የሴቶችን ቀን ትርጉም ባለው መንገድ ለማክበር

ወይዘሮ ሻሼ ድሪባ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ዳቦና ኬክ ከመቁረስና ከፈንጠዝያ ያለፈ ፋይዳ አለው ብላ አታምንም ነበር:: አደባባይ ወጥቶ ቀኑን ማክበሩም ቢሆን አስፈላጊ አይደለም የሚል እምነት ነበራት:: ከዚህ የተነሳም በየትኛውም መድረክ ብትጋበዝ ለመገኘት ፈቃደኛ አልነበረችም::

“ከዚህ ቀደም ከቤት ወጥቼ አላውቅም:: ሌላው ቀርቶ የወር አስቤዛዬን ባለቤቴ ሸምቶ ስለሚያመጣልኝ አካባቢዬንና የገበያ ስፍራ እንኳን አላውቅም ነበር” ትላለች ፤ ረጅም ጊዜዋን ያሳለፈችው በቤት እመቤትነት ነው:: ባለቤቷ በቤቷ ውስጥ ማንኛውም ክፍተት ሲኖር በነገረችው ጊዜ የሚያሟላ ቢሆንም ፤ ይሄን አድርጊ ብሎ በእጇ የሚሰጣት ምንም ዓይነት ገንዘብ ግን አልነበረም::

የእሷ ሥራ ከ3 እስከ 6 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ልጆቻቸውን ሲንከባከቡና የቤት ውስጥ ሥራ ሲያከናውኑ መዋል ነበር:: በሥራው ጫና የተነሳ ማልዳ ብትነሳም ሌሊቱ ሲጋመስ ነበር ወደ መኝታዋ የምትሄደው:: ባለቤቷም ሆነ እራሷ ለዚህ ሥራዋ እውቅና ሰጥተውት አያውቁም:: ከዚህ ቀደም በግሏ “ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ሠርቼ ገቢ ማግኘትና ያለሁበትን አሰልቺ ሕይወት ማሻሻል እችላለሁ” የሚል ግምትም፤ እምነትም አልነበራትም::

የዛሬ ዓመት እንደሷ አባባል “ወጣ ወጣ በምትልና አስገድዳ በቀረበቻት ጎረቤቷ ግፊት ተጋብዛ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ለበዓሉ በተዘጋጀ መድረክ ተገኘች” ይህም ከቤት መውጫ ሆናትና ስለ በዓሉ ግንዛቤ ጨበጠች::

“አካባቢዬን ያወኩትና ሥራ ያገኘሁት በበዓሉ ሴት ጓደኞች ካፈራሁ በኋላ ነው:: አሁን ከነሱ ጋር በማህበር ተደራጅቼ በዶሮ እርባታ ተሰማርቻለሁ:: የራሴ የሆነ ገቢም ማግኘት ችያለሁ:: በማገኘው ገቢ የቤት ሠራተኛ ስለቀጠርኩም በቤት ውስጥ ያለው የሥራ ጫና ቀንሶልኛል:: በጊዜም እየተኛሁ ነው:: አሁን ላይ እኔና ጓደኞቼ የብድር አገልግሎት ከተመቻቸልን ከዶሮ እርባታው ሳንወጣ ሥራውን አስፍተን ለመሥራት ዝግጁነት እንዳላቸው ትናገራለች።

የሴቶች በዓል በየዓመቱ መከበሩ በራሱ እንደ አንድ እርስ በርስ የሚያገናኝ መድረክ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑ መገንዘብ ስለመቻሏም፤ በዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንም ተደራጅታ አብራቸው ከምትሠራቸው ሴቶች ጋር በዓሉን በባለቤትነት መንፈስ ሌሎች ከቤት ያልወጡ ሴቶችን የሚያሳትፍ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ታነሳለች::

“ሴቷ እቤቷ ተቀምጣ በተደራጀ መልኩ አደባባይ በመውጣት መብቷን ማስከብር አትችልም” የምትለው ደግሞ በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መስጠት መሪ ሥራ አስፈፃሚ የሴቶች መብት ሥርጸት ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሪት ማህሌት አማረ ነች::

ማህሌት እንደምትለው፤ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን እውቅና ተሰጥቶት መከበር ከጀመረ ከብዙ አሥርት ዓመታት በኋላ በዓሉ ከኬክ ቆረሳ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የሚሰማቸው ወገኖች አሉ::

ይሄ ትክክለኛ አስተሳሰብ አይደለም:: በዓሉ በብዙ መልኩ ሴቶች በተደራጀ አግባብ አደባባይ ወጥተው መብቶቻቸውን ለማስከበር ትልቅ ግንዛቤ የሚያገኙበት ነው:: ተደራጅቶ መብትን ማስከበር አስፈላጊ እንደሆነም የተሻለ ግንዛቤ ፈጥረውበታል::

በዓሉ መከበሩ በርካታ ሴቶች የራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው በር መክፈቱንም ትናገራለች:: አደባባይ መውጣቱ በሴቶች ላይ የነበረውን የአትችልም አስተሳሰብ ስለመስበሩም ታነሳለች:: ይህን አስተሳሰብ መቀየር በመቻሉም በኢትዮጵያ በተለይ ቤት ውስጥ ተደብቀው የቆዩ ሴቶች ከባሎቻቸው ጥገኝነት የሚላቀቁበት ሁኔታ እንዲፈጠር እያስቻለ ነው::

ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉና ለሀገራቸውም ኢኮኖሚ መጎልበት በተለያየ መልኩ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አስችሏል:: ቢሮም የነበሩት በተለየዩ የኃላፊነት ደረጃዎች እየታዩ መጥተዋል። የማይደፈሩ የሥልጣን እርከኖችም በሴቶች እየተያዙ ነው። አትችልም የሚለውን አስተሳሰብ በዓሉን ለማክበር በሚደረግ ውይይት፣ በተደረጉ የተለያዩ የተሞክሮ ልውውጦችና በተሠሩ የአደረጃጀት ለውጦች መስበር ተችሏል ትላለች።

አሁን ላይ መንግሥታዊ የሆኑና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በየዓመቱ ለሴቶች የእውቅና መድረክ እያዘጋጁ መሆናቸውን ትጠቁማለች። የሚሠሩና አርአያ የሚሆኑ ሴቶችም በዓለም የሴቶች ቀን ብቅ እያሉ መምጣታቸውን ትጠቅሳለች። ይህም ሌሎችም ሴቶች እነርሱን እንዲከተሉ እየገፋፋ መሆኑንም ታወሳለች::

ባለፉት በዓላት የዓለም የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣት ሴት ተሞክሮዋን ስታካፍል በቴሌቪዥን ስክሪን መመልከቷን ታስታውሳለች:: ይሄ መድረክ ባይመቻች ኖሮ ይህች ሴት በየትኛው መድረክ ነበር ልትወጣ የምትችለው? ስትልም ትጠይቃለች:: በተጨማሪም በዚሁ በዓል ታሪክ ሠርተው የነበሩ ሴቶች ተሳትፏቸው እንዲዘከር የሚደረግበት አጋጣሚ ብዙ መሆኑን ትጠቁማለች።

እንደ ማህሌት ከሆነ፤ እንደዚህም ሆኖ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ስለማይቻል የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወንዶችን በጉዳዩ ማሳተፍ ያስፈልጋል። ምንም እንኳን የሴቶች በዓል ሴቶችን በተለየ ሁኔታ የሚያጎላ ቢሆንም ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን ከማረጋገጥ አንፃር የወንድ አጋርነት የግድ ነው። ያለበለዚያ የሴቶች ተጠቃሚነት በቀላሉ ሊሳካ አይችልም። ሴት ብቻዋን ተሰብስባ እኩል ነኝ፤ እኩልነቴን በራሴ አረጋግጣለሁ ብትል ከወንዶች ተሳትፎ ውጭ አይሆንም።

በማህበራዊውና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ብሎም በሥልጠናም ሆነ በሥራ ቦታ ከወንዶች ጋር አብሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ካልተሠራና ወንዶችን የመፍትሔው አካል ማድረግ ካልተቻለ ውጤት ማምጣት አይቻልም። በመሆኑም ለብቻ ተነጥሎ የሚመጣ ለውጥ የለምና በሴቶችም በወንዶችም አስተሳሰብ ላይ እኩል ሥራ መሥራት ይገባል ስትልም ትመክራለች::

ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓሉን በየዓመቱ እንደሚከበር፤ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ “For ALL Women and Girls: Rights. Equality. Empowerment.”፤ በኢትዮጵያም ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሃሳብ በብሔራዊ ደረጃ በሁሉም የሀገሪቱ ከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ትርጉም ባለው መልኩ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ለማክበር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገው በእቅድ ወደ ሥራ መገባቱን አመልክታለች ::

ዝግጅቱ የራሱ የሆነ አቢይ ኮሚቴም ተዋቅሮለት ከየካቲት 1/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱን፤ ኮሚቴው የተለያ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መሆኑን አስታውቃለች። ከመርሀ ግብሮቹ መካከል፤ በከተማ ደረጃ በተለያየ ሥራ ቡድንም ሆነ በተናጠል ሞዴል ሴቶች የሠሩትን ሥራ የመጎብኘት እውቅና መስጠት የመስጠት ሥራ ተከናውኗል:: በተጨማሪም በተለያዩ የቁጠባ አማራጮች ላይ ሴቶች ከ100 ብር ጀምሮ የቁጠባ ደብተር (ቡክ) እንዲከፍቱ በማድረግ የቁጠባ ንቅናቄውን የማስቀጠል ሥራ ተሠርቷል::

ከየካቲት 15 እስከ የካቲት 22/2017 ዓ.ም በመላው ሀገር ያሉ ሴቶች የማህጸን በርና የጡት ካንሰርን በሚመለከት ግንዛቤ እንዲፈጠርላቸው እና ምርመራ እንዲያደርጉ ሲሠራ ቆይቷል:: ከየካቲት 22 እስከ የካቲት 26/2017 ዓ.ም ድረስም የሕዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢ ላይ መላው ሴቶች እንዲሳተፉ ተሠርቷል:: በአጠቃላይ በሁሉም የሀገሪቱ ከተማ አስተዳደሮችና ከልሎች ሴቶችን ተጠቃሚም ተሳታፊም ባደረገ ትርጉም ባለው መልኩ በዓሉን ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል::

በዚህ አብይ ኮሚቴ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራትም ሲከናወኑ ቆይተዋል:: ሴቶች በብድርና ቁጠባ በመደራጀት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ጋር ተያይዞ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንዲቆጥቡና ለ15 ሺህ ሴቶች የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት ሲሠራ የቆየበት አንዱ ማሳያ ነው ትላለች::

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች በፆታ ምክንያት የሚደርስባቸውን መድሎ እና በደል ለመታገል ያደረጉትን ጉልህ አስተዋፅኦ ለመዘከርና ቀጣይ እድሎችን ለመፍጠር በየዓመቱ የሚከበር ታላቅ ዓለም አቀፍ በዓል እንደሆነ የምታነሳው ማህሌት፤ የካቲት 1/2017 ዓ.ም የጀመረው በዓሉ እስከ መጋቢት 30 ድረስ ተጨባጭነት ባላቸው ተግባራት ክንውን እየተከበረ እንደሚዘልቅም ትናገራለች::

“በአንድ ወቅት በካቢኔ ያላቸውን ተሳትፎ ከወንዶች እኩል ለማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት በተሠራው ሥራ ከ20ው የካቢኔ አባላት አሥሩ ሴቶች እንዲሆኑ የሚያስችል ለውጥ መጥቷል” የምትለው ወይዘሪት ማህሌት፤ እስከ መጋቢት 30/2017 ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱም ይሄው ስለመሆኑ ታወሳለች::

ከዚህም በኋላ በተሠሩ ሥራዎች በመስኩ በመሥራት በርካታ ሴቶችን ማብቃትና ማሳተፍ ስለመቻሉ ታወሳለች:: አሁን ላይ በሚንስትርነት ብቻ ሳይሆን በሚንስትር ዴኤታነት እንዲሁም በተለያዩ ውሳኔ መስጠት የሚያስችሉ ከፍተኛ የአመራር ኃላፊነት ቦታዎች ሴቶችን ከፍ በማድረግ ማስቀመጥ መቻሉንና እስከ መጋቢት 30 ባለው ጊዜም ይሄው ሴቶችን በየመስኩ ወደ ላይ በማውጣት በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚከናወኑ አያሌ ተግባራት የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራበት መሆኑንም ጠቁማለች::

ሴቶች በኢኮኖሚ መጎልበትን በተመለከተ በሀገረ መንግሥት ግንባታው ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ የግድ ተሳታፊ መሆን አለባቸው:: በዚሁ ላይ ያላቸው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦም የሚለካው በየደረጃው ለኢኮኖሚው መጎልበት በሚያበረክቱት አስተዋጽኦና በሚያደርጉት ተሳትፎ ነው:: በመሆኑም እስከ መጋቢት 30/2017 በዓሉን አስመልክቶ ከሚከናወኑ አበይት ተግባራት መካከል 45 ሺህ ሴቶች የሚሳተፉበት የ22 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ግዢ ክንውን ታነሳለች::

በተጨማሪም ሴቶች የኢኮኖሚ አቅም እንዲፈጥሩ ለማድረግ ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት እስከ ሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር እንዲቆጥቡ የሚደረግበት አንዱ ስለመሆኑም፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም ለ15ሺህ ሴቶች የተመቻቸው የብድር አገልግሎት ወደ መሬት ወርዶ በተጨባጭ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሠራው ሌላው የሚከናወን ተግባር እንደሆነም ታወሳለች::

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You