መሐመድ ሳቢት በሀረሪ ክልል የኤረር ወረዳ የመስኖ ባለሙያ ነው። እዚያው ክልል ሶቢ ወረዳ ደከር በሚባል አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አላጌ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በማምራት በስሞል ስኬል ኢሪጌሽን ትምህርት ክፍል ለሦስት ዓመታት ትምህርቱን ተከታትሎ ተመርቋል።
ወደ ትውልድ ቀዬው ተመልሶ በኤረር ወረዳ በመስኖ ባለሙያነት ተቀጠረ። መሐመድ ተወልዶ ካደገበት ወረዳ በ23 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኙት የኤረር ወረዳ ነዋሪዎች በዓመት አንድ ጊዜ ማሽላ በመዝራት፣ ከብት በማርባት እና እንጨት ወደ ከተማ ወስደው በመሸጥ ኑሯቸውን ሲገፉ ቆይተዋል።
“አካባቢውን ስመለከተው የውሃ ሀብት እንዳለው ተረዳሁ” የሚለው መሐመድ ነዋሪዎቹን ሰብስቦ ይህ ሁሉ መሬት እና ውሃ አላችሁ፤ አትክልት እና ፍራፍሬ በማምረት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ትችላላችሁ ብሎ እንዳወያያቸው ይናገራል። በውይይቱ የተሳተፉት የአካባቢው ነዋሪዎች “እኛ አባቶቻችን እንዳወረሱን ዝናብ ጠብቀን ማሽላ እንዘራለን፣ ከብቶችን እናረባለን እንጂ አትክልትና ፍራፍሬ አልምተን አናውቅም” የሚል መልስ ይሰጡታል።
በዚህ ጊዜ መሐመድ እኔ የመስኖ ባለሙያ ነኝ። እናንተ እኔ የምሰጣችሁን ሙያዊ ምክር እየተቀበላችሁ አብረን የምንሠራ ከሆነ መሬታችሁ ብዙ ምርት ያስገኝላችኋል ይላቸዋል። ከዚያም በሃሳቡ የተስማሙ 10 አርሶ አደሮችን ይዞ ወደ ሥራ ገባ። ከሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ ዘር በመውሰድ ሽንኩርት ለአንድ ወር እንዲሁም ቲማቲም ከ20 እስከ 25 ቀናት መደብ ላይ እንደሚቆይ ካስረዳቸው በኋላ በመደብ ላይ እንዴት ማጽደቅ እንደሚችሉም አብሯቸው በመሥራት በተግባር አሳያቸው።
ቀጥሎም መደብ ላይ ያለው ዘር እስኪደርስ አብሯቸው መሬቱን ማረስ ተያያዘ። በመጨረሻም የደረሰውን ተክል ከመደብ ወደ እርሻ ተሸጋገረ። በማሳ ላይ ያለው ሽንኩርትና ቲማቲም በተለያዩ በሽታዎች ሲጠቃ ተመልክቶ መድኃኒቱን በመለየት ከክልሉ ግብርና ቢሮ በሚደረግለት ድጋፍ እንዲታከም አደረገ። ለመጀመሪያ ጊዜ በአካባቢው መሬት ላይ ሽንኩርትና ቲማቲም እንዲመረት ማድረግ ቻለ። መሐመድ ሥራውን ይሰራ የነበረው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር እያዋለና እያደረ የሚበሉትን እየበላ የሚጠጡትን እየጠጣ ነበር።
ምርቱ በደረሰ ጊዜም አርሶ አደሮቹ ወስደው የሚሸጡበት ቦታ ስላልነበራቸው በወቅቱ የሀረሪ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወደ ነበሩት ወይዘሮ ምስራ አብደላ አመራ። አግኝቷቸውም አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን ምርት የምንሸጥበት ቦታ አጣን፤ የገበያ ቦታ ይመቻችልን ብሎ ጠየቃቸው። ምክትል ፕሬዚዳንቷም ወዲያውኑ ሐረር ከተማ ውስጥ ቦታ እንዲዘጋጅላቸው አደረጉ። ምርት ማጓጓዣ መኪናም ተመደበላቸው።
መሐመድ ከአርሶ አደሮቹ ጋር በመሆን ምርቱን በተዘጋጀው መኪና ጭኖ ወደ ከተማ በማምጣት አብሯቸው ተቀምጦ እንዴት መሸጥ እንዳለባቸው እያሳየ ገንዘባቸውን እንዳይሰረቁ እየጠበቃቸው ከጎናቸው ሳይለይ ደገፋቸው። በመጨረሻም የባንክ ሂሳብ ቁጥር እንዲከፍቱ በማድረግ ገንዘባቸውን እንዲያስቀምጡ አደረገ። አርሶ አደሮቹ እጅግ በጣም ተደሰቱ። “መሬታችን እንዲህ ያለ ምርት መስጠት እየቻለ እስከዛሬ እንዲሁ መቀመጡ ቆጭቶናል” ሲሉም ተደመጡ።
በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ “እጅግ በጣም ደስተኛ ሆነው ሳያቸው በጣም ነው ደስ ያለኝ” ይላል። መሐመድ እንደሚናገረው ከኮሌጅ ተመርቆ ሲወጣ የነበረው ፍላጎት ደመወዝ የሚያገኝ የመንግሥት ተቀጣሪ መሆን ሳይሆን የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር ነበር።
ፈቃደኛ በሆኑ 10 አርሶ አደሮች 10 ሄክታር ማሳ ላይ ቲማቲምና ሽንኩርት ተተክሎ መጽደቁን እና የመሬቱ ባለቤቶች መጠቀማቸውን የተመለከቱ ሌሎች የአካባቢው ነሪዎችም በመሐመድ እገዛ መሬታቸውን ማረስና ሽንኩርትና ቲማቲም መትከል ጀመሩ። የአርሶ አደሮቹ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ አንድ ሞዴል አርሶ አደር ከ29 አርሶ አደሮች ጋር በማደራጀት 30 ሆነው በቡድን ስሜት እየተጋገዙ እንዲሠሩ አደረገ።
በአትክልት ልማቱ በስፋት የተሳተፉት ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች በብዛት ሊሳተፉ የቻሉት መጀመሪያ ላይ መሬታቸው ላይ አትክልት ማምረት እንደሚችሉ ሲያስረዳቸው ከአዋቂዎቹ ይልቅ ወጣቶቹ አምነውት አብረውት ስለተሰለፉ ነው።
ዛሬ የአርሶ አደሮቹ ቁጥር ከሁለት ሺህ 500 በላይ ደርሷል። ከአንድ ሺህ 500 ሄክታር በሚልቅ ማሳ ላይ በዓመት ሦስት ጊዜ ያመርታሉ። መጀመሪያ መስከረም ሳይደርስ በቆሎ ይዘራሉ። አካባቢው ሞቃት በመሆኑ በፍጥነት በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይደርሳል። በቆሎ እየደረሰ ሲመጣ መደብ ላይ ሽንኩርት ያለማሉ። መደብ ላይ ለአንድ ወር ከቆየ በኋላ በቆሎ ታጭዶ መሬቱ ሲጸዳ ወደ ማሳ ይሸጋገራል። ሽንኩርቱ ሲደርስ ደግሞ ማሽላ ወይም በቆሎ ይዘራሉ። እየቀያሩ በማምረታቸው ምርቶቹ በበሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ይቀንሳል።
መሐመድ እንዴት እንዲህ ያለ አመርቂ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደቻለ ሲጠየቅ፤ “እኔ ወደ አካባቢው ከመሄዴ በፊትም የሚመደቡ ባለሙያዎች ነበሩ። ልዩነት መፍጠር የቻልኩት የነዋሪዎቹን ሕይወት ለመቀየር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ ነው” ሲል ይመልሳል።
የፈጠረው ተጽዕኖ ሊሰፋ የቻለበትን ምክንያት ሲያስረዳም፤ “መጀመሪያ በቀበሌ ደረጃ የመስኖ ባለሙያ ሆኜ ነበር የምሠራው፤ ሦስት ዓመታት ከቆየሁ በኋላ ቀበሌውን ቀይሯል በሚል የወረዳ የመስኖ ባለሙያ እንድሆን ተደረገ። መጀመሪያ ሥራ የጀመርኩት ዶዶታ በተባለው ቀበሌ ነበር። የወረዳ የመስኖ ባለሙያ ሲያደርጉኝ በሌሎች ሦስት ቀበሌዎችም የእርሻ ሥራ እንዲስፋፋ አድርጌያለሁ›› ይላል።
ወጣቱ የመስኖ ባለሙያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በሠራው ሥራ ውጤታማ በመሆኑ ምን እንደሚሰማው ሲገልጽ “ትምህርቴን አጠናቅቄ የተመረኩት በመስኖ ነው። ያገኘሁትን እውቀት ሥራ ላይ በማዋሌ በሺህ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ሕይወት ሲቀየር ስመለከት መግለጽ የማልችለው የደስታ ስሜት ይሰማኛል” ብሏል።
አክሎም በተለያየ ጊዜ እውቅና እና ሽልማት እንደተሰጠውና በዚህም በጣም ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል። የመጀመሪያውን ሽልማት ያገኘው ከሚሠራበት ወረዳ ነው። መሐመድ ሁልጊዜም እንደሚያደርገው አርሶ አደሮቹ ምርታቸውን ወደ ሐረር ከተማ ወስደው ሲሸጡ መሐመድ አጠገባቸው ቁጭ ብሎ ገንዘቡን ይሰበስብላቸዋል። አንድ ቀን ይህን ተግባሩን በመወጣት ላይ ሳለ በገበያ መሀል ስልኩን ተሠረቀ። በዚህ ጊዜ መሐመድ አምርሮ እንዳለቀሰ ይናገራል። የሚሠራበት ወረዳ ሁኔታውን ተመልክቶ የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻል በሙያው ላደረገው አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠት ሳምሰንግ ጋላክሲ 33 ስማርት ስልክ ሸልሞታል።
ሀረሪ ክልልም በግብርና ዘርፍ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥቶታል። ቀጥሎም የ2016 ዓ.ም. አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ግብርና ሚኒስቴር ባካሄደው የግብርና ባለሙያዎች የእውቅና ሥነ ሥርዓት በሙያው የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር ባደረገው አስተዋጽኦ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞተር ሳይክል፣ ላፕቶፕ እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል። የሽልማቱን ሂደት ሲገልጽ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ እንደምሆን ተነግሮኝ ሽልማቱን ለመቀበል ስሄድ ከተሸላሚዎቹ መካከል ወጣት እኔ ብቻ ነበርኩኝ። “ምን ሠርተህ ነው በዚህ ዕድሜ ተሸላሚ የሆንከው እያሉኝ የሚገረሙ ብዙ ነበሩ” ይላል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የቀድሞ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሚስራ አብደላን ስለ መሐመድ ጠይቋቸው በሰጡት ምስክርነት፤ የሀረሪ ክልል ግብርና ቢሮ የበጋ መስኖን ከጀመረ አራት ዓመቱ ነው። የበጋ መስኖ የሚሠራው በክልሉ በሚገኙት በሦስቱም የገጠር ወረዳዎች ነው። አፈጻጸሙን ስንገመግም በሶስቱም ወረዳዎችና በውስጣቸው በሚገኙ ቀበሌዎች የተለያየ ነው። ከፍተኛ ውጤት የሚመዘገበው መሐመድ በሚመራው ወረዳ ላይ ነው። ልዩነቱ የሚታየው ከፖለቲካ አመራሩ ባሻገር የግብርና ባለሙያው ቁርጠኝነት እጅግ ወሳኝ ስለሆነ ነው። መሐመድ ሕዝቡን ከማወያየት ጀምሮ ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቶ አብሮ ከአርሶ አደሩ ጋር በመሥራት ምርቱን ከገበያ ጋር እስከ ማስተሳሰር ድረስ በከፍተኛ ኃላፊነት ሲወጣ ነበር ብለዋል።
አያይዘውም የበጋ መስኖ በየጊዜው እያደገ መጥቶ በ2016 ዓ.ም. አራት ሺህ ሄክታር መሬት ተሸፍኗል። በሀረሪ ክልል ለእርሻ ከሚውለው መሬት 30 በመቶ ያህሉ በበጋ መስኖ ተሸፍኗል። ይህ ሥራ ሲሠራ አርሶ አደሩ ጋር የነበረውን አመላካከት ከመቀየር ጀምሮ እያንዳንዱ ማሳ ላይ የሚሠራ ሥራ እየደገፈ ቀን እና ሌሊት ከአርሶ አደሩ ጋር ቆይታ እያደረገ ምርቱ ሲደርስ ደግሞ ከአርሶ አደሩ ጋር ወደ ገበያ በማምጣት የገበያ ትስስሩ እንዲሳለጥ በማድረግ በትጋት ሲሠራ የነበረ ጠንካራ የልማት ሠራተኛችን ነው። በዚህ ሥራውም ግብርና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመረጣቸው ጠንካራ የልማት ሠራተኞች አንዱ ሆኖ ተሸላሚ ሆኗል ነው ያሉት።
ስለወጣቱ የመስኖ ባለሙያ ምስክርነቱን የሰጠው ወጣት አርሶ አደር አሊ አብዲ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በዓመት ሶስት ጊዜ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ቃሪያ እንደሚያመርት ይናገራል። በገበያው ሁኔታ የሚወሰን ቢሆንም በዓመት ከ200 እስከ 300 ሺህ ብር ገቢ አገኛለሁ ነው የሚለው። አሊ አሁን በዓመት ሶስት ጊዜ የሚያመርትበት ቦታ ከዚህ ቀደም የከብቶች መዋያ ነበር። ሌላ አካባቢ ባለው አንድ ቦታ በዓመት አንድ ጊዜ በዝናብ ውሃ ማሽላ ያመርታል። “መሐመድ ወደ አካባቢያችን መጥቶ ካወያየን በኋላ ከብቶች ይውሉበት የነበረውን መሬቴን እያረስኩ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት ጀምሬያለሁ” ይላል።
“ከዚህ በፊትም በቀበሌያችን ባለሙያ ነበረ ነገር ግን እንደ መሐመድ ያለ ሰው ገጥሞን አያውቅም። በፊት የነበሩት ባለሙያዎች መጥተው እናንተ ለምን አትሠሩም ብለው ወቅሰውን ነበር የሚሄዱት። መሐመድ ግን አብሮን እየዋለና ከእኛ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ አሳምኖን ወደ ሥራ እንድንገባ አድርጎናል። መሬታችንን ማረስ ስንጀምርም አብሮን ማሳችን ውስጥ ከእኛ ጋር እየደከም ውጤት አምጥቷል። መሐመድን ማባዛት ብንችልና ሌሎችም እኛ ያገኘነውን ዓይነት ድጋፍ ማግኘት ቢችሉ ብዬ እመኛለሁ። እኛ እርሱን በማግኘታችን ዕድለኞች ነን ከዜሮ ተነስቶ ሁሉን ነገር ከእኛ ጋር ሰርቶ ሕይወታችን እንዲለወጥ አድርጓል። እኛ ወጣቶች ነን። በዚህ ዕድሜያችን በአካባቢያችን ሠርተን ገንዘብ በማግኘታችን ደስተኞች ነን” ሲል ስለ መሐመድ ትጋት መስክሯል።
ወጣት አርሶ አደር አሊ አብዲ ባለፉት ስድስት ዓመታት በመሐመድ እገዛ ጠንክሮ በመሥራቱ ሕይወቱ ምን ያህል እንደተለወጠ ሲናገር፤ “በምኖርበት የገጠር ቀበሌ ከተማ ውስጥ ቤት ሠርቻለሁ። ለባለቤቴ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ከፍቼላት እየሠራች ትገኛለች። በተጨማሪም በመቶ ሺህ ብር ሁለት ከብቶችን ገዝቻለሁ። በቀጣይ ከተማ ውስጥ መሬት ገዝቼ ቤት የመሥራት ዕቅድ አለኝ” ብሏል።
መሐመድ ለግብርና ባለሙያዎች እና ለአርሶ አደሮች ባስተላለፈው መልዕክት፤ ሰው ጠንክሮ ከሠራ ይለወጣል የሚል ነው። ባለሙያዎች አርሶ አደሩን በሚገባ ከደገፉት እንዲሁም አርሶ አደሮችም በባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክር ተቀብለው በትክክል የሚተገብሩ ከሆነ ለውጥ መምጣቱ የማይቀር ነገር ነው ሲል በርግጠኝነት መልዕክቱን አስተላልፏል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም