
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች፣ ትውልድን በማፍራትና ኮትኩቶ በሥነ ምግባር በማሳደግ ረገድ ልዩ ፀጋ የተጎናጸፉ ናቸው:: ከዚህ ባሻገርም ኢትዮጵያውያን ሴቶች ርህሩሆች፣ መለኞች፣ ክንደ ብርቱዎችም ናቸው:: ቀደም ባለው ዘመን የነበሩትም ሆነ አሁን ያሉት ሴቶች የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር አለ:: ከዚህም አንዱ ሰላም ወዳድ መሆናቸው ነው:: የሚያጋጥሟቸውን ማናቸውንም ችግሮች ከፀብ ይልቅ ዲፕሎማሲያዊውን መንገድ ተከትሎ መፍታትን በብርቱ ይሻሉ::
ችግሩ በሰላማዊ መንገድ የማይፈታ ከሆነ እና ወደኃይል አቅጣጫ የሚያመዝን ከሆነ ጥቃትን መቀበል ፈጽሞ አይሹም፤ ስለዚህም ሽንፈትን ባለመቀበል ለሀገራቸው ለሚከፈለው መስዋዕትነት ዝግጁ ይሆናሉ:: በዚህ ረገድ ልበ ሙሉና ቁርጠኞችም ናቸው:: የዛሬ 129 ዓመት ሴቶች እምቢኝ ለሀገሬ በማለት በነቂስ ወጥተው ወደ ዓድዋው ጦርነት በመዝመት ከራሳቸው አልፎ ተርፎ የጦር መሪውን እና ሠራዊቱን በተለያየ ቀረርቶ፣ ፉከራና ሽለላ ሲያጀግኑትም እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው::
ውጊያ መሐል ገብተውም ለሀገራቸው መስዋዕትነት መክፈላቸው የሚታወቅ ነው:: ጎራዴ ታጥቀውና ሳንጃ መዘው በርካታ ግዳይ ይጥሉ የነበሩ ጀግኖች አርበኞች ሴቶች እንደነበሩ የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በተሰኘውና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፉ ላይ ለታሪክ ተሰንዶ ተቀምጧል::
ስንቅ በማዘጋጀት፣ በማቀበል፣ ባህላዊ መድሃኒት ቀምሞ በማዘጋጀት፣ ቁስለኛ በማከም፣ በቃሬዛ በማንሳትና በሌሎች ሌሎች ተግባራትም በዓድዋ ጦርነት በትንሹ 30 ሺህ ሴቶች መሳተፋቸውንም የታሪክ ተመራማሪው ይጠቅሳሉ:: ከዚህ ውስጥ በቀጥታ ውጊያ የተሳተፉ በርካታ እንደነበሩም ይጠቀሳል:: ከዚህ በተጨማሪ የንጉሡ ዓፄ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ የራሳቸውን ጦር ይዘው ዘምተው የነበሩ መሆናቸውንም ይጠቁማል:: በእቴጌይቱ ስር ባለውና ይዘው በዘመቱት ጦር ሥር ብቻ አምስት ሺ በቀጥታ ውጊያ የተሳተፉ ሴቶች ነበሩም ይላል:: እቴጌይቱ በውጊያው መሐል ገብተው በመዋጋት ጭምር ያደረጉትን ተጋድሎም በታሪክ መጽሐፉ ተብራርቷል::
በዓድዋ ጦርነት እቴጌ ጣይቱ በተለይ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያንና መላ አውሮፓን ለአስደመመው አስደናቂ ድል ያበቃ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ ያመላክታል:: የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው::
የእንግሊዝ ጋዜጦች በድሉ ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ፤ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪቃ ተቀሰቀሰ፤ ብለው እስኪጽፉና እስኪ መሰክሩ ድረስ የደረሰና በዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጥ ያመጣ ነው ሲሉም ገልጸዋል:: በዚህ ረገድ በመጣው ውጤት እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ በዘመኑ የነበሩ ሴት የነፃነት ታጋዮች የተጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደነበርም አውስቷል::
“እቴጌ ጣይቱ ውበት የተርከፈከፈባቸው እጅግ ቆንጆ ሴት ብቻ ሳይሆኑ፤ በጣም አዋቂና መለኛም ሴት ነበሩ::” የሚለው የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ፣ ከዓድዋ ጦርነት በፊት ባሉት ጥቂት ወራትና ሣምንታት መቀሌና አምባላጌ ላይ የተደረጉ ጦርነቶች ላይ በተለይም በመቀሌ ከውሃ ጋር ተያይዞ ስለፈፀሙትና ለዋናው ዓድዋ ድል ስላበቃው ሥልጡን ወታደራዊ መለኛ ገድል በስፋት ይተርካል::
“መቀሌ በጣይቱ ልዩ ወታደራዊ ብቃት ከጣሊያኖች መዳፍ ተላቃ በኢትዮጵያውያኑ ጀግኖች ተያዘች::” በዚህ በመለኛይቱ ንግሥት ምክንያትም የዲፕሎማሲያዊ ድሉን የተቀዳጀችው ኢትዮጵያም በኢጣሊያዊው ኮሎኔል ጋሊያኖ የሚመራውን የአውሮፓዊ ሠራዊት ለማስለቀቅ በቃችም ይላል::
እቴጌይቱ ከድል በኋላም ቢሆን በዓለም ሕዝብ ዘንድ ኢትዮጵያን ተወቃሽ ከሚያደርገው ኢ-ሰብዓዊ የምርኮኞች አያያዝ የትኛውም የጦር መሪና ሠራዊትም ሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲታቀብ “አስቀድመው ያልሠለጠኑ በመሆናቸው ጨካኞች ናቸው መሰኘት የለብንም” የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል:: የጣሊያን ምርኮኞች በሙሉ በምቾትና በክብር እንዲያዙ አድርገዋል::
ይሄ እቴጌይቱን ርህራሄና ትሕትና የነበራቸው ሴት መሆናቸውን ከማሳየት ባሻገር ቀደም ያለ ዲፕሎማሲያዊ እውቀትና ብስለት የነበራቸው ብቁ ሴት መሆናቸውንም ያመለክታል:: እቴጌ ጣይቱ ከዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በስተጀርባ ሆነው ከድል በፊትም ሆነ በኋላ የተለያዩ አመራሮችን ይሰጡ ነበርም ብሏል::
ከዚህ አንፃር ለድሉም ሆነ ከድሉ በኋላ ለተከናወነው ተግባር ሁለቱም የየራሳቸው ድርሻ ያላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ጣይቱ በመለኛነታቸው የላቀ አስተዋፅዖ ነበራቸው ማለት እንደሚቻልም አብራርተዋል:: ከድል በኋላ ሌሊቱ እየተቃረበ ሲመጣ ሠራዊቱና አጠቃላይ በዓድዋ ጦርነት የተሳተፈው ተሰባስቦ ሳይኩራራ ለድል ላበቃው ፈጣሪ ምስጋና እንዲያቀርብ ለባለቤታቸው ለዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ሀሳብ ማቅረባቸውም በታሪክ መጽሐፉ ተጠቅሷል::
ከሰላም ግንባታ ጋር ተያይዞ መንግሥታዊ በሆነ ተቋም እየሠሩ የሚገኙት ወይዘሮ ቅድስት አሳልፍ በኢትዮጵያ በወታደራዊ መረጃ፣ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ፣ እንዲሁም በቀጥታ ሀገርን በማስተዳደር ከእቴጌ ጣይቱም በፊት በርካታ አስደናቂ ገድሎችን የፈፀሙ ብቃት ያላቸው ሴቶች መኖራቸውን ይናገራሉ:: በታሪክ መዛግብት ሰፍረው ስለመገኘታቸውም ያመለክታሉ::
ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረችውን እና በክብረ ነገሥት የተመዘገበችውንም ንግሥት አዜብ፣ ማክዳ እና ሳባ እየተባለች በተለያየ ስም የምትጠራውን እንዲሁም የምትታወቀውን የሳባ ንግሥት በቀዳሚነት ያነሳሉ::
ይህች ጥበብ ወዳድ ሴት ጠቢቡ ሰለሞንን ሳይሆን የጥበቡን ልምድ በመቅሰም ወደ ሀገሯ ልታመጣ በርካታ ሠራዊት በማስከተልና ጓዝ በመጫን እንደ ዛሬ መኪና ባልነበረበት ዘመን በበቅሎና በፈረስ በመታገዝ ወደ ኢየሩሳሌም (እሥራኤል) እስከ መጓዝ መድረሷንም በማሳያነት ያቀርባሉ:: ከሀገራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በዲፕሎማሲው መስክ ብዙ መሥራቷንም ይናገራሉ:: እንዲያውም ኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ የጀመረችው የዛሬ መቶ ዓመታት ሳይሆን ከሳባ ጀምሮ ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው ማለት እንደሚቻልም ያብራራሉ::
ወይዘሮ ቅድስት፣ ክንደ ብርቱ ሴት ብለው የጠቀሷት ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ጀግና ሴት ንግስት እሌኒ ናት:: ይህች በ15ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት በመካከለኛው ዘመን ብቅ ያለችው ንግሥት ናት ይላሉ:: ንግሥት እሌኒ ታድያ ባለቤቷ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ ከሞቱ በኋላ ሀገር አስተዳድራለች ይላሉ::
ንግሥቲቱ በዲፕሎማሲው መስክም ዛሬ ሀገራችን ላለችበት ዲፕሎማሲያዊ ደረጃ መሠረቱን የጣለ ብዙ አበርክቶ አድርጋ አልፋለች:: ኢትዮጵያ እንደዛሬዋ አሜሪካና ሌሎች ሀገራት ኃያል ከሚባለው ከፖርቹጋል መንግሥት ጋር ሃይማኖታዊ ግንኙነት እንድትመሠርት አድርጋለች:: ከሚሲዮናዊው ሃይማኖታዊ ግንኙነት አልፎም የፖርቹጋል መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት በጦር እንዲያግዝ ወደ ፖርቹጋል ለመጀመሪያ ጊዜ ልዑክ በመላክ ጉልህ ሚና ተጫውታለች::
ቀጥላ የተነሳችው ንግሥት ሰብለወንጌል አባቱን ከተካው ከአፄ ገላውድዎስ ጋር በመሆን ሠራዊቱን እንደገና በማደራጀት የግራኝ አሕመድ ጦር በክርስቲያኖች አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጋለች ይላሉ:: በጦርነቱ ግራኝ አሕመድ ከሞቱ በኋላ ባለቤቱ ባቲድል ወንበራ በሽንፈታቸው ያደራጁትን ሠራዊት እንዳይበታተንና ለእልቂት እንዳይዳረግ የሚያደርግ አስደናቂ ገድል መፈፀሟ በታሪክ ሰፍሯል::
