የ“ቃልን በተግባር” ሌላኛው አብነት!

አዲስ አበባ የአፍሪካውያን የነፃነት ምልክት ብቻ ሳትሆን፣ የጋራ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት የኅብረታቸው መዲና እንዲሁም ሦስተኛዋ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልም ናት፡፡ ከፍ ያለ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ የስበት ቦታም ናት፡፡ ሰፊ የቱሪዝም አቅም ያላት፤ የኮንፍረንስ መዳረሻም ናት፡፡

ታዲያ እነዚህ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ መገለጫዎቿን በልካቸው ከመጠቀም አኳያ ለረጅም ጊዜ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳይሠራ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ የቱሪዝም አቅሟን አውጥታ ጥቅም ላይ ከማዋል እንዲሁም የኮንፍረንስ ማዕከልነቷን የሚመጥን መሠረተ ልማቶችን ከመዘርጋት አኳያ የሚታዩ ክፍተቶች በርካታ ነበሩ፡፡

በለውጡ ዘመን ላለፉት ስድስት ዓመታት ግን እነዚህን ችግሮች በልካቸው ተገንዝቦ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ፤ ኢትዮጵያ በልኳ እንድትገለጥ ከማድረግ አኳያ የተከናወኑ በርካታም፣ ዘርፈ ብዙም ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ገጽ የቀየሩ፤ የመንግሥትንም አቅዶ የመተግበር አቅም የገለጡ ሆነዋል፡፡

እነዚህ በለውጡ ማግሥት ታስበው የተተገበሩ እና ሪቫን የተቆረጠላቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች፤ በአንድ በኩል የኢትዮጵያን መልክ የቀየሩ ናቸው፡፡ በሌላም በኩል ሀብቷን አልምታ የቱሪዝም አቅሟን አውጥታ እንድትጠቀም፤ የዓለም የፖለቲካና ኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን የሚመጥኑ መሠረተ ልማቶች ባለቤትም እንድትሆን አስችለዋታል፡፡

ለዚህ ደግሞ የቤተ መንግሥት ልማት ሥራዎች፤ ሰው ተኮር የሆነው የኮሪደር ልማት ሥራ፤ መስቀል አደባባይ፣ እንጦጦ፣ አንድነትና ወዳጅነት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፤ የገበታ ለሸገር እና ለትውልድ ፕሮጀክቶች ወዘተ… እያሉ አያሌ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከሰሞኑ ተመርቆ እውን የሆነው አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ደግሞ የእነዚህ አብነቶች ተደማሪ አቅም፤ የኢትዮጵያ ገጽ ድምቀት ሌላው አካል ሆኖ የተተገበረ ነው፡፡

ለዚህም ነው፣ “ዛሬ የመረቅነው የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ ሀገራችን ታላላቅ ኮንፈረንሶችን እና ዐውደ ርዕዮችን እንድታስተናግድ የሚያስችላት ነው፤” ሲሉ ማዕከሉን መርቀው በከፈቱበት ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሩት፡፡ አያይዘውም “በዚህ ማዕከል ንግድ እንነግድበታለን፤ ሃሳብ እንለዋወጥበታለን፤” ሲሉ የማዕከሉን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ “የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የስብሰባ፣ የኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን ዘርፍን (MICE) ለማጠናከር ለምናደርገው ጥረት አንድ ተጨማሪ አቅም ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃን እንደጠበቀ ተቋምነቱ የንግድ ቱሪዝምን በማሳደግና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በመሳብ ሀገራችንን የኮንፈረንሶች እና ስብሰባዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታል፤” ሲሉም ስለ ማዕከሉ ከፍ ያለ ሀገራዊ አበርክቶ አብራርተዋል፡፡

የማዕከሉን መጠናቀቅ ተከትሎ ሁነቱን “አዲስ ድል፤ ሌላ ስኬት!!” ሲሉ የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ “የረዳን ፈጣሪ ይመስገን ካሉ በኋላ ከጅማሮው አንስቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አብራችሁን የለፋችሁትን እና ያሳካችሁትን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ፤” ሲሉ ቃልን ወደ ተግባር በመለወጥ ሂደት ሚናቸውን ለተወጡ አካላት ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

እናም በዚህ መልኩ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ይህ ግዙፍ እና ኢትዮጵያ ስሟን የሚመጥን፤ ታላቅነቷን የሚተካከል፤ ገናንነቷን የሚያስተጋባ ሆና እንድትገለጥ በማድረግ ጉዞ ውስጥ እውን ከሆኑት ሀገራዊ ግን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያላቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡

ማዕከሉ እንደ አዲስ አበባ ከተማም፣ እንደ ሀገርም አዳዲስ እድሎችን የሚከፍት፣ የማያቋርጥ የሀብት ምንጭ መፍጠሪያ የሚሆን፣ ብሎም ለገጽታ ግንባታ እና ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያም እንደ ሀገር የምትኮራበት፤ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ የሚመኩበት፤ መንግሥትም እንደ መንግሥት በተግባራቱ እንዲኮራና ለቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም እንዲተጋ አቅም የሚሆን ነው፡፡

15ሺ ካሬ የውጪ ሁነት ማስተናገጃ ቦታ ያለው ብቻ ሳይሆን፤ ባለ 5 ኮከብ ዘመናዊ ሆቴል፣ ሬስቶራንቶች፣ የስፖርት፣ የጤና፣ የመዝናኛ እና የልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ፤ በአንድ ጊዜ እስከ 2000 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ ያለው ሲሆን ማዕከሉን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የሚያገናኝ ሰፊ የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታም እየተከናወነለት የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡

በተጨማሪም ማዕከሉ ዓለም አቀፋዊ ኮንፍረንሶችን፣ የንግድ ውይይቶችንና ስምምነቶችን፣ ባሕላዊ መድረኮችንና ልዩ ልዩ ኤግዚቢሽኖችን ለማስተናገድ እድል የሚሰጥ፣ በጥቅሉም አዳዲስ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ የንግድና የኢኮኖሚ ስምምነቶች የሚጎለብቱበት፤ ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጠርበት፤ በጥቅሉም ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች የሚከናወኑበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ፣ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደ ሀገር የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ብቻ ሳይሆን፤ አልቆ የመፈጸም አቅምን ያሳየ፤ አስቦ የመጀመርን፣ ጀምሮም የማጠናቀቅን አዲስ ባሕል የገለጠ፤ ከምንም በላይ ደግሞ ቃልን በተግባር የመተርጎምን፤ ተግባርም ከልምምድ አልፎ ባሕል የመሆኑን እውነት የመመስከሪያ አብነት ነው!

አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You