«በተያዘው በጀት ዓመት 25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለማከናወን አቅደናል» -አቶ አብዶ አሕመድ የቡታጅራ ከተማ ከንቲባ

ከተቆረቆረች አንድ ምዕተ ዓመት ልትደፍን የቀራት አራት ዓመት ብቻ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከተማ 135 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለችየቡታጅራ ከተማ፡፡ የዛሬ 96 ዓመት የተቆረቆረችው ይህችው ከተማ፣ የሪፎርም ከተማ ሆና የከተማ አስተዳደር ውክልና ካገኘች ወደ ሃያ ዓመት አካባቢ አስቆጥራለች፡፡

በተለይ ራሷን በራሷ ማስተዳደር ከጀመረችበትና እውቅና ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገች የመጣች ከተማ ነች፡፡ በከተማዋ እየተከናወነ ስላለው የልማት ሥራ እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚነት በተመለከተ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከሆኑት ከአቶ አብዶ አሕመድ ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡

አዲስ ዘመን፡በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር እየተካሔደ ያለው የመሠረተ ልማት ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ አብዶ፡የቡታጅራ ከተማ የሪፎርም ከተማ መሆኗ የከተማዋ ነዋሪዎችም ተቋማቱም ተነቃቅተው የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አስችሏል። የተሻለ የልማትና የእድገት ጎዳና ላይ ለመግባት የሚያስችል በር ለከተማዋ ከፍቶላታል። በየዓመቱ አዳዲስ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በማከናወን በአንጻራዊነት በተመሳሳይ ደረጃ ካሉ ከተማዎች የተሻለ ተወዳዳሪ መሆን የቻለች ከተማ ናት።

ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር አንጻራዊና የተሻለ ሊባል የሚችል መሠረተ ልማት የተሟላላት ናት። ለአብነት ያህል በርከት ያሉ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት ሥራዎች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ተሠርተዋል። ይህም ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ድርጅት ውል በመግባት በየዓመቱ ለመገንባት ተችሏል። ይህ ማለት ለከተማው እድገት፣ ውበትና ምቹነት ትልቅ እድል የሰጠ ነው።

ከዚህ ባሻገር የከተማዋ ማስፋፊያ አካባቢ ማለትም የከተማዋ አዋሳኝ ድረስ ያለው የመሠረተ ልማት ሥራ በስፋት የተሠራበት ነው። በያዝነው በጀት ዓመት ጭምር ወደ ሶስት ኪሎ ሜትር በ334 ሚሊዮን ብር ወጪ ተፈራርመን አዲስ የአስፓልት ግንባታ ለከተማዋ እድገትና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወሳኝ የሆነ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት ከዚሁ ድርጅት ጋር ተፈራርመን እየሠራን ነው።

ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 100 ሚሊዮን ብር ለአስፓልት መንገድ ሥራ ወጪ አድርገን በመሠራቱ በአሁኑ ሰዓት ለአገልግሎት ክፍት መሆን ችሏል። ከዚህ የተነሳ ከመንገድ ሥራ ጋር ተያይዞ የተሻለ እንቅስቃሴ በከተማችን አለ ብሎ መውሰድ ይቻላል። በቀጣይም የተያዙ እቅዶች ያሉ ሲሆን፣ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡ከንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ምን የተሠራ ሥራ አለ? ለመሥራት የተያዘ እቅድም ካለ ይግለጹልን?

አቶ አብዶ፡ ከውሃ ጋር ተያይዞ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የተሻለ ሊባል የሚችል ነው። በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ መቶ በመቶ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። እንዲያም ሆኖ በየዓመቱ እንሠራለን። የከርሰ ምድር ውሃ በማስቆፈር ተደራሽነቱን በማረጋገጥ በማስፋፊያ አካባቢም ሆነ መሃል ከተማ ላይ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መቶ በመቶ ስኬታማ የሆነ ነው። ይህን ግን አስጠብቆ የመሄድ ኃላፊነት የቡታጅራ ከተማ አስተዳደርም የሕዝቡም ኃላፊነት ነው ብለን እናምናለን። ሥራው አንዴ ተሠርቶ የሚያበቃ ሳይሆን በየጊዜው እየጎለበተ የሚሄድ ነው።