ባቲድል ወንበራ የግራኝ ሠራዊት መሸነፉ ሲረጋገጥ በተደራጀ ሁኔታ እንዲያፈገፍግ በማድረግ ሠራዊቱን ይዛ ወደ ሐረር አቅንታለች:: የዓፄ ቴዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ተዋበችም ከባለቤታቸው በስተጀርባ ሆነው ሀገር በማስተዳደሩም ሆነ በማማከሩ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይወጡ እንደነበር ታሪክ ይመሰክርላቸዋል::
ቁጣቸውን እንዲያበርዱ፣ ትዕግስት እንዲያደርጉ ከመምከር ጀምሮ ሥራቸውን በብልሃት እንዲሠሩ ኃያልነታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል:: አፄው፣ እቴጌ ተዋበች በሞት ከተለይዋቸው በኋላ አስተዳደራቸው እየተሸረሸረ መምጣቱ እና በኋላም ኢትዮጵያን ከማዳን ባሻገር ከሽንፈት ይልቅ ራሳቸውን ለማጥፋት መገደዳቸውም የእቴጌይቱ አስተዋፅዖ ትልቅ ዋጋ የነበረው እንደሆነ ያመላክታል::
በዘመነ መሳፍንት ጎንደር ብቅ ካሉት ነገሥታት አንዷ እቴጌ ምንትዋብም ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ሀገር እንዳትበታተን ሕዝብ እንዳይተላለቅ በማድረግ ረገድ መለኛ ሚና ተጫውተዋል:: ሀገሪቱን ሁከት ከሚፈጥሩ አካላት ለመታደግ የባለቤታቸውን ሞት ደብቀው ቆይተዋል::
ከተደራጁና ቁልፍ በሚባሉ ቦታዎች ተሿሚዎቻቸውን ካስቀመጡ በኋላ ነው መሞታቸውን የገለፁት:: እንዲህም ሆኖ እነግሣለሁ፤ እነግሣለሁ በሚል ሁከት የሚፈጥሩ አካላትን በቸልታ አልተመለከቱም:: ወይኒ አምባ በተሰኘ ሥፍራ ተሰባስበው እንዲቀመጡ ነው ያደረጉት:: ሆኖም ቦታው አካላቱ አለን ለሚሉት ክብርና ዝና በሚመጥን ሁኔታ ክብካቤ እየተደረገላቸው የሚኖሩበት እንጂ እስር ቤት አለመሆኑ መልካም ስብዕና ያላቸው ትሑት እና ርህራሄ ያላቸው ሴት መሆናቸውን ያሳያል::
እንደ እናት አርበኛ ማሚቴ በላይሁን አስተያየት አሁን ላይ ከኢትዮጵያ አልፋ የአፍሪካ መዲና እየተባለች የምትጠቀሰውን አዲስ አበባን በመቆርቆርና ስያሜዋንም በመስጠት የሚታወቁትና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ብቅ ያሉት ጀግና ሴት እቴጌ ጣይቱ፣ ለዛሬው ዓድዋ ድል አድርገውት ያለፉት አስተዋፅዖ በዓለም ጭምር ጉልህ ስፍራ የተሰጠው ነው ይላሉ:: እንደ እርሳቸው አነጋገር ጣይቱ በዓድዋ ጦርነት የጀግንነት ግለቱ ሳይበርድ የሎጂስቲክ (ስንቅ፣ ትጥቅ እና መድኃኒት) እንዲደርስ በማድረጉ በኩል ሚናቸው የጎላ ነው ይላሉ:: አቅም ሳይዳከም በፍጥነት ጦር መግጠም እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ረገድ ታላቅ ሚና መጫወታቸውን ያመለክታሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ጣሊያን በወቅቱ የመሸገው እጅግ አስቸጋሪ በነበሩ የኤርትራ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ነበር:: በመሆኑም የኢትዮጵያ ሠራዊት እዚህ ድረስ ዘልቆ ጣሊያንን ጦርነት የመግጠሙ ነገር አይታሰብም:: ከወታደራዊ ሳይንስ አንፃርም ለሽንፈት የሚዳርግ በመሆኑ አይመከርም:: በመሆኑም እቴጌይቱ ጣሊያኖች ወደ ዓድዋ እንዲመጡ ማድረግ የግድ የመሆኑን ዘዴም ከዓፄ ምኒልክ ጋር በመመካከር ቀይሰዋል::
ከእምዬ ምኒልክ ጋር በመመካከር ከጦርነቱ በፊት በኢትዮጵያ በተጨባጭ ከነበረው የጦርነት ዝግጅት ውጭም፤ ስንቅ ማለቁና ተስቦ በሽታ በሠራዊቱ ውስጥ መግባቱ ብዙ ኢትዮጵያውያኑን ለሽንፈት የሚዳርግ ክፍተት ያለ የመሆኑ ጉዳይ ኮሎኒያሊስት ጣሊያን ወራሪዎች የሚሠልሉ የሀገር ተወላጅ (ፌርማቶሪዎች) ባሉበት በይፋ እንዲለፈፍም አድርገዋል::
ይሄ ዜና በፌርማቶሪዎቹ እና ከነዚሁ ጋር ያደሙ በሚመስሉ እና ባሻዬ አውዓሎም በኩል ለአውሮፓዊው ወራሪ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ እንዲደርሰው ሆነ:: ይህ የመለኛይቱ ጣይቱ በሳል ጥበብ የታከለበት መልዕክትም ጊዜው አሁን ነው በማሰኘት ጄኔራል ባራቴሪን በፍጥነት ወደ ዓድዋ ገስግሶ ኢትዮጵያውያንን ጦርነት እንዲገጥም አደረገው:: በዚሁ መላም ኢትዮጵያውያን ድል ለመቀዳጀት በቁ::
በምርምሩ መስክ ትኩረት አድርገው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየሠሩ የሚገኙት ቆንጅት ኃይሉ (ዶ/ር)፣ ይህ ቀደምት የኢትዮጵያውያን ሴቶች ጀግንነት ዛሬም በልማትና በሀገር ግንባታ መደገም አለበት ይላሉ:: በእርግጥም እየቀጠለ ስለመገኘቱ ማስረጃ ያሏቸውን ማሳያዎች ያነሳሉ::
ያኔ በጦር ግንባር በመሰለፍ ጭምር ለዓድዋ ድል ያበቁ ጀግኖች ሴቶች ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ዛሬም በልማቱም ሆነ በዲፕሎማሲው መስክ በመሳተፍ ሀገራቸው እንደ ሀገር በሉዓላዊነቷ ፀንታ እንድትቆም ያደረጉ ጀግኖች ሴቶች እንዳሉ ይናገራሉ:: በፖለቲካው መስክ አሁን ትልልቅ ሥልጣን ይዘው ከሀገር ፕሬዚዳንትነት እስከ ሚኒስትርነት ደረጃ የደረሱ ሴቶችን ማንሳት በራሱ ማሳያ ስለመሆኑም ያወሳሉ::
በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥቅምት 2018 አካባቢ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሾሙት 20 የካቢኔ አባላት መካከል 10ሩ ሴቶች መሆናቸው በራሱ ጀግኖችና ብቁ ሴቶች በዚህም ዘመን መኖራቸውን ስለመግለፁ ያነሳሉ:: በአትሌቲክሱ መስክ እነ ደራርቱ ቱሉን፣ መሠረት ደፋርን፣ ጌጤ ዋሚን፣ ጥሩነሽ ዲባባን በኢንዱስትሪው መስክ ደግሞ ቤተልሔም ጥላሁንን ይጠቅሳሉ::
አሁን አሁን በግብርናው ዘርፍም ብዙ አርሶ አደር ሴቶች እየተፈጠሩ መጥተዋልም ይላሉ:: ይህ ተሳትፎ እንደ ሀገር በየመስኩ እንዲሰፋ እና እንዲጠናከር ይሻሉ:: እንዲሁም ሴቶችም፣ የአስተዋፅዖው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከመሻታቸው በተጨማሪ አሁንም ጠንክረው መሥራት እንደሚገባቸው ይናገራሉ:: ጠቃሚ ፖሊሲዎችን በማውጣትና በተለያዩ መንገዶች ሴቶችን መደገፍና ማበረታታትም አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታሉ::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም