
ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሀላባ ከተማ ይካሄዳል። ለ22ኛ ጊዜ የሚካሄደው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 18ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።
ውድድርና ፌስቲቫሉን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ብዙ ትውፊታዊ የባህል ስፖርቶች ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ፤ በየዓመቱ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ሲካሄድ መቆየቱን በማስታወስ ዘንድሮ “ባሕላዊ ስፖርቶቻችን ለጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ከሌላ ጊዜው በተሻለ መልኩ ከልዩ ልዩ ደማቅ መርሀግብሮች እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ “አንድ ማህበረሰብ በረዥም ዓመታት ታሪካዊ ጉዞው ውስጥ ባህላዊ ስፖርቶችን ለተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና መስተጋብሮች በስፋት የሚጠቀምባቸው ናቸው” በማለት የውድድርና ፌስቲቫሉን ሀገራዊ ፋይዳ አስረድተዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በባህል እሴቶችና ህብረ ብሄራዊ አንድነቶች የተገነባች ሀገር እንደመሆኗ የብዝሀ ባህላዊ ስፖርቶች ማዕከልም ጭምር ናት” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በየአካባቢው የሚገኙት በርከት ያሉ ባህላዊ ስፖርቶችን ለሀገር ግንባታ ለመጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ፤ የባህል ስፖርት ዋነኛ ዓላማው ከውድድር ባሻገር የእርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከርና ወንድማማችነትን በመፍጠር ባህላችንን የምናሳይበት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፣ ሁሉም ሊስማማበት የሚገባ አንድ ነገር አለ። ይህም በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ለመሆን የቻሉት ዘመናዊ ስፖርቶች የኋላ ታሪክ መሠረታቸው ባህል መሆኑ ነው።
የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሕይወት መሐመድ በበኩላቸው፣ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ሕዝባዊ መሠረት ያለውን የባህል ስፖርት ተሳትፎን በማጎልበትና በማስፋፋት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራችንን ባህላዊ ስፖርቶች እውቅና እንዲያገኙ፣ ዋነኛ ትኩረቱን ተደራሽነታቸውን ማሳደግ ላይ አድርጎ እንደሚሠራ ገልፀዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለፃ፣ በኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚያዘወትሩዋቸው የተለያዩ የባህል ስፖርቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ በስፋት ተጠቃሚ የሚሆኑባቸውና በንቃት የሚሳተፍባቸው ስፖርቶች ናቸው። የህብረተሰቡን የስፖርት ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በተለይ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና መላው ህብረተሰብ ባህሉን፣ ወጉንና አንድነቱን የበለጠ ለማጠናከር እና በእረፍት ጊዜው ውድድሮችን በማዘጋጀት እንዲዝናና ለማስቻል ወደ ውድድር ስፖርቶች እንዲያድጉ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ደንቦች እየተዘጋጁ ከህብረተሰቡ የዕድገት ደረጃ ጋር መጣጣም የሚችሉበት ደረጃ ላይ ስፖርቱን የማድረስ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ በአዋቂ የባህል ስፖርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በታዳጊ ፕሮጀክቶችና በትምህርት ቤቶች ውስጥ እየሠራ የሚገኘውን በማንሳት “እንደ ሀገር በሚደረጉ የትምህርት ቤቶች እና የዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ውድድር ላይ የባህል ስፖርቶችን እንደ አንድ የውድድር ዓይነት አድርገው እንዲያካትቱ ፌዴሬሽኑ እየሠራበት ይገኛል” በማለት ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም የባህል ስፖርት ውድድሮች በተካሄዱባቸው ጊዜያቶች፣ አልፎ አልፎ የሚታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈቶች እንደነበሩ በመጥቀስ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዚዳንቷ፣ መሰል የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች እንደነበሩና ዘንድሮ ግን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ዝግጅት እንደተደረገ ተናግረዋል። ለዚህም የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች መንስኤ ናቸው ተብሎ በታመነባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ሥራዎች እንደተሠሩ አስረድተዋል። በውድድር ወቅት አግባብ ያልሆኑ ነገሮችን የሚያስነሱ አብዛኛዎቹ እንደ ምክንያት ከሚያቀርቡት አንዱ በዳኝነትና ፍትሃዊነት ላይ መሠረት ያደረገ እንደሆነ በመጠቆምም ፤ ተወዳዳሪዎቹን ከደምብና ሥነ ምግባር አንጻር ከመፈተሽ ባለፈ ለዳኞች ቅድመ ሥልጠና በመስጠት ውድድሩን እንዲመሩ የተመረጡ ዳኞች በልምድና ክህሎት የካበቱ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በሆሳዕና ከተማ አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም በሚካሄደው የ2017 ዓ.ም የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል፤ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች፣ በ11 የባህል ስፖርት ዓይነቶች በድምሩ ከ1386 በላይ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። ከእነዚህም መካከል 789 ወንድ እና 596 ሴት ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡ 5 የባህል ስፖርት ኢንስትራክተሮች እና 5 የባህል ፌስቲቫል ዳኞችም ይመሩታል፡፡
ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት የሚካሄደው ውድድርና ፌስቲቫል፣ ከባህላዊ ሙዚቃና የሙዚቃ መሣሪዎች ጋር በልዩ ልዩ ሀገርኛ ጨዋታዎች የሚደምቅ ይሆናል፡፡
ሙሉጌታ ብርሀኑ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም