የውሃ ስፖርቶች ገፅታን ለመቀየር የተጋችው ብርቱ ሴት

በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስፖርት ታሪክ በተለይም በአትሌቲክስ ውጤታማነት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት ሴቶች ናቸው:: በስፖርት አመራርነት ረገድ ግን የሴቶች ተሳትፎ እጅግ ውስን የሚባል ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡ ከ31 በላይ የስፖርት ማህበራት (ፌዴሬሽኖች) መካከል ሴቶች ቁንጮ ሆነው የሚመሩት እጅግ ጥቂቶቹን ነው።

በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በተወዳዳሪነት፣ አሠልጣኝነት፣ ዳኝነትና ሌሎች ሙያዎች ላይ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ በርካታ ሴቶች ቢኖሩም ወደ ዘርፉ አመራርነት በዚያው ልክ መታየት አለመቻላቸው ሁሌም የሚነሳ ጥያቄ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማውን የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ስፖርት በፕሬዚዳንትነት ለሁለት የሥራ ዘመን የመራችው ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን የመሳሰሉ ብርቱ ሴቶች ዘርፉን የበላይ ሆነው በመምራት ለብዙዎች ተነሳሽነትን መፍጠር ችለዋል። ያምሆኖ አሁንም ድረስ የሴቶች የስፖርት አመራርነት ሚና እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም።

ብርቅዬዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የነበራት የፕሬዚዳንትነት የሥራ ዘመን መቋጨቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የስፖርት ማህበራትን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩ ሴቶች ቁጥር ባለፉት ዓመታት ከነበረው ቀንሷል። ወደ ሶስትም ዝቅ ሊል ችሏል:: ከእነዚህ ሴት የስፖርት አመራሮች መካከል ደግሞ ላለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ጥንካሬዋን ማሳየት የቻለችው ወይዘሮ መሠረት ደምሱ አንዷ ናት::

ለውሃ ዋና ስፖርት የተለየ ፍቅር እንደነበራት የምታስታውሰው ወይዘሮ መሠረት ወደ ስፖርቱ አመራርነት እንድትገባ ያደረጋትም ይሄው ምክንያት ሲሆን፤ ለዓመታት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነትና በሴቶች ኮሚሽን አባልነት እንዲሁም ጸሃፊነት አገልግላለች። በተለያዩ አጋጣሚዎች በስፖርት የሴቶች አመራርነት ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎችን በመውሰድና ራሷን ማብቃትም ነበር ወደ አመራርነት መምጣት የቻለችው::

በሪዮ 2016 ኦሊምፒክ የውሃ ዋና ተሳትፎ የኢትዮጵያ ገጽታ በተበላሸበት ማግስት በመልካም ዓይን የማይታየውን ፌዴሬሽን ቁንጮ ሆና ለመምራት መቀላቀሏን ተከትሎም ተቀዳሚው ሥራዋ የፌዴሬሽኑን ገጽታ መገንባት እንደነበር ታስታውሳለች:: ኢትዮጵያ የውሃ ማማ የሚል ቅጽል ያላት ሀገር ሆና ሳለ በጸጋዋ ላለመጠቀሟ የመሠረተ ልማት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጉዳዮች እንቅፋት ሆነውባት ቆይቷል:: ይህንን ለማረምም ጊዜ፣ ትዕግስትና የተለየ ጉልበት ይጠይቅ ነበር ትላለች::

በዚህም ላለፉት አራት ዓመታት ያልተነገረላቸው ነገር ግን አስደናቂ የሆኑ ሥራዎች ተከናውነዋል:: የፌዴሬሽኑን መልካም ገጽታ ከመገንባት ጎን ለጎን በሀገር ውስጥ መጠሪያው የሆነው ‹‹የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን›› በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የነበረው አልነበረም:: ‹‹የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን›› ይባል ነበር፤ በሁለቱ መካከል ሰፊ ልዩነት ያለና የሀገሪቷንም ተሳትፎ የሚገድብ በመሆኑ ምክንያትም ስሙን የማስቀየር ሥራ ቀዳሚው ነበር:: በዚህም ኢትዮጵያ በውሃ ስፖርቶች ስር የሚጠቃለሉ 6 ዓይነት ስፖርቶችን (ስዊሚንግ፣ ዳይቪንግ፣ ሃይ ዳይቪንግ፣ ዎተር ፖሎ፣ አርቲስቲክ ስዊሚንግ እና ኦፕን ዎተር ስዊሚንግ) በሀገር ውስጥ መምራትና ማስፋፋት እንዲቻል ወይዘሮ መሠረት የአንበሳውን ድርሻ ተጫውታለች።

በአፍሪካ የውሃ ዋና ቻምፒዮና ተሳትፋ የማታውቀው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍ መቻሏም ፌዴሬሽኑ በወይዘሮ መሠረት መሪነት ባለፉት ዓመታት ካስመዘገባቸው ስኬቶች መካከል ሊጠቀስ የሚችል ነው:: በምስራቅ አፍሪካ በተካሄደ ‹‹ማስተር ስዊሚንግ›› የተሰኘ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ተሳታፊዎች በሚወዳደሩበት መድረክ ኢትዮጵያ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቧም በስፖርቱ ታሪክ የመጀመሪያው ነው::

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ዞን ደረጃ ያላትን የውድድር ተሳትፎ አጠናክሮ ከመቀጠል ባለፈ ዓለም አቀፍ ተሳትፎዋ እያደገ በመምጣቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስፖርቱን የሚመራው ተቋም የራሱን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል:: ከዓመታት በፊት በኦሊምፒክ አንገት የሚያስደፋው ተሳትፎ የሀገር ውስጥ ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ማስተካከል የተቻለበትም ሆኗል:: የታዳጊዎችን ሥልጠና በማሳደግ ረገድም በዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን በሚደረገው እገዛ የቁሳቁስ ድጋፍ በስፋት እየተገኘና እንደሀገር በስፖርቱ ላይ አበረታች ለውጥ እየታየ ነው::

ፕሬዚዳንቷ ስፖርቱን ለማሳደግ ባለሙያዎችን ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን በማመንም ባለፉት ዓመታት በዚሁ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደተሠራ ትናገራለች። በዚህም 5 ዓለም አቀፍ ዳኞችን ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን፤ “በስፖርቱ ስመጥር ከሆኑ ሀገራት እኩል ኢትዮጵያ ስሟ በየመድረኩ ይጠራል” የምትለው ወይዘሮ መሠረት፣ በአፍሪካ ደረጃ ባለው የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥም አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ተቀላቅሎ ትልልቅ ውድድሮችን የመምራት እድል እንደተፈጠረለት ታስረዳለች።

ፕሬዚዳንቷ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ሥልጠና በኢትዮጵያ እንዲሰጥ ለማድረግም ከዓለም አቀፉ ተቋም ጋር በተከናወነ ሥራ የአመራርነት አቅሟን ማስመስከር ችላለች። በዚህም የሀገር ገፅታን ከመገንባት ባለፈ ባለሙያዎችም የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል::

ፕሬዚዳንቷ በቅርብ ካሳካቻቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የምስራቅ አፍሪካ ዞን 3 የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታን ማግኘት መቻሏ ነው:: ሌሎች ሶስት ባለሙያዎችም በዞኑ የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ውስጥ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል መሆን መቻላቸው ኢትዮጵያ በውሃ ስፖርቶች አመራርነት የራሷን ተሳትፎ እንድታደርግ አስችሏታል:: ባለፉት አራት ዓመታት በብርቱዋ ሴት አመራርነት በተከናወኑ የተለያዩ ሥራዎች እንደ አጠቃላይ የፌዴሬሽኑ አፈጻጸም በኢትዮጵያ ካሉ የስፖርት ማህበራት በጥንካሬው ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፉን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እውቅና ሰጥቶታል።

ፕሬዚዳንቷ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽንን ጥሩ ያልነበረ ገፅታ ለማስተካከልና ስፖርቱንም ለማሳደግ ላለፉት አራት ዓመታት ብዙ ርቀት ብትጓዝም፣ ነገሮች አልጋ ባልጋ እንዳልነበሩ ትናገራለች። ከተለያዩ አካላት የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ እንድትለቅ ዛቻና ማስፈራሪያን ጨምሮ በበርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፏንም ታስታውሳለች:: ስፖርቱን በሕግ ለመምራት በሚደረገው ሂደት ጥቅማቸው የተነካ የመሰላቸው ግለሰቦች ማስጠንቀቂያ፣ ሴራ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት የያዘችውን መንገድ የማሳት ጫናዎች ቢደረጉም በብቃት ማለፍ ችላለች:: ‹‹ባለፉት ዓመታት ሀገሬንና ሕዝቤን በማገልገሌ ደስተኛ ነኝ ስኬታማ ሥራዎችንም ማከናወን ችያለሁ:: ስፖርትን ለመምራት ማለፍ ከሚጠበቁ ችግሮች በላይ ሀገርንና ሰንደቅን መውደድ የሚቀድም በመሆኑ በተቆርቋሪነት ስሜት መሥራት ተገቢ ነው›› በማለትም ተናግራለች።

ሴቶች በሌሎች ጉዳዮች የመጠመድና ሕገወጥ ነገሮች ላይ የመሳተፍ ዝንባሌያቸው እምብዛም በመሆኑ ለያዙት ሥራ ሙሉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ውጤታማ መሆናቸው በብዙ አጋጣሚዎች ታይቷል። በጥናትም የተረጋገጠ ሃቅ ነው:: ይሁንና በስፖርቱ ዘርፍ እንደ ኢትዮጵያ ያለው የአመራርነት ተሳትፎ አናሳ ነው:: ነባራዊው ሁኔታ እንደሚያሳየው ከሆነም ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትን በመምራት ላይ የሚገኙት ሴቶች ጥቂት፤ በተለያዩ ሁኔታዎች ደግሞ እየቀነሰ የመጣ ነው:: ለዚህም ብቁ የሆኑና የተማሩ ባለሙያዎች ጠፍተው ሳይሆን ወደ አመራርነት ለመግባት ያለው ፈተና ከባድ በመሆኑ ነው:: አብዛኛዎቹ ማህበራት በወንድ አመራሮች ከመያዛቸው ባለፈ አላስፈላጊ ትስስሮች ያሉበትም ጭምር በመሆኑ ይህንን ሰብሮ ለመውጣት ከባድ ትግልና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል::

በየትኛውም የስፖርት ዘርፍ የሴት አመራሮች ተሳትፎ 50 ከመቶ ሊሆን ይገባል ቢባልም በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን ይህንን ስለማበረታታቱም ፕሬዚዳንቷ ጥርጣሬ አላት:: በእርግጥ ሴቶችም ‹‹እችላለሁ›› በሚል ስሜት በወንዶች የበላይነት የተያዘውን ዘርፍ በጥንካሬ መቀላቀላቸውም አጠያያቂ ነው:: ነገር ግን ሴቶች በሚያገኟቸው ዕድሎች ሁሉ ብቃታቸውን ማሳየትና ችግሮች ሲኖሩም በመጋፈጥ ተወዳዳሪነታቸውን ሊያስመሰክሩ ይገባል ባይ ናት:: ሴቶች በተፈጥሮ የተሰጣቸው ጸጋና ጥንካሬ ስላለ በጥበብ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በማለፍ ወደ አመራርነት መምጣት ይችላሉም የሚል እምነት አላት:: ወይዘሮ መሠረት ለዚህም በዘርፉ ላሉ ሴቶች በማሳያነት የኢትዮጵያን ስፖርት እየመሩ የሚገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካን ምሳሌ አድርጋ ትጠቅሳለች። ወደ ሥልጣን ከመጡ ወራት ብቻ ቢያስቆጥሩም ተቋርጠው የነበሩ ውድድሮችን በማስጀመርና ከዚህ ቀደም የተበላሹ አሠራሮችን በማስተካከል እያከናወኑ የሚገኙት አበረታች ሥራዎች ሴቶች መሥራት እንደሚችሉ ብቻ ሳይሆን ውጤታማ እንደሆኑም በግልጽ የሚያስመሰክሩ ናቸው:: በመሆኑም ሴቶች በግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ ወደ አመራርነት እንዲመጡ ለማድረግ በየስፖርት ማህበራቱ ያለውን የምርጫ ሂደት ማስተካከልና ማበረታታት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቅ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ጠቁማለች::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You