ደግሞም ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ምቹ ናት የመባሉ ምስጢር አንዱ ያለው የውሃ አቅም ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጠና ጥናት መሠረት የቡታጅራ ከተማ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሶስተኛ ላይ የተቀመጠች ናት። አንደኛዋ አዳማ፣ ሁለተኛዋ ደግሞ ሐዋሳ ስትሆን፣ ሶስተኛዋ ቡታጅራ ነች። ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ይህን አስጠብቆ የመሔድ ኃላፊነትን ወስዶ እየሠራ ነው።

ባለፈው ዓመት ወደ 60 ሚሊዮን ብር ወጪ አውጥተን ቅሬታ ተፈጥሮ የነበረበት አካባቢ ተደራሽ ማድረግ ችለናል። አሁንም ሁለት አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራን ነው። ስለዚህ አንዱ ትልቁ ጸጋ እና አቅማችን ነው ብለን የምንወስደው የውሃ አቅርቦታችንን ነው። ከተማዋ የኮንፈረንስ ማዕከል መሆን አለባት ብለን እየሠራን ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ድርሻ ውሃ ነው። ስለዚህ ከውሃ ጋር ተያይዞ ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን።

ከመብራት ጋር ተያይዞም ትራንስፎርመር ሲቃጠል ወዲያው የመተካት እና ማስፋፊያዎች አካባቢ ተደራሽ የማድረግ ሥራ በስፋት እየሠራን ነው። በአጠቃላይ በመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ከተማ አስተዳደሩ የተሻለ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል። በየሁለት ዓመቱ በሚካሔደው የከተሞች የሀገር አቀፍ ውድድር ላይ ቡታጅራ ፊተኛው መስመርን ለቅቃ አታውቅም። ባለፈው በወላይታ ሶዶ በተደረገው የከተሞች ውድድር ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከ26 ከተሞች ወይም በተመሳሳይ ደረጃ ካሉ ከተማዎች የወጣው አንደኛ ነው።

ይህንኑ የሀገር ውስጥ ውድድር አሸናፊነትን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብሪክስ አባል ሀገራት የከተሞች ፎረም እንዲሁ ከኢትዮጵያ ከተሳተፉ አራት ከተሞች ውስጥ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር አንዱ ነው። የከተሞች ኅብረት ምሥረታ ጉባዔ የተካሔደው በሩሲያ ሲሆን፣ ቡታጅራም በዚያ መሳተፍ የቻለችና ዐሻራዋን ማሳረፍ የቻለች ከተማ ናት። በዚህም ምክንያት ቡታጅራ አጠቃላይ ኢትዮጵያንም ያለችበትንም ክልል ማስጠራት በመቻሏ በክልሉ ልዩ ተሸላሚ መሆን ችላለች። ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ሴክተሮች እውቅና ያገኘችበት ሁኔታም ያለ ሲሆን፣ እንደዞንም መሸለም የቻለች ናት።

የከተማ አስተዳደራችን የሚሠራው ከሌሎች ከተሞች ጋር ለመፎካከር አይደለም። ዋናው የሕዝቡ ተጠቃሚነት ነው። ወደፊት ካቀድነው እቅድ ጋር ስለሆነ እየሠራን ያለነው ወዳቀድነው ግብ ለመድረስ ነው። የተቀመጠው እቅድ እየተሠራ ያለው በውስጥ አቅም፣ በሕዝብና በባለሀብት ተሳትፎ ነው።

በኮሪደር ልማቱ ሥራ ብቻ በግማሽ ቀን ከሕዝብ ጋር በተደረገ ውይይት 101 ሚሊዮን ብር ከሕዝብ መሰብሰብ ተችሏል። ይህ ቀላል የሚባል ተሞክሮ አይደለም። ምክንያቱም ማኅበረሰቡ የኮሪደር ልማቱ ደርሶበት ቦታውን እየለቀቀ እና ቤቱን እያፈረሰ እራሱ ደግሞ መልሶ እየገነባ ደግሞ ለኮሪደር ልማት ርዳታ ያደረገበት ሁኔታ በጣም የሚበረታታ ሆኖ አግኝተነዋል።

በዘንድሮ ሥራችን ያቀድነው 25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለመሥራት ነው። ይህ ሥራ ደግሞ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር ወጪ የሚያስወጣ ነው። ይህ ገንዘብ ከሌላ ከማንም የሚመጣ ሳይሆን በውስጥ አቅም የሚሠራ ነው። የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን እንዴት እንደቀየረ ግልጽ ነው። በርካታ ከተሞችን ከመፋዘዝና ከእርጅና እንዴት እንደታደጋቸው ማየት ብቻ በቂ ነው። ይህ የኮሪደር ሥራ ወደተለያዩ ከተማዎች እየሰፋ ነው።

የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር በከንቲባ ፕሮጀክት ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት ወደሁለተኛው ምዕራፍ ተሸጋግረናል። እየተሠራ ያለውም በሶስት ምዕራፍ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር እየተሠራ ያለው ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ነው። ሌሎቹም እንዲሁ ወደሥራ ተገብቶባቸዋል። ይህ ገቢን አሟጥጦ በመሰብሰብ እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የሚሠራ ልማት ነው።

በቡታጅራ ከተማ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ እየተሠራ ያለው ሥራ መልካም ነው፤ ከዚህ በመነሳትም ከተሞቻችን ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የሚያሟሉ ባለመሆናቸው ኢትዮጵያን የሚመጥኑ ከተማዎች ያስፈልጉናል። ለኑሮ፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም ማዕከልነት፣ ለኮንፍረንስ ተመራጭ የሆኑ ከተማዎች እንሻለን።

በእኛም ከተማ የሚለሙ የወንዝ ዳርቻዎች አሉ። የሕዝብ አደባባዮችም አሉ። ሌሎች በርካታ ሥራዎችንም የኮሪደር ልማቱ የያዘ ነው። እየተሠራ ያለው ሥራ ከተማዋን በአዲስ መልክ የመሥራት ያህል ነው። ይህን እየሠራን ያለነው ከማኅበረሰባችንና ከባለሀብቱ ጋር ተግባብተን ነው። የጋራ ጥረት፣ ቁርጠኝነትና ግብ ጥለን እንደ አንድ ትልቅ ፕሮጀክታችን አሰበን እየሠራን እንገኛለን። እስካሁንም ያለው አፈጻጸም የተሻለ የሚባል ነው።

አዲስ ዘመን፡ከወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ከተማ አስተዳደሩ እየሠራ ያለው ሥራ እንዴት ይገለጻል?

አቶ አብዶ፡ እንደ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ልዩ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው ሥራ ከወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ እየተሠራ ያለ ሥራ ነው። እዚህም አካባቢ ያለው አንዱ የሀገራችን ፈተና ነው ተብሎ የተወሰደውና ትልቅ ክብደት ተሰጥቶት እየተሠራ ያለው የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ነው። ለምሳሌ እንደ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር በየቀኑ የምንገመግመው ከገቢ ቀጥሎ የሥራ እድል ፈጠራን ነው። ለሁሉም ተግባሮቻችን ገቢን አሟጥጦ መሰብሰብ፣ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቁጥር አንድ የምንገመግመው ገቢን ነው። ምክንያቱም ገቢን ሰብስበን ለልማት ማዋል መቻል አለብን።

ከገቢ ቀጥሎ በየቀኑ የምንገመግመውና በትኩረት የምንመራው የሥራ እድል ፈጠራን ነው። ይህ እየተገመገመ ያለው እንደ ሀገርም ጭምር ነው። ከዚህ አንጻር በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት ከ12 ሺህ በላይ ሥራ አጥ ለይተናል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ከሁለት ሺህ በላይ ምሩቃን ናቸው። ይህን በተለየ መልኩ ካልሠራን በጣም ፈታኝ ነውና የሠራነው ልዩ ርብርብ ልናደርግበት ይገባል በሚል መንፈስ ነው።

በመሆኑም በዚህ ስድስት ወር ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሥራ እድል መፍጠር ችለናል። የተፈጠረላቸውም የሥራ መስክ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በአገልግሎቱና በሁሉም መስክ በቋሚና በጊዜያዊነት ነው። ይህ በክልልም የተሻለ አፈጻጸም ተብሎ የተወሰደ ነው። ይህ እየሰፋ የሚሄድ ይሆናል፤ ምክንያቱም ገና እድሉን ያላገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች አሉን። ከዩኒቨርሲቲ፣ ከኮሌጅ እንዲሁም ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው ቤታቸው የተቀመጡ አሉ። እነሱን የሚመጥን የሥራ እድል መፍጠር መቻል አለብን በሚል የስድስት ወሩን እቅድ ከልሰን ወደተግባር ገብተናል።

ወጣቱ፣ ሴቱ በአጠቃላይ ሥራ አጡ ሥራ መናቅ የለበትም፤ የተገኘውን ሥራ እየሠራ የተሻለ ሥራ እስኪገኝ ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል። ‹‹ይህኛው ሥራ አይመጥነኝም፤ ያኛውም ይቅርብኝ›› በሚል አስተሳሰብ ሥራ አጥቶ መቀመጥ የለበትም የሚል መልዕክት አለኝ።

ለምሳሌ በእኛ ከተማ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አለ፤ ይህ ፋብሪካ በርከት ያለ የሰው ኃይል የሚፈልግ ነው። ስለዚህ ‹‹አይሆነኝም› የሚባለውን አስተሳሰብ ወደጎን በመተው በተገኘው የሥራ እድል መጠቀም ብልህነት ነው። እየሠሩ የተሻለ ሥራ መፈለጉ አዋጭ ነው።

የተለያየ ፈንድ በማፈላለግና ብድርም በመስጠት ለወጣቶቹ የተሻለ የሥራ እድል ለማመቻቸት የበኩላችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን። ብድር ከወጣ በኋላ የመመለሱ ሒደት በተወሰነ መልኩ ፈተና ያለበት ነው። ብድር መመለስ ለቀጣዩ ወጣት የሥራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ የተበደረው አካል ይህን ታሳቢ አድርጎ እየመለሰ ቢንቀሳቀስ መልካም ነው።

አዲስ ዘመን፡በትምህርቱ ረገድ በተለይም የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ እየተሠራ ያለው ሥራ ምንድን ነው?

አቶ አብዶ፡ የትምህርት ጥራትን በተመለከተ እንደ ሀገር ያለብን ውድቀት የሚታወቅ ነው። ከዚህ ውድቀት ለመውጣት እንደ ሀገር እየተደረገ ያለው ጥረትም ግልጽ ነው። በትምህርት ጥራት በኩል ያጋጠመንን ውድቀት ለመምህሩ፣ ለተማሪው፣ ለወላጅ ወይም ለአመራሩ ነጥለን የምንሰጠው ጉዳይ አይደለም፤ ችግሩ ለግለሰብ የሚተው አይደለም። ሁላችንም ጨከን ብለን ከዚህ ውድቀት መውጣት ይኖርብናል። እየተሠራ ያለውም በዚሁ ልክ ነው።

ትውልድን የምናስብ ከሆነ፤ የነገዋን ኢትዮጵያ የምንፈልግ ከሆነ ትምህርት ላይ ጨክነን መንቀሳቀስ አለብን በሚል ነው እየተሠራ ያለው። እንደ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደርም ይህንኑ ወስደን ከተማውን ሊመጥን የሚችል የትምህርት ጥራት ውድቀትን ለመታደግ የተሻለ ሥራ እየሠራን እንገኛለን።

በመጀመሪያ ሥራችንን የጀመርነውም ተቋሞቻችንን፣ አቅሞቻችንንና ጉድለቶቻችንን በመገምገም ነው። ይህንንም ያደረግነው ከተማሪዎቻችን፣ ከወላጆች፣ አጠቃላይ ከስታፉ ጋር በመሆን ነው። ውድቀቱንም እንዴት መታደግ እንደምንችል ተወያይተንበታል። በእርግጥ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ወይም 50፣ 60፣ 70 በመቶ ተማሪዎችን ልናሳልፍ አንችልም የሚለውን አጢነናል።

በጣም የደከሙ ትምህርት ቤቶች ነበሩ፤ ዙሪያቸው የተለያየ ሸቀጥ መሸጫ ከመሆናቸው የተነሳ ለሱስ ተጋላጭ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ነበሩ። ይህን ከማኅበረሰቡ ጋር ተነጋግረን መታደግ ችለናል። ምትክ የሚሰጠውን ምትክ እየሰጠን፤ ካሳ የሚከፈለውን እየከፈልን ትምህርት ቤቶችን በዙሪያቸው ካሉ ለሱስ አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች መታደግ ችለናል። ተጨማሪ ክፍሎችን መገንባት፣ ቤተ መጻህፍትና ቤተ ሙከራን ከመሥራት ጎን ለጎንም አዳዲስ ትምህርት ቤቶችንም መገንባት ችለናል።

ባለፈው ዓመት በሠራነው ሥራ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በማሳለፍ ምጣኔ ረገድ በስድስት በመቶ ማሻሻል ችለናል። ይህም ማለት ከነበረው አምስት በመቶ ወደ 12 በመቶ ከፍ ማድረግ ችለናል። ካለን አቅም አንጻር ግን በቂ ነው የሚል እምነት የለንም። ከዚህም የተነሳ ያለንን አቅም ባለመጠቀማችን የመጣ ክፍተት በሚል በውድቀት ገምግመናል። ከዚህ ባሻገር አብዛኛው ተማሪ በሬሚዲያል እንዲገባ የተደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአጠቃላይ ከ55 በመቶ በላይ ተማሪ በሬሚዲያል እና በቀጥታ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መቀላቀል ችሏል። ሌላው 45 በመቶ አካባቢው ወደ ቴክኒክና መሰል ተቋማት እንዲገቡ ያደረግንበት ሁኔታ አለ። አምና የነበረው ክፍተት እንዳይደገም በሚል ዘንድሮ ከባለድርሻዎች ጋር በመሆን በጋራ እየሠራን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡ከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎች የምገባ መርሃግብርን በተመለከተ እየሠራ ያለው ሥራ ይኖር ይሆን? ካለ ምን ያህል ትምህርት ቤቶችን ያካትታል?

አቶ አብዶ፡የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ አንዱ እንደ ሀገር እየተሠራ ያለው በተማሪዎች ምገባ ላይ ነው። እንደሚታወቀው በተማሪዎች ምገባ እንደ አዲስ አበባ የተጀመረው ሥራ ወደ ተለያዩ አካባቢዎችም እየሰፋ ሔዷል። እንደ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደርም አምና በሁለት ትምህርት ቤት ጀምረን ዘንድሮ በአምስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ቀጥለናል።

ሁሉም የመንግሥት ቅድመ መደበኛን ጨምሮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እርጎ እና ዳቦ በማቅረብ እየሠራን ነው። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተማሪዎች ላይ ለውጥ ማሳየት የጀመረ መሆኑን አስተውለናል። ወደሌሎችም አካባቢዎች መስፋፋት አለበት ብለን እናምናለን። ሰዎችም ይህን በጎ ተግባር ያግዛሉ። ከዚህ አኳያ ሲታይ ማኅበረሰቡ እራሱ ቅን ነው። መርሃግብሩን ለመደገፍ ወደኋላ የሚል ተቋምም ማኅበረሰብም የለም።

ሌላው በከተማችን የአዳሪ ትምህርት ቤት የለም። ከዚህ የተነሳ አዳሪ ትምህርት ቤት ያስፈልገዋል በሚል እንደቡታጅራ ከተማ አስተዳደር በተለየ ቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለን። በዚህም ከባለፈው ክረምት ጀምሮ ማኅበረሰቡና ባለሀብቱ የአቅሙን ድጋፍ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታን ፈጥረን እየሠራን ነው። መሬት በስጦታ ቀርቦ ለሽያጭ የዋለበት፣ ለዚሁ አዳሪ ትምህርት ቤት መሥሪያ ወደ ሶስት ሔክታር መሬት ያዘጋጀንበት እና ሁሉንም ነገር ማለት በሚቻል መልኩ አጠናቅቀን ወደመሠረት ድንጋይ ወደማስቀመጡ ሒደት የደረስንበት ሁኔታ መፍጠር ችለናል። እንዲሁም ደግሞ የበጀት አካል አድርገን በምክር ቤት ደረጃ አጽድቀነዋል።

ይህም ለትምህርቱ ጥራት እንደ ሀገር የራሱን ጠጠር ይወረውራል ብለን እናስባለን። ይሁንና ይህ ብቻ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ በቂ ባለመሆኑ በቀጣይም የበኩላችንን ለመወጣት የምንሠራ ይሆናል። ሁሉም ሊረባረብበትም ይገባል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡ኢንቨስተሮች ወደከተማዋ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚሹት የሰላሙ ሁኔታ ሲረጋገጥ ነውና በከተማው የሰላሙ ሁኔታ የሚገለጸው እንዴት ነው?

አቶ አብዶ፡የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር አንዱ መገለጫው ሰላሙ የተረጋገጠ መሆኑን ነው። 24 ሰዓት ማንኛውም አካል በየትኛውም ቦታ የሚንቀሳቀስባት ከተማ ናት። ‹‹ማነህ? ወዴት ነህ?›› የሚባልበት አካባቢ አይደለም። በየትኛውም ሰዓት ምንም አይነት እንከንም ሆነ ኮሽታ የሚሰማባት አይደለም።

ለዚህ ሰላም አንዱ ምክንያት ማኅበረሰቡ በመቻቻልና በመከባበር፣ በመደማመጥና በመተጋገዝ የሚታወቅ በመሆኑ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ማኅበረሰቡ በእንግዳ ተቀባይነቱ የሚታወቅ ነው። ጸጥታ ተቋሞቻችንም አካባቢ እና ፖሊስ አካባቢ ያለው መዋቅር የተሻለ ነው። ምክንያቱም እንደ ክልልም ተሸልሟልም፤ እውቅና ተሰጥቶታልም። ለክልልም ጭምር ደጀን እየሆነ የመጣ መዋቅር ነውና ከሰላም አኳያ ቡታጅራ ከተማ ኮሽታ የለም ማለት ይቻላል።

ማኅበረሰቡ እራሱ ሰላምን አንዱ መገለጫዬ ነው በሚል እንደ መርህ ይዞ በማስቀጠል ላይ ይገኛል። ከተለያየ አቅጣጫ የሚወረወር አጀንዳ አለ፤ ነገር ግን ማኅበረሰቡ ያንን አጀንዳ አይቀበልም። ምክንያቱም አጀንዳው አንድነቱንና አብሮነቱን የሚነካ መሆኑን ያውቃል። የከተማችን ሰላም ሲታወክ የራሱም፣ የሁላችንም ሰላም እንደሚታወክ ያውቃል። የቱንም ያህል ያልተመቸው ነገር ቢኖረውም በሰላሙ ጉዳይ የማይደራደር ማኅበረሰብ ነው። እንደ ጸጥታ መዋቅርም የማያዳግም ርምጃ ይወሰዳል። የሰላም ጉዳይ አንዴ ሠርተን አጠናቀናል ብለን የምናቆመው ጉዳይ ሳይሆን ሁሌም ሥራን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ለመሥራት ዝግጁዎች ነን። ሀገራችን ወደአስቀመጠችው የብልፅግና ርዕይ እንዳትደርስ እየጎተታት ካለው ነገር ውስጥ አንዱ የሰላም መታጣት በመሆኑ በዚህ ጉዳይ አጥብቀን እንሠራለን።

አዲስ ዘመን፡በቡታጅራ ከተማ ለኢንቨስትመንት ምቹ ነው ተብሎ የሚጠቀሰው መስክ የትኛው ነው? የከተማ አስተዳደሩ አቀባበልስ ምን ይመስላል?

አቶ አብዶ፡– ቡታጅራ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የምትገኝ ከተማ ነች። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መውጫም መግቢያም ከተማ ነች። እንደሚታወቀው አራት ስትራቴጂክ መንገዶች ያሏትም ናት። ከዚህ ጎን ለጎን ትርፍ አምራች ከተማ ስትሆን፣ በኢንቨስትመንትም ተፈላጊነቷ እጅግ የላቀ ነው። ኢንቨስተሮች በእጅጉ ይፈልጓታል፤ ምክንያቱም በቡታጅራ ሠርቶ ከሰርኩ የሚል አካል የለም። ከተማዋ ለኢንቨስትመንት በቂ የሆኑ ግብዓት ያሉባት ናት። የሰው ኃይልም ያለበት ነው። የተመረተው የትኛውንም ምርት ለገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ ያላት ናት።

ከዚህ የተነሳ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ወደ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር መጥተው ኢንቨስትመንቱን በመቀላቀል ላይ ላይ ናቸው። ከዚህ በላይ በጣም ትልልቅ የሆኑ ኢንቨስተሮች መጥተው እንዲያለሙ እየሠራን እንገኛለን። በሆቴል፣ በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ እና በተለያዩ ዘርፎች እንደ ሀገር ትልቅ የሆኑ ኢንቨስተሮችንም መጠየቅ ጀምረናል። ስለዚህ እነሱን የመጋበዝ፣ ወደከተማችን እንዲመጡ የማድረግ፣ ቦታ የማመቻቸትና መሰል ሥራዎችን እየሠራን ነን። ይህን አጠናክረን እናስቀጥላለን። ምክንያቱም ሀገር እንድትለማና እንድትቀየር የምንፈልግ ከሆነ አንዱ ኢንዱስትሪ ላይ በትኩረት መሥራት መቻል ነው። አሁንም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሠማራ ኃይል አጥብቀን እንሻለን። የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር አገልግሎት ዘርፍ ላይ እንደ ሀገር የኮንፈረንስ ማዕከል እንዲሁም የሥልጠና ማዕከል መሆን አለባት ብለን ካልን በሆቴል፣ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ አሁን ካሉት በላይ ኢንቨስተሮች ያስፈልጋሉ።

ከዚህ አኳያ ባለሀብቶች ወደ ከተማችን መጥተው ኢንቨስት ቢያደርጉ በእርግጠኝነት ይጠቀማሉ፤ ማኅበረሰቡንም ይጠቅማሉ፤ የኢትዮጵያንም ከፍታ ያረጋግጣሉ የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።።

አዲስ ዘመን፡በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና እንዴት ይገለጻል?

አቶ አብዶ፡የከተማ ግብርና እንደ ከተማ አስተዳደራችን በጣም በልዩነት እየተሠራ ያለ ነው። አቅሙም አለን። መሬቱ ምንም ቢጣልበት ከማብቀል ወደኋላ አይልም። ከዚህ አንጻር እያንዳንዱ ቦታ ሥራ ላይ መዋል እየጀመረ ነው። ተቋማት አካባቢ ያለ መሬት መልማት መቻል አለበት። የእያንዳንዱ ነዋሪ ጓሮ አነስተኛም ቢሆን ወደጎንም ሆነ ወደላይ አማራጩን በመጠቀም በሌማት ትሩፋቱ መሠማራት መቻል አለበት። ሁሉ ነገር በእጃችን እለ መራብ የለብንም በሚል በትኩረት ርብርብ እየተደረገ ነው።

ከተማችን ውስጥ 24 ሰዓት የማይታጣ የወተት አቅርቦት አለ። ከአካባቢው አልፎ ለወራቤ ዩኒቨርሲቲና ለዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ወተት ያቀርባል፤ ቡታጅራ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ወተት የሚጫንባት ከተማ ናት። ስለዚህ ከወተትም አኳያ ካየነው ትርፍ አምራች ከተማ ነች። በከብትና በዶሮ ርባታ፣ በከብት ማደለብ፣ በንብ ማነብ የተሻለ ሥራ የሚሠራባት ናት።

አሁን ከአራት ሺህ በላይ ዶሮ ያላቸው ሰዎች በርካታ ናቸው። እንቁላል ወደ 13፣ 14 እና 15 ብር በሚሸጥበት ሰዓት በከተማችን በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ለተለያዩ ተቋማት በሰባት፣ ስምንትና ዘጠኝ ብር በቅናሽ ሲያስረክቡ ነበር። ያውም ሲያስረክቡ የነበረው በመኪና እያዞሩ ነው። ከዚህም በኋላ በእያንዳንዱ ቤት መግባት አለበት በሚል አስተሳሰብ እየተሠራ ነው፤ ኢንሼቲቩ ይህ ነው።

አብዛኛውም ማኅበረሰብ የዚህ ኢንሼቲቭ ተጠቃሚ በመሆኑ እሱን እያሳደግን እንሔዳለን። በንብ ማነቡ ላይ ተደራጅተው የተሰማሩ ወጣቶች ወደ ኤክስፖርት እንቅስቃሴ ገብተዋል። ቦታ ሲያንሳቸውም ተጨማሪ ቦታ ሰጥተናቸው በማር ምርት በመሰማራታቸው ውጤት በማስመዝገብ ላይ ናቸው። እንደ ክልልም ሆነ ሀገርም ከሚታወቁ መካከል እንደ ቀሽት አይነት ማዕከል በጣም የተሻለ ሥራ እየሠሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለሌሎች ወጣቶችም አርዓያ በመሆን ላይ ይገኛሉ። ሥራ የለንም ብለው ለተቀመጡ ወጣቶች ሞዴል የሆኑ ናቸው።

ተቋማት አካባቢ ያሉ ክፍት ቦታዎች የስንዴ ማሳ ሆነው ይታያሉ፤ ማሳው ሲታይ ከስፋቱ የተነሳ ቡታጅራ ከተማ ውስጥ እየተሠራ ያለ የከተማ ግብርና አይመስልም። እያንዳዱ ቦታ ላይ ቆጥረን እየሰጠን ሲሆን፣ ቆጥረንም እየተረከብን ነው። ይህን ስንሠራ ከኑሮ ውድነቱ ጋር በማስተሳሰር ነው።

በአሁኑ ወቅት የተደራጀ የቅዳሜ ገበያ አለ። ማኅበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችንም ሆነ ሸቀጦችን እንዲያገኝ እየተደረገ ነው። ሸማቹ በደላላ ሳይዋከብ በቀጥታ ከአምራቹ መግዛት የሚችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። አርሶ አደሮችም ሳይዋከቡ ምርታቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው የሚያቀርቡበት ሜዳ ተመቻችቷል።

ከዚህ የተነሳ ይህን ማሳደግ አለብን በሚል ከእሑድ እስከ እሑድ በሚል የተለያዩ መሰል ገበያዎችን መሥርተናል። ዋና ዓላማችን የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን አለበት ከተባለ የሚጀምረው ከታች ነው። የብልፅግና ጉባዔ ላይ ወሳኝና መሠረታዊ የሆኑ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። ይህ አቅጣጫ ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ የሚጀመረው ከእኛ ነው በሚል መንፈስ በመሥራት ላይ እንገኛለን። ሊገመገም የሚችለው ደግሞ እንደ ሀገር ያለው ድምር ውጤት ነው።

ኢትዮጵያ ከፍ ልትል ከሆነ ቡታጅራ ከፍ ማለት አለባት። ስለዚህ ቡታጅራን ከፍ በማድረግ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ይቻላል በሚል ተግባብተን እየሠራን ነው። ዋናው ግባችን የከተማችንንም ሆነ የሀገራችንን ከፍታ እውን ማድረግ ነው።

ከዚህ የተነሳ ሥራችንን በጥራት፣ በፍጥነትና በቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለን። የተሻለ ከተማ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚል ግብ ይዘን በመሥራት ላይ ነን። በዚህም ሥራ የተሻለ ውጤት እየታየ ነው። የሕዝቡም ሆነ የተቋማት ግብረ መልስ እያመላከተን ያለው ይህንኑ ነው። ለዚህ ምስክር መሆን የሚችለው በኮሪደር ልማት ምክንያት ቤቱ ስምንት ዙር እየፈረሰበት እንኳ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለኮሪደር ልማቱ ድጋፍ የሚያደርግ ማኅበረሰብ የሚገኝባት ከተማ ነች። ህንጻ ፈርሶበት ሳያማርር ደስተኛ ሆኖ ‹‹እኔም ለከተማዬ ዐሻራዬን አሳርፋለሁ›› በሚል ሁለትና ሶስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እያደረገ ነው። ይህ ያልተጠበቀ በጎነት ነው። ይህን ሕዝብ ደግሞ በልማት መካስ ከእኛ የሚጠበቅ ነው። አንድ ኪሎ ምስማር መግዣ የሌላት እናት እንኳ ቤቷን፣ አጥሯን አፍርሳለች። ይህን የምንክሳት በልማት ነው።

አዲስ ዘመን፡ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ አብዶ– እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You