
በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እና በካናዳ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የኢለን መስክ በሚያራምደው አቋም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ካናዳውያን የባለፀጋው ኢለን መስክ ዜግነት እንዲነጠቅ ፊርማ እያሰባሰቡ መሆኑ ተሰማ፡፡
ከአምስት ቀናት በፊት የተጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ኢለን መስክ ከካናዳ ብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ እና ሉዓላዊነቷን በሚያኮስስ መልኩ እንቅስቃሴ አድርጓል ሲል የወነጀለ ሲሆን ካናዳውያን ‹‹ገንዘባቸውን እና ሥልጣናቸውን ምርጫችን ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ተጠቅመውበታል›› ሲሉም ኢለን መስክንና ትራምፕን ኮንነዋቸዋል፡፡
‹‹ኢለን መስክ የውጭ ሀገር መንግሥት አባል በመሆን የካናዳንና የካናዳውያንን ሉዓላዊነት ለማጥፋት እየሞከረ ነው›› በማለት ለተጠያቂነት እንዲበቃ የፊርማ ዘመቻ በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ በዘመቻው ላይ በርካታ ካናዳውያን የተሳተፉ ሲሆን በእስከአሁኑ እንቅስቃሴ ከሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ በላይ ካናዳውያን ፊርማቸውን ያሰፈሩ ሲሆን ሂደቱም እስከ መጪው ሰኔ አጋማሽ ድረስ ክፍት እንደሚሆን ታውቋል፡፡
በካናዳ ሕገ-መንግሥት መሠረት አንድ የካናዳ ዜግነት ያለው ግለሰብ ዜግነቱን የሚነጠቀው ማጭበርበር ሲፈጽም፣ ባልተገባ መንገድ ራሱን ሲገልጽ ወይም ለኢሚግሬሽን አሊያም ዜግነት ጉዳይ መረጃ ሲደብቅ ከተገኘ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የተወለደው መስክ የካናዳ እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያለው ግለሰብ ሲሆን የካናዳ ዜግነቱን ያገኘው በእናቱ በኩል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የምድራችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር የሆነው ኢለን መስክ ስለፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻው በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ‹ካናዳ እውነተኛ ሀገር አይደለችም› በማለት የጻፈ ሲሆን ወዲያውኑ ልጥፉን ከገጹ ላይ እንዳጠፋ ታውቋል፡፡ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻው በአንጻራዊነት ሕግ ማስፈጸም የሚያስችል አለመሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በእንደራሴዎች ምክር ቤት አባል ድጋፍ ካገኘ ግን በመንግሥት ኃላፊዎች በኩል ምላሽ የሚያገኝ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
የዶናልድ ትራምፕን ወደሥልጣን መምጣት ተከትሎ አዳዲስ ክስተቶች እየታዩ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በካናዳ እና በአሜሪካ መካከል የተፈጠረው አለመግባባትም የዚሁ አንድ አካል ነው፡፡ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካናዳን ለመጠቅለል ፍላጎታቸውን በተደጋጋሚ ጊዜ ከመግለጽ ባለፈ ወደአሜሪካ በሚገቡ የካናዳ ምርቶች ላይ ታሪፍ ለመጣል ዝግጅት እያደረጉ ነው፤ ይህን የትራምፕን አቋም ተከትሎ የካናዳ ነዋሪዎችም አፀፋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጁ እንደሆነ ታውቋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው መቃቃር በመንግሥታት ብቻ የተገደበ ሳይሆን ካናዳውያን በተቃውሞ ወደአሜሪካ ግዛት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መሰረዝ፣ የአሜሪካንን ምርቶች አለመጠቀም እና በስፖርታዊ ጨዋታዎች ላይ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር ተቃውሞ ማንሳት የመሳሰሉ ድርጊቶች ላይ በመሳተፍ ተቃውሟቸውን እያሳዩ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻው የዚህ ተቃውሞ አንዱ አካል እንደሆነ ነው የታወቀው፡፡
የሕይወት ታሪኩ እንደሚያስረዳው ከሆነ ቱጃሩ ኢለን መስክ አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላው ተወልዶ ካደገባት ደቡብ አፍሪካ ወደካናዳ ጠቅልሎ በመሄድ የኮሌጅ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ አሁን ወደሚኖርበት አሜሪካ አቅንቷል፡፡ በአውሮፓውያኑ 2002 ደግሞ ተፈጥሯዊ የአሜሪካ ዜግነትን እንዳገኘ የግል ማኅደሩ ይገልጻል፡፡
የፕሬዚዳንት ትራምፕን ጠንካራ ፖሊሲዎች በመደገፍ የሚታወቀው መስክ በአሜሪካ የትምህርት ቪዛ ሕገ-ወጥ ሥራ ሠርቷል በሚል ውንጀላም እየቀረበበት ይገኛል፡፡ ሆኖም የቴስላ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ውንጀላውን ያጣጣለ ሲሆን በሕገ-ወጥ መንገድ ምንም ዓይነት ሥራ አልሠራሁም የሚል ምላሽን ሰጥቷል፡፡ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ መመረጥ በኋላ ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው መስክ ወሳኝ በሆኑ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይም እየታየ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ የመረጃ ምንጫችን ቢቢሲ ነው፡፡
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም