
ለአንድ ሀገር ሰላም እና ደህንነት ከዚያም አልፎ ሉዓላዊነት መከበር ወሳኝ ከሆኑ ተቋማት መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሱት የመከላከያ ተቋማት ናቸው። ከዚህ የተነሳም ሀገራት ከፍ ያለ ሀብት በመመደብ የመከላከያ ተቋሞቻቸውን በቴክኖሎጂ እና በሠለጠነ የሰው ሃይል ያደራጃሉ። የመከላከያ ኃይላቸውን በሁለንተናዊ መንገድ ጠንካራ ቁመና እንዲኖረው አበክረው ይሠራሉ።
የመከላከያ አቅምን ማሳደግ ፤ የሀገራትን ሉዓላዊነት ሰላም እና ደህንነት ከማስከበር ባለፈ አሁን ላይ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እና በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስጋቶችን ለመከላከል ስትራቴጂክ አቅም ይሆናል። ይህን ተከትሎም ሀገራት ከመቼውም ጊዜ በላይ የመከላከያ በጀታቸውን በማሳደግ የመከላከያ ኃይላቸውን ወይም ተቋሞቻቸውን ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ እያዘመኑ ናቸው።
ዓለም አሁን ካለችበት ተጨባጭ እውነታ አኳያም የመከላከያ አቅምን የማሳደግ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ይስተዋላል። የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች ራሳቸውን ከማዘመን ባለፈ፤ አዳዲስ ዘመኑን የሚዋጁ የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን ለአደባባይ እያበቁ ናቸው። የዘርፉ ተወዳዳሪነትም በየዕለቱ እያደገ ነው።
ይህንን እውነታ ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት አምስት ዓመታት ፤ የሀገሪቱን መከላከያ ሠራዊት በሁለንተናዊ መልኩ ሀገሪቱን እና ታሪኳን የሚመጥን እንዲሆን ፤ የሀገሪቱን ሰላም ፣ መረጋጋት እና ሉዓላዊነት ፤ ከዚያም ባለፈ ብሄራዊ ጥቅሞቿን በተሻለ መልኩ ማስጠበቅ እንዲቻል ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን ሠርቷል ።
ሀገራችን ካለችበት መልካክዓ-ምድራዊ ስትራቴጂክ ቀጣና ፤ በቀጣናው ካሉ የተለያዩ ፍላጎቶች እና ፍላጎቶቹ ሊፈጥሩት ከሚችሉት ጫና እንዲሁም ሀገራዊ ለውጡ ይዞት ከመጣው ሀገር እና ሕዝብን የማበልጸግ ከፍ ያለ ራእይ አኳያ መንግሥት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል በሁለንተናዊ መንገድ ብቁ ለማድረግ እየሄደበት ያለው መንገድ ሊበረታታ እና ተገቢው እውቅና ሊሰጠው ይገባል።
በእነዚህ አምስት ዓመታት ሠራዊቱ በቂ የሰው ኃይል እንዲኖረው ሰፋፊ ምልመላዎች ተካሂደዋል፤ ኅብረብሔራዊ እንዲሆንና ሁለንተናዊ የውጊያ ብቃቱ እና ግዳጅ የመፈጸም አቅሙ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለማድረግም የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲያገኝ ተደርጓል። ዘመኑን የሚዋጁ የጦር መሣሪያዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን እንዲታጠቅ ለማድረግ የተሄደበት ርቀትም በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የፈጠረው በራስ የመተማመን መንፈስ ከፍተኛ ሆኗል።
የሀገሪቱ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች ራሳቸውን እያዘመኑ ሀገሪቱ በዘርፉ የምትፈልጋቸውን ወታደራዊ አቅርቦቶች በራስ አቅም ለመሸፈን እያደረጉ ያሉት ጥረት እና እየተመዘገበ ያለውም ስኬትም ሀገሪቱ የተሟላ ቁመና ያለው የመከላከያ ኃይል ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት ተጨማሪ የጥንካሬ ምንጭ እየሆኑ ነው።
ቀደም ባሉት ጊዜያት መከላከያ ኃይሉ በእጁ ያሉ ወታደራዊ መሣሪያዎችን ወይም ስትራቴጂክ የጦር መሣሪያዎችን ጭምር አቅም በማሳደግ የፈጠረው በራስ መተማመን ፤ የራሱን የደንብ ልብስ በራሱ አቅም በማምረት ራሱን የቻለበት መንገድ ፤ ከዚያም አልፎ አሁን ላይ ተተኳሾችን፣ የነፍስ ወከፍ እና የቡድን መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ከማምረት አልፎ ለውጪ ገበያ እያቀረበ ያለበት ሂደት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የቱን ያህል ውጤታማ እንደሆነም ያመላክታል።
ይህ በመከላከያው ዘርፍ እንደሀገር እየተመዘገበ ያለው ስኬት፣የሀገርን ሰላም እና መረጋጋት ብሎም አልፎ ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል መተማመን ፈጥሯል። ሀገሪቱ በቀጣናው ያላትን ጥቅሞች ማስጠበቅ የሚያስችል አቅም እየገነባች ስለመሆኑም በተጨባጭ ያሳያል።
እንደ ሀገር የጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጉዞ ከውጪም ከውስጥም ሊያጋጥሙት የሚችሉትን ተግዳሮቶችንም በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት ያስችላል። በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት፤ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የሚነሱ ኃይሎች ደጋግመው እንዲያስቡም መልዕክት ያስተላልፋል!
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም