
– ባለፉት ሰባት ወራት 233 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት አድርገዋል
አዲስ አበባ፡- በቤት ሠራተኝነት ላይ ተወስኖ የነበረው የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ከ20 በላይ ሙያዎች እንዲካተቱበት ተደርጓል ሲል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት 233 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እንዳደረጉም ተገለጸ፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አለቃ፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በቤት ሠራተኝነት ላይ ተወስኖ የነበረው የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ከ20 በላይ ሙያዎች እንዲካተቱበት ተደርጓል፤ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪቱ ሙሉ ለሙሉ የሠለጠኑትንም ሆነ በከፊል የሠለጠኑትን ያካትታል፡፡
የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት የተለያዩ አማራጭ ሊኖሩት ይገባል ያሉት ኃላፊው፤ እዚህ ሀገር መሄድ አልፈልግም የሚሉ ዜጎችም መርጠው የሚሄዱበት አማራጭ ሀገር ማግኘት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ለዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት ሦስት የነበሩት የመዳረሻ ሀገራት ወደ ስድስት ከፍ እንዲሉ ተደርጓል፡፡ ሁለት ሀገራትንም ተጨማሪ መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር በአንድ ሙያና በጥቂት ሀገራት የተወሰነ እንደነበር አስረድተው፤ ይህ የተጣበበ እድል ብዙዎችን ለሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭ ስለሚደርጋቸው፤ በዓመት ከ40 ሺህ በላይ ዜጎች ጉዟቸው እንደሚስተጓጎል አመላክተዋል።
የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት በሥነ-ሥርዓት ተመርቶ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ባላት ስትራቴጂካል ጠቀሜታ ለማደግ ምክንያት ይሆናት ነበር ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የሰው ኃይል ከሚፈልጉት መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የ4፡00 ሰዓት የአየር በረራ ርቀት ላይ እንደመገኘቷ እና እንዳላት የባህልና የሃይማኖት መቀራረብ ብዙ ሰዎችን ማሰማራት ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እንደኢትዮጵያ ቅርበት የሌላቸው ሀገራት እድሉን በመጠቀም በዓመት እስከ 40 ቢሊዮን ዶላር የሚያገኙ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ቤተሰብ ንብረቱን ሸጦና በአራጣ አሲይዞ የሚልካቸው ልጆቹ ተጎድተውና በሽተኛ ሆነው በመምጣት ወደ ጎዳና የሚወጡበት ሥርዓት መቀየር አለበት በሚል ሪፎርም መደረጉን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ዜጎች አስተማማኝ ስምሪት እንዲያገኙ ፤ ከብልሹ አሠራርና ከሌብነት የጸዳና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 7 ወራት በተዘረጋው አዲስ ሲስተም የባዮሜትሪክስ ዐሻራ የሰጡ፣ ማንነታቸው የሚታወቅና ከየት ተነስተው የት እንደሚደርሱ የተለዩ 233 ሺህ ዜጎች ወደ ተለያዩ ሀገራት የሥራ ስምሪት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ሥራ ባልጀመረበት 2014 ዓ.ም 57 ሺህ ዜጎች ብቻ ህጋዊ የሥራ ስምሪት ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ ሥራ ከጀመረበት 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን 705 ሺህ ዜጎች በውጭ ሀገራት ህጋዊ የሥራ ስምሪት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ አሁን በከፊል የሠለጠነ የሰው ኃይል ወደ ሳውዲ አረቢያ፣ ጆርዳን፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ፣ ኩዌትና ሊባኖስ እየተሠማራ ነው። ቁጥሩ ትንሽ ቢሆንም በተመሳሳይ ወደ አውሮፓ ሀገራት ማለትም ጀርመን፣ ፖላንድ፣ ስዊድንና ኖርዌይ ይሠማራል ብለዋል፡፡
በግል ጥረት የሥራ እድል ያገኘ ሰው የትኛውም የዓለም ክፍል ቢሆን ደህንነቱ አስተማማኝ ከሆነ እንዲሠማራ ይፈቀዳል ብለዋል፡፡ ሰው በግሉ ያመጣውን የሥራ እድል ደህንነት ለማረጋጥ ኤምባሲዎች ከሲስተሙ ጋር የተሳሰሩ መሆኑንና የደህንነት ማረጋገጫ ሲሰጥ ፍቃድ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዜጎች ከስደት መልስ ድጋሚ ስደት እንዳያስቡ ለማድረግም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የሥራ ውላቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ምን መሥራት እንደሚፈልጉ የሚያሳይ የኢንተርፕርነርሽፕ ፎርም ሞልተውና የቢዝነስ ምክር ወስደው የሚሄዱ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በተሰማሩበት ሀገር በሚያስቀምጡት የቁጠባ አካውንት መጠን ልክ የፋይናንስ ብድር ተመቻችቶላቸው ከስደት ሲመለሱ ማሟላት ለሚፈልጉት ጉዳይ መጠቀም የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል፡፡ ከሚኖሩበት ቀበሌ እስከ ኤምባሲ ድረስ ትስስር ተፈጥሮ ዜጎች ምንም ሳይደርስባቸው እንዲሠሩ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም