ስለትምህርት ዓላማ፣ ምልዓት እና መከወኛ ዘዴ

መግቢያ

ለመሆኑ የትምህርት ዓላማና ባሕርይ ምንድነው? ከዚህ የትምህርት ዓላማ የሚያደርሰው ዘዴስ (Methods)? ትምህርት የሚዋቀርበት መንገድስ? የትምህርት መሣሪያው ወይንም ምልዓቱስ (Content, Material) ምን መሆን አለበት? በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ሃሳብ የተወሰኑ የጥያቄ ሰበዞችን መዝዤ ለመፈተሽ ሞክራለሁ።

ከሁሉ አስቀድሞ፣ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ዘመናዊ የትምህርት ሥነ-ዘዴያችንን ጉድለቶች ማሳየትና በአንጻሩ ደግሞ የነባሩን የሥርዓተ ትምህርታችንን ጠቃሚ ተሞክሮዎች በንጻሬ በማቅረብ፤ እነዚህን በጎ ልምዶች እና ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ለዘመናዊ የትምህርት አውዶች እንዲሆኑ አድርገን አሻሽለንና አዘምነን፣ ካስፈለገም ከዘመኑ የት/ት ሥነ ዘዴ ጋር አስተጻምረን ወደ ሥርዓተ ትምህርታችን በውጤታማነት በማሻገር፤ በውጤቱም የትምህርት መዋቅሩን በማስተካከል የትምህርት ስብራታችንን ልንጠግንባቸው እንደምንችል ሃሳብ ለማቅረብ ነው። ሁለተኛውና ዋነኛው የጽሑፌ ዓላማ ግን፤ ስለ ትምህርት በተለይ ለማሰብ ለመነጋገር እና ለመሥራት እንድንነሳሳ የሕዝባችንን መንፈስ እና ስሜት መቀስቀስ ነው።

ይህ መጣጥፍ፣ የሦስት ክፍሎችን ቅንብር የያዘ ነው። በመጀመሪያ፣ ስለ ሁለቱ የትምህርት ዓላማዎች (ዕውቀት እና ሠናይነት) ትርጉምና ምንነት በጥቂቱ ከገለጸ በኋላ በአንጻሩ ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓታችን አንዱን ወሳኝ የትምህርት ዓላማ (ሠናይነትን /Virtue) ቸል ማለቱ ያስከተለውን (ማለትም የሥነ ምግባር ግዴታዎችን የትምህርታችን መሠረት አለማድረጋችን እያስከፈልን ስላለው ዋጋ) ሃሳብ ካቀረበ በኋላ፤ ስለ አስተማሪና ተማሪ ግንኙነት በሁለተኛ ደረጃ ይዳስሳል፡፡ በሦስተኛው ክፍል ደግሞ፣ ስለ ሦስት ተጨማሪ የሥርዓተ ትምህርታችን (ነባሩ) አላባዎች ያትታል።

ሁለቱ የትምህርት ዓላማዎች ዕውቀትና ሠናይነት፡-

እዚህ ላይ አሁን በገሀድ ያሉን ዩኒቨርሲቲዎቻችንን በግብራቸው ከመፈተሻችን በፊት፣ በቅድሚያ የዩኒቨርሲቲ ዓላማ ምን ሊሆን እንደሚገባው ከኀልዮታዊ መደቡ አንጻር በጥቂቱ እንመልከት። የዩኒቨርሲቲ ዓላማ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ተማሪዎችንስ ማፍራት ይገባዋል? የተማረ የሚባለውስ ሰው በውስጡ ምን የያዘ ምን ያከማቸ መሆን ይገባዋል? የሚለውን በተመለከተ ሊቁ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲቋቋም የበሩን ሁለት አዕማድ በዕውቀት እና በሠናይት (Virtue) በመመሰል “ሠናይትና ዕውቀት እነዚህ ሁለቱ የዚህ ኮሌጅ ብቻ ሳይሆን የመላ አውሮፓ የትምህርት ዓላማ ወሳኝ አኃዞች ናቸው” በማለት ከፍተኛ ታሪክ ያላቸውን የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ሲቋቋሙ የተሰጣቸውን ዓላማ በመጥቀስ ያብራራሉ።

ከዚህ እውነታ ስንነሣ፣ ዩኒቨርሲቲ የቀኝና የግራ መወጣጫው በዕውቀትና በሠናይነት በሚዋቀር መሰላል የሚመሰል፣ ዕውቀትን ከሠናይነት ያጣመረ፣ ወደ ከፍታ የሚያደርስ መወጣጫ ነው። ወደ ሕሊና ከፍታ ብቻ ሳይሆን ወደ ንጹሕ ልቦና ወደ በጎ ምግባርም የሚያደርስ ነው። ተቀዳሚ ግቡም የተኮተኮተ አእምሮ እና የታረቀ ልቦናን ያጣመሩ ምሉዓን ዜጎችን ማፍራት ነው።

ዩኒቨርሲቲ የዕውቀት፣ የሳይንስ፣ የመረጃ፣ የግኝት፣ የምርምር፣ የሞያ፣ የክሂል ማዕከል ብቻ ሳይሆን የሠናይ ምግባር፣ የበጎ እሴት፣ የመልካምነት፣ የደግነት፣ የርትዕ፣ የጽድቅ የእነዚህ ሁሉ ኁባሬ (Compositum) መገኛ ነው። በአጭር ጽሕፈት፣ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚያዊና የሞራላዊ ተናባሪዎች ኁባሬ የሚገኝበት አምባ ነው፡፡ ዐብይ ተልዕኮውም በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በምግባርም አርአያ፣ ሠናይ እና ፍትሐዊ የሆኑ ምሉዕ ዜጎችን መፍጠር ነው።

በመሠረቱ፣ ሰው ከምሉዕነት የሚደርሰው ለሕሊናው የሚያስፈልገውን ምግብ (ዕውቀት) ስላገኘ ብቻ አይደለም። ይልቁንም፣ ልቦናውም መኮትኮትና መሠልጠን አለበት። ይህም ማለት፥ ዕውቀት ብቻውን ምሉዕ አያደርግም። ዕውቀት ብቻውን ቅንጭብ ነው። አንካሳ ነው። አንድ ዓይና ነው። ጎደሎ ነው። ዕውቀት በሠናይነት በደግ ፍላጎት ልጓም ካልተገራች አዝማሚያዋ አደገኛና ጥፋት አምጪም ነው።

ይህም የሚሆንበት ምክንያት፣ ዕውቀትን የሚጠቀምበት ፍላጎት ደግ ካልሆነ ውጤቱ ትዕቢት እና ጥፋት ስለሚሆን ነው። ስለዚህ፣ ዕውቀት ምሉዕነትን እንዲያጎናጽፍ ሌላ አጣማሪውን፣ አጣማጁን፣ አቀናጁን ይፈልጋል። ይህም አቀናጅ፣ አጣማጅ፣ አከናዋኝ ሠናይት (Virtue) ይባላል። ለዚህም ነው፣ ዕውቀትን የሕሊና ሀብታችን ስሜትን እነርሱን የሚመስሉትን ሁሉ የሚያርቅ ደግ ፍላጎት ግድ ይላል የምንለው። የአንድ ዩኒቨርሲቲ ተቀዳሚ ሚናም፣ ይህንኑ፣ የሰው ልጅ የሕሊናና የልቦና ምግብ በምልአት ለማሟላት መጣር ነው፡፡

ይህን የዩኒቨርሲቲ ዐብይ ተልዕኮ ሃሳብ ይዘን፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችንን በምናይበት ጊዜ፣ አሁን በገሃድ ያሉን ዩኒቨርሲቲዎቻችን ዕውቀትን ከሠናይነት አጣምረውና አሳክተው ተማሪዎቻቸውን መመገብ እና ምሉዕ የሆነ ዜጋ ማፍራት ቢጠበቅባቸውም ቅሉ፤ ይህ ተሽሮ በምትኩ ትኩረታቸውም፣ የሚመዝኑትም፣ እውቂያ የሚሰጡትም አካዳሚያዊ አቅምን ብቻ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠውልናል።

ተማሪዎቹም ቢሆኑ ለማግኘት የሚሯሯጡት (በትጋትም ይሁን በስርቆት) ይህንኑ አካዳሚያዊ ውጤት ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው። በዚህም ሳቢያ፣ በተቋማቶቻችን ውስጥ በምግባር አርአያ፣ ሠናይ እና ፍትሐዊ ለመሆን የሚያተጋ ምንም ዓይነት ገፊ ምክንያት አይገኝም ለማለት ይቻላል። በጥቅሉ፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚገመግሙትም ዕውቂያ የሚሰጡትም አካዳሚያዊ አቅምን ብቻ መሆኑ፣ የተማረ ማለት አዋቂም በምግባሩ አርአያም የሆነ ጥሩ ሰው ማለት ነው የሚለውን ነባሩን የሥርዓተ ትምህርታችንን ኅልዮት መሻራቸውን ያሳያል።

ለዚህም ነው፣ የተማረ ሰውነት አንዱ መለኪያ መሆን የሚገባውን ሠናይነትን፣ በጎ ምግባርን ችላ በማለታቸው፣ የተማረ ሰውን መለኪያው በሞላ በጎደል የምስክር ወረቀት ብቻ ሲሆን ደጋግመን የምንታዘበው። የዲግሪ ባለቤቱን ከተማረው ጋር አቻ በማድረግ የማምታታቱም ነገር የዚህ ውጤት ነው ቢባል ስህተት አይሆንም።

ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓታችን ይህን ወሳኝ የትምህርት አዕማድ (ሠናይትን (Virtue) ቸል በማለት እናም ትኩረቱ እና መመዘኛው ዕውቀት ብቻ በመሆኑ፤ ዕውቀት ከደግ ፍላጎት፣ ከጽድቅና ከርትዕ ከሠናይ ምግባር እንድትነጠል ሆኗል። ተማሪዎቻችንም መሠረቱ መልካም ምግባር በሆነ ዕውቀት ሞያና ችሎታ መታነጽ ሲገባቸው፤ በምትኩ ግን፣ መልካም ምግባር ላይ ያልበቀለ ዕውቀት፣ ሞያ እና ችሎታ እየመገብን ስለምናስመርቃቸው የሚበልጡት ፕሌቶ እንዳለው ለስላሳ (Noble) እግዜርን የሚመስሉ ፍጥረታት ከመሆን ይልቅ ወደ ተቃራኒው ገጸ ሰብዕና መሳባቸው። ለዚህ አንዱ ማሳያ የሚሆነው፣ የገጠመን የተማሪዎቻችን፣ የተማሪነት ዲሲፕሊን ድቀት ነው። መቼስ አሁን ባሉን ተቋማቶቻቸን ውስጥ የታረቀ ልቦና፣ ደግ ምግባር እና ጠባየ ሠናይነት የሚያሸልም፣ የሚገድ አልያም ከአንድ የትምህርት ደረጃ ወደ ቀጣዩ ለመሸጋገር የሚያስፈልግ ነው ብሎ ማመን ተላላነት ነው፡፡

እዚህ ላይ፣ አንባቢው በሀገራችን ሲሰጡ የቆዩት የሥነ- ምግባር እና የሥነ-ዜጋ ትምህርቶች ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓታችን ሠናይነት የተሰኘውን የትምህርት አዕማድ ቸል ማለቱን ያሳያሉ ወይ የሚል ጥያቄ ማቅረቡ የሚጠበቅ ነው። በእኔ እምነት፣ የነዚህ ትምህርቶች ውጤት ምን እንደሆነ ለማወቅ የምናስመርቃቸውን ተማሪዎች የምግባር ሁኔታ በአንክሮ መመልከቱ ብቻ ነገሩን በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ አድርጎ ያሳያል። የእነዚህ ትምህርቶች ነገር ወዴት  የነዚህ ትምህርቶች ውጤት ምን እንደሆነ በጥናት የተደገፈ ማሳያ ካስፈለገ ደግሞ የኢትዮጵያ የሥነ-ምግባር ማዕከል ያወጣውን የጥናት ውጤት ማስታወሱ ብቻ ይበቃል። የኢትዮጵያ የሥነ ምግባር ማዕከል ለ3 ዓመታት ባካሄደው ጥናት በሀገራችን ሲሰጡ የቆዩት የሥነ-ምግባር እና የሥነ-ዜጋ ትምህርቶች ያልተሳኩ መሆናቸው በጥናቱ ማረጋገጡን አስረግጦ ነግሮናል። ይልቁንም፣ ሙስና፣ ምዝበራ፣ እምነት የሚጣልባቸው ባለሞያዎች መመናመን እና መጥፋት እነዚህ ሁሉ ከቁጥጥር ውጭ እየወጡ እንዳሉ የማዕከሉ ሪፖርት በስፋት ያብራራል። እዚህ ላይ፣ አስተውሎት እንዲኖረን ይገባል ብዬ የማስበው፣ የሥነ ምግባር ግዴታዎችን የትምህርታችን መሠረት አለማድረጋችን ከዚህም በላይ ዋጋ ሳያስከፍለን በፍጥነት መላ ልንዘይድለት ይገባል የሚለውን በተመለከተ ነው።

በአንጻሩ፣ እንደ ነባሩ የት/ት ሥርዓታችን አንድ ተማሪ ከአንድ የትምህርት ደረጃ ወደሚቃጥለው ለመዘዋወር የተወሰኑ ጥብቅ አካዳሚያው መስፈርቶችን ማሟላት እና ምዘናዎችን ማለፍ ቢጠበቅበትም፤ ተማሪው በትምህርቱ ለማደግ በሚማረው መስክ በቂ ዕውቀትና መረዳትን ማካበቱ ብቻ በቂ አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ ተማሪው የትምህርቱን ይዘት እና ምልዓት (Content) ማወቁ/ መረዳቱ ብቻ ከአንድ የትምህርት ደረጃ ወደሚቀጥለው አያሸጋግረውም።

ምክንያቱም፣ የተማሪው አቅም በነዚህ አካዳሚያዊ በሆኑ መስፈርቶች ብቻ አይገመገምም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ለምሳሌ የተማሪው ምግባር እና ባሕሪ በመምህሩ በየጊዜው ይገመገማል። ከአካዳሚያዊ አቅም ባሻገር ምግባርን፣ ባሕሪን፣ አርአያነትን፤ እና አጠቃላይ ለማኅበረሰብ ያለን አስተዋጽኦ/ አበርክቶ ጭምር ነባሩ የትምህርት ሥርዓታችን ይገመግማል፤ ለዛም ዕውቂያ ይሰጣል። ስለዚህ፣ እንደ ነባሩ የት/ት ሥርዓታችን እሳቤ የተማረ ሰው ማለት በዙሪያው ላሉት ሁሉ ምሳሌ አርአያ የሚሆን ጥሩ ሰው እና በተማረው መስክ በቂ ልቀት ያለው ነው ለማለት ይቻላል።

ለማጠቃለል፣ በነባሩ የት/ት ሥርዓታችን ዕውቀት እና በጎ ምግባር ተሳክተው ተጣምረው ስንኝ በሆነ አካሄድ ተከናውነው ስለተገኙ ይህም የትምህርቱ መሪ አኃዝ በመሆኑ ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ እንዳለው “የተሟላ መንፈስ ያለው ሰውነት ለማግኘት ተችሏል። ተማሪውም ለጥቂት ወይም ለቅርብ ተድላ ደስታ ከማሰብ አልፎ በተለይ የማርካት ኃይል ያለው ንጹሕ የመንፈስ ደስታ መኖሩን ይረዳል። እንዲህ ያለውን ንጹሕ ደስታን የቀመሰ ሰው ለሕይወት ዋጋዎች ሁሉ በትጋት ያስባል። ለእውነት ይከራከራል። ለነፃነት ይታገላል። ለትክክል ፍርድ ይታገላል። ለውበት ይደንግጣል ፤ ያደንቃል። ይህ ከማናቸውም ጥቅማዊ ነገር የበለጠ ደስታ፣ በቁዔት ያስገኝለታል።”

በመሆኑም ደግ ፍላጎትን ከዕውቀት ጋር በማሰናሰል በትምህርቱ ብቻ ሳይሆን በባሕሪውም የታረቀ፣ አዕምሮውን ብቻ ሳይሆን ልቦናውንም ያሰለጠነ ምሉዕ ሰውን በማፍራቱ ረገድ ነባሩ የትምህርት ሥርዓታችን የተሳካለት ነውና፤ ከዚህ በብዙ ልንማርበት የሚገባ እና ዘመናዊ የትምህርት ሥነ-ዘዴያችንንም ልናሻሽልበት የሚያስችለንን ትልቅ እና ጠቃሚ ተሞክሮን የሚያቀብል ነው ቢባል ስህተት እንደማይሆንብን አምናለሁ።

ስለ አስተማሪና ተማሪ ግንኙነት፡-

የትምህርት ሥራ ከእውነተኛው ዓላማ የሚደርሰው በእውነተኛዎቹ አስተማሪዎች ድካም እና ትጋት ነው። ይህ ካልሆነ ትምህርትም አይከናወን፣ ኑሮም አይሰምር፣ ሕዝብም ወደፊት ለመራመድ /ለመሻሻል አይችልም። ለመሆኑ ምን ዓይነት የትምህርት፣ የልምድና፣ የሞራል እርካብ ያለው ነው ትክክለኛ አስተማሪ? በአስተማሪነት ለመሰየም ምን መሥፈርት መሟላት አለበት? የአስተማሪና የተማሪ ግንኙነትስ ምን መሆን ይገባዋል?

ከሁሉ በፊት፣ የአስተማሪና የተማሪ ግንኙነት ምን መሆን አለበት ለሚለው ጥያቄ ግሪኮች በብዙ የሥልጣኔ ተግባር ቀዳሚነት ያላቸው በመሆናቸው ሃሳብ ፍለጋ በቅድሚያ ወደዛው ሰፈር እናቅና። እነዚህ የቀድሞ ዘመን የግሪክ ልሂቃን ስለ ነገሩ በጥልቅ በማሰብ፣ በመመራመር እና በመከራከር የደረሱበትን ጥበብ እና ዕውቀት እንደሚነግሩን አስተማሪነት ሦስት መልክ ያለው መስሎ ይታያል።

እነርሱም፤ አንደኛ፦ ለተማሪዎቹ ከፍ ያለ አብነት፣ አርአያ የሚሆን ነው፣ ሁለተኛ፦ መሪ ኮከብ አልያም አቅጣጫን የሚመራ ምሥራቃዊ ኮከብ የሚሆን ነው [ወደ ዕውቀት፣ ወደ ተገቢ ስሜት፣ ወደ ደግነት፣ ወደ እውነት፣ ወደ ርትዕ፣ ወደ ፍትሕ ወዘተ. የሚመራ የሚጠቁም የሚያደርስ ነው] ፣ ሦስተኛ፦ ሞግዚት፣ አሳዳጊ /ምትከ-ወላጅ የሚሆን ማለት ነው፣ በላቲን አፍ “in loco parentis” ይሉታል።

በመጀመሪያው መልክ የሚገለጠው ሃሳብ እንዲህ የሚል ነው። አስተማሪ ማለት ዘወትር ራሱን ለማስተማር ለማሻል የሚተጋ፣ ራሱን ለማሻሻል እየተጋም ተማሪዎቹን የዚሁ ጠባይ ተካፋይ እንዲሆኑ የሚጣጣር ነው። በድርጊቱ በተግባሩ አብነት የሚሆን፣ በምግባሩ አርአያ የሚሆን፣ ተማሪዎቹንም በመሰል ተግባር እንዲሠማሩ የሚያበረታታ ነው ለማለት ይቻላል። ተማሪዎቹም እሱን በመምሰል ከእርሱ በመነጻጸር ከእርሱም ለመላቅ በመጣጣር ይታነጻሉ ይበለጽጋሉ የማለትን ያህል ሃሳብ ይገልጻል።

ሌላኛው በጥንታውያኑ የግሪክ ጸሐፍት የተመ ላከተው ጠባይ እንደሚነግረን ደግሞ መምህር፣ አስተማሪ ማለት ረቂቅ ሕሊናን በዕውቀት፣ ንጹሕ ልቦናን በሠናይት የሚያሳድግ የሚያጎለብት፤ ትክክለኛውን የሰው መንፈስ የሚያንጽ የሚያበጅ መሐንዲስ ነው ለማለት ይቻላል። ከዚህ አኳያ፣ መምህር፣ አስተማሪ አእምሮን ኮትኳችና ተንከባካቢ ብቻም ሳይሆን በሠናይ በተገቢ ስሜትም የሚያሳድግ ነው። ሰው የተባለውን ሕያው ሕንፃ የሚያበጅ፣ የሰውን ልጅ ከምሉዕነት ማዕረግ እንዲደርስ የሚረዳ፣ ተግቶ የሚያተጋ ነው ለማለት ይቻላል።

ወደ ሦስተኛው መልክ ስናልፍ፥ አስተማሪ ማለት ሞግዚት ወይንም ምትከ-ወላጅ የሚሆን ማለት ነው። ይህም ማለት፥ አስተማሪው ከአስተማሪነት ባሻገር ለተማሪው እንደ አማካሪም፣ ሞግዚትም፣ ምትከ-ወላጅም ሆኖ ስለሚያገለግል፣ በአስተማሪው እና በተማሪው መካከል የቅርብ የአንድ ለአንድ ግንኙነት እንዲፈጠር ያስችላል። ይህም በአስተማሪው እና በተማሪው መካከል የሚፈጠር የቅርብ የአንድ ለአንድ ግንኙነት በጥልቅ መከባበር፣ መተሳሰብና ፍቅር ላይ የሚመሠረት ነው ለማለት ይቻላል።

ስለዚህ፣ አስተማሪው እና ተማሪው ጥልቅ በሆነ የፍቅርና የወዳጅነት መንፈስ ይተሳሰራሉ የሚል ሃሳብን ይገልጣል። ስለዚህ፣ የአስተማሪ-ተማሪ ግንኙነቱ አንዳንዴ የአማካሪነት፣ አንዳንዴ የጠባቂነት፣ አንዳንዴ የአርአያነት፣ አንዳንዴም የሞግዚትነት /የአሳዳጊነት /የምትክ ወላጅነት መልክ ይይዛል። ተቀዳሚ ግቡም የተማሪውን አእምሯዊ፣ ሞራላዊ፣ አካላዊ እድገት እና ማህበራዊ ኃላፊነት በመከታተል እና በመንከባከብ ለምሉዕ ሰውነት ማብቃት ነው። በጥቅሉ፣ የመምህሩ ተልዕኮ ዕውቀትን ማስጨበጥ ብቻ ሳይሆን የተማሪውን ሁለንተናዊ እድገት በመከታተል ለማህበረሰቡ ረብ ያለው አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ምሉዕ ሰውን መፍጠር ነው።

እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን፣ ይህ የቀድሞ ዘመን ግሪኮች የትምህርት ዓላማ መሪ አኃዝ እና ስለ አስተማሪና ተማሪ ግንኙነት የቀረበ አስተያየት ከጥንት ጀምሮ በሀገራችን ከነበረው ነባሩ የሥርዓተ ትምህርታችን አስተምህሮ እና ልማድ ጋር የሚመሳሰል ነው። እዚህ ላይ አስረጂ እንዲሆነኝ የዳባዲን ምስክርነት እጠቅሰዋለሁ። ዕውቁ ፈረንሳያዊ ተጓዥና ሀገር ጎብኚ አርኖ ሚሼል ዳባዲ ባዘጋጁት እና በገነት አየለ በ2010 ዓ.ም. “በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ” በሚል ርእስ ተተርጉሞ በቀረበው መጽሐፋቸው ውስጥ ስለአስተማሪና ተማሪ ግንኙነት የሚከተለውን ግምጋሜ አቅርበዋል፡፡

“ተማሪዎቹ ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ጥልቅ በሆነ የፍቅርና የወዳጅነት መንፈስ ይተሳሰራሉ፡፡ ወጣቶቹ ለመምህራኑ የሚያሳዩትን ፍፁም ታዛዥ፣ መንፈሳዊ ፍቅርና እንክብካቤ ለሚያየው ሰው ሁሉ ከልብ ስሜትን ይነካል፡፡ ይህን የመሰለው ፍቅር፣ መተሳሰብና መከባበር በእኛ ሠለጠንን በምንለው ሕዝቦች መካከል እየጠፋ መሄዱ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡”

ሀገር በቀሉ የት/ት ሥርዓታችን የተዋቀረባቸው ሌሎች ሦስት መሪ አኃዞች

ይህኛው ንዑስ ርዕስ የሦስት ነባር የት/ት ሥርዓታችን አላባዎችን ቅንብር የያዘ ነው፡፡ እነዚህ አላባዎች የተያያዙ ስለሆነና ውስጣዊ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ አንድ ላይ እንመልከታቸዋልን። እነርሱም፤ አንደኛ፡- ይህ ነባር የት/ት ሥርዓታችን በተግባር ልምምድ መታገዙ፣ ሁለተኛ፡- የተገኘውን ትምህርት ለማኅበረሰባዊ ጥቅም ማዋሉ፣ ሦስተኛ፡- ትምህርቱ ከነባሩ የማኅበረሰብ እሴቶች ጋር መጣጣሙ አልያም እንግዳ ወይም ባዕድ እሴቶችን አለማስተዋወቁ የሚሉ ናቸው፡፡

የተግባር ልምምድ ፡-

እዚህ ላይ ይህ ነባር የትምህርት ሥርዓታችን በተግባር ልምምድ የታገዘ መሆኑን ማስታወሱ ጠቃሚ ይሆናል። ይህም ማለት፥ በእነዚህ ት/ት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች በት/ት ቤት ያገኙትን ትምህርት በተለይ የግብረ ገብ ትምህርትን በተግባር በሚተርጎም ልምምድ ያጎለብቱታል። ለምሳሌ አስተማሪዎቻቸውን እና አረጋውያንን በእንጨት ለቀማ፣ በውሃ መቅዳት፣ ቤት ማጽዳት እና በሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎች በመርዳትና እና በማገልገል ታዛዥነትን እና ታላላቆችን ማክበር የተሰኙ የሞራል እሴቶችን ያዳብራሉ ያጎለብታሉም። ይህ በተግባር የተፈተነ የማስተማር ሥነ ዘዴ እንግዳ የመቀበልንም ተግባር ይጨምራል። ይኸውም፣ አዲስ ተማሪ ወይም ጎብኚ ወደ ትምህርት ተቋሙ በሚመጣበት ወቅት ተማሪዎቹ ለእንግዳው ምግብ የማቅረብ፣ እግሩን የማጠብ፣ እና መኝታውን የማሰናዳት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ።

ትምህርት ለማኅበረሰብ ጥቅም፡-

በእነዚህ ት/ት ቤቶች ተማሪዎቹ የተማሩትን በተግባር ማዋል /በውጤት መተርጎም የሚጀምሩት ምንም ጊዜ ሳያጠፉና በትምህርታቸው ብዙ ሳይገፋ ነው። በዚህ ረገድ፣ በት/ት ቤቶቹ የሚሰጠው ት/ት (ሁሉም እንኳ ባይሆን በአብዛኛው) ማኅበረሰቡ ጋር ወርዶ በተግባር ጥቅም የሚሰጥ ነው ለማለት ይቻላል። ተማሪዎቹ ገና ግዕዙን በቅጡ ማንበብ ሲጀምሩ ጀምሮ (የሚያነቡትን ሙሉ በሙሉ የሚረዱት እንኳ ባይሆን) በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ክህሎታቸውን በተግባር እንዲያውሉት ይደረጋል። ለምሳሌ፣ ጥሩ የማንበብ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች በቁርባን አልያም በሌላ የቤተክርስቲያኗ አገልግሎቶች ወቅት የቅዱሳት መጻሕፍትን ምዕራፎች በማንበብ ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ ይደረጋል።

ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ዘልቀው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ዲያቆን ለመሆን ብቁ ይሆናሉ። ከዚህም ጊዜ ጀምሮ ተማሪዎቹ ክርስትና፣ ቀብር፣ እና ቁርባንን በመሳሰሉት የቤተክርስቲያኗ አገልግሎቶች ላይ አገልግሎታቸውን ይሰጣሉ። በምላሹም ሌሎች የቤተክርስቲያኗ አገልጋዮች የሚያገኙትን አብዛኛዎቹን ጥቅማ ጥቅሞች ያገኛሉ። ተማሪዎቹ በትምህርቱ በገፉ መጠን ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት ጥቅም /አበርክቶ እየጨመረ ይሄዳል። ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ አስተማሪዎች ሲሆኑ በተመሳሳይ ወቅትም ቤተክርስቲያኗን በልዩ ልዩ ሞያ ያገለግላሉ። የተቀሩት ደግሞ አማካሪ፣ የታሪክ ፀሐፊ፣ ወዘተረፈ እየሆኑ በመንግሥት ይቀጠራሉ።

በተጨማሪም፣ በእነዚህ ነባር የት/ት ሥርዓቶች ውስጥ በሚሰጠው ት/ት እና በማኅበረሰቡ ፍላጎት መካከል አለመጣጠም ብዙ ጊዜ አይስተዋልም። በሌላ አነጋገር፣ ት/ቱ ከማኅበረሰቡ ፍላጎት የተነጠለ አይደለም፤ ይልቁንም፣ ከማኅበረሰቡ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ነው። ከዚህም የተነሳ፣ የተማሪው ክህሎት በየትኛው የትምህርት ደረጃ ቢሆን አልያም የት/ት ዓይነት የሚፈለግ ነው። ይህም ማለት፥ ተማሪው በየትኛውም የትምህርት ደረጃ አልያም የትምህርት ዓይነት ውስጥ ቢገኝ የተማረውን ትምህርት ማሕበረሰብን ለመጥቀም በአግባቡ ማዋል ይችላል። ስለዚህ፣ ሁሌም የተማረ ሰው ፍላጎት አለ።

የተማረ ሰው ለአስተማሪነት፣ ለፀሐፊነት፣ ለአማካሪነት ወዘተረፈ ይፈለጋል። በአንጻሩ፣ አሁን በዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚስተዋለው ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ አካሔድ ነው። ማለትም፣ ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሰጡት ትምህርት የሚበልጠው ከሀገራዊ ፍላጎት ጋርም ካለው የሥራ ፍላጎት ጋር የማይጣጣም ነው። በዚህም ሳቢያ፣ ተማሪው ትምህርቱን ተከታተሎ ሲያጠናቅቅ ወይ ሥራ አያገኝም ቢያገኝም የሚሠራው ከተማረው ጋር የማይገናኝ ይሆናል። ከዚህም አንጻር፣ ይህ የነባሩ የትምህርት ሥርዓታችን ጠቃሚ ልምድ በብዙ ልንማርበት የሚገባ እና ዘመናዊ የትምህርት ሥነ-ዘዴያችንንም ልናሻሽልበት የሚያስችለንን ትልቅ እና ጠቃሚ ተሞክሮን የሚያቀብል ነው የሚል እምነት አለኝ።

በነባር እሴቶችና በተማረው መካከል ተቃርኖ አለመስተዋሉ፡-

ነባሩ የትምህርት ሥርዓታችን ከማሕበረሰቡ ነባር እሴት፣ ባሕልና ልምድ የሚያፈነግጥ አዲስ፣ ባዕድ፣ እንግዳ ሃሳብ አልያም ጣዕም ወይንም ጠባይ ስለማያስተዋውቅ /ስለማያጎለብት፣ ከማኅበረሰቡ ጋር በቀላሉ መቀላቀል መዋሐድ እና መጣጣም የሚችሉ ተመራቂዎችን ማፍራት ችሏል። በዚህም ሳቢያ፣ በማኅበረሰቡ ነባር እሴቶች እና በተማረው መካከል ተቃርኖዎች እምብዛም አይስተዋሉም ለማለት ይቻላል። ስለዚህ፣ ነባሩ የት/ት ሥርዓታችን የማኅበረሰቡን ነባር እሴት የሚያንፀባርቅ ነው ለማለት ይቻላል።

ይሁን እንጂ የዘመናዊ ትምህርት በሀገራችን ከተዋወቀ ጊዜ ወዲህ ባዕድ እና እንግዳ ሃሳቦችን በማስተዋወቁ ምክንያት ብሎም ከነባሩ የተለየ ባሕል በማንፀባረቁ እና በማብቀሉ፤ በማኅበረሰቡ ነባር እሴት፣ ባሕልና ልማድ እና በተማረው መካከል ግጭት እና ተቃርኖ እንዲፈጠር ሆኗል። በዚህም ሳቢያ፣ የተማረውም ከማኅበረሰቡ ጋር በቀላሉ መቀላቀል መዋሐድ እና መጣጣም የማይችል እንዲሆን ሆኗል። ከዚህም የተነሳ የተማረው ከማንነቱ የተጣላ፣ ከሥሩ የተነቀለ፣ የተከፈለ ነፍስ ባለቤት እንዲሆን ሆኗል።

ከዚህም የግጭት እና የተቃርኖ ምዕራፍ በዘላቂነት ለመውጣት የምንችለው እነዚህንና መሰል ጠቃሚ የት/ት ዘዴዎችን እና ተሞክሮዎችን ለዘመናዊ የትምህርት አውዶች እንዲሆኑ አድርገን አሻሽለንና አዘምነን ወደ ሥርዓተ ትምህርታችን በውጤታማነት ለማሻገር ከቻልን እና በውጤቱም የትምህርት መዋቅሩን ለማስተካከል ከቻልን ብቻ ነው።

ለማጠቃለል፣ ነባሩ የትምህርት ሥርዓታችን ለዘመናችን የትምህርት ሥራ ስንቅ የሚሆን ብዙ ጠቃሚ ልምዶችን፤ የዳበሩና በጊዜ የተፈተኑ የትምህርት መሳሪያዎችን፣ የትምህርት ምልዓቶችን፣ የማስተማሪያ ሥነ ዘዴዎችን፣ ጥልቅ የትምህርት ፍልስፍናዎችን፣ ትምህርትን የማዋቀሪያ ብልሀቶችን፣ …ወዘተ. ይዟልና ቢፈተሽ፣ ቢጠና ቢመረመር ለተቋሞቻችንም፣ ለሀገርም፣ ለመላው ማኅበረሰባችንም በእጅጉ ይበጃል የሚል ነው።

በተጨማሪም፣ የራሳችንን ነባር ዕውቀቶች፣ የተደላደሉ ሥርዓቶች፣ ጠቃሚ ተሞክሮዎች፣ መኗኗሪያችን የነበሩ የማኅበራዊ ትዳር ሕግጋቶቻችንን ሁሉ በማቃለል በንቀት እና በትዕቢት በመመልከት በጥራዝ ንባባችን እና ዕውቀታችን ተወስነን ከምንሽራቸው፤ ይልቁንም፤ ብንፈትሻቸው፣ ብናጠናቸው እና ብንመረምራቸው በብዙ ልንማርባቸው የሚገባ ብሎም ወደ ፊት ለመራመድ የሚያስችለንን፤ ለወደፊቱም ጉዞአችን ስንቅ የሚሆኑንን ትላልቅ እና ጠቃሚ ተሞክሮዎችን የሚያቀብሉ ናቸው የሚል እምነት አለኝ።

ሕዝቂያስ ታደሰ (የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ መምህር)

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You