተገደዋል። በዚህም ላልተገባ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች ተዳርገዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ከተቸራቸው ሥልጣኔዎቻቸው ወርደው አሁን ላይ ላሉበት፣ መገለጫቸው ለሆነው ድህነት እና ኋላቀርነት ተዳርገዋል። ብዙዎችን ያስደመሙ የታሪክ ትርክት ባለቤት የመሆናቸውን ያህል፤ አንገት ለሚያስደፋ ጠባቂነት /ተመጽዋችነት የተዳረጉበት እውነታ ተፈጥሯል።

ልዩነቶችን በሰከነ መንፈስ በውይይት እና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ዘመን እና ጊዜ ባለፈበት የእንሞካከር /ይዋጣልን እሳቤ የተቃኘው የፖለቲካ ባሕላችን፣ እንደ ሀገር ትናንት ሆነ ዛሬ ላይ እያጋጠሙን ላሉ ፈተናዎች ዋነኛ ምክንያት ነው። ከዚህ ዘመኑን ከማይዋጅ ትውልዱን ከማይመጥን አስተሳሰብ መውጣት ካልተቻለ፣ ችግሩ የነገ ሀገራዊ ተግዳሮት መሆኑም የማይቀር ነው።

ከመጣንበት ረጅም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክም ሆነ አሁን ካለንበት ተጨባጭ እውነታ አኳያ፣ ይህ ኃይልን መሠረት ያደረገ “በአሸናፊ ተሸናፊ” ትርክት ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ባሕላችን ማንንም ተጠቃሚ አላደረገም። የትውልዶችን ህልም ከመንጠቅ ባለፈ ባለ ራዕይ ትውልዶችን የራዕያቸው ባለቤት አላደረገም።

ይህ ደግሞ እያንዳንዱ ትውልድ ከትናንት ወጥቶ የራሱን ዛሬ እንዳይኖር አድርጎታል። ትውልዶች የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው ወስነው እንዳይሄዱ የዘመናት ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል። ዛሬም ቢሆን ትውልዱ ዘመኑን መስሎ እንዳይራመድ ፤ የራሱን ዕጣ ፈንታ እንዳይወስን ጥላ ሆኖ እየተከተለው ነው። በብዙ መልኩም ያልዘራውን እንዲያጭድ እያስገደደው ነው ።

ይህንን ሀገራዊ ችግር ለመፍታት በየዘመኑ የነበረው ትውልድ ብዙ ጥረዋል፤ ብዙ ዋጋም ከፍለዋል። ይህም ሆኖ ግን ዛሬም ከዚህ አክሳሪ አስተሳሰብ ያልተፋቱ ግለሰቦች እና ቡድኖች መኖራቸው ችግሩ አሁንም ከዚህ ችግር ሙሉ ለሙሉ እንዳንላቀቅ አድርጓል።

ችግሩ ለዘመናት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ጸንቶ የቆየውን ሀገረ- መንግሥቱን ስጋት ውስጥ ከመጨመር አልፎ ፤ ለዘመናት በክፉም በደጉም አብሮ የኖረውን ሕዝባችንን በመከፋፈል የፖለቲካ ቁማር የመቆመሪያ ሸቀጥ ወደ ማድረግ ያደገ የጥፋት /የነውር እሳቤ ነው።

ይህንን ከዘመኑ የራቀ፤ ከሕዝባችን በሰላም አብሮ የመኖር ሃይማኖታዊ ባሕላዊ እና ማኅበረሰባዊ እሳቤ ያፈነገጠ፤ በብዙ መስዋዕትነት ለዚህ ትውልድ የተላለፈን ሀገረ መንግሥት የህልውና ስጋት ውስጥ በመጨመር ሕዝብን ሀገር አልባ ሊያደርግ የሚችል የጥፋት እና የነውር አሳቤዎች በቃችሁ ለማለት ጊዜው አሁን ነው። ይህንን ለማለት ሁሉም ዜጋ የሰብዓዊነት፣ የታሪክ እና የሞራል ኃላፊነት አለበት፡፡

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You