የአንድን ሀገር ሰላም እና መረጋጋት ከዚያም ባለፈ ልማት እና ብልፅግና ተጨባጭ ለማድረግ ከሁሉም በላይ ስልጡን የፖለቲካ መንገድ መከተል ወሳኝ ነው። በተለይም ባለንበት ዘመን ዓለም ከደረሰበት የአስተሳሰብ ልዕልና አኳያ ዘመኑን በሚዋጅ የፖለቲካ እሳቤ እና መንገድ ላይ መገኘት ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መተኪያ የሌለው ምርጫ ነው።

በተለይም እንደኛ ባሉ ለዘመናት በተዛነፈ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ በወለደው ግጭት እና ጦርነት ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ለተገደዱ ሀገራት እና ሕዝቦች፤ ዘመኑን በሚዋጅ የሰለጠነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ የመገኘት እና ያለመገኘት ጉዳይ በሀገራቱ ሕዝቦች ዛሬ እና ነገዎች ላይ የሚኖረው አሉታዊ ሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ ከግምት ያለፈ ነው።

የእኛን ሀገር የትናንቱን ትተን የዛሬ የፖለቲካ እውነታችንን ወስደን ለማየት ብንሞክር፤ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት እንደ ሀገር የመጣንበት የፈተና መንገድ እና መንገዱ ያስከፈለን ያልተገባ ዋጋ ስልጡን የሆነ የፖለቲካ መንገድ እና መንገዱ ለተገዛለት አስተሳሰብ ተገዥ መሆን ባለመቻላችን ነው። ከዘመኑ እሳቤ ጋር መጣጣም አቅቶን ፤የትናንት ጥላ ሰለባ ከመሆናችን ጋር በተያያዘ ነው።

በአንድ በኩል ስለዘመናዊነት እና ዘመናዊ የፖለቲካ እሳቤዎች ከንፈሩ እስኪደርቅ የሚያነበንብ፤ በሌላ በኩል አስተሳሰቡ ለሚጠይቀው የባህሪ ማንነት ባዕድ የሆነ፤ በውስጡ ለተፈጠረው የማንነት መደበላለቅ እና የአስተሳሰብ መዛነፍ ሀገር እና ሕዝብን የመስዋዕት በግ አድርጎ በሚመላለስ ፖለቲከኞች ፖለቲካችን በመጠለፉ ነው።

አንድ ቋንቋ እየተናገረ፤ ከአንድ የዕውቀት ገበታ ማዕድ እየተቋደሰ በሕዝብ እየማለ እና እየተገዘተ ፤ያልተገራ ራስ ወዳድነት በፈጠረው መሻት ግራ ተጋብቶ፤ በትውልዶች ላይ የግራ መጋባት ዘር የሚረጭ፤ የትውልዶችን ብሩህ እጣ ፈንታ በማጨለም እና በጨለመው የሚቆምር ፖለቲከኛ እዚህም እዚያም በመፈጠሩ ነው።

ይህንን ካልተገራ ማንነት እና ከተዛነፈ አስተሳሰብ የሚመነጨውን በትውልዶች ዕጣ ፈንታ መቆመር፤ እንደ አንድ አዋጭ የፖለቲካ መንገድ ወስደው፤ ያለ እፍረት ከፍ ባለ ድምጽ በአደባባይ የሚጮሁ፤ ይህንን መሻታቸውን ተጨባጭ ለማድረግ የሚተጉ ኃይሎች በእዚህ ዘመንም መታየታቸው ነው።

እነዚህ ኃይሎች ስለ ሕዝብ እና በሕዝብ ይሁንታ ወደ ስልጣን ስለሚመጣ መንግሥት እና መርሆች እየደሰኮሩ፤ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን ለመጣ መንግሥት ዕውቅና ከመስጠት ይልቅ በግርግር የመንግሥት ስልጣን ለመያዝ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲወራጩ ማየት እና መስማት የተለመደ ነው።

ስለ ሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ከአቅማቸው በላይ እየደሰኮሩ ፤የምርጫ ሥርዓትን ተከትለው ወደ ስልጣን በሚወስደው መንገድ ላይ ከመገኘት ይልቅ፤ በሕጋዊ መንግሥት ላይ ሕገ ወጥ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችሉ የጥፋት መንገዶችን ሲያነፈንፉ፤ ለእዚህም የሚሆን የመቆመሪያ መንገድ ሲፈልጉ መሽቶ የሚነጋባቸው ናቸው።

ስለ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በአደባባይ እየጮሁ፤ በየጓዳቸው እና በየጥጉ የሕዝብ ስልጣን የሚጨብጡበትን አቋራጭ የጥፋት መንገድ በማፈላለግ የሚዳክሩ፤ ላልተገባ የፖለቲካ መሻታቸው ስኬት ከአቋራጭ መንገድ ውጭ ተስፋ እንደሌላቸው አውቀው፤ የሕዝብ ስሜት እና ተስፋ እያጠለሹ ይህንንም የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

እነዚህ ኃይሎች በእዚች ሀገር የትናንት የፖለቲካ ትርክት ውስጥ አቋራጭ የፖለቲካ መንገድ ሀገር እና ሕዝብን የቱን ያህል ፈተና ላይ እንደጣለ ፤በዚህ መንገድ የተነሳ ምን ያህል ትውልድ ከህልሙ ተጣልቶ ውድ ዋጋ እንደከፈለ ለማየትም ሆነ ለመስማት ፈቃደኞች አይደሉም። ሁልጊዜ ለምኞታቸው አቋራጭ የሚመስላቸውን መንገድ በማነፍነፍ በሀገር ሕልውና ጭምር የሚቆምሩ ናቸው።

ሕዝብን በአንድም ይሁን በሌላ ከተስፋው ማፋታት ለሚፈልጉት የፖለቲካ ስልጣን የተስፋ ርካብ አድርገው የሚወስዱ፤ የሕዝብን ስሜት በሆነ ባልሆነው በመፈታተን ከስሜቱ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በተገኘው አጋጣሚ የአዞ እንባ ለማንባት የተዘጋጁ እና በእዚህም በቂ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው።

በስመ ሽግግር መንግሥት እነዚህ ኃይሎች ትናንት ሆነ ዛሬ ላይ የመጡበት መንገድ ለሕዝቡ የተሰወረ አይደለም። በቀደመው ጊዜ ስለእነሱ ያለውን መረዳት በምርጫ ካርዱ በተጨባጭ አሳይቷቸዋል። ነገ ላይ የሚሆነውን ደግሞ ጊዜው ሲደርስ የሚታይ የአደባባይ እውነት ይሆናል። ሃሳብ አፍልቆና ሃሳቡን ሕዝብ እንዲገዛው አድርጎ መመረጥ ብሎም መንግሥት መመስረት የአሁኒታዋ ኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነት ነው፡፡ ከእዚያ ውጪ ያለው የስመ ሽግግር መንግሥት ግርግር በራሱ የሚያመጣው አዲስ ነገር ግን አይኖርም።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በግርግር የፖለቲካ ስልጣን አገኛለው ብሎ ማሰብ አንድም የሕዝቡን እና የሀገርን አሁናዊ ንቃተ ሕሊና ካለመረዳት አለበለዚያም ከተለመደው የሕዝብ ንቀት የሚመነጭ ነው!

አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You