
የህብረተሰቡ ግማሽ አካል የሚሆኑት ሴቶች በብዙ የሥነ ልቦና ተጽዕኖ ውስጥ ኖረዋል:: በሚደርስባቸው ቀላል የማይባል የሥነልቦና ጫና ሳቢያም ለተለያዩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ይዳረጋሉ::
የሥነ ልቦና ጫናን መቋቋም የቻሉ ጥቂት ሴቶች አፈትልከው ሲወጡ ቢስተዋልም፣ አብዛኞቹ ግን ተጽዕኖ መቋቋም አቅቷቸው ካሰቡበት መድረስ ተስኗቸው፣ ሕልማቸው ተጨናግፎባቸው ለከፋ ጉዳት ይዳረጋሉ::
ሴቶች ምንም አይነት የሥነ ልቦና እንዳይደርስባቸው ከማድረግ ጎን ለጎን ጫናው የደረሰባቸውን ደግሞ ጫናውን መቋቋም የሚያስችላቸውን ሥነልቦና እንዲገነቡ ማድረግ ይገባል ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ::
ዛሬ የሚከበረውን የዓለም የሴቶች ቀን በተመለከተ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባዘጋጀው ልዩ እትምም ሴቶች የሚደርስባቸውን ሥነ ልቦናዊ ጫና በምን መልኩ ተቋቁመው ስኬታማ መሆን ይችላሉ፤ ምንስ አይነት ሥነልቦና መገንባት አለባቸው የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ያነሳንላቸው የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ወይዘሮ ምህረት አብርሃ እንዳሉት፤ የሴቶች ሥነ ልቦና ከሀገሪቱ አኗኗር ፣ ማህበረሰብ፣ እሴቶች፣ አስተዳደግ እና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው::
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህርትና አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ምህረት፤ ሴቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና ታዳጊ በሚባሉ ሀገሮች ሁሉ ከልጅነታቸው ጀምሮ በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሚኖሩ ይገልጻሉ::
ጫናውም ከቤት ውስጥ እንደሚጀምር ጠቅሰው፣ ማህበረሰቡ ለሴት ልጅ ዝቅ ያለ ግምት ሲሰጥ መኖሩን ይናገራሉ:: ሴት ልጅ ያላትን ስፍራ በሚገባ ባለማወቅ ከልጅነት ጊዜዋ አንስቶ ተጽዕኖ እንደሚደርስባትም ያመላክታሉ::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሥነልቦና ማለት ከጽንሰት ይጀምራል፤ የሰው ልጅ የአኗናር ሁኔታ ሲሆን፣ ልክ እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ሊታይ ይችላል፤ የሰው ልጅን የሚሰማው፣ የሚያየውና የሚያንጸባርቀው ሁሉ ሙሉ ያደርገዋል:: ያደጉት ሀገራት ይህን በሚገባ በመገንዘብ እዚህ ላይ በደንብ ይሠራሉ::
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት እነዚህ ነገሮች አልተለመዱም ሲሉ ጠቅሰው፣ በእነዚህ ሀገሮች ሴት ልጅ ገና በጨቅላ እድሜዋ ኃላፊነት እንደሚሰጣትም ይገልጻሉ:: ትንሹ ኃላፊነት ከስምንትና ከዘጠኝ ዓመት እንደሚጀምር ጠቅሰው፣ ይህም ቡና በማፍላት፣ እቃ በማጠብና በመላላክ እንደሚገለጽ አመልክተዋል::
እሳቸው እንደሚሉት፤ ሴት ልጅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ እያለች ወይም በተለምዶ የጉርምስና እድሜ ላይ ስትደርስ ጥያቄ ማቅረብ ትጀምራለች:: በዚህ እድሜዋ ሙሉ የመሆን ስሜት ስለሚሰማት ሴት ብትሆንም ወንድ እንደሚያስበው እሷም ታስባለች:: ወንድ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች እሷም ታነሳለች::
ሙሉ መሆን የመፈለግ ስሜቱ በተፈጥሮ የተሰጠ ቢሆንም፣ በአኗኗር ዘይቤ የበለጠ ይዳብራል:: ከዚያም እንደ ማንኛውም ወንድ ልጅ ወይም ጓደኞቿ ወደፊት ይህን መሆን እፈልጋለሁ፤ ለእዚህ ምን ማድረግ አለብኝ የሚሉ ጥያቄዎችን ልታነሳ ትችላለች:: ይህን ጊዜ በሴቶች ሕይወት ውስጥ ትልቁ ግጭት ይጀምራል ሲሉ ያመለክታሉ::
በዚህ ውስጥም አልፋ ዩኒቨርሲቲ ልትገባ ወይም ወደ ትዳር መመስረት ሊኖርባት ይችላል:: ችግሩ ወደ ትውልዱ እየተላለፈ እሷም ሴት ልጇን ለመርዳት፣ ባለቤቷንም ለማገዝ ይከብዳታል:: በመሆኑም ብዙ ትዳር ውስጥ ግጭት ይፈጠራል::
ይህም ሴቷ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የሆነ የበታችነት ስሜት አላስፈላጊ ድርጊቶችን ሊያመጣ ይችላል:: በራስ መተማመን ካልገነባችም የሕይወት አጋሯ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ውስጥ ይገባል፤ እሷም የምትታዘዘውን ብቻ የምታደርግ ትሆናለች ሲሉ ይገል ጻሉ ::
በአጠቃላይ ሴቶች ከማህበረሰብ ጀምሮ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚያልፉ የሳይኮሎጂ መምህሯ ጠቅሰው፣ ይህንን ሁሉ ጥሰው የሚወጡ ጀግና ሴቶች እንዳሉ መዘንጋት እንደሌለበትም ይገልጻሉ:: ‹‹እችላለሁ፤ ይሆንልኛል፤ ይሳካልኛል›› ብለው በትምህርታቸውም በሥራ ቦታቸውም የሚታገሉ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች እንዳሉም ጠቁመዋል::
‹‹ሕይወታችንን ወደ ጥሩ መንገድ የሚመሩ አጋጣሚዎች አሉ›› የሚሉት መምህርቷ፤ በዚህ በኩል ወቅቱ ይለያያል እንጂ ሁሉም ሰው የየራሱ ተሞክሮ ይኖረዋል ሲሉም ይገልጻሉ:: አንዳንዶች በልጅነታቸው፣ አንዳንዶች በወጣትነታቸው፣ ሌሎች ደግሞ በእድሜው አጋማሽ ላይ ይህ ተሞክሮ ሊኖራቸው እንደሚችልም ያመለክታሉ::
እንደዚህ አይነት ክስተቶች ወደ ሕይወታችን ሲመጡ ለመጠቀም ቆርጦ መሰወን የግድ ይሆናል ሲሉ ጠቅሰው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፖለቲካ ፣በንግድ፣ በማህበራዊና በመሳሰሉት ዘርፎች ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ሴቶችን የሕይወት ታሪክ መለስ ብለን ብንመለከት አንድ ወቅት ላይ ያሳለፉት ውሳኔ አሁን ለደረሱበት ከፍታ አስተዋጽኦ ማድረጉን መረዳት እንችላለን ብለዋል::
እነዚህ ሴቶች በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ሥነ ልቦናዊ ጫናዎች ውጪ ሆነው ይኖራሉ ማለት ግን አስቸጋሪ ነው ሲሉም ይገልጻሉ:: አንዳንድ ጊዜ ቤተሰብ በጣም የተማረ ሆኖ የልጆች አስተዳደጉም መልካም ሆኖም በሴት ልጆች ላይ ውጫዊ ተጽእኖዎች ሊደርሱ እንደሚችሉም አመላክተዋል:: ልጆች የሚያድጉት በትምህርት ቤት፣ ጓደኛ፣ ጎረቤትና የእምነት ተቋምትና የመሳሰሉት ውስጥም መሆኑን አስታውቀው፣ የቤተሰብ መልካም መሆን ብቻውን ልጆችን ሊቀርጽ አይችልም ሲሉም ያብራራሉ::
መምህርቷ እንዳስታወቁት፤ ጠንካራ ሴቶች የሆነ ጊዜ ቆም ብለው ሲያስቡና ወደፊታቸውን ሲያዩ አንድ ወቅት ላይ ያሳለፉት አንድ በጣም ትልቅ ውሳኔ ይታሰባቸዋል:: ያ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት፣ በትዳር ውስጥ በራስ መተማመን ኖሯቸው፣ ማህበረሰቡ እንደሚለው ሳይሆን ለእኛ መኖር እንዳለብን ብለው ያሳለፉት ውሳኔ ያሻገራቸው መሆኑን ይረዳሉ:: ‹‹በሕይወታችን አንድ ቀን ያሳለፍነው ውሳኔ የሚያሻግረንም፣ የሚጥለንም ሊሆን ይችላል ›› ሲሉም አስገንዝበዋል::
የሴቶችን ሥነ ልቦና በማነጽ ረገድ በቤተሰብ የሚደረግላቸው ከፍተኛ ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቅሰው፣ ወላጆች ለሴት ልጆቻቸው ከፍተኛውን ድጋፍ በማድረግ መጪውን ትውልድ ጭምር መቀየር እንደሚችሉ ያመላክታሉ::
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከፍተኛው የሕይወት እድሜ ወይም ምቹ አጋጣሚ ያለበት የሕይወት እድሜ ሲታይ የወጣትነት እድሜ ይጠቀሳል:: ከ14 እስከ 26 ዓመት ያለው እድሜ ይህ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጠርበት የሚባለው ነው:: ይህም እድሜ ቅድመ፣ መሀልና ረፈድ ተብሎ የሚለይ ሲሆን፣ በተለይ መሀል እድሜ የሚባለው (ከ21 እና 22 ያለው እድሜ) የወጣት ሴቶች ትልቁ የሕይወት ፍሬም የሚቀረጽበት እድሜ ነው ሲሉ ይገልጻሉ::
በሚገርም ሁኔታ በሕይወት ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችም ሆኑ እድሎች የሚመጡበት የእድሜ ክልል ይህ የእድሜ ክልል መሆኑንም በማመልከት፣ በጾታ ግንኙነት፣ በትምህርት ከፍተኛ እድሎች የሚመጣበት መሆኑን ጠቁመዋል፤ ይህ የእድሜ ወቅት ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፤ ማህበረሰቡ፣ ቤተሰብ ካሳደረብን፣ እንዲሁም እኛ ራሳችን ላይ ካሳደርነው የሥነ ልቦና ጫና ለመውጣት መጀመሪያ የቆምንበትን ቦታ ማወቅ ያስፈልገናል ብለዋል::
‹‹በተለይ የአሁኑ ትውልድ ምናባዊ በሆነ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነው:: ምክንያቱም ግሎባላይዜሽን ከፍተኛው ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል›› ሲሉም ተናግረው፣ በዚህ ዘመን አንዲት ሴት እኔ ማነኝ ብሏ በመጠየቅ ቆም ብሏ ማሰብ እንዳለባት ይመክራሉ:: ይህንን ጉዳይ አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩም ‹‹ሴቷ የምትፈልገው ጥሩ የቢዝነስ ሰው መሆን ከሆነ ማንበብ፣ ማወቅ፣ ሰዎችን ማግኘት፣ ሕልሟ ላይ መሥራት የማንም ድርሻ ሳይሆን የራሷ ድርሻ ነው›› ሲሉ አስታውቀዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ወንዱ ትችላለህ ታደርገዋል ተብሎ ስላደገ ከልጅነቱ ጀምሮ ከራሱ ጋር ያንን አስማምቶ ይኖራል:: 20ዎቹ እድሜ ልክ እንደ ሴቷ ራሱን ለማወቅ ሳይሆን ጥረት የሚያደርገው በተግባር ራሱን ለመግለጽ ነው:: እሱ ጥሩ የቢዝነስ ሰው መሆን ከፈለገ በ20ዎቹ እድሜ መጀመሪያዎቹ መስመር ውስጥ ገብቶ ሊገኝ ይችላል::
‹‹ዩኒቨርሲቲ ስናስተምር የምናገኛቸው ተማሪዎች አንዳንዶቹ ስታርትአፕ ቢዝነስ አላቸው:: ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ ያህል ወንዶች ናቸው:: በጣም ጎበዝ ሴት ተማሪዎች እያሉም ነው:: በተጨባጭ ያጋጠመኝን ልጥቀስ፤ አንድን ተማሪ ከተመረቅሽ በኋላ ምንድነው የምትሰሪው ብዬ ጠየኳት፤ ‹እኔ እንጃ ሥራ እፈልጋለሁ› የሚል ምላሽ ሰጠችኝ›› ብለዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሴት ልጅ መሰማራት ስለምትፈልገበት የሥራ ዘርፍ ማንንም ሰው ሳትጠብቅ ራሷ ላይ መሥራት ይኖርባታል:: ይህ ሲሆን በራስ መተማመን ታዳብራለች:: ለራስ ዋጋ መስጠት ለሴት ልጅ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ለመረዳት ቆም ብላ ማሰብ አለባት::
‹‹አንዲት ሴት ቀድማ ዋጋዋን በደንብ መለየት አለባት፤ ለራሷ ጥሩ ዋጋ ካልሰጠች፣ የሆነ ወቅት ላይ ራሷን ልትጥል ትችላለች:: ስለዚህ ምን ያህል ነው ዋጋዬ፤ ምን ያህል ውድ ነኝ፤ የቱ ጋ ነው የማስፈልገው፤ መቼ ነው የምፈለገው የሚሉትን ማሰብ አለባት›› ሲሉ አብራርተዋል::
የሳይኮሎጂ መምህርቷ እንዳለችው፤ ከምንም በላይ ቤተሰብ ስትመሰርት ፣ እናት ስትሆን፣ የምታሳድጋቸው ልጆች በራሳቸው መተማመን ያላቸው፣ ለሀገር የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ለማድረግ በማሰብ ቀድማ ራሷ ላይ መስራት ይኖርባታል፤ ለእዚህም ማንበብ ብዙ ማወቅና ሰዎች ማማከር የሚመጡ እድሎችን አጥንቶና አጥርቶ መጠቀም ያስፈልጋታል::
‹‹ብዙ ጊዜ ሴቶች ከሚያጋጥሙን ተግዳሮቶችም ሆነ ሰዎች ከሚነግሩን ለራሳችን ደጋግመን የነገርነው ጨለምተኛ የሆነ አስተሳሰብ አስሮ ያስቀምጠናል›› የሚሉት መምህርቷ፤ በተለያየ አጋጣሚ የማገኛቸው ብዙ ሴት እህቶቼ የይቻላልን መንፈስ ከውስጣቸው አውጥተው በሆነ ሰው ላይ ተደግፈው የሚገኙ ናቸው ብለዋል:: ይህ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ በራስ የመተማመን ችግር እና ጨለምተኝነት አስተሳሰብ እንደሚከተል ጠቁመው፣ ይህን ጊዜ ሴቷ የሚያንገዳግድ ችግር ሲያጋጥማት ተሰብራ ትወድቃለች ሲሉ ተናግረዋል ::
እንደ መምህርቷ ማብራሪያ፤ እዚህ ላይ ማይንድሴት በጣም ያስፈልጋል:: ማይንድሴት ማለት ለራሳችን ያለንና ለሌሎች ያለን የእውነተኛው ዓለም እይታ ነው:: ማይንድሴት ያላት ሴት አንድ ወቅት ላይ የጾታ ጥቃት ሊያጋጥማት ወይም በቤተሰብ ውስጥ ትደብድባ ወይም ተደፍራም ሊሆን ይችላል:: ‹‹የሆነው አንዴ ሆኗል ፤ሕይወት ግን ይቀጥላል፤ አይቆምም›› ሲሉም አስገንዝበው፣ በሕይወት እስካለን ድረስ እያንዳንዱ ቀን ራሱን የቻለ ዋጋ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል ይላሉ:: መሽቶ ሲነጋ በሕይወታችን ውስጥ አዲስ ቀን ይመጣል:: ይህን ቀን እንዴት እናስተናግደው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል:: ጨለምተኛነት፣ ተስፋ መቁረጥ በሞላበት ዓለም ውስጥ ሕይወት እኛ ስለመረጥነው አያቆምም፤ ይቀጥላል:: በመሆኑም መጪው ሕይወት እንዴት ይቀጥል የሚለው በጣም ትልቅ ውሳኔ ይፈልጋል ይላሉ::
ወጣት ሴት ነገሮች ከአቅሟና ከቁጥጥሯ ውጪ ሲሆኑ ርዳታ ማግኘት የምትችልበት ቦታ ካለ ወደዚያ ብትወሰድ የመጀመሪያው መልካም ነገር መሆኑን፣ የሚያማክራት ባለሙያም ብታገኝ ነገሮች በትንሹም ቢሆን ሊቀሉላት እንደሚችሉም ያመለክታሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ሴቶች ራሳቸው በቤት ውስጥና በማህበረሱቡ የሚደርሱባቸውን ችግሮች ለመፍታት ምን ልናደርግ ይገባል የሚለው ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል፤ በቅድሚያ ራሳቸውን ለማዳመጥ ጊዜ መስጠት ይኖርባቸዋል:: በቀን ለአንድ ሰዓት ያህልም ቢሆን ሃሳባቸውን መልሰው መገንባት ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል፤ ራሳቸውን ከራሳቸው በማውራት ለችግሮች መፍትሔ ማስቀመጥ አለባቸው:: በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ደግሞ ርዳታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል:: ለራሳቸው የሚያነሱት ጥያቄ መልሶ መፍትሔ ሊያመጣላቸው ይችላል::
አንዲት ሴት ስላጋጠማት ችግር ለአስር ሰዎች ታወራ ይሆናል፤ አስሩ አስር አይነት መፍትሔ ሊሰጧት ይችላሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ሊጠቅሟት የሚችሉት ሁለቱ ብቻ ሊሆኑም ይችላሉ:: የተቀሩት ችግሮቿን የሚያወሳስቡ ሊሆኑ ይችላሉ:: እንዲህ አይነቷ ሴት ከራሷ ጋር አውርታ ችግሮቹን ለይታ መፍትሔ ካላስቀመጠች ችግሮች ይበልጥ ሊወሳሰቡባት እንደሚችሉም ያስረዳሉ::
ራሷን ማውራትና ለራስ መፍትሔ መስጠት መሞከር እና የባለሙያ ድጋፍ ማግኘት ከምንም በላይ እንደሚመከር ይገልጻሉ:: የበለጠ ማይንድሴት ያላት ወጣት፣ እናት፣ ሠራተኛ፣ የሥራ ቦታ መሪም የመፍትሔ ሰው ትሆናለች ሲሉም አመልክተው፣ ይህን ሁሉ በማድረግ ሴቶችን ከሥነልቦና ጫናዎች ማውጣት እንደሚቻል ይገልጻሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ሕይወት እንደተመልካቹ ነው፤ አክብዶ ላየው ይከብዳል፤ ላቀለለውም ይቀላል፤ በርካታ ሴቶች ሕይወትን በማክበድ ይጎዳሉ፤ የሚያስፈልገውን አውቆ በሚያስፈልገው ላይ መልስ የሚሰጥ ከሆነ ምንም አይነት የሕይወት አጣብቂኝና ጡዘት ውስጥ ሳይገባ ስኬታማ መሆን ይቻላል::
‹‹አንዳንዴ በራስ የመተማመን ዝቅ ማለትም ሊያጋጥም ይችላል:: በዚህ ጊዜ የምናየውን ሁሉ መሆን እንፈልጋለን፤ ዝቅ ያልን ይመስለናል:: የራሳችንን ዋጋ ባለማወቅ ሌሎች ጋ ያለውን በማድነቅ ቀድመን ተስፋ እንቆርጣለን፤ ይህ ደግሞ በጣም ይጎዳል›› ሲሉም ያስገነዝባሉ:: ሴቶች የራሳቸውን ዋጋ በደንብ ለይተው እንዲያውቁ መክረው፣ በእነሱ መኖር ማህበረሰቡ፣ ቤታቸው፣ አካባቢያቸው፣ ጎረቤቶቻቸው እና ዘመዶቻቸው ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሆኑ አስቀድመው በማወቅ የራሳቸውን ዋጋ እንዲያውቁም አሳስበዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም