ከዛሬ ትውልድ የሚፈለገው ጀግንነት ምን ዓይነት ነው?

ኢትዮጵያ በጀግኖች ደምና አጥንት ዛሬ ላይ የደረሰች ሀገር ነች። እልፍ አዕላፍ ጀግኖች ተሰውተው ዛሬዋን ኢትዮጵያን አስረክበውናል። በየዘመናቱ ባደረጉት ተጋድሎም በአንድ የጦር አውድማ ውለው በጋራ ድል አድርጎ መመለስ መለያቸው ሆኖ ኖሯል። ለዚህም ነው ባለቅኔው ፤-

”የኢትዮጵያ ልጆች ተማክረው ከወጡ፣

እንኳን ሊያስወስዱ ከሌላም ባመጡ።

ከቅቤው ከሆነ ከቅቤው ስጧቸው፣

ከማሩ ከሆነ ከማሩ ስጧቸው፣

ይህችን የደም አጥር እንዳታስነኳቸው።”

ሲል ያወደሳቸው። ደማቸውን ያፈሰሱላት አጥንታቸውን የከሰከሱላት የአርበኞች ምድር ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ስለምን ልጆቿ ሞራላቸው ዛለ? እዝነ ልቦናቸውስ ዋለለ? እንዴት ህሊናቸው ሻከረ? ልባቸው በምን ዛከረ? እያልን መጠየቃችን አልቀረም።

ሳሉ ጀግኖቻችን ለሀገር የሞቱ፣

ምነው የኔ ትውልድ ለአልጋ መሰዋቱ።

የሚለው ስንኝ ዘመናችንን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን ይመስለኛል። የጥንቱ የአባቶቻችን ገድል ዛሬ ላይ እንደምን ደምቆ መነሳት ተሳነው ፤ የዛሬውስ ትውድል አጥንቱን ባይከሰክስ፤ደሙን ባያፈስ እንኳን እንደምን የሀገሩን ሰላም መጠበቅ ተሳነው፤ ክንዱን አበርትቶ የሀገሩን ልማት ማፋጠን ለምን አታከተው የሚል ጥያቄ በእያንዳንዳችን አእምሮ መነሳቱ አይቀሬ ነው። እኛም ጥያቄውን በማንገብ ለርዕሰ ጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ባለሙያዎች አነጋግረን የሚከተለውን ጽሁፍ አሰናድተናል።

በርዕሰ ጉዳዩ ላይም ገጣሚ፣ ባለቅኔ፣ ጽሀፊተውኔት እንዲሁም በአዲስ አበባ መካነ/አምሮ [ዩንቨርሲቲ] መምህር የሆኑት አቶ አያልነህ ሙላቱና የበርካታ መጽሃፍት ደራሲ ታደለ ገድሌ ዶ/ር በርእሰ ጉዳዩ ዙርያ ሃሳቦችን አካፍለውናል።

አቶ አያልነህ ርዕሰ ጉዳዩን ለማብራራት ቀድሞ ጀግኖችን ተጋድሎ በማንሳት ነበር ውይይታችንን የጀመሩት። የሰው ፍጡር ቀርቶ እንስሣትም እንኳን ልብ ለልብ ተግባብተው መሪ ከመሪ ተስማምተው የተዋደቁለት የአርበኝነት ተጋድሎ የድል አክሊል አጎናጽፎና በማዕረግ ሸልሞ ከታሪክ ድርሳናት አስፍሯቸዋል። የጾታ፣ የእድሜ፣ የኑሮ ደረጃ፣ የሥልጣን ልዩነት ሳይገድባቸው የኢትዮጵያ አርበኞች ተፋልመው ዘመን አይሽሬ ስማቸውን ተክለዋል።

“ጣሊያን በኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሃፍ የሸዋው አርበኛ ሃይለማርያም ማሞ በአምስት ዓመታቸው እናታቸው ለአርበኞች መረጃ እንዲያቀብሉ ይልኳቸው እንደነበር ተጠቅሷል። ከቀሚስ ውጪ መልበስ ነውር በሆነበት በዚያ ዘመን በዱር በገደሉ እንደልብ ለመራመድ እንዲያመቻት ሸዋረገድ ገድሌ ሱሪዋን ታጥቃ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ ዓለምን ምሽግ የሰበረች ጀግኒት ናት።

የወልቃይቱ አባ ሃይለማርያምም የሞተን እየፈቱ በሕይወት ያለን አባታዊ ቡራኬ እየሰጡ አርበኞችን አስተባብረው ጣሊያንን የተዋጉና ከአቡነ ጴጥሮስ አስቀድመው በሰባት ጥይት ተደብድበው ሕይወታቸውን ያጡ ጀግና የሃይማኖት መሪ ናቸው። በደም የሚወርሱት በነፍስ የሚዋሃዱት አርበኝነት ከግለኝነት ወጥቶ የጋርዮሽ መንፈስን የገለጠ ከእኔነት ይልቅ እኛነትን ያጎለበተ አንዱ ለሌላው አለኝታነቱን ያሳየበት የሀገር ፍቅር ስሜት የጸነሰው ሕያውነት ነው።

“እናት ሀገር እንዳትደፈር፣

በወራሪ ሃይል ቅንጣት እንዳትሸበር፣

ዘብ እቆማለሁ ለህልውናዋ መከበር።”

በማለት ሸልሎ ውድ ሕይወቱን ያለስስት የሰጣት ኢትዮጵያ ጀግና የማይነጥፍባት ቅድስት ምድር የጥቁር ዕንቁ የዓለም ፈርጥ ነች።

ተመስገን ገብሬ አደባባይ ላይ ቆሞ “ሕዝቤ ሆይ ንቃ! ጣሊያን የአርባ ዓመት ቂም አዝሎ እየመጣ ነው ለከፋ ትግል ተዘጋጁ” እያለ ቢለፈልፍም እንደዕብድ ከመቆጠር በቀር ሰሚ አላገኘም፤ ይሁን እንጂ 1927 ዓ.ም ለሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት መመሥረት ምክንያት ሆኗል። አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ ቦንብ ከጣሉ በኋላ ወደ ደብረሊባኖስ ያሸሻቸውን ኋላም በባንዶች ጥቆማ ከጣሊያኖች እጅ ገብቶ በግፍ የተገደለው የታክሲ ሹፌሩን ስምዖን አደፍርስንና በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና ህንድ የተማሩ የኢትዮጵያ ወጣት ምሁራንን ያሰባሰበው ተመስገን ገብሬ የአርበኞችን ትግል ከማቀናጀትም በላይ ጣሊያን በኢትዮጵያ አርበኞች ላይ ያደረሰውን ፋሺሽታዊ ግፍ ለዓለም የሚያጋልጡ ሰነዶችን ያዘጋጅ ነበር።

የተመስገንን ሁኔታ የተረዱት ጣሊያኖች ሊይዙት ሲኳትኑ አንድ ቀን እጃቸው ውስጥ ገባ፤ ተመስገንም ነገሩ እንዳለቀለት ሲገነዘብ የመጨረሻ ብልሃቱን ተጠቀመ። “ተመስገንን ነው የምትፈልጉት?” ይላቸዋል። “አዎ” ይሉታል። “እሱንማ አውቀዋለሁ ኑ ላሳያችሁ” ይልና ራሱን በራሱ አብሮ ያፋልጋቸው ጀመር፤ እነሱም የተመስገን ተንኮል ሳይገባቸው ቀርቶ በፍለጋው ቁርጥ ሲያውቁ 18ሺ000 ኢትዮጵያውያን ከታሰሩበት ማጎሪያ ጨመሩት።

ተመስገንም በውሃ ጥም የረገፉ እልፍ አርበኞችን ተመለከተ፤ ወደካምፑ ቦንብ ተጥሎ የደም ማእበል ሲጎርፍ “ከውሃ ጥም ይሻላል” ብለው የገዛ ወገናቸውን ደም ሲጠጡ ባየ ጊዜ ምሬቱ አይሎ በሚጽፋቸው ምስጢራዊ ደብዳቤዎች ለአርበኞች የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን አስተጋባ። ጣሊያኖች በዚህ ብቻ አላበቁም፤ የራሳቸውን መቀበሪያ ካስቆፈሯቸው በኋላ ተመስገን ገብሬን ከፊት አስቀድመው ከጉርጓዱ አፍ አቆሟቸውና መተኮስ ሲጀምሩ ተመስገን ቀድሞ ስለዘለለ ሁሉም አስከሬን እሱ ላይ ተነባበረ። የሚጮኸውንና ትንፋሽ ያለውን እያዳመጡ ጨረሷቸው። ቀኑ ጨለማ ለብሶ ገዳዮች ሲሄዱለት በታምር የተረፈው ተመስገን ተሽሎክልኮ አክስቱ ቤት ደረሰና አንድ ቀን አርፎ በግሩ እየተጓዘ ሀገሩ ጎጃም መግባት ቻለ።

ማርቆስ እንደደረሰ ባንዳዎች አሁንም ሊያሲዙት እንደሆነ ሲሰማ በበቅሎና በፈረስ እያቆራረጠ ሱዳን ጠረፍ ገዳሪፍ ገብቶ ከድል ማግሥት “ሕይወቴ” በሚል ርዕስ አሳትሞ ለንባብ ያበቃውን ደብዳቤ ለጃንሆይ ጻፈላቸው። የላከላቸውን ጽሁፍ እንዳነበቡ አንጀታቸው ተኮማትሮ ፈጣሪ በታምር ያተረፈው የሰማእታቱን ገድል እንዲመሰክር ስለሆነ ታሪክ በማስቀረቱ እንዲበረታ ገልጸው የሰደደላቸውን ደብዳቤ ይዘት ሳይለውጡና ፊደል ሳያጎሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት [ተመድ/ሊግ ኦፍ ኔሽን] መድረክ ላይ አቀረቡት።

ንጉሡ ምንም እንኳን በስላቅ ፉጨት ታጅበው አድማጭ ባያገኙም ታሪክ ግን ሲዘክረው ይኖራል። ጭፍን ጥላቻን ያዘለ ፍልስፍናዊ ስብከት ከሄግልና ከኢማኑኤል ካንት አንደበት ሲዥጎደጎድ ምራባውያኑን የዘረኝነት ትብታብ ቀየዳቸው። ሄግል “አፍሪካውያን ታሪክና እምነት አልባ ሕዝቦች እንዲሁም ለሥልጣኔና ለጥበብ ምንም አይነት አበርክቶ የሌላቸው እድሜ ልካቸውን በጨለማ ዘመን የሚኖሩ ፍጡሮች ናቸው” ሲል ኢማኑኤል ካንት ደግሞ “ከቀደምት አሜሪካውያንና ከቀይ ህንዶች በበለጠ ለባርነት ጉልበታቸው አስተማማኝ ሕዝቦች ናቸው” ይላል፤

ይህም አውሮፓውያኑን አስጎምጅቶ ጉልበታቸውንና ተፈጥሯዊ ሀብታቸውን ሊመጠምጡ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል የሆነችውን ኢትዮጵያን ገፍተው አፍሪካን ሊቀራመቱ ለቅኝ ግዛት አሰፈሰፉ፤ ሆኖም የጀግኖች መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያ በዱር በገደሉ በመትመም ጣሊያንን ተደላድሎ እንዳይቀመጥ እሾህ ሆኑበት።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?” በተሰኘው መጽሃፋቸው “ጴጥሮሳዊነት” በሚል ንዑስ ርዕስ ያሰፈሩት የአቡነ ጴጥሮስ ሃይማኖታዊ ግዝት በባልቻ አባ ነፍሶ እምነት ሰርጾ እናገኘዋለን። በወጣትነት እድሜያቸው ያንበረከኩት ጣሊያን በስተርጅናቸው እጅ እንዲሰጡ ቢጠይቃቸው “ሰማይ ቤት ጣይቱና ምኒልክ ሲጠይቁኝ ለጣሊያን እጅ ሰጠሁ ልላቸው ነው?” በማለት እስከመጨረሻው የሕይወታቸው ህቅታ ድረስ ፋሺሽቱን ተፋለሙት፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ስሙን በደማቅ ቀለም የጻፈው መንግሥቱ ወርቁ እንኳን የጣሊያን ክለቦች ማሊያቸውን ሊያለብሱት ቢከጅሉም እሱ ግን “የአባቶቼ ገዳዮች ናችሁ” ብሎ እሽታውን ነፈጋቸው።

ከሊቅ እስከደቂቅ ብርቱ ሕዝቦቿ ያሳዩት ተጋድሎ የሀገራቸው ዳር ድንበር መሸርሸር የሃይማኖታቸው መደፈር አንገብግቧቸው ለዱር ለገደሉ ያበቃቸው የአርበኝነት ስሜት ነው።

ታዲያ ይህ ሁሉ በታየበት ሀገራችን ከወግና ባህሉ ተፋቶ ከራሱ ተጣልቶ ብልጭልጩ ዓለም ስቦት ቅርቡን የናቀ ሩቁን የናፈቀ ኮብላይ ትውልድ ስለምን በቀለ? “የመጀመሪያ ጓደኛህን በምን ቀበርከው? በሻሽ፣ የኋለኛው እንዳይሸሽ።” ሲሉ ሃሳባቸውን የቀጠሉት አያልነህ ሙላቱ “ከማን ምን አይቶ ምን ተምሮ ነው ባሁኑ ትውልድ ላይ ለወቀሳ ጣታችንን የምንቀስረው?” በማለት ይጠይቃሉ፤ ቀጥለውም የፑሽኪንን የቤት ቃጠሎ አጋጣሚና የሩሲያውያንን የጀግና አከባበር ባህል ለወጋችን ማዋዣ እንዲሆን አስከተሉ።

ፑሽኪንና የዘመኑ ንጉሥ መጽሃፍና ትርጉም ሆነው በሸውራራ አመለካከት ተያይተው “ዓይንህን ላፈር” ተባብለው ነበርና ቤቱ ሲቃጠል “አይዞህ” ያለው የመንግሥት አካል የለም፤ የከተማው ሕዝብ ግን ከልጅ እስከአዋቂው ድረስ ተረባርቦ የቤቱን እቃ ማትረፍ ባይችልም ሰነዶቹን ከሳት አደጋ መታደግ ችሏል። ቀን ፈቅዶ ቤቱን በሠራ ጊዜ አመድ ከመሆን ያዳኗቸውን ቁራጭ ወረቀቶች እንኳን ሳይቀሩ አመጡለት። ዛሬ ላይም ከሳት የተረፉ የፑሽኪን ሰነዶች በሚሊዮኖች ይጎበኛሉ።

ይህን የሩሲያውያንን የጀግና ማክበር ልማድ ወደኛ ሀገር አምጥተን ብንለካው ሚዛን ያነሳል? በፈረሰ መንግሥት ሥርዓት አልበኝነት እንዳይከሰት ጥለውት የሄዱትን ሀገር ከውጭ ወራሪ ሃይል ታድገው ላቆዩላቸው አርበኞች ንጉሡ ሲመለሱ በሹመት ፋንታ ስቅላትን በምርቃት ፋንታ እርግማንን ነው የደገሱላቸው፤ አርበኞችም ቢሆኑ የከፋ ጦርነት ውስጥ ከምንገባ ብንተወው ይሻላል ሲሉ ተዉት እንጂ “ያፈረሰ ቄስ አይቀድስም የሸሸ ንጉሥ አይነግስም” ብለው ነበር። ይህን እየሰማ ያደገ ትውልድ “ለነበላይ ዘለቀ፤ ለነተመስገን ገብሬ ያልሆነች ሀገር” ብሎ አብርሃም ሊንከን “ሀገር የምትወድቀው ዜጎቿ ምን አገባኝ ያሉ ጊዜ ነው” ሲል የተናገረውን የኛ ወጣቶችም በምን አገባኝ ስሜት ሀገራቸውን ዘነጓትና ለባእዳን ምድር ላባቸውን ሲያፈሱ ይኖራሉ።

ጀግናው አርበኛ ደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ ገመድ ላይ ሲውል ጸሃፈተውኔት ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ “በላይ መሞትህ አይደለም የሚከነክነኝ፤ ከባንዳ ጋር መሰቀልህ ነው እንጂ” አሉት እንባቸውን እያዘሩ። እንደዚህ አይነቱ መከፋት አያሌ የኪነጥበብ ሰዎችን በየሥራዎቻቸው የአርበኞችን መገፋት ትኩረት አድርገው እንዲጽፉ አድርጓቸዋል፤ ከዚህም የተነሳ ወጣቱ ለሀገሩ ራሱን መስጠትና ሃላፊነትን መቀበል አይሻም። ይህ ደግሞ እንደማህበረሰብም እንደመንግሥትም የሀገር ባለውለታዎቻችንን የምናከብርበትና የምንይዝበት መንገድ ጉድለት እንዳለበት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ለዚህም ይመስላል ጽሃፊ ተውኔት ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ

“እናት ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ።”

ሲሉ ማንጎራጎራቸው። ኢትዮጵያ ጠኔ ሲያጎማዣት አርበኞች መና ሆነው ነፍሷን መልሰውላታል፤ አካሏ ረግፎ ውበቷ በደበዘዘ ጊዜም ደማቸውን አፍስሠው አጥንታቸውን ከስክሰው ህያው ቁንጅና አልብሰዋታል። ስለሆነም ከማር የጣፈጠ ውለታቸውን ትውልዱ እንዲያውቀው በሥርዓተትምህርቱ ታሪካቸውን ማካተት፤ እንጀራ የማይሆን ማእረግ መጫን ብቻ ሳይሆን ለሕይወታቸው ዋስትና በመስጠት እነሱን በሚመጥናቸው ልክ ኑሯቸውን መደጎም፤ መገናኛ ብዙሃንም የአሜሪካንና የእንግሊዝን ታሪክ ከማነብነብ ይልቅ የሀገራቸውን የአርበኞችን ታሪክ እየፈለፈሉ ለማውጣት መሥራት አለባቸው በማለት ብሶትና ምክር ቀላቅለው አቶ አያልነህ ሙላቱ ሃሳባቸውን አካፍለውናል።

ታደለ ገድሌ ዶ/ር በበኩላቸው “የትውልዱን ልቦና አርቆ የወገኖቹን ተጋድሎ አሳውቆ ከአለት የጸናች ሀገርን ለማስረከብ ብሎም የገጠመንን የዕንዝላልነት ባህር በጥበብ ለመሻገር የኪነጥበብ ሚና የጎላ ነውና አስታራቂ የብዕር ትሩፋቶችን በውል ልንጠቀምባቸው ይገባል” ብለዋል።

አያይዘውም አርበኝነት የሚገለጠው በጦር ሜዳ ብቻ እንዳልሆነና አባቶቹ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ያሳዩትን ጀግንነት የአሁኑ ትውልድ ድህነትን በመዋጋት፣ ሰላምን በማስጠበቅና ልማትን በማፋጠን አርበኛነቱን ሊያሳይ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በዘረኝነት ቋት ተሸሽገው ጥላቻን ከሚዘሩ ሰዎች ራሱን በማቀብና በመለያየት ጀልባ ባለመሳፈር የአርበኞችን ውለታ መክፈል ይኖርበታል። የዓድዋ ዋጋ አንድነት ነውና። በመጨረሻም በተባበረ ክንድ የጀመርነውና ለመጨረስ የምንታትረው ህዳሴ ግድባችን የአሁኑ ትውልድ ያባቶቹን ገድል የደገመበትና ለአርበኝነቱ ማሳያ ስለሆነ ወደፊትም ሀገርን የሚያኮሩ ስምን የሚያስጠሩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ቁርጠኛነቱ ለአፍታም ቢሆን ሳይዝል መቀጠል ይጠበቅበታል በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You