የውጫሌ ውል ያዋለደው የአፍሪካውያን የነፃነት ፍኖት

ጣሊያን በአፍሪካ ቀንድ የመጀመሪያ እግሯን ያስገባችው ሩባቲኖ በተባለ የእንፋሎት መርከብ ኩባንያ አማካኝነት ነው:: ሩባቲኖ በቀይ ባሕር መስመር ላይ የስዊዝ ካናል እ.አ.አ. በ1869 መከፈትን ተከትሎ አሰብ ወደብ ይመጣል:: በዚህ ወቅት በአካባቢው ከነበሩት የራህይታ የአፋር ሡልጣን እና ኩባንያው ለመርከቦቹ ነዳጅ ማደራጃ በሚል ለዚሁ አገልግሎት የሚውል መሬት በ9፣440 አሜሪካ ዶላር በሊዝ ኪራይ ይስማማሉ:: በዚህ ሁኔታ ኩባንያው በአፍሪካ ቀንድ እየቆየ ሲሄድ ቀጣናው በባሕር ንግድ መስመር የተባረከ በመሆኑ ለወደፊት መስመሩን በመቆጣጠር የባሪያ ንግድና የመሣሪያ ንግድ ዝውውርን ለማስፋፋት ሌላም ተስፋ ነበረው::

እ.አ.አ. በ1872 ጣሊያን እንደገና ሀገራዊ አንድነቷን በእነርሱ አባባል “Risorgimento” የሚሉትን ሀገራዊ ሉዓላዊነቷን አረጋገጠች:: በፈረንጅ አቆጣጠር 1884/85 የአውሮፓ ኃያላን ሀገሮች አፍሪካን ለመቀራመት ጉባኤ ተቀመጡ:: በዚህን ጊዜ ለቅርጫው ዘግይታ የተቀላቀለችው ጣሊያን በስብሰባው ላይ አንድ ጥያቄ አቀረበች እርሱም በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግዛት ውስጥ የምቆጣጠረው ቦታ ስላለኝ በቅርጫው ክፍፍል ኢትዮጵያ ትሰጠኝ የሚል ነበር:: ጉባኤተኛውም የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት አያውቁም ወይም ዘንግተውት ነበርና የጣሊያንን ጥያቄ ይሁን ብለው የጠየቀችውን ጀባ አሏት:: ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ የእንፋሎት መርከብ ኩባንያም የሊዝ ይዞታውን ለጣሊያን መንግሥት አስረከበ::

በንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ አራተኛ እና በእንግሊዛዊው አድሚራል ሕይወት መካከል የተደረገውን ስምምነት (የ1884 ዓድዋ ወይም ሕይወት ስምምነት በሚል የሚታወቀውን) ተከትሎ እንግሊዝ በሠራችው የፖለቲካ ሴራ ግብፅ ይዛ የነበረችውን የምፅዋ ወደብ ስትለቅ ጣሊያን ባልነበረ ስምምነት እንድትተካ ተደረገ:: በዚህ ሁኔታ ጣሊያን ከአሰብ ወደብ ወደ ምፅዋ በመምጣቱ የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል::

ይሁን እንጂ በትግራይ ጀግኖች ልጆች እና በእነ ራስ አሉላ አባነጋ ወታደራዊ አመራር የጣሊያን ወታደሮች ሞት እንጂ እንዳሰቡት በወቅቱ ሊስፋፉ አልቻሉም:: እንዲሁም በአሰብ በኩል ወደ መሐል ለመግባት ሲሞክሩም በአፋር ጀግኖች ድባቅ ተመተዋል:: በዚህ ሁኔታ የቆየው የጣሊያን ወራሪ ኃይል አፄ ዮሐንስ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከድርቡሾች ጋር ሲዋጉ መስዋዕት መሆናቸውን ተከትሎ ጣሊያኖች አዲስ ስትራቴጂ ወይም ስልት አሰቡ::

አዲሱ ስልታቸው በሰሜን ኢትዮጵያ የተቆጣጠሩትን ሁለቱን ወደቦች ጨምሮ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከአፄ ምኒልክ ዳግማዊ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ማድረግ ነበር:: ይህንንም ለማስፈፀም ቀደም ብሎ ከአፄው ጋር ወዳጅነት የመሠረተው ዲፕሎማት ካውንት ፔትሮ አንቶኔሊ በሀገሩ መንግሥት ተመራጭ ነበር:: አንቶኔሊ ከአፄው ከመቀራረቡ የተነሳ የቤተ መንግሥቱን ጓዳ እንደ ልቡ ይገማሸርበት ነበር:: አንዳንድ ፀሐፊዎች ከመኳንንቶቻቸውም በላይ ልዩ አማካሪያቸውም እንደነበር ይገልፃሉ::

ይህን ግንኙነት የተገነዘበው የጣሊያን መንግሥት አንድ በጣሊያንኛ ቋንቋ የተፃፈ ረቂቅ ሰነድ ለዲፕሎማቱ አንቶኔሊ ይልካል:: ዲፕሎማቱም የሰነዱን ረቂቅ ሃሳብ ወደ አማርኛ ቋንቋ ለመተርጎም የመረጠው ደጃዝማች ዮሴፍን ነበር:: እኒህ በትርጉም ሥራው እንዲሳተፉ የተደረጉት ደጃዝማች የቋንቋ ችሎታቸው አማርኛና ፈረንሳይኛ ሆኖ ሳለ የማያውቁትን ጣሊያንኛ ቋንቋ እንዴት ሊተረጉሙ ይችላሉ በማለት በአማርኛ ትርጉሙ የጣሊያኖች ሴራ እንዳለበት አንዳንድ ጥናቶች ይገልፃሉ:: በመጨረሻም የዓድዋ ጦርነትን ያዋለደው ስምምነት የውጫሌ ውል የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በጣሊያንኛና በአማርኛ ቅጅዎች ተዘጋጅቶ ሕጋዊ የሁለትዮሸ ስምምነት ሆነ::

ይህ የውጫሌ ውል ሲረቅም ሲፀድቅም የተሳተፉት አፄ ምኒልክ፡ ዲፕሎማቱ እና ደጃዝማች ዮሴፍ ብቻ መሆናቸውና ከቤተ መንግሥቱ መኳንንቶች እና ከሕዝቡ ምስጢር ተደርጎ መያዙ እንዲሁም የትርጉም ስህተት መኖሩ ውሉ አወዛጋቢ ነበር የሚሉ የታሪክ ሰዎች አሉ:: ለአብነት የውሉን ረቂቅ ለማየት ዕድል የነበራቸው የቤተመንግሥቱ ሰው አለቃ አፅመ የውሉ ረቂቅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ቀድመው በመገንዘባቸው ወደ አፄ ምኒልክ ቀርበው ውሉን እንደገና ቢያዩት በማለት ያሳስባሉ::

አፄ ምኒልክም የአማርኛውን ቅጂ ያነቡና ምንም ስህተት አላገኘሁም በማለት አለቃ አፅመ ወደ እስር ቤት እንዲወረወሩና ንብረታቸውም እንዲወረስ ያዛሉ:: አለቃም ጥቂት ጊዜ እንደቆዩ ቅጣት ተጥሎባቸው ከእስር ይፈታሉ:: ቆይቶም ቢሆን አፄ ምኒልክ የአለቃ አፅመ ስጋት ትክክል መሆኑን ሲረዱ ወደ ቀደመው ጥሪ አዋጅ ሥራቸው እንዲመለሱና ንብረታቸውም እንዲመለስላቸው ያደርጋሉ::

በመጨረሻም አወዛጋቢው የውጫሌ ውል አንቀፅ 17 የጣሊያንኛው እና የአማርኛው ሃሳብ ርስ በርሱ የሚቃረን ከመሆኑም በላይ የጣሊያንኛው ቅጅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የደፈረ በመሆኑ ንጉሠ ነገሥቱ ውሉን በይፋ በመሰረዝ ከባለቤታቸው እና ከመኳንቶቻቸው ጋር በመሆን ለማይቀረው ጦርነት መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንቀሳቀስ ጀመሩ::

በበርሊን ከተማ ጀርመን ባስተናገደችው አፍሪካን የመቀራመት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን የቅርምት ድርሻዋ አድርጋ የቀጠረችው ጣሊያን የውጫሌ ውል መሰረዙን ተከትላ ወደ መሐል የኢትዮጵያ ግዛት መገስገስ ጀመረች:: አፄ ምኒልክም የጠሩትን የክተት አዋጅ ሕዝቡ እና መሳፍንቱ በመቀበል በአፄው አገዛዝ ላይ ያለውን ቅሬታ ወደ ጎን በመተው በዘር እና በሃይማኖት ሳይከፋፈል በአንድ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ሀገሩን ከባዕድ ወረራ ለመከላከል ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ጦርነቱ በጀግንነት ተመመ::

የጣሊያን ወራሪ ኃይልና የኢትዮጵያ ጀግና የጦር ሠራዊት ከ129 ዓመት በፊት ዓድዋ ላይ ፊት ለፊት ተጋጠሙ:: በውጤቱም ኢትዮጵያውያን ወራሪውን በማሸነፍ ድል ቀናቸው:: ለዚህም ነው እኛ ኢትዮጵያኖች የካቲት 23 ቀንን በየዓመቱ የድል በዓል አድርገን የምናከብረው:: የሌላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦችም አስበውት የሚውሉት::

የዓድዋ ድል ጥቁር ሕዝቦች እንዴት ነጮችን ሊያሸንፉ ይቻላቸዋል በሚባልበት ዘመን የተፈፀመ ድል ነው:: ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓውያንን ያሸነፉበት ጦርነት በመሆኑ በጥቁር ሕዝቦች እንደተዓምር ሊታዩ ችለዋል:: አውሮፓውያኖችም ቢሆኑ እውቅና በመስጠት የአፍሪካውያን ድል ተደርጎ በዓለም ታሪክ መዝግበውታል::

የዓድዋ ድል በተለይ በቅኝ ግዛት ስር በነበሩት አፍሪካውያን ለትግሎቻቸው የሞራል ስንቅና የአሸናፊነት ስሜት እንዲኖራቸው ከኢትዮጵያ የተሰጠ በረከት አድርገው በመቁጠር ጉልበት እንደሆናቸው ዛሬም ቢሆን ይመሰክራሉ:: አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከነፃነት በኋላ ለነበራቸው የአሸናፊነት መንፈስ እንደውለታ በመቁጠር የኢትዮጵያን ሦስቱን ኅብረ-ቀለማት ሰንደቅ ዓላማ በተለያየ መንገድ የሉዓላዊነት መገለጫ ዓርማዎቻቸው አድርገዋል::

የዓድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ከአደረገው መነቃቃት በተጨማሪ ኢትዮጵያ የነፃነት ታጋዮችን በማሠልጠንና መጠለያም በመስጠት የአፍሪካውያንን የነፃነት ተጋድሎ በእጅጉ አግዛለች:: ከነፃነት በኋላም አፍሪካውያንን በአንድ ጥላ ስር እንዲሰባሰቡ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና በታላቁ የዲፕሎማት ሰው በክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ እልኸ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በ32 አፍሪካ ሀገሮች ስምምነት እ.አ.አ. ግንቦት 25 ቀን 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤቱን አዲስ አበባ በማድረግ ሊመሠረት ችሏል::

የዓድዋ ድል የፈጠረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴም ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል በማድረግም ላይ ነው:: የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዛሬም ቢሆን በአፍሪካ መሪዎች ይቀነቀናል:: አፍሪካውያን የዓድዋ ድል ዐሻራ የሆነውን የፓን አፍሪካኒዝም ርዕዮታዊ እሳቤ ወደ ተግባር ለመለወጥ ሲሞክሩ ዛሬም ቢሆን በምዕራባውያን የሚደረግባቸውን ተፅዕኖ ፈተና ሆኖባቸዋል::

ይህን ፈተና መወጣት የሚቻለው ግን የጋራ ቤታቸው የሆነውን የአፍሪካ ኅብረትን በማጠናከር ነው:: እንዲሁም ርስ በርስ በመደማመጥና በነፃነት ተጋድሎው የነበረውን የትብብርና የመተጋገዝ መንፈስ እንደገና በማምጣት እንጂ ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎች ርዳታ እና ብድር በመቀበል የእነርሱን የውክልና አጀንዳ ለማስፈፀም ርስ በርስ በመጋጨት አይደለም::

በተለይ ኢትዮጵያ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ እየተለማመደች ያለችው የአገዛዝ ፖሊሲ በማንነት ላይ ያተኮረ ነው:: በመሆኑ የዓለም ሕዝቦች በዓድዋ ጦርነት የተገኘው የድል ምስጢር አንድነታችንና ኢትዮጵያዊነት ስሜት የተገኝ አድርገው የተደመሙበትን እሴታችንን የጎዳና ሊካድ በማይቻል የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የከተተን ነው:: በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የአፍሪካ እናት የምትባል ሀገር ነበር ያደርጋታል::

እኛ ኢትዮጵያውያን ጥንታዊና ለረጅም ጊዜ ነፃነቷን ጠብቃ እንደኖረች ሀገር ጠብቀን ለትውልድ ለማሸጋገር እንድንችል ርስ በርሳችንን የሚያጋጨንን የፖለቲካ አስተሳሰብ በዓድዋ ድል ጊዜ ወደ ነበረው ስሜት ተመልሰን የጋራ ጠላታችን አድርገን መታገል ስንችል ነው::

ኢትጵያችን ክፉ አይንካት ለዘላለም ትኑር

የካቲት 19 ቀን 2017

አዲስ አበባ

በትዕግስቱ አወሉ ሐሰን

ፖለቲከኛና የምሥራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲክስ ተንታኝ

nantigi1990@gmail.com

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You