
የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካም ብቻ ሳይሆን፣ ለሰው ልጆች ሁሉ የፍትሕ ተምሳሌት የሆነው የዓድዋ ድል ይህን ገናና ታሪክ ያገኝ ዘንድ እነዚህ ብልህ እና ጀግና የጦር መሪዎች ያስፈልጉት ነበር:: እነዚህ ብልህ እና ጀግና የጦር መሪዎች ደግሞ ይህን ድል ያገኙ ዘንድ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይነት ጀግንነት ባሕሉ የሆነ ሕዝብ ያስፈልጋቸው ነበር:: ሕዝቡም የጦር መሪ ያስፈልገው ነበር:: እነዚህን የጦር መሪዎች እናስታውስ::
ለዚህ ጽሑፍ የተክለጻደቅ መኩሪያ እና የጳውሎስ ኞኞን የታሪክ መጻሕፍት፣ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተለያየ ዓመት ዕትም፣ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኤን ቢ ሲ መገናኛ ብዙኃን ድረ ገጾቻቸውን በዋቢነት ተጠቅመናል::
ንጉሥ ሚካኤል
ዓድዋን ለዚህ ገናና ታሪኩ ካበቁ መሐንዲሶች አንዱ ንጉሥ ሚካኤል (የልጅ እያሱ አባት) ናቸው:: ንጉሥ ሚካኤል አሊ ሊበን ንጉሠ ወሎ ወትግሬ የሚል የንጉሥነት መጠሪያ የነበራቸው ሲሆኑ፤ በፈረስ ስማቸው ደግሞ አባ ሻንቆ ይባላሉ::
ንጉሥ ሚካኤል የደሴ ከተማ መሥራች፤ የወሎው ባላባት፤ የልጅ እያሱ እና የወይዘሮ ስኅን አባት፤ የዓፄ ምኒልክ አማችና ቀኝ እጅ የሸዋ ረገድ ምኒልክ ባል፤ የእቴጌ መነን አያት፤ ወሎን ለ30 ዓመታት ያስተዳደሩት የወረሂመኖ ባላባትና ገዥ ከነበሩት አሊ አባ ቡላ ከእናታቸው ገይቲ ገባቤ ጥር 27 ቀን 1842 ዓ.ም እንደተወለዱ ታሪካቸው ያሳያል:: እንዲህም ተብሎላቸዋል::
አባ ሻንቆ የዓድዋው እንቆቆ
ጠላትን የሚጥል ሰይፍ ጋሻ አጥልቆ
የተንታው ግስላ የአምባላጌው ነብር
ከጠላት መሐል ዘሎ የሚከመር
ንጉሥ ሚካኤል ባለ ሦስት ግንባር
የወንዶች ቁና የማይደፈር
ተብሎ የተገጠመላቸው ደፋርና የጦር አዝማች መሆናቸውን ዓፄ ምኒልክ መስክረውላቸዋል:: የወሎው ራስ ሚካኤል በሦስቱም ዓውደ ውጊያዎች በመሳተፍ ድል አድርገዋል:: ራስ ሚካኤል ዓሊ ጠንካራ እና በቁጥር ብዙውን የጦር ሠራዊት በመገንባታቸው ይታወቃሉ::
ከራስ ሚካኤል ጦር በቀር በሦስቱም ዓውደ ውጊያ የተሳተፉ የኢትዮጵያ ጦር አለመኖሩ በታሪክ ተመዝግቧል:: ለዚህም ነው ራስ ሚካኤል በዓድዋ ዘመቻ ግንባር ቀደም ከነበሩት ዘማቾች እና በዓድዋ ጦርነት ጉልህ ሚና ከነበራቸው ውስጥ አንዱ እንደሆኑ ታሪክ የሚዘክራቸው::
የታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት የራስ ሚካኤል ጦር በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ቁጥሩ 70 ሺህ ደርሶ እንደነበር ፅፈዋል:: ይህንን ጦር በጀግንነት በመምራት የዓድዋ ጦርነቶች ላይ ተሳትፈዋል:: በተለይም ራስ ሚካኤል በዓድዋ ጦርነት የተጫወቱት ሚና ደማቁ ታሪካዊ ክስተት ነው::
ከዓድዋ በፊት የመጀመሪያው የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት አምባላጌ ላይ ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት የራስ መኮንን፣ የራስ ሚካኤልና የራስ መንገሻ ጥምር ጦር ለሁለት ሰዓታት ያህል ተራራውን ከቦ ከተዋጋ በኋላ የጣሊያንን ጦር መሪ ሜጀር ቶሰሊን መግደል ችሏል:: ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተሰኘው መፅሐፋቸው ራስ ሚካኤል በአምባላጌው ጦርነት 15 ሺህ ጦር በማሰለፍ አኩሪ ታሪክ እንደሠሩ ጽፈዋል::
በዓድዋ ጦርነት ወቅት በጄኔራል ኦሬስቴ ባራቲየሪ ፊት አውራሪነት የተመራው የጣሊያን ጦር ወረራ ያካሄደው በሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ነበር:: በኢትዮጵያ በኩል ወደ ዓድዋ የዘመቱትን የጦር አዝማቾችና ያዘመቱትን የሠራዊት ብዛት በተመለከተ ከንጉሠ ነገሥቱ በመቀጠል ሁለተኛ የሚባለውን የሠራዊት ብዛት ይዘው የዘመቱት ራስ ሚካኤል እንደነበሩ ታሪክ መዝግቧል::
የጣሊያን ጦር የካቲት 22 ቀን ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዝ አድሮ ሊነጋጋ ሲል የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዓድዋ ጦር ግንባር ደረሰ:: ከደቂቃዎች በኋላ ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ተጀመረ::
በዚህ ጦርነት በመካከለኛው ግንባር ራስ ሚካኤል ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ከጠላት ጦር ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው በአሪሞንዲ የተመራውን ጦር ድል ማድረጋቸውን እና የጣሊያኑን ጦር መሪ ጄኔራል አሪሞንዲም በዚሁ ጦርነት መሞቱን ታሪክ ያሳያል::
የራስ ሚካኤል ሚና በዚህ የተገደበ አልነበረም:: ከዳቦር ሚዳ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሲፋለም የነበረው የራስ አሉላ ጦር ከፍተኛ ጫና ላይ ስለነበር ዓፄ ምኒልክ የራስ ሚካኤል ጦር ወደስፍራው ሄዶ እንዲያግዝ ትዕዛዝ በሰጡበት ወቅትም ከዳቦር ሚዳ ተናንቆ የነበረውን የራስ አሉላን ጦር ለማገዝ ወደ ግራ ግንባር ተንቀሳቀሰ:: በዚህን ጊዜ ወታደሮቻቸው የሚከተለውን የፉከራ ዜማ አዜሙ::
ማን በነገረው ለጣሊያን ደርሶ
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ
እንዲህ ባለ ሁኔታ የአሉላ እና የሚካኤል ጦር የጠላትን ጦር አሸንፎ ጄኔራሉን ዳቦር ሚዳን ገድሏል:: ጥምር ጦሩ እኩለ ቀን ላይ ሙሉ በሙሉ የጣሊያንን ጦር ደመሰሰ:: መሪውን አልበርቶኔንም ማረከ:: ጦርነቱ በግማሽ ቀን ውስጥ በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት ሲጠቃለል ሃምሳ ስድስቱም የጣሊያን መድፎች፣ በርካታ ከባድና ቀላል መትረየሶች እንዲሁም ጠመንጃዎች ተማርከዋል:: ከእነዚህም ወስጥ በራስ ሚካኤል የተማረኩት በደሴ ሙዚዬም ይገኛሉ::
ራስ ወሌ ብጡል (አባ ጠጣው)
ወሌ የራስ ብጡል ኃይለ ማርያም የበኩር ልጅ፤ የጣይቱ ብጡል ታናሽ ወንድም፤ የራስ ጉግሳ ወሌ አባት ናቸው::
ወሌ ብጡል በመቅደላ፣ በአምባ ማርያም እና በደብረታቦር ሳሉ ነበር ከሸዋው ልዑል ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ) ጋር የተዋወቁት። ዓፄ ምኒልክ በ1857 ዓ.ም ከመቅደላ አምባ አምልጠው ወደ ሸዋ ከገቡ በኋላ ነሐሴ 24 ቀን 1857 ዓ.ም በአባታቸው ዙፋን ላይ ነገሡ::
እንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገውን ዘመቻ እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ወሌ ከአሉላ ጋር ከአምባ ማርያም እስር አምልጠው ወደ ሸዋ ሸሹ።
ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ ተብለው ሥልጣን ከጨበጡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወሌ ከወንድማቸው ከአሉላ ጋር ከዓፄ ምኒልክ ጋር መኖር ጀመሩ:: በዚህም ወሌ ብጡል የደጅ አዝማችነት፤ አሉላ ደግሞ የፊታውራሪነት ማዕረግን አገኙ። በ1876 ዓፄ ምኒልክ ወሌን የየጁ አስተዳዳሪ አድርገው ሾሙ:: ወሌ ብጡል የደጅ አዝማችነት ማዕረግን ካገኙ ከስድስት ዓመታት በኋላ ታላቅ የፖለቲካ ክስተት ተፈጠረ። በ1883 ዓ.ም የወሌ እህት ጣይቱ ብጡል ከንጉሥ ምኒልክ ጋር በትዳር ተሳሰሩ::
ከጋብቻቸው በኋላ ደጅ አዝማች ወሌ በአገልግ ሎታቸውም ሆነ በአማችነታቸው ስለተደሰቱ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ የራስነት ማዕረግ አግኝተው ታላቅ ባለሟል ሊሆኑ ችለዋል። እ.ኤ.አ በ1889 ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ የደጃዝማች ወሌን ግዛት አስፋፍተው በጌምድርን ጨምረው የራስነት ማዕረግን ሰጧቸው።
ራስ ወሌ በአምባላጌ፣ በመቀሌ እና በዓድዋ ጦርነት ላይ ከፍተኛ ጀብዱ የፈጸሙ ጀግና ናቸው:: ‹‹አስር ደጅአዝማች የደገሰውን፤ የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን!›› የተባለላቸው ራስ ወሌ በአምባላጌ በተደረገው ውጊያ ላይ የራሳቸውን 10 ሺህ ሠራዊት በማሰለፍ ድል በማድረግ ታላቅ ጀብዱ እና አኩሪ ገድል አስመዝግበዋል::
ወደ ዓድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር 120 ሺህ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ጠቅሰዋል:: ራስ ወሌም የጥቁር ሕዝቦች ድል በሆነው የዓድዋ ጦርነት ከበጌምድር፣ የጁ፣ ዋድላ እና ዳውንት የተውጣጣውን ሠራዊታቸውን በመያዝ በጦርነቱ ተዋግተዋል:: ከግዛታቸው 10 ሺህ የሚደርሱ እግረኛ ወታደሮችን አሰልፈዋል። በዓድዋው ጦርነት ቅድሚያ ከተላኩት የጦር አበጋዞች መካከል ራስ ወሎ ግንባር ቀደሙ ናቸው::
ሰባት ደጃዝማች አሥር ፊታውራሪ የጠመቀውን
የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን፣
ወሌ በቡሎ ዘሎ ሲወጣ
ይመስላል ሐምሌ ክረምት የመጣ፣
ወሌ ወሌ ወሌ ቢሏችሁ
የሳቱ ጒማጅ መርጦ አለላችሁ፣
የወሌ ፈረስ ቀጭኑ ቡሎ፣
ዥራቱ አውሳ ግንባሩ ወሎ!
ንጉሥ ተክለሃይማኖት
ልጅ አዳል (በኋላ ንጉሥ ተክለሃይማኖት) አያቱ ጎሹ (ደጃች ጎሹ) በካሣ ኃይሉ (አጼ ቴዎድሮስ) ከተገደሉበትና አባቱ ተሰማ ጎሹ ከተጋዘ በኋላ ዘመድ የጭንቅ ዕለት ነውና በአባቱ አደራ ባይነት ወደ አጎቱ ተድላ ጓሉ ወደ ደብረ ማርቆስ ተልኮ ከልጆቹ ከንጉሤና ከደስታ ጋር እየተማረ አደገ::
ከዚያ በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም ገዥ ለመሆን ብዙ ፈተናዎችን አልፈዋል:: በቀድሞዋ መንቆረር በአሁኗ ደብረ ማርቆስ የሚገኘው የጎጃም ገዥዎች ቤተመንግሥት በ1845 ዓ.ም ደጃዝማች ካሣ (ዳግማዊ ቴዎድሮስ) የጎጃምን ግዛት ለማደላደል ዘመቻ አድርገው ክረምት በ1845 መንቆረር (አሁን ደብረ ማርቆስ) ውስጥ ቤተ መንግሥቱ በሚገኝበት ቦታ የሳር ሰቀላ ቤቶችን አሠርተው መክረማቸውና በቦታውም ከተማ እንዲቆረቆር ትዕዛዝ ስለማስተላለፋቸው የቤተመንግሥቱ ጅማሬም ለደጃዝማች ካሣ እና ለደጃዝማች ተሰማ ጎሹ (የንጉሥ ተክለሃይማኖት አባት) መካረሚያ ነበር::
ከደጃዝማች ደስታ ተድላ በኋላ ጎጃምን የገዙት ራስ አዳል ተሰማ (ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) በዘመናቸው የቤተ መንግሥቱን የውስጥ አደረጃጀት በማስፋፋት የአስተዳደር ሥራ በተደራጀ መንገድ እንዲከናወን በመደረጉና በሣር ክዳን ሰፊና ትልቅ አዳራሽ አሠርተው ስለነበር በአካባቢው ማኅበረሰብ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት በሚል ስያሜ መጠራት እንደጀመረ ይነገራል:: ሥያሜው ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በኋላም ሳይለወጥ አሁን ላይ ደርሷል::
ራስ አዳል ተሰማ በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ጥር 13 ቀን 1873 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ ላይ ‹‹ንጉሠ ከፋ ወጎጃም›› ተብለው የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ በተገኙበት ነግሠዋል::
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ራስ እያሉ ጀምሮ ከጎጃም የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸው ጋር እና ከኢትዮጵያ ነገሥታት ጋር በርካታ ጦርነቶችን አካሂደዋል:: የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሁለት ታላላቅ ዘመቻዎችን አድርገዋል:: እነዚህም ከሱዳን ደርቦሾች ጋር ያደረጉት እና በታላቁ የዓድዋ ድል ላይ የነበራቸው ሚና ነው::
ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት በር በከፈተው ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ወቅት የጎጃምን ጦር በመምራት ሦስት ሺህ ሠራዊት ይዘው በመዝመት ታላቅ ድል አስመዝግበዋል።
የንጉሥ ተክለሃይማኖት የግዛት ዘመን፤ ራስ አዳል ተብለው ከ1861 ዓ.ም እስከ 1872 ዓ.ም ድረስ፤ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ተብለው ደግሞ ከ1873 ዓ.ም እስከ 1893 ዓ.ም ድረስ፤ ለ32 ዓመት ጎጃምን ገዝተዋል:: ከሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውና ከነገሥታቱ ጋር በነበራቸው ጦርነት እንዲህ ተብሎ ተዘፍኖላቸዋል::
ሴቶች ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሂራ
ጦርነት አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ
አሉላ አባ ነጋ
ጣሊያን ሰሓጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ
እንደ ገብስ ቆላው አሉላ አባ ነጋ
አሉላ እንግዳ ቁቢ (በፈረስ ስማቸው አሉላ አባ ነጋ) የጦር መሪ፣ ሀገር አቅኚ፣ ዲፕሎማት፣ የደኅንነት ሰው፣ አርቆ አሳቢ እየተባሉ ይገለጻሉ:: ከኩፊት ጀምሮ እስከ ዓድዋ ድረስ ነበልባል ክንዳቸውን የቀመሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች የእርሳቸውን ማንነት ይመሰክራሉ::
ራስ አሉላ የተወለዱት በተምቤን ሲሆን፤ አመራርን በተፈጥሮ የተቸሩ መሆናቸውን እሥራኤላዊው የታሪክ ጸሐፊ ሀጋይ ኤርሊች “የራስ አሉላ ታሪክ በመላው ትግራይ የታወቀ ነው፤ በልጅነታቸው ልጆችን እንደ ወታደር ሰብስበው እየመሩ ወደ ሠርግ ቤት የሚሄዱ ሰዎችን አስቁመው ወደ የት እንደሚሄዱ ይጠይቋቸው ነበር” ብለዋል። ሰዎችም “ወዲ ቁቢ ‘ቤተመንግሥቴ ነው’ ብለው በሰፈሩበት የእቃ እቃ ጨዋታ ቦታ እየሄዱ ‘ራስ አሉላ’ በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸው ነበር ይላሉ የታሪክ ጸሐፊው።
በ1867 እና በ1868 በተካሄዱት የጉንደት እና ጉራዕ ጦርነቶች ለውጭ ወራሪዎች የሚፋጅ ክንዳቸውን በማሳየት ወታደራዊ ክህሎታቸውን ማሳየት ጀመሩ። በነዚያ ጦርነቶች ወራሪውን የግብፅ ጦር አንኮታኮቱት። አፄ ዮሐንስ በሐማሴን አመጽ የቀሰቀሱትን ራስ ወልደ ሚካኤል ሰለሞንን ለማስታገስ ይህን ልዩ ክህሎት ያለው ወጣት ፈለጉት፤ አሉላን ራስ ብለው ሾመው ወደ ቦጎስ የሸሹትን ራስ ወልደ ሚካኤልን እንዲይዙ ላኩት። ራስ አሉላም ተልዕኳቸውን በስኬት አጠናቀው በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ግርማ ሞገስን አገኙ:: ንጉሠ ነገሥቱ ራስ አሉላን የመረብ ምላሽ እና የምድሪ ባሕሪ (የዛሬው የኤርትራ) አስተዳዳሪ አድርገው ሾመዋቸዋል::
የራስ አሉላ የጦር ሜዳ ውሎዎች ሁሉ የድል እና የስኬት ነበሩ:: የኢትዮጵያን ጠላቶች እየቀጡ ወደ ግዙፉ እና ታሪክ ቀያሪው የዓድዋ ድል ያመሩት ወዲ ቁቢ ከዓድዋ በፊት ከግብፅ፣ ከመሃዲስት (የሱዳን) እና ጣሊያን ጋር ሦስት ታላላቅ ፍልሚያዎችን አድርገው ለወራሪዎቹ ነበልባል ክንዳቸውን አቅምሰዋቸዋል::
የውጫሌን አጭበርባሪ ውል ተከትሎ ጣሊያኖች በዓድዋ ዙሪያ መስፋፋታቸውን ቀጠሉ። ዓፄ ምኒልክ ይህን ክህደት ባወቁ ጊዜ ውሉን መሰረዛቸውን አሳወቁ። ራስ አሉላን ጨምሮ ዋና ዋናዎቹ መኳንንት እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት በአንድ ድምፅ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ለመውጋት ዝግጅት ጀመሩ። ከእነዚህ የጦር መሐንዲሶች አንዱ ራስ አሉላ አባ ነጋ ነበሩ::
በዚህ ውጊያ ላይ የራስ አሉላ፣ የራስ መኮንን እና የራስ ሚካኤል ጦሮችን በማጣመር ንጉሡ እና ንግሥቲቱ ከሚመሩት ጦር በስተግራ በኩል ተሰልፈው በአዲ አቡኔ ከፍታዎች ላይ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል አንኮታኮቱ። የአጋሜው የደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ ኃይሎችም የራስ አሉላ እና ራስ መንገሻን ጦሮች ተቀላቅለው ድሉን አጀቡት።
ራስ አሉላ ጣሊያኑን ጦር መሪ ጋስጎሪ እንቅስቃሴ እንዲከታተሉ እና የጣሊያን ደጀን ከአዲ ኳላ ግንባር ላለው ጦር እንዳይደርስ እንዲከለክሉ እና እንዲያጠቁ ተመደቡ። ጀግናውም የተሰጣቸውን ተልዕኮ በትክክል በመወጣት ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች ያበራችው የነፃነት ችቦ እንድትለኩስ የድርሻቸውን ተወጡ::
አሉላ አባ ነጋ የደጋ ላይ ኮሶ
በጥላው ያርዳል እንኳንስ ተቀምሶ!
ራስ መኮንን
ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል በመንዝ አውራጃ በአንኮበር ውስጥ ደረፎ ማርያም በምትባል ስፍራ ግንቦት 2 ቀን 1844 ዓ.ም ተወለዱ:: አባታቸው ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ወልደ መለኮት እንደ ሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት እና እንደ ንጉሥ ሳሕለ ሥላሴ ያሉ ታዋቂ አርበኛ ሲሆኑ የወግዳ እና የዶባ ባላባት ነበሩ::
አባታቸው ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ልጃቸውን መኮንን በ14 ዓመታቸው በወቅቱ የሸዋ ንጉሥ ለነበሩት ለንጉሥ ምኒልክ ወስደው አስረከቧቸው:: መኮንን ወልደ ሚካኤልም ቀስ በቀስ የምኒልክ ልዩ ጓደኛ ሆኑ:: በ1879 ዓ.ም የሐረርን ግዛት እንዲያስተዳድሩት በአጎታቸው ልጅ በሆኑት በዳግማዊ ምኒልክ ተሰጣቸው::
ልዑል ራስ መኮንን በለንደን የንጉሥ ኤድዋርድ ስምንተኛን የዘውድ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተዋል:: እግረ መንገዳቸውንም ጣሊያንን፣ ፈረንሳይን፣ ቱርክንና ጀርመንን ጎብኝተዋል:: በ1898 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ከመወለዳቸው አስቀድሞ የተወለዱት ደጃዝማች ይልማ መኮንን የሐረር ገዥ ሆነው አባታቸውን ልዑል ራስ መኮንን ተክተው ነበር::
በ1865 ዓ.ም አካባቢ ራስ መኮንን የደጃዝማች ዓሊ እና የወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ልጅ የሆኑትን ወይዘሮ የሺመቤት ዓሊን አገቡ:: ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ተወለዱ:: በኋላም የይልማ መኮንን ታናሽ ወንድም የሆኑት ተፈሪ በተራቸው የሐረር ገዥ እንዲሆኑ ሥልጣን ተሰጣቸው::
ልዑል ራስ መኮንን አውሮፓን በጎበኙበት ወቅት በፓሪስ ውስጥ ካለው የፈረንሳይ የሾፌርነት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተምረው የመንጃ ፈቃድ ያገኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ ይነገራል:: የራስነት ማዕረጋቸውን ያገኙት ቦሩ ሜዳ ነው::
ራስ መኮንን ዓድዋ ላይ የእነ ራስ ሚካኤልና የእነ ራስ ወሌን ጦር በበላይነት ያዘመቱ የጥቁር ድሉ ኮኮብ ናቸው::
ባለቅኔና ጸሐፊ ተውኔቱ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በ 1927 ዓ.ም በጻፉትና የዓድዋን ጀግኖች በሚያነሱበት ታዋቂ መወድሳቸው ደጋግመው ስሙን የሚጠሩትን ራስ መኮንንን ዓድዋ ላይ ስለሠሩት ጀብዱ፤ ድል ያደረጉባቸውን ቦታዎች እየጠሩ እንዲህ እያሉ ያሞካሹታል::
ይህ ራስ መኮንን ውብ ገበሬ ነው
አላጌ ላይ ዘርቶ መቀሌ አጨደው
ዓድዋ ከምሮ መረብ ላይ ወቃው::
ባልቻ ሳፎ
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ
በነሐሴ ወር 1854 ዓ.ም እንደተወለዱ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ::
ባልቻ ሳፎ ገና በልጅነት እድሜያቸው በጦር ሜዳ የተገኙ ጀግና ናቸው::
የዓድዋው ጦርነት ሥመ ጥር ጀግናው ባልቻ አባ ነፍሶ ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያን በድጋሚ ስትወር ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር ፀብ ስለነበራቸው ባልቻ ከጣሊያን ጎን ይሰለፋሉ ብለው ጣሊያኖች ጓጉተው ነበር። ደጃዝማች ባልቻ በንጉሡ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸውም በሀገር ጉዳይ ግን የሚደራደሩ አልሆኑም::
ባልቻ አባ ነፍሶ ጦራቸውን አሰባሰቡ:: ስለ ጦርነቱ የምስጢር ደብዳቤ መለዋወጥ ጀመሩ። አምስት ሺህ ጦራቸውን ይዘው በ75 ዓመታቸው ከአገምጃ ሶዶ ተነስተው አዲስ አበባ ደረሱ:: ረጲ ተራራ ላይ ሆነው መድፋቸውን ጠምደው የሌሎችን አርበኞች መልዕክት ይጠባበቁ ጀመር። ጣሊያን በአውሮፕላን ሆኖ የደጃዝማች ባልቻን ጦር እየተከተለ በጣም ብዙ ሰው የፈጀባቸው ቢሆኑም፤ በሕይወት ዘመናቸው ጣሊያንን ሁለት ጊዜ የተዋጉት ብዙ ወታደር የነበራቸው ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ግን የሚበገሩ አልነበሩም::
ደጃዝማች ባልቻ በ33 ዓመታቸው 3 ሺህ ጦራቸውን መርተው ዓድዋ ላይ አኩሪ ታሪክ ሠርተዋል:: የአምባላጌን ምሽግ በጀግንነት የሰበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ የካቲት 23 ቀን በውጊያ መሐል ተገደሉ:: ጠላት ድል እንዳያገኝ ባልቻ አባ ነፍሶ ወዲያውኑ የመድፍ ተኳሽነቱን ድርሻ ያዙ:: በዚህም፤
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ
በማለት ታሪክ ያስታውሳቸዋል::
በዓድዋው ጦርነት ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ከሊቀ-መኳስ አባተ ጋር በመሆን በመድፍ ስላደረጉት ፍልሚያ በርክሌይ ሲጽፍ፣ “ጣሊያኖች እንዳሥላሴ ወጥተው ‘የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን ልቀቁ፤ ጦርነቱ ሲያልቅ በትልቅ ሕንጻ እንሠራላችኋለን።’ አሏቸው እና አንድ ሺህ ብር ሰጧቸው። ሁሉም ቤተክርስቲያኑን ሲለቁ አንድ የሃምሳ ዓመት ቄስ ግን እምቢ አሉና ወዲያውኑ ተገደሉ። ከዚያም ቤተ ክርስቲያኑንና ቦታውን ጣሊያኖች ተቆጣጠሩት። ሆኖም ክርስቲያን የሆኑ የጣሊያን ወታደሮች ‘ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን አንዋጋም’ በማለታቸው ክርስቲያን ያልሆኑ ወታደሮች እዚያ ገብተው ጦርነቱ ቀጠለ፤ ያ ቀን መጥፎ እለት ነበር።
በጣሊያኖቹ ወገን ከእንዳሥላሴ የሚተኮሰው መድፍ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ጨረሰ። በኢትዮጵያ በኩል የተተኮሰው የመድፍ ጥይት፤ የጣሊያኑ መድፍ አፍ ውስጥ ገብቶ ሁለት ወታደሮችን አቆሰለ… እሳትም ተነስቶ አፈር የተሞሉ የምሽግ ጆንያዎች ተቃጠሉ።” ብሏል።
የደጃዝማች ባልቻ የጀግንነት ታሪክ በተለይ ከዓድዋ ድል በኋላ እየገነነ መጥቶ በዓፄ ምኒልክ ዘመን የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ሲቋቋም፣ የግምጃ ቤቱ ኃላፊ ሆነው የኢትዮጵያን ጦር መሣሪያ በዓይነት በዓይነት ማስቀመጥ መጀመራቸው ይነገራል።
እነሆ የጀግና ምሳሌ ሆነው ከሆስፒታል እስከ ትምህርት ቤት ተሰይሞላቸው በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ::
ፊት አውራሪ ገበየሁ
ያ ጎራው ገበየሁ
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው
ለምሳም ሳይደርሱ ቁርስ አደረጋቸው!
በፈረስ ስማቸው ጎራው በመባል ይታወቃሉ፣ ከዓድዋ በፊት ከኢጣሊያ ጋር በተደረጉ የአምባላጌ እና የመቀሌ ጦርነት ላይ በጀግንነት የተዋጉ የጦር መሪም ናቸው ፊታውራሪ ገበየሁ!
በአምባላጌው ጦርነት ድሉ የኢትዮጵያ ቢሆንም ፊታውራሪ ገበየሁ ግን ገና ያልታዘዘ ጦርነት ነው ያስጀመርከው ተብለው እንዲታሰሩ ተወሰነባቸው። ፊት አውራሪ ገበየሁም “ጀግና የጦር መሪ የምኒልክ አብሮ አደግ ነኝ እንዴት ይሆናል” ሳይሉ ፍርዱን ተቀብለው በሠንሠለት ታሰሩ። በኋላ ላይም በመቀሌው ጦርነት ወቅት ተፈትተው በጀግንነት ተሳተፉ።
በዓድዋ ላይ በአምባ ኪዳነምሕረት በኩል የኢጣሊያ ጦር ጥቃት በጨመረ ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማፈገፈግ ሲጀምር ፊታውራሪ ገበየሁ “እንዴት ትሸሻላችሁ እንዴት እንደምሞት ሂዱና ለንጉሥ ተናገሩ” ብለው መድፍና ጥይት በሚዘንብበት መሐል ተወርውረው ገቡ። ሲያፈገፍግ የነበረው ሌላው ሠራዊትም እርሳቸውን እያየ ተከትሏቸው ወደ ጦሩ ገባ፤ ጎራው ገበየሁ ግን በመትረየስ ተመትተው ወደቁ ሕይወታቸውም በዚያው አለፈ። ከሰባት ዓመት በኋላም በቃላቸው መሠረት አፅማቸው በትውልድ መንደራቸው አንጎለላ እንዲያርፍ ተደረገ።
ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ (አባ ጎራው) ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ አንጎለላ እንደተወለዱ ታሪካቸው ያሳያል:: ከዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጋር አንድ ቀን መወለዳቸው የታሪክ አጋጣሚ አድርጎታል::
በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ፊታውራሪ ገበየሁ ፊት ለፊት የገጠሙት በእንዳ ኪዳነ ምሕረት በኩል የመጣውን እና በጄኔራል አልበርቶኒ የሚመራውን የጠላት ጦር ነበር:: በጦርነቱ ፊታውራሪ ገበየሁ ከሠራዊቶቻቸው በመለየት ጎራዴያቸውን መዘው በዋናው የትግል አውድማ፣ በተፋፋመ እና በቀለጠው ውጊያ ላይ ተወርውረው ገቡ:: ዘለው እንደገቡም ከጀግናው ጓደኛቸው ከቀኝ አዝማች ታፈሰ ጋር እየፎከሩ የጠላትን አንገት በጎራዴ ሲቆርጡ እና ሲጥሉ ቆይተው ከርቀት በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ::
በተክለጻዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ይገለጻል:: ‹‹ጦርነቱም እጅግ በበረታ ጊዜ የኢትዮጵያ ጦረኞች ወደኋላ እንደማፈግፈግ ሲል፤ ቀይ የክብር ልብስ የለበሰው ፊታውራሪ ገበየሁ “ወደ ሸዋ በሕይወት የተመለሰ አሟሟቴን ይናገር” ብሎ ዘሎ ወደ ተፋፋመው ውጊያ ገባ በዚያም እየተዋጋ ሳለ ተመትቶ ወደቀ የጣሊያንም ወታደሮች አብረው ወድቀው ሬሳውን አከበሩት ድሉም ለኢትዮጵያ ሆነ።” እሱን ሲያይ ሁሉም እየሮጠ ተከታትሎ ገብቶ ከመድፈኞቹ ጋር ተጨፋጭፎና ገድሎ መድፈኞችን ማረከ:: የገበየሁ ሬሳ ከወደቀበት ቦታ የእኛዎቹ ጀግኖች አብረው በመውደቅ የእርሱን ሬሳ አከበሩት”
ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ ዓድዋ ሲዘምቱ ተናዘውም ነበር:: “ስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፣ ከሸሸሁ እኔ እንደ አባቶቼ አይደለሁምና ወግ አይገባኝም፤ ከፊት ለፊት ስፋለም ከወደቅሁ ግን እሬሳዬን ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝ” አሉ:: እንደተባለውም ሆነ፤ አፅማቸው በአንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ይገኛል!
ራስ መንገሻ ዮሐንስ
ራስ መንገሻ ዮሐንስ የተወለዱት በ1857 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ ሲሆን የትግራይ አስተዳዳሪ ነበሩ። የንጉሠ ነገሥት ዓፄ ዮሐንስ አራተኛ ልጅ ሲሆኑ፤ እናታቸው ወለተ ተክለ ሃይማኖት ይባላሉ። ራስ አርዓያ ኃይለሥላሴ ዮሐንስ የሚባሉ ታናሽ ወንድም አላቸው::
ራስ መንገሻ ዮሐንስ በዓድዋ ጦርነት የጣሊያንን ወረራ ከቀለበሱ አመራሮች አንዱ ናቸው።
ራስ መንገሻ ዮሐንስ የአጼ ዮሐንስ ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ራስ አሉላ ጠንካራ የወታደራዊ እና የፖለቲካ ድጋፍ ነበራቸው። በተጨማሪም ራስ መንገሻ ዮሐንስ የዓፄ የሐንስ 4ኛ ወራሽ በመሆናቸው የጦር መሣሪያዎች እና ወታደሮች አቅም ጨምሮላቸዋል።
ዓፄ ዮሐንስ አራተኛ እንደሞቱ እና ዓፄ ምኒልክ የንጉሠ ነገሥትነቱን ቦታ እንደያዙ ራስ መንገሻ የትግራይ አገረ ገዥነት ተሰጣቸው:: ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከዓፄ ምኒልክ ጋር የተወሰነ ቁርሾ ነበራቸው። ፋሽስት ጣሊያን ሁለቱ ያላቸውን ልዩነት ለመጠቀም ብዙ ሞክራለች።
የዓድዋ ጦርነት ሲከሰት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከዓፄ ምኒልክ ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው በሀገራቸው የመጣውን ጠላት በጋራ ለመመከት ተንቀሳቀሱ። ራስ መንገሻ በዓድዋ ዘመቻ ያሰለፉት የሠራዊት ብዛት 12000 እንደነበር ሰነዶች ያሳያሉ::
ከዓድዋ ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ ጣሊያኖች በስተጀርባ ሆነው በንጉሠ ነገሥቱ ላይ እንዲያምፁ ይገፏፏቸው ነበር:: ምፅዋ ላይ የነበሩት ጣሊያኖች ራስ መንገሻን እንዲያምፁ የሚያደርጉት የሥልጣንን ጉዳይ እያነሱ ነበር:: ራስ መንገሻ የጣሊያን ውትወታ አሸንፏቸው በአፄ ምኒልክ ላይ ሸፈቱ::
ዓፄ ምኒልክም ከራስ መኮንን ጋር ከራስ (በኋላ ንጉሥ) ሚካኤልን፣ ዋግሹም ጓንጉልን እና ደጃዝማች (በኋላ ራስ) አባተን አጋዥ አድርገው “አውቆ እጁን ቢሰጥ ይዛችሁት፤ እምቢ ካለ ውጉት” ብለው ወደ ትግራይ ላኳቸው:: እቴጌ ጣይቱም ደብዳቤ ፅፈው ላኩለት::
ደብዳቤው ቢደርሳቸውም ራስ መንገሻ በሰላም ሊመለሱ ባለመፍቀዳቸው በልዑል ራስ መኮንን የሚመራው ጦር ወደ እደጋ ሐሙስ በመሄድ ከበባ አደረገ::
ጦርነቱ ከመደረጉ በፊትም ራስ መኮንን እና የአባታቸው የዓፄ ዮሐንስ የክርስትና ልጅ ከሆኑት ከዚያን ጊዜው ራስ ሚካኤል በሰላም እንዲገቡ በሚል የምክር ቃል ተላከባቸው::
ለውጊያ መዘጋጀታቸው ስለተሰማ ይገኙበት ከነበረው ሥፍራ በስተጀርባ በአጋሜ በኩል አራት ሺህ ባለጠመንጃ ጦር ዘልቆ ሄዶ ጦርነት ገጠማቸው:: የራስ መንገሻም ጦርም ክፉኛ በመጎዳቱ እጃቸውን ሰጡ:: ራስ መንገሻም በአንኮበር አምባ ታስረው ተቀመጡ::
ራስ መንገሻ በትዳር ሕይወታቸው የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅ ከሆኑት ከጎንደሯ እመቤት ከወይዘሮ ከፋይ ወሌ ብጡል ጋር ተጋብተው ወይዘሮ አስቴር መንገሻን፣ ወይዘሮ አልማዝ መንገሻን እና ወይዘሮ ብርሃኔ መንገሻን ወልደዋል::
መለኛው ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ
ሀብተጊዮርጊስ በምዕራብ ሸዋ በጨቦ እና ጉራጌ አውራጃ 1844 ዓ.ም ተወለዱ:: ከልጅነታቸው ጀምሮ በሳል እና ቀልጣፋ ነበሩ:: ከ18 ዓመታቸው ጀምሮ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ገብተው በርካታ ኃላፊነቶችን ሲወጡ ቆይተዋል:: ሚያዚያ 30 ቀን 1874 ዓ.ም በተካሄደው የእምባቦ ጦርነት ሀብተጊዮርጊስ ከፍተኛ ድርሻን በመያዝ ጀግንነታቸውን አሳይተዋል:: ለችግር መውጫ መላ የማያጡት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ በንጉሡ ‹‹አባ መላ›› የሚል ቅፅል ስም ወጥቶላቸዋል:: በፈረሳቸው በአባ መቻል መጠሪያ ስምም ይጠሯቸዋል::
የመጀመሪያው ጦርነት ተንቤን ላይ ተካሂዶ ሳለ ሜጀር ሳልሳ የተባለ ጣልያን ዲፕሎማት ጦርነት መደረጉ ቀርቶ ከምፅዋ እስከ አላጌ ድረስ ያለው ሀገር ይሰጠን ብሎ የጣሊያን ሃሳብ ለዓፄ ምኒልክ ባቀረበ ጊዜ ነገሩን የሰሙት አብዛኞቹ የጦር አለቆቻቸው በጣሊያን ሀሳብ ሲስማሙ ንጉሡ በመለኝነታቸው የሚተማመኑባቸው ፊታውራሪ ጉዳዩ ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ ወደሳቸው ላኩ:: ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስም እቴጌ ጣይቱ ጋር በመምከር የጠላትን የአመጣጥ ሁኔታና ሀሳብ አውቀውት ነበርና ‹‹የመጣነው ለጦርነት ነው ጠላት ሀገራችንን መያዙ ሲያሳዝነን እንደገና ልጨምር ሲል መፍቀድ ሀገሪቱን በሙሉ ጠቅልሎ ለመውሰድ እንጂ በዚህ ክልል የጣሊያን መንግሥት በቃኝ ይላል ማለት ዘበት ነው:: ይልቁንም ወታደራችን በቻለው አቅም ይግጠመው እና እግዚአብሔር የሚሰጠንን ዕድል ብናይ ይሻላል›› በማለት ልቡ ወደ ጣሊያን መንግሥት ሃሳብ ያደላውን የጦር አለቆች ሃሳብ በማስቀየር ወደ አንድ ዓላማ መርተዋል::
120 ሺህ አርሶ አደር በአንድነት የተሰለፈበት የዓድዋ ጦርነት ሲታወጅ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ አንድ መቶ ሀምሳ አጋሰስ የተጫነ ማር እንዲሁም በጊዜው ከሚያስተዳድሩት የጨቦ ግዛት በ600 አጋሰስ የተጫነ ስንቅ ይዘው ከተወሰኑ ጦራቸው ጋር ሊዘምቱ ድንኳናቸውን ተከሉ:: ታዲያ ንጉሡ የስንቁን መሰናዶ፣ የወታደራቸውን ዝግጅት፣ የፈጠሩትን መነቃቃት ባዩ ጊዜ ‹‹ሀብተጊዮርጊስ ማለት ሰው ነው›› ብለው ከልባቸው አድንቀዋቸዋል::
የመጀመሪያው የጦር ሚኒስትር ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ የጣሊያን ወራሪው ጦር ሀገርን ለመውረር በቃጣው በዚያ ወቅት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክን እና እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የጦሩ ፊታውራሪ እና አዝማች ከነበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ(አባ ጎራው) ጋር እንዲሁም ዋና ዋና የጦር መሪዎች ጋር ግንባር ላይ በመሆን 3 ሺህ የሚሆን ጦራቸውን ይዘው ደማቅ ታሪክ ፅፈዋል::
ፊታውራሪ ገበየሁ በዓድዋ ጦርነት ላይ በተሰው ጊዜ ከድል መልስ ንጉሡ በእሳቸው ምትክ የትኛውን ጀግና ይሾሙ ይሆን ተብሎ በርካታ ለቦታው የሚመጥኑ የጦር አለቆች ሲጠበቁ ዓፄ ምኒልክ ከእነማዕረጉ የፊታውራሪ ገበየሁን ቦታ ለፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ሰጥተው የጦር አለቅነትን ሾሟቸው::
አባ መላ ዘመናቸውን እንደፊታውራሪ፣ እንደ ጦር ሚኒስቴር እንዲሁም በወቅቱ ስያሜው ባይኖርም እንደጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነው በርካታ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል:: ከንጉሡ ጋር በመጣመር በርካታ ግዛቶችን ወደ አንድነት ለማምጣት የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ጦር ከራስ ጎበና ዳጬ፣ ከወሎ ራስ ሚካኤል አሊ እና ከባልቻ አባ ነፍሶ ጦር ጋር በአንድነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል::
በጥበባዊ የዲፕሎማሲ እና የፍርድ አሰጣጣቸው የሚታወቁት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ የጨቦን አካባቢ ጨምሮ ሞያሌን፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ከደቡብ ምዕራብ እስከ ኬንያ ያስተዳድሩ ነበር:: ከተሰጧቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው ቦረና ላይ እንግሊዞች ያለፈቃድ ወደ ግዛታቸው በኬንያ በኩል ገብተው ስለተገኙ ተገድለው ነበር፤ አዲስ አበባ ተቀማጭ የሆነው የእንግሊዝ መንግሥት ቆንሲል ያለአግባብ ዜጎቼ ተገድለውብኛል ሲል አቤቱታውን ለዓፄ ምኒልክ አመለከተ:: ንጉሡም መክረን እንነግርሃለን ካሉት በኋላ የእንግሊዙን ቆንሲል ወደ አባ መላ እንዲሄድ አደረጉ::
የእንግሊዙ ቆንሲል ወደ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ቤት ሄዶ ሰዎቻችን ያለአግባብ ተገድለውብናል ደማቸው የፈሰሰበት መሬት ይሰጠን ባሉ ጊዜ ፊታውራሪ በሀገራችሁ ይህን መሳይ ደንብ አለ እንዴ ሲሉ ጠየቁ:: ‹‹አዎን!›› ሲሏቸው፤ ደግ እንግዲያውስ እኛም የዓፄ ቴዎድሮስ ልጅ ዓለማየሁ ከዚህ ሄዶ በሀገራችሁ ተገድሎብናልና ለእኛም ሎንዶንን ስጡን ለእናንተም ይህን ውሰዱ ብለው ቃል አርቅቀው ፈረሙና በል ፈርም ብለው አማራጭ አሳጥተው ልከውታል::
የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ተደማጭነት እና ክብር በዓፄ ምኒልክ ጊዜ ብቻ ያበቃም አልነበረም:: አልጋ ወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ ሹመት ሽረት ሲያደርጉ ሥልጣንን ካለአግባብበ መጠቀም እና መሰል ችግር ፈጥረዋል የተባሉትን የዓፄ ሚኒሊክ የጦር ሚኒስትሮች ከሥልጣን ሲያስነሱ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስን ደፍሮ የሚነካ አልነበረም::
አባ መላ ዘመናቸውን በጀግንነት ኖረው በደረሰባቸው ሕመም ሳቢያ ታኅሣሥ 3 ቀን 1919 ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ::
ራስ አባተ ቧያለው
በዓድዋ ጦርነት ጎልተው ከታዩት አብሪ ኮከቦች መካከል ራስ አባተ ቧ ያለው አንዱ ናቸው። በ1865 ዓ.ም በመንዝና ግሼ የተወለዱት ራስ አባተ በፈረስ ስማቸው ‹‹አባ ይትረፍ›› ይባላሉ። መድፍን እንደ በትር በእጃቸው መዳፍ እንዳሻቸው የሚያገላብጡ ናቸው ይባልላቸዋል::
የዓድዋ ጦርነትና ድል ሲነሳ አብሮ የሚነሳና የኢትዮጵያውያን የጀግንነትና የብልሃት ማሳያ የሆነው የመቀሌው ምሽግ ውጊያ ነበር። ጣሊያኖች የመረብ ወንዝን ተሻግረው ወደ ትግራይ ሲገቡ ጠንካራ ምሽግ ከሠሩባቸው ቦታዎች አንዱ መቀሌ እንዳ ኢየሱስ ነበር። ምሽጉን ማጆር ቶዞሊ አስጀምሮት እርሱ በአላጌው ውጊያ ሲሞት ማጆር ጋልያኖ አጠናቅቆታል። ለመቀሌው ምሽግ መጠናከር ዋናው ምክንያት ጣሊያኖች አላጌ ላይ በራስ መኮንን በሚመራው የኢትዮጵያ ጦር የገጠማቸው ሽንፈት ነው። ጄኔራል አርሞንዲ ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም የደረሰበትን የአላጌን ግንባር ሽንፈት ተከትሎ ወደ ኋላ በሸሸው የጣሊያን ሠራዊት አማካኝነት ከባሕር ወለል በላይ በ2 ሺህ 240 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ የበለጠ እንዲጠናከር አደረገ። በቦታው የሚገኘውን የኢየሱስን ታቦት አስወጥቶ ቦታውን ሙሉ በሙሉ ምሽግ አደረገው።
ዓፄ ምኒልክ ጦራቸው መቀሌ ደርሶ ሰፈሩን ተከፋፍሎ ከያዘ በኋላ በጣሊያን ምሽግ ዙሪያ ራቅ እያለ ሰፈረ። ድንኳን በሚተከልበት እና ጭነት በሚራገፍበት ጊዜ አንድ በቅሎ ደንብሮ ወደ ጣሊያኖች ምሽግ ሮጠ። ጣሊያኖችም አንድ ሰው ሊመልሰው ሲሮጥ ባዩ ጊዜ ተኩስ ጀመሩ። ንጉሠ ነገሥቱ ጣሊያኖቹ አብዝተው መተኮሳቸውን በተመለከቱ ጊዜ ራስ አባተ ቧ ያለውን እና ደጃዝማች ባልቻ ሳፎን ሂዱ እናንተም ተኩሱባቸው ብለው አዝዘው የምሽቱ ጊዜ በመድፍ ተኩስ አለፈ።
ወደ ማታ ንጉሡ እንደገና ራስ አባተን እና ደጃዝማች ባልቻን ጠርተው “እነዚህን ጣሊያኖች ከጉድጓዳቸው ሳላስወጣ የትም አልሄድም፤ እናንተም የጠላት መድፍ ጥይት የማይደርስበትን ስፍራ መርጣችሁ ያዙና ምሽጉን በመድፍ ምቱት” ብለው አዘዟቸው።
ራስ አባተ ጦራቸውን ይዘው በምሽጉ በስተግራ የጣሊያኖችን ቃፊር (ጠባቂ) አባርረው፣ ምሽግ አበጅተው፣ መድፍና መትረየሳቸውን እንዳጠመዱ ደጃዝማች ባልቻም በስተቀኝ በኩል ሌሊቱን ምሽግ ሠርተው መድፍ እና መትረየሳቸውን ጠመዱ። ጣሊያኖችም የእነሱን መጠጋት ባወቁ ጊዜ የመድፍ እና የጠመንጃ ተኩስ አበዙ። አነጣጥሮ በመተኮስ የተመሰገኑት ራስ አባተም በሩቅ ማሳያ መነጽራቸው ተመልክተው አነጣጥረው ሲተኩሱ የመድፉ ጥይት የጠላትን መድፍ እግር ሰባበረው። ጣሊያኖችም ከተበላሸው መድፋቸው ጭስ ሲወጣ ባዩ ጊዜ በአፀፋው የመድፍ ጥይት ራስ አባተን እና ደጃዝማች ባልቻ ባሉበት ቦታ ላይ እሩምታ አወረዱባቸው። ነገር ግን አንድም ሰው አልቆሰለም። ይህን ውጊያም ዓፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት እና ሌሎችም መኳንንቶች ከፍተኛ ስፍራ ላይ ሆነው በመነጽር ሲመለከቱ ነበር።
እቴጌ ጣይቱም ሁኔታውን ሲመለከቱ ስለነበር በአቅራቢያቸው ወደ ነበሩት አዛዥ ዘአማኑኤል ፊታቸውን አዙረው፥ “ሂድ እና ከራስ አባተ ጋር እየተመካከርክ የውኃውን ምንጭ ለመያዝ ትችል እንደሆነ ሞክር” በማለት አዘዟቸው። እሳቸውም ወዲያው በመሄድ እንደታዘዙት ራስ አባተ ጋር ሲነጋገሩ ሊቀ መኳስ አባተ “የምንጩ ስፍራ ጥልቅ እና ወደ ጠላት ምሽግ የቀረበ ነው፤ በምንጩ እና በጠላት ምሽግ መካከል አንድ መቶ ሃምሳ ክንድ የሚሆን ርቀት አለ፤ ቢሆንም ግን መተላለፊያውን በመድፍ ሳስጠብቅ እቆይና ከዚያ በሌሊት ወታደር ልኬ ምንጩን አስይዛለሁ” ብለው መለሱላቸው።
አዛዥ ዘአማኑኤልም ራስ አባተ ያሉትን ለእቴጌ ጣይቱ ሲነግሯቸው በጣም ደስ ስላላቸው፥ “ጠላት ውኃ እንዳይቀዳ ምንጩን ጠብቁ፤ እናንተም እስካሁን ምሽግ ገብተን እንዋጋለን የምትሉት የሜዳን ጦርነት እንደማትፈሩ ተስፋ አለኝ፤ በዚህ ጦርነት ተዋግተው ለተረፉት ደስ የሚያሰኝ የክብር ሽልማት እሰጣቸዋለሁ፤ ለሞቱትም ተዝካራቸውን አወጣለሁ፤ ልጆቻቸውንም አሳድጋለሁ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን” ብለው ወደ እነ ራስ አባተ ላኳቸው።
ኢትዮጵያውያኑ የጦር መሣሪያቸውን በደንብ አዘጋጅተው፣ ወደ ምንጩ ተጉዘው ተቆጣጠሩት። ጣሊያኖቹ ምንጩ ወደ እነሱ ምሽግ በመቅረቡ ይያዛል ብለው አላሰቡም ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታው በገባቸው ጊዜ ምንጩን በሚጠብቁት ኢትዮጵያውያን ላይ ድንገት ተኩስ ከፈቱባቸው፤ ጠባቂዎቹም ጠንክረው በመዋጋታቸው ጣሊያኖቹ ወደመጡበት መመለስ ግድ ሆነባቸው።
በማግስቱ ራስ አባተ ከደጃዝማች ባልቻ ጋር ተስማምተው ጣሊያኖቹ ያሉበትን እና መድፋቸውን የጠመዱበትን ቦታ በመነጽር ተመልክተው በመድፍ መቱት። ጣሊያኖቹም ዕቃቸውን መድፍ ወደማይደርስበት አዛወሩ። ሊቀ መኳስ አባተ እና በጅሮንድ ባልቻ በምሽግ ያሉትን በጥብቅ እየጠበቁ ወዲያና ወዲህ እየተዘዋወሩ በመድፍ እና በመትረየስ እየመቱ ጠላት ምሽጉን እስኪለቅ ድረስ ለአሥር ቀን ድረስ ሳይተኙ እና ከመሣሪያቸው ሳይለዩ ሰነበቱ።
እቴጌ ጣይቱም በየቀኑ ከሌሊቱ ከዘጠኝ እስከ አሥር ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውኃውን ለሚጠብቁ ወታደሮች መጠጥ የያዘ እንሥራ እና በመሶብ እንጀራ ሥጋ እየጨመሩ ይልኩ ነበር። በሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለው እና በበጅሮንድ (በኋላ ደጅአዝማች) ባልቻ አባ ሳፎ የሚመሩት የጦር ወታደሮችም እየበሉ፣ እየጠጡ ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ለመሰዋት ሲሉ አንድ ቀንም መሣሪያቸውን ትተው ሳይተኙ ጠላት ውኃ እንዳይወስድ አድርገው ቆይተው በመጨረሻ ምሽጉን እንዳስለቀቁ ተክለጻዲቅ መኩሪያ ጽፈዋል።
ወንጌል ተምሯል ወይ ያባተ ፈረስ
ይትረፍ ለነገ አይል ምንም ቢደገስ
አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ ሰው
ይህን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው
አበሻ ጉድ አለ ጣሊያን ወተወተ
አይነ ጥሩው ተኳሽ ቧ ያለው አባተ!
ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም
ስማቸው ብዙም ጎልቶ ከማይታወቅ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል አንዱ የሆኑት ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም፤ በፈረስ ስማቸው አባ ገድብ ይባላሉ:: በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅና በነገሥታቱም የተከበሩ ናቸው:: አርበኛ፣ የአስተዳደር ጥበብ አዋቂ፣ የንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ነበሩ::
ስለ ትውልድ ዘመናቸው ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መረጃ ባይኖርም በጎጃም ደጋ ዳሞት መወለዳቸውን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ::
ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም በወጣትነት ዘመናቸው ለውትድርና ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው አባታቸው ወደ ጎንደር ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ቴዎድሮስ ጋር ላኳቸው:: በወቅቱ ወጣቱ ምኒልክም ከሸዋ መጥተው አጼ ቴዎድሮስ ጋር ስለነበሩ አንድ ላይ አደጉ፤ የውትድርና ሙያንም አብረው ተማሩ:: በመቅደላ መድኃኒዓለም አምባ የአብነት ትምህርትን አብረው በመማራቸው ሳቢያ ወዳጅነታቸውና መተማመናቸው እጅጉን የጠነከረ ነበር::
የአጼ ምኒልክ ስም ሲነሳ የራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ስም ሳይነሳ አይቀርም:: ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ንግሥናቸውን ሲይዙ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ሀገርን የማቅናት ሥራ ላይ በጦርነቱም በምክሩም ከጎናቸው አልተለዩም::
ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም የመተማ ጦርነትን ጨምሮ የሀገሪቱን ሉዓላዊ ድንበር ለማስጠበቅ በተደረጉት ጥረቶች ሁሉ ዐሻራቸው ጎልቶ ይታያል:: ራስ ቢትወደድ መንገሻ በ1858 ዓ.ም የፊታውራሪነት፤ በ1881 የጃዝማችነት፤ በ1887 ዓ.ም ደግሞ የቢትወደድነት ማዕረግ ያገኙ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ የራስነት ማዕረግ ተሰጣቸው::
ቢትወደድ ማለት በልዩ ሁኔታ የተወደደ፤ ብቸኛ ወዳጅ ማለት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ ራስ እና ቢትወደድነት የሚባሉት ማዕረጎች በአንድ ላይ የተሰጣቸው ግለሰብ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ናቸው:: በንጉሠ ነገሥት ዓፄ ምኒሊክ ተወዳጅ መሆናቸው ማዕረጉን የማግኘታቸው ምክንያት መሆኑ ይነገራል::
አፄ ምኒልክ የራስ ቢትወደድነትን ማዕረግ ከሰጧቸው ከአንድ ዓመት በኋላ የዓድዋው ጦርነት ተጀመረ:: ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከምም “የዳሞት እና የአገው ምድር ጦር” በሌላኛው መጠሪያው “የገበሬ ሠራዊት”ን እየመሩ የጠላት ሠራዊትን ሽንፈት አከናንቦ ወደመጣበት ለመመለስ ወደ ዓድዋ ዘመቱ::
ጦራቸውን አሰባስበው ከአምባላጌ እስከ ዓድዋ ሶሎዳ ተራራ ያዋጉት ራስ ቢትወደድ መንገሻ 6 ሺህ ሠራዊት የያዘው ጦራቸው ከራስ መኮንን እና ከዋግ ሹም ጓንጉል ጦር መካከል ሆኖ ለጠላት ሠራዊት ጀግንነቱን አሳይቷል::
ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም በሙሉ እንደራሴነት፣ በአፄ ምኒልክ ዋና አማካሪነትና ባለሟልነት ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተው በ1903 ባደረባቸው ድንገተኛ ሕመም ሕይወታቸው አለፈ::
ከጣሊያን የአምስት ዓመታት የወረራ ሙከራ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በጐጃም ትምህርት ቤቶችን ሲያስገነቡ፤ አንደኛው በ1935 ዓ.ም በምዕራብ ጐጃም ዞን ቡሬ ከተማ የተገነባው በራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም የተሰየመው ትምህርት ቤት ታሪካቸውን ያስታውሳል::
አፈ ንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ
አፈ ንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ (አፈ ንጉሥ ነሲቡ አባተ ምትኩ ቦርጃ) በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እጅግ የታፈሩና የተከበሩ ዳኛ ነበሩ:: በአፈ ንጉሥነትም ሥልጣን ከ1874 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1900 ዓ.ም ድረስ 26 ዓመት የቆዩ ናቸው:: በፍርዳቸው ጨካኝና ጠንካራ ስለሆኑ ማንም ሰው በተከሰሰ ጊዜ “እባክህ በነሲቡ ፊት አታቁመኝ” እያለ ከባላጋራው ጋር ይታረቅ ነበር ይባላል::
አፈ ንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ የዓድዋ የጦር መሪ የነበሩ ቢሆንም በአብዛኛው ተጽፎ የሚገኘው ታሪካቸው ግን ሌብነትን በተመለከቱ ጉዳዮች ነው::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም