ከዋክብት አትሌቶች በዓድዋ ሰማይ ስር ይፋለማሉ

የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነው ታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ነገ በድምቀት ይከበራል። የዘንድሮውን የዓድዋ የድል በዓል ደማቅ ለማድረግም ጀግኖች አባቶች ጣሊያንን ድል በነሱበት በዓድዋ ሰማይ ስር የአትሌቲክሱ ዓለም ጀግና ከዋክብት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሊፋለሙ ቀጠሮ ይዘዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የማራቶን ዱላ ቅብብል(ሪሌ) ውድድር ለ20ኛ ጊዜ ዓድዋ ላይ ይካሄዳል። የዓድዋ ድል በዓል ከሚከበርበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ዛሬ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይም የዓለማችን ከዋክብት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለመፋለም ማረጋገጫ መስጠታቸው ታውቋል።

ውድድሩን በዓድዋ ከተማ በድምቀት ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ከቀናት በፊት መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፤ በዚህ ታላቅ ውድድር ላይ በተለያዩ የግልና ሀገራቸውን ወክለው በመሳተፍ ስኬታማ የሆኑ ትልልቅ ስምና ዝና ያተረፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደሚሳተፉ አሳውቋል።

በውድድሩ ከሚሳተፉ ከዋክብት አትሌቶች መካከል በኦሊምፒክና በዓለም ቻምፒዮናዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ የቻለው አትሌት ኃጎስ ገብረህይወት፣ አብርሃም ስሜ፣ ኃይለማርያም አማረ፣ ገመቹ ዲዳ፣ ሳሙኤል ተፈራና ሌሎችም ትልልቅ ስም ያላቸው አትሌቶች በወንዶች መካከል በሚደረገው ፉክክር ተካፋይ ናቸው።

የ2023 የለንደንና የ2024 የአምስተርዳም ማራቶን አሸናፊዋ ኮከብ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው፣ ለምለም ኃይሉ፣ አክሱማይት እምባዬ፣ እጅግአየሁ ታዬ፣ አሳየች አይቸው፣ አያል ዳኛቸው እና የወርቅውሀ ጌታቸውን የመሳሰሉ በውጤት ያሸበረቁ ታላላቅ ከዋክብት ሴት አትሌቶችም በዓድዋ ሰማይ ስር እንደሚፋለሙ ተጠቁሟል።

በክለብ ደረጃም በውድድሩ ታዋቂ የሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ አትሌቶችን በማፍራት የሚታወቁት ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ሲዳማ ቡና፣ ሸገር ከተማ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻልን የመሳሰሉ ክለቦች ተሳታፊዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኮሙኒኬሽን ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ምሩፅ እና የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ በጋራ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ ውድድሩ ለክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዕድል ለመፍጠር፣ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እና ክልሎች ፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች በማራቶን ሪሌ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ዓላማ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ ሦስት ክልሎችና፣ አንድ ከተማ አስተዳደር ፣ ስምንት ክለቦች በድምሩ ከአስራ ሁለት ተቋማት የተውጣጡ ሰላሳ ስድስት ሴቶች፣ ሰላሳ ስድስት ወንዶች በድምሩ ሰባ ሁለት ኢሊት አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሏል።

ውድድሩን የሚመሩ በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ ስልጠናዎችን (ኮርስ) የወሰዱ ስልሳ ዳኞች መመደባቸው በመግለጫው የተጠቆመ ሲሆን፤ ለሽልማትና በአጠቃላይ ለውድድሩ አስፈላጊው በቂ በጀት መመደቡ ተገልጿል።

ውድድሩ ላይ በቡድን ከ1ኛ-3ኛ ለሚወጡ የቡድን አትሌቶች የሜዳልያና የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም በቡድን አሸናፊ ለሚሆኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወይም ክለቦች የዋንጫ ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል።

ታሪካዊውን ፉክክር ከ1-3 ለሚያጠናቅቁ እንደየደረጃቸው 40 ሺህ፣ 20 ሺህ እና 15 ሺህ ብር በሽልማት መልክ እንደተዘጋጀላቸው ተጠቁሟል። ውድድሩ በታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ዋዜማ ዛሬ በታሪካዊቷ የዓድዋ ከተማ ከማለዳው 12:30 ላይ ይጀመራል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You