እንችላለን!

ሴቶች ቀደም ባሉት ዘመናት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከወንድ አቻዎቻቸው እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊ አልነበሩም። ሴት ልጅ የሚሰፈርላት፣ ተለክቶ የሚሰጣት ፣ መብቷንም ሆነ ፍላጎቷን መጠየቅ የማትችል ፣ የቤት ውስጥ አገልጋይ ሆና ትቆጠር እንደነበር በታሪክ የምናውቀው ሀቅ ነው። ስለዚህ ሴቶች በማንኛውም ጉዳይ ከወንዶች እኩል ተሰላፊ፣ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ አልነበሩም ሲባል በምክንያት ነው።

የመማር እድል አልነበራቸውም፤ በእውቀታቸውና በችሎታቸው የመሥራት መብትም አልተከበረላቸውም። ሌላው ቀርቶ በራሳቸው ጉዳይ ላይ የሚወስኑት ራሳቸው አልነበሩም። የኢኮኖሚ ጥገኛ መሆናቸው ደግሞ በማንኛውም ጉዳይ ውሳኔ መስጠትም ሆነ ስለመብታቸው ለመከራከር የሚያስችላቸው ሁኔታ አልፈጠረላቸውም።

ይሄ የሴቶች ጭቆና በእኛ ሀገር ብቻ አልነበረም ፤ ዓለም የወንዶች ብቻ ተደርጋ የምትቆጠርበት እስክትመስል ድረስ ማንኛውም እንቅስቃሴና ውሳኔ የወንዶች ብቻ ነበር። ይህ የሴቶች ጭቆና በዓለም አቀፍ ደረጃም ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ሴቶች መብቶቻቸውን ለማስከበር አደባባይ ወጡ ፤ ድምጻቸውን ማሰማት ቀጠሉ ።

የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታሪካዊ መነሻም የሠራተኞች እንቅስቃሴ ነው። በወቅቱ 15 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች በኒውዮርክ ከተማ ላይ የሥራ ሰዓት መሻሻል (ማጠር)፣ የተሻለ ክፍያና ሴቶች በምርጫ መሳተፍ አለባቸው በሚል የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

ከአንድ ዓመት በኋላም የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ የመጀመሪያውን ብሔራዊ የሴቶች ቀን አወጀ። ቀኑን ዓለም አቀፍ የማድረጉ ሃሳብ የመጣው ክላራ ዜትኪን በምትባል ግለሰብ አማካይነት ነው። በዴንማርክ ኮፐን ሀገን እአአ 1910 የሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ሃሳቡን አነሳች። በወቅቱ ከ17 ሀገራት የተውጣጡ 100 ሴቶች ተሳትፈው ነበር።

ሃሳባቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ መልካም አጋጣሚ ነበርና በሃሳቧ ሙሉ ለሙሉ ተስማሙ። ከዚህም ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦስትሪያ ዴንማርክ ጀርመንና ሲዊዘርላንድ በአውሮፓውያን 1911 ተከበረ። ከዚያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋዊ በዓል ሆኖ መከበር ቀጠለ።

የሴቶች መብታችን ይከበር ፖለቲካዊ ትግል አንድ ሁለት እያለ አሁን ያለንበት ዘመን ደርሷል። በሀገራችንም ከሚፈለገው ደረጃ ደርሷል ባይባልም የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ ይበል የሚያሰኙ እንቅስቃሴዎች ግን እየተደረጉ ነው። ይሁን እንጂ ጅምሩ አድጎና ጎልብቶ ባህል ሊሆን ይገባል። ከቃል አልፎ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር ሊለወጥም ያስፈልጋል።

አሁን ላይ በተለይም በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚያሰኝ አይደለም። ይሄ ለምን ሆነ የሚለው ጥያቄ ዛሬም ጥያቄ ሆኖ መነሳት እና መልስ ማግኘት አለበት። « ሴቶች አይችሉም » የሚለው የማኅበረሰብ አስተሳሰብም ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት።

ሴቶች ይችላሉ፤ እንደሚችሉም እድሉን ያገኙ አሳይተዋል፤ መምራት እንደሚችሉ መርተው አስመስክረዋል። በማንኛውም መስክ በማንኛውም ሙያ የተሻለ የመፈጸም አቅምና ብቃት እንዳላቸው ጥቂቶችም ቢሆኑ ሰርተውና መርተው አሳይተዋል።

እነ ንግሥት ሳባ፣ ጣይቱ ፣ ዘውዲቱ ፣የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመሳሰሉት በሴቶች ሀገርን የመምራት ታሪካችን ማሳያዎቻችን ናቸው። አሁንም ትልልቅ ተቋማትንና ፕሮጀክቶችን የመሩ እና እየመሩ ያሉ አስደናቂ አፈፃፀም ያላቸው ሚኒስትሮች ፣ የክልል ፕሬዚዳንት፤ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የኮሌጆች ዲኖች … አሉ። ሆኖም በቂ አይደለምና ሊያድግ ይገባዋል።

በእያንዳንዱ ዘርፍ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ የግድ ይላል። በሁሉም ሙያዎች ኃላፊነቶች፣ ውሳኔ ሰጪነቶች ላይ መታየት አለባቸው። አሁንም ለሴቶች የሚተው ዘርፎች ጥቂቶች ናቸው ። በተለያዩ ተቋማት ላይ ሴቶች ይችላሉ ብሎ ማመን ላይ አሁንም ክፍተቶች አሉ። ሌላው ቀርቶ ከራሳችን ከሴቶች እንኳን እንችለዋለን ብሎ ደፍሮ የመውጣት ባህል ገና የዳበረ አይደለም።

በራሳቸው በሴቶች ጭምር የኖሩበት የማኅበረሰብ ተጽዕኖ ወደ ኋላ ይጎትታቸዋል። ወደፊት ለመምጣትም ይቸገራሉ። ያንን ጎጂ ባህል ሰብረው ወደፊት ሲወጡ ደግሞ « ሴቶች አይችሉም» የሚሉ አስተሳሰቦች ወደኋላ ሲጎትቷቸው ቆይተዋል።

ይሁንና ተጨባጩ እውነታ ሴቶች ሁኔታው ከተመቻቸላቸው ምንም የሚያቅታቸው ነገር እንደሌለ ያሳያል። በብዙ ችግሮችና ፈተናዎች መካከል ሆነው እንኳን መቻላቸውን አስመስክረዋልና ፤ የትርክት ለውጥ ያስፈልገናልና ፤ ሴቶች ይችላሉ እንበል !

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You