
በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የካቲት በብዙ ታሪኮች የታጀበ ወር ነው፡፡ ታላላቅ አብዮቶችና ታላላቅ ድሎችም በየካቲት ወር ተገኝተዋል፡፡ ዓድዋን ያህል ለጥቁር ሕዝቦች ከፍታው ሰማየ ሰማያትን የሚነካ ድል የተገኘው የካቲት ወር በገባ በ23 ቀን ነው፡፡ ይህ በሆነ ከ39 ዓመታት በኋላ በድሉ ኃፍረትን ተከናንቦ የነበረው ፋሽስት ከ30 ሺህ በላይ ዜጎቻችን (የአዲስ አበባ ኗሪዎች ብቻ) በግፍ የተጨፈጨፉትም የካቲት 12 ነው፡፡ የካቲት ድልም ደምም ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የየካቲት ወር በኢትዮጵያ ላቅ ያለ ታሪካዊ ቦታን የያዘ ነው። የቀደመው የካቲት 12 ቀን 1929ዓ.ም ሲታወስ አካፋና ዶማ፣ ፋስና መጥረቢያ ለሰው ልጅ መጨፍጨፊያነት ውለዋል። አዛውንት እናትና አባቶች ሕጻናትን ጨምሮ በመኖሪያቸው በእሳት ጋይተዋል። ዋይታና ጩኸት፣ የሰቆቃ ድምፆች እሪታና ጣር እያሰሙ ንፁሐን ዜጎች በየመንገዱ፣ በየጉራንጉሩ፣ በየመንደሩ ተዘርግተዋል።
የኢትዮጵያውያን ያለመገዛት ጽናት የታየበት፤ ለነፃነታችን የተዋደቅንበት የየካቲት 12 ሰማዕታት 88ኛው ዓመት መታሰቢያ ቀን ከሰሞኑ ተከብሯል። ይህ ቀን ኢትዮጵያውያን በቅኝ አንገዛም፣ አንበረከክም፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነት አናስደፍርም ብለው ለአሁኑ ትውልድ በነፃነት እንዲኖር ዘመን የማይሽረው መስዋዕትነት የከፈሉበት ዕለት ነው። ቀኑን በየዓመቱ እናስታውሰዋለን፤ ታሪኩንም እንዘክረዋለን።
በ1929 ዓ.ም በጄኔራል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ትዕዛዝ ሰጪነት በአዲስ አበባ ከሠላሳ ሺህ በላይ ዜጎቻችን ሕፃን፣ ሴት፣ ወጣት፣ አዛውንት ሳይባል ጭካኔ በተሞላው መንገድ ተጨፍጭፈዋል። እነዚያ ዜጎቻችን ዘግናኙን መከራ ተቀብለውና ታሪካቸውን በወርቅ መዝገብ ጽፈው ለእኛ ደግሞ ነፃነትን አጎናጽፈውናል ።
ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች፣ ለነጭ ያልተንበረከከች ብቸኛዋ ነፃ አፍሪካ ሀገር ሆና እንድትኖር አድርገዋል። የጀግንነትና የሀገር ፍቅርን አውርሰውናል። እነዚህ ጀግኖች ታዲያ በየዓመቱ ይታወሳሉ። በስማቸው በተሠራው የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ስርም ጉንጉን አበባ ይቀመጣል። ለታላቅ ስም ታላቅ ክብር ይገባዋልና።
ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት ሀገር መሆኗ አንዱ ከዓድዋ ቀጥሎ ትልቁ ታሪካችን በመሆኑ ሁሌም የምንዘክረው እና የምንኮራበት ነው። ይሄ አንዱ ምዕራፍ ነው። አሁን ግን በሌላኛው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ይሄኛው ምዕራፍ ያለፉ አባቶችና አያቶቻችን የሠሩትን ታሪክ ብቻ በማወደስና በመኩራራት ላይ ብቻ ከማተኮር አለፍ ብሎ የራስን የታሪክ ዐሻራ ለማሳረፍ የሚሠራበት ዘመን ነው። የሚያስብ አዕምሮ የሚሠሩ እጆችን ይዞ ለልማት የሚሮጥበት ጊዜ ነው። አሁን ከነፃነት እና ከሉዓላዊነት እኩል ከፍ የሚያደርጉንን የሀገራችንን ብልፅግና ማረጋገጥ የሚጠይቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ተረጂነትና ልመና ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ተግባር መሆኑ ግልጽ ነው። ከተረጂነት ጎን ለጎን ቅኝ ግዛት፤ ነፃነት ማጣት በዓለም ላይ በተደጋጋሚ ታይቷል። ዛሬ ላይ የትናንት ታሪካችንን በመዘከር ብቻ ሳይሆን ታሪክን በመጠበቅ ተደማሪ አኩሪ ታሪክ መሥራት ይገባል፡፡
የሀገራችን ነፃነት ጠብቀንና አረጋግጠን በአደባባይ የምንቆመው ብልፅግናችንን በኢኮኖሚው፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በፖለቲካ… ማረጋገጥ ስንችል፤ እንደ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የራስን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ የሚያስችለንን ቁመና በሁሉም ዘርፍ ማረጋገጥ ስንችል አንገትን ቀና፤ ልብን ሞልቶ መቆም ይቻላል።
ለዚህም የሀገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይገባል። በሁሉም መልኩ ታሪካችንን ማስቀመጥና አሻራችንን ማኖር አለብን። ይህን ሁሉም ዜጋ ሊያውቀውና ሊገነዘበው ይገባል። ዛሬ የተጀመረው የስንዴ አብዮት ሀገራችንን በዓለም ላይ ካሉ የስንዴ አምራቾች ተርታ አሰልፏታል።
ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች ሀገር፤ ከስንዴ ተረጂነት ወደ ስንዴ አምራችነት፤ ራስን ከመቻል ወደ መላክ ደረጃ አድርሷታል። ይሄ ይበል የሚያሰኝ ጅምር ቢሆንም ገና ብዙ መሥራትን ይጠይቃል። የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት፣ የመስኖ እርሻ … ሥራዎች ላይ መረባረብ ይገባል።
ታላቁ ህዳሴ ግድብ ይሄ ትውልድ በእውቀቱ፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ ሠርቶና ደግፎ ዓለምን ድንቅ ያሰኘ ታሪካችን ነው። የኮሪደር ልማት፣ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማስዋብ፣ ማስፋፋት እና ማደስ፤ እንዲሁም አዳዲሶቹ የገበታ ለሀገር፤ የትውልድ ለሀገር፤ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ጨበራ ጩርጩራ የመሳሰሉት ድንቅ የቱሪስት መዳረሻዎች ተገንብተዋል።
አቧራ ለብሰው አቧራ መስለው የተቀመጡት ታሪካዊ ቅርሶቻችን ታላቁ ቤተመንግሥት፣ ላልይበላ፣ ዓፄ ፋሲል፣ ጅማ አባጅፋር…ን አድሶና አስውቦ ልዩ የቱሪስት መዳረሻዎች እና ሰፊ የገቢ ምንጭ የማድረግ ሥራዎች የዚህ ዘመን የታሪክ አሻራዎች ናቸው።
የኤክስፖርት ምርት አቅማችንን በማሳደግ የቡና፣ የሻይ ቅጠል፣ የቅመማ ቅመም፣ ማዕድንና ሌሎችም ላይ የተሠራውን ሥራ በዓይናችን የምናየው በአፋችን የምንመሰክርለት ውጤቶቻችን ናቸው። ነፃነት ሙሉ የሚሆነው በሁሉም መልኩ ሙሉ ሆኖ መገኘት ሲቻል ነው። በመሆኑም ይሄ ትውልድ የራሱን የልማት ዐሻራ በጉልህ መጻፍ፤ ሀገራችንን ወደታላቅነቷ የሚመልሱ ታላላቅ የልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር ይገባዋል።
ብልፅግናችንን በየአቅጣጫውና በየዓይነቱ ማረጋገጥ ከቻልን ኩሩ ሕዝቦች የሚለውን ስማችንን እናስቀጥላለን። ካልሆነ ግን “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት” እንደሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ይሆንብናል። ስለዚህ የቀደመውን ታሪክ ከማውራት በዘለለ የሀገራችን ብልፅግና በሁለንተናዊ መልኩ ማረጋገጥ አለብን። የልማት ጀግንነታችንን ነፃነታችንን ባረጋገጥንበት ልክ ወደፊት ማምጣት ይገባል።!
አባ መቻል ከኮልፌ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም