ከካራማራ ድል በመማር …

ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ናት። በየዘመናቱ የሀገሬን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር አላስደፍርም ያሉ ጀግኖች ልጆቿ እምቢ ለሀገሬ በማለት አጥንታቸውን ከስክሰው፤ደማቸውን አፍስሰውና ህይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስጠብቀዋል፤ ለተተኪው ትውልድም ነጻነትንና ኩራትን አስረክበዋል፡፡

ልጆቿ የብሔር፤ የሃይማኖት፡ የጾታ እና ሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ሳይበግራቸው በአንድነት በዓድዋ ቅኝ ገዥዎችን፤ በካራማራ ተስፋፊዎችን አሳፍረው መልሰዋል። ዛሬም በዚሁ መንፈስ ሀገራቸውን ለመታደግ የነቁ እልፍ አእላፍ ልጆች አሏት።

ለሉዓላዊነቱና ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትናንት በዓድዋ ሀገሩ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ልትወድቅ መሆኑን በሰማበት ቅጽበት ቀፎው እንደተነካበት ንብ ከአራቱም ማዕዘናት በአንድነት ተሰባስቦ ሀገሩን ታድጓል፤ ታሪክ ጽፏል፤ ለመላው ጥቁር ሕዝቦችም መከታ ሆኗል።

ይህንኑ የታሪክ ክስተት የዛሬ 47 ዓመት በካራማራ ታላቂቷን ሶማሊያ እመሰርታለሁ በሚል የቀን ቅዥት ታውሮ የመስፋፋት ወረራ በፈፀመው የዚአድባሬ ወራሪ ሠራዊት ላይ መድገም ችለዋል። በዚህም አትንኩኝ ባይነታቸውን ዳግም በታሪክ አደባባይ አስመስክረዋል።”… ታፍራና ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያ ተደፍራለች፡፡ በአ ሁኑ ሰዓት የአብዮታዊት እናት ሀገራችን ዳር ድንበር ና የማይገሰሰው አንድነታችን በውጭ ኃይል እየተደፈ ረ ነው፡፡

በአብዮታችንና በአንድነታችን በጠቅላላው በብሔራዊ ህልውናችን ላይ የሚደረገው ወረራና ድፍ ረት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል… ለብዙ ሺህ ዘመናት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አ ብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም፡፡ ሀ ገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ የኢት ዮጵያ ሕዝብ፣ ክብርንና ነፃነትህን ለመድፈር፣ ሀገርህ ን ለመቁረስ… የተጀመረውን ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሠልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋ ጅበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ተነስ! ታጠቅ! ዝመት! ተዋ! እናሸንፋለን!!››

የሚለውን የወቅቱን መሪ ጓድ የሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን የክተት አዋጅ በመቀበል፤ በጥቂት ወራት ዝግጅት ሀገሩን መታደግ ችሏል። የእብሪተኛውን የዚያድ ባሬ ጦር ካራማራ ላይ ድል በማድረጉ የአሸናፊነት ታሪካዊ ትርክቱን አድሷል።

ከጣሊያንና ከእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ነፃነቷን በ1952 ዓ.ም ያገኘችው ሶማሊያ በነጻነቷ ማግሥት ሶማሊያን ለ21 ዓመታት ያስተዳደሩት ዚያድባሬ፤ ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት በሚል “ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል” እያሉ በመዛት የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽመዋል።

በወቅቱም እስከ ድሬዳዋ ድረስ የዘለቀውን ወራሪ ኃይል አሳፍሮ በመመለስና ብሎም ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዲደርስበት በማድረግ ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር መሆኗን ያስመሰከሩ በርካታ ጀብዱዎች ተፈጽመዋል። ከዚህ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የካራማራ ድል ነው።

ሀገርና ሕዝብ በአይነኬ የሉአላዊነት ስም የሚጠሩባት ሀገራችን ኢትዮጵያ ፤በልጆቿ የህይወት መስዋዕትነት በካራማራ ተራራ ላይ ወድቆ የነበረውን ባንዲራዋን በታላቅ መስዋእትነት ዳግም በማንሳት ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል። በታሪክ ሂደት ውስጥ ለወዳጅም ለጠላትም አስተማሪ የሆነ ተጨማሪ ድል ባለቤት ሆነዋል። ድሉ እንደ ቀደሙት ዘመናት የላቀ የሀገር ፍቅር፣ የነጻነት እና የአትንኩኝ ባይነት ውጤት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጣሊያን ሀገሩን ልትወር ስትመጣ በንጉሱ የክተት አዋጅ ሳያንገራግር ወደ ጦር ሜዳ እንደከተተ ሁሉ ፣ የካራማራው ትውልድም የወቅቱን መሪ የተነስ ፣ታጠቅ ፣ ዝመት ጥሪ ተቀብሎ ለግዳጁ ዝግጁ ሆኗል።

በወቅቱ፣ከሠራዊቱ ቁመና ጀምሮ በውስጥና በውጪ ያልተፈቱ ቅራኔዎች ቢኖሩም፤ቅራኔዎችን ወደኋላ በመተው፤ በቀደመ አንድነቱ ሉአላዊነቱን አስከብሯል። ቀፎው እንደተነካበት ንብ ከአራቱም ማዕዘናት በአንድነት ተሰባስቦ ሀገሩን ታድጓል፤ አዲስ ታሪክም ጽፏል።

“ሀገሬ ስትደፈር ከምመለከት ህይወቴ ቢያልፍ እመርጣለሁ” ያሉ በርካታ ጀግኖች በአውደ ውጊያው መስዋዕት ሆነው የሀገራቸውን ሉአላዊነት አስከብረዋል። ይህ አኩሪ ድላቸውና መስዋዕትነታቸው በታሪክ ዘላለም ሲዘከር ይኖራል።

እኛ የዛሬ ትውልዶችም ከዚህ ትምህርት ልንቀስም ይገባል። ለሀገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ውለታ የሚመለሰው የሰላምና የልማት አርበኛ መሆን ስንችል ነው።

በተለይም ሰላም ለራቃት ሀገራችን የሰላም አምባሳደር በመሆን የአባቶቻችን መስዋዕትነት ደምቆ እንዲኖር ለማድረግ የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል። የግጭት፣ የጦርነት፣ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ እሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል።

በአባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ ያገኘነው ኩራትና ነጻነታችን ሙሉ እንዲሆን ሀገሪቱን በልማት ማበልጸግና በሚመጥናት ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። አሁን ላይ ይህ ትውልድ ታላቁን የዓባይ ግድብ ሰርቶ እያገባደደ ነው።

ይህን የሀገር ኩራት የሆነ ግድብ አጠናቆ በተመሳሳይ መንገድ ሌሎች ግድቦችን በመሥራት ለሀገር ብሎም ለአፍሪካ ብርሃን ማጎናጸፍ የዚህ ትውልድ አንዱ አደራ ነው። በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ የተገኘውን አኩሪ እንቅስቃሴ ዘላቂ ማድረግና ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካን መመገብ ሌላው የዚህ ትውልድ አሻራ ሊሆን ይገባል።

አረንጓዴ አሻራ በማኖር ረገድ ኢትዮጵያውን ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛሉ። ይህ አኩሪ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት የማይወዱ አካላት ሊያጣጥሉት ቢሞክሩም ተግባሩ የሚደበቅ አይደለምና ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው መድረኮች ሁሉ በውጤታማነቱ እየተወሳ ይገኛል።

ወቅቱ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያ ልክ እንደ ዓድዋና ካራማራ በዓለም መድረክ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ወጣቱ ትውልድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ክህሎት በመታጠቅ የሀገሩን ልማት ወደፊት ማራመድ ይጠበቅበታል።

ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል በዓድዋም ሆነ በካራማራና በሌሎችም የጦር አውድማዎች የሀገርን ዳር ድንበር አላስደፍርም በማለት ደማቸውን በማፍሰስ፤ አጥንታቸውን በመከስከስ ውድ ህይወታቸውን መስዋዕት ሲያደርጉ ኖረዋል።

የአሁኑ ትውልድም የሀገሩን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን በሰላም እና በልማቱም መስክ ሀገሪቱን ወደፊት ሊያራምዱ የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈጸም መስዋዕት የከፈሉ ቀደምት አባቶችን ፈለግ ሊከተል ይገባል። ይህ ሲሆን ነው የአባቶች መስዋዕትነት ተገቢውን ዋጋ ሊያገኝ የሚችለው !

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